Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሥርዓቱ የሰላም፣ የእኩልነትና የፍትሕ መሰረትን ጥሏል!

0 354

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሥርዓቱ የሰላም፣ የእኩልነትና የፍትሕ መሰረትን ጥሏል!

          ዳዊት ምትኩ

ኢትዮጵያ ዛሬ የምትገኝበትንን የተረጋጋ ሰላም፣ ፈጣን ልማትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መንገድን ስናስብ ትናንትን ልንዘነጋው አንችልም፡፡ በየትኛውም ሀገር ውስጥ የትናንት ጥፋትም ሆነ ውድቀት በአሁኑ ማንነት ላይ አሉታዊም ሆነ አወንታዊ አሻራ አለው። የሀገራችንም ሁኔታ ከዚህ አጠቃላይ አስተሳሰብ የሚቀዳ ነው፡፡ እናም የኢትዮጵያን ሕዝቦች ያስተሳሰረው የጋራ አስተሳሰብ ሲታወስ፣ በቅድመ ፌዴራል ኢትዮጵያ በገዥዎች ሰፍነው የነበሩ የተዛቡ ግንኙነቶችን ብቻ ሳይሆኑ፤ ዜጎች በታሪካዊ ትስስራቸው የፈጠሯቸው ተፈላጊ ቁርኝቶችም አብረው ይወሳሉ፡፡ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ አሁን ላለንበት ሁለንተናዊ የሰላም፣ የእከኩልነትና የፍትህ ተጠቃሚነት መሰረት መጣሉን በዋነኛነት ማንሳት ይገባል፡፡

ሀገራችን የምትከተለው ፌደራላዊ ስርዓት ከሌሎች አገራት ፌዴሬሽኖች የሚጋራቸው የጋራ መገለጫዎች እና የሚለዩት የራሱ የሆኑ ባህሪያት ያሉት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊ ፌዴራል ሥርዓት አንዱ መሠረታዊ መነሻ አስተሳሰብ ወይም እምነት ለረዥም ዓመታት በኢትዮጵያ ሰፍኖ የነበረውን የተዛባ የሕዝቦች ግንኙነት በማስተካከል አዲስ የኢትዮጵያዊነት ሕብርና ዝምድና መመሥረቱ ነው፡፡

ሀገራችን ከ75 በላይ የተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ያቀፈች አገር ነች፡፡ እነዚህ ማንነቶች ባለፉት የዘውድና ወታደራዊ አገዛዝ ዘመናት ማንነታቸውን እንዲሸሽጉ አሊያም ጨርሰው እንዲፍቁ የተገደዱበት ሥርዓቶች ነበሩ፡፡ በነገሥታቱ ዘመን የኢትዮጵያዊነት መለኪያ የራስ ማንነትን በመተው የገዥዎችን ቋንቋ መጠቀም፣ ባህልና ኃይማኖትን መከተል፣ ገዥዎቹ የደገፉትን መቀበልና መስሎ መታየትን ነበር፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ ለም መሬት በመኳንንትና በገዥዎች አገልጋዮች የተያዘ ስለነበር ገበሬዎች ሙሉ በሙሉ ከመሬት ባለቤትነት ባይነቀሉም የመሣፍንቱን መሬት በማልማትና ሀብት በመሰበሰብ አገልጋዮች እንዲሆኑ ተደርገው ነበር፡፡ በደቡብ ኢትዮጵያ ደግሞ የማንነት ጭቆና የአካባቢዎቹ ሕዝቦች የሀብት ምንጭ የሆነውን መሬታቸውን ሙሉ በሙሉ ከመንጠቅ ጋር ተያይዞ የተፈፀመ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

በመሣፍንታዊ ሥርዓተ መንግሥት “አንድ አገር” የመፍጠርና የማቃናት ሂደት፤ “አንድ ቋንቋ፤ ባህል፤ ኃይማኖትና አገር” በሚል ፍልስፍና ማንነትን በማፈን የተከናወነ ሆኖ ከኢኮኖሚ ጭቆና ጋር በማስተሳሰር የተፈፀመ ነበር፡፡ በነገሥታት ዘመን ሌሎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችም የማይታሰቡ ነበር፡፡ የሥርዓቱን ፍፁማዊነት ለመግለጽ “ንጉስ አይከሰስ፤ ሰማይ አይታረስ” በሚል ተረት ይገለጽ ሁሉ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡

ዘውዳዊውን ሥርዓት ተክቶ የመጣው የደርግ አስተዳደር በዘውድ ዘመን የነበረውን የማንነት አፈናና የኢኮኖሚ ጭቆና አጠናክሮ ቀጥሎበታል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነታቸውን ለማስከበር በአፄው ዘመን የጀመሩትን ትግል ለማጥፋት አስከፊ ጭፍጨፋ ፈፅሟል፡፡ ማንነትን የማስከበርና እኩልነትን የማረጋገጥ የመብት ጥያቄዎችን በሠላማዊ መንገድ ማንሳት ይቅርና ማሰብ በራሱ የሕይወት ዋጋን ያስከፍላል፡፡

ደርግ በዘውድ ዘመን የነበረውን የአንድ ኃይማኖት የበላይነት በመሠረቱ ሳይቀይር ነገር ግን ለውጥ ያመጣ በማስመሰል ሁሉም ኃይማኖቶች እምነታቸውን በነፃ እንዳያራምዱ አፍኗል፤ የኃይማኖት ተቋማትን ዘግቷል፤ በርካታ አማኞች አገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ አስገድዷል፡፡ ደርግ የዘውዳዊው አገዛዝ የኢኮኖሚ ምንጭ የነበረውን መሬት በመንጠቅ የመሣፍንታዊ ሥርዓት መሠረት እንዲነቀል አድርጓል፡፡ ይሁንና ለገበሬዎች ያከፋፈለው መሬት ግን ፍትሃዊነት የጎደለው ነበር፡፡ አርሶ አደሮች ምርታቸውን በገበያ ዋጋ እንዳይሸጡ የዋጋና የኮታ ቁጥጥር ሥርዓት በመዘርጋት፤ ሀብታቸውን፣ ጉልበታቸውንና እውቀታቸውን አሟጥጠው ለተሻለ ምርታማነት እንዳይሰሩና ኑሯቸውን እንዳይለውጡ ነፃነታቸውን ያፈነ ሥርዓት የትናንት ትውስታችን ነው፡፡

እነዚህ ሁሉ አፈናዎች የትናንት ትውስታችን ይሁኑ እንጂ፤ ዛሬ ላይ የተመሰረተው ፌዴራላዊ ስርዓት እነዚህን አፈናዎእ የሻረና የሰላም፣ የእኩልነትና የፍትሕ መሰረቶችን መጣል የቻለ ነው፡፡ የሀገራችን ህዝቦች እነዚህን መብቶቻቸውን እንዲጠቀሙም ያስቻለ ነው፡፡

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ ተረጋግጧል፡፡ ዜጎች በህግ ፊት እኩል ሆነዋል። የሚከተሉት የኃይማኖትና እምነትም በእኩልነትን የሚታዩበት ህገ መንገስታዊ ስርዓት ተረጋግጧል፡፡ ፍትሕን እንዲቋደሱና በፍትሕ ስርዓቱ ውስጥ ሁነኛ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ በዚህ አዲስ የእኩልነት ግንኙነትም ሁሉም በየደረጃው ተጠቃሚ እንዲሆን ተደርጓል፡፡

ትናንት ዜጎች በልማት አጀንዳ ተሳታፊ ስላልነበሩ ህይወታቸውን የሚለውጥ ሀብት የማፍራትና ከአገሪቱ ሀብት በፍትሃዊነት የመጠቀም መብት አልነበራቸውም፡፡ የሕብረ ብሄራዊ ፌዴራል ሥርዓቱ አንዱ መሠረታዊ እምነት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል በመሆኑ ይህ እንዲረጋገጥና ህገ መንግስታዊ ዋስትና እንዲያገኝ ተደርጓል፡፡

ባለፉት መንግሥታት በአገሪቱ ተንሰራፍቶ የኖረውን የተዛባ ግንኙነት በመፋቅ አዲስ ኢትዮጵያዊ ማንነት ለመገንባት የሚያስችሉ የማንነቶች እኩልነት ማረጋገጥ፣ ሁሉም ዜጎች ኢትዮጵያን በመገንባት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ማድረግ፣ በአካባቢ ጉዳዮቻቸው ላይ ወሳኝ የሚሆኑበትን የራስ አስተዳደር ማረጋገጥ በአጠቃላይ ከአገሪቱ ልማት ተመጣጣኝ ጥቅም እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል፡፡

የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ማንነቶች አዲስ የእኩልነት መንገስ መክፈቱንነና እንደ ማረጋገጫ መሣሪያ ስለተወሰደም በዚህ አወቃቀር አዲስ የእኩልነት ግንኙነትና የጋር ህልውና እንዲመሠረት ተደርጓል፡፡ በዚህም የአዲሲቷን ኢትዮጵያ የወደፊት ዕድል የመወሰን ሥልጣን ባለቤት መሆን እንዳለባቸው በወኪሎቻቸው አማካይነት ይፋ አድርገዋል፡፡ በፌዴሬሽኑ ምሥረታ ወቅት የገቡትን ቃል በአፈፃፀም ሂደት እንዳይዛነፍ የመጠበቅ ኃላፊነት የሚሰጣቸውን ህገ መንግሥት የመተርጎም ሥልጣን ህዝቦች እውን አድርገዋል፡፡ ይህም በመከባበር፤ በመተማመንና በመተባበር በእኩልነት አብሮ ለመኖር የሰላም ዋስትና ሆኗል፡፡

በፌደራል ስርዓቱ አመሰራረት ወቅትም እነዚህን የተራራቁ ፍላጎቶች የነበሯቸው የፖለቲካ ኃይሎች ተቀራርበውና ተሰባስበው በህብረቱ እንዲቀጥሉ በመስማማታቸው፤ ለቁርሾ የሚያበቃ ነገር እንዳይኖር ሰርተዋል፡፡ በተለይም ኃይማኖቶችና እምነቶች ተቻችለውና ተከባብረው ለመኖር የነበራቸው ፍላጐት የሚጫኑ የአክራሪነት ድርጊቶችን በመቃወም እኩልነታቸውን ማረጋገጥ ችለዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ብዙ ፈተና የገጠመው ቢሆንም ቅሉ በጋራ በመሆን በእኩልነት መንፈስ አዲሲቷን ኢትዮጵያ እውን እያደረጉ ነው፡፡

እርግጥ ከእነዚህ ዕውነታዎች መረዳት የሚቻለው ነገር ህገ መንግስታዊው ስርዓት ለሰላም፣ ለእኩልነትና ለፍትሕ መሰረት የጣለ ብቻ ሳይሆን፤ መሰረቱን በህዝቦች መፈቃቀድ ላይ ተመርኩዞ በማስፋት አዲሲቷ ኢትዮጵያ አሁን ለምትገኝበት የመተሳሰብና የመካባበር ቁመና ላይ እንድትሆን ያስቻለ ነው፡፡ አበቃሁ፡፡  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy