Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሥጋትን ወደ መልካም አጋጣሚ

0 339

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሥጋትን ወደ መልካም አጋጣሚ /ብ. ነጋሽ

ሥር የሰደደ ድህነት ዜጎች የመኖር ዋስትናው ባልተረጋገጠ አስከፊ ሁኔታ ውስጥ እንዲኖሩ ከማድረግ ያለፈ መዘዝ አለው። ሥር የሰደደ ድህነት ገዢ በሆነባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች በኑሯቸው ተስፋ ይቆርጣሉ። በመኖርና ባለመኖር መካከል ያለው ልዩነት ጠፍቷቸው ተስፋ የቆረጡ ሰዎች ምንም ነገር ቢመጣ የሚያጡት ነገር እንደሌለ ስለሚሰማቸው ማንኛውንም ርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ አይሉም። ሥር የሰደደ ድህነት ያለበት ሁኔታ ለእርስ በርስ ግጭት፣ ለአክራሪነት እንቅቃሴና ለአሸባሪነት መፈጠርና መስፋፋት አመቺ ነው።

አሜሪካ በኢራቅ ላይ ባወጀችው “የፀረ ሽብርተኝነት” የጦርነት ዘመቻዎች ላይ የተካፈለ የባህር ላይ መኮንን ጃክ ሃሪሰን የተባለ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን ሽብርተኝነትና የኃይል እንቅስቃሴዎች መሠረታዊ መንስዔ ሥር የሰደደ ድህነት ነው የሚል አቋም በመያዝ ይታወቃል።

ይህ የጦር ሜዳ ጀብዱ ተሸላሚ መኮንን የፀረ ሽብርተኝነት ትግሉን በቀጥታ በመሣሪያ አሸባሪዎችን ከመዋጋት ድህነትን ወደመዋጋት ቀይሯል። ጃክ ሃሪሰን ኑሩ ኢንተርናሽናል የተባለ በድህነት ቅነሳ ላይ የተሰማራ በጎ አድራጎት ድርጅት አቋቁሞ በአሁኑ ጊዜ አስከፊ ድህነት በሰፈነበት ኩሪያ በተባለ የኬንያ አካባቢ በድህነት ቅነሳ ተግባር ላይ ተሰማርቶ ይገኛል።

አሜሪካ አሸባሪ ብላ የፈረጀቻቸውን ቡድኖች በመሣሪያ ገጥሞ የነበረው ጃክ ሃሪሰን፣ ሽብርተኝነትን መከላከል የሚቻለው በመሣሪያ ሳይሆን አስከፊ ድህነትን በመዋጋት መሆኑን መገንዘቡን ተናግሯል።  ሃሪሰን ለዚህ እምነቱ አስረጂነት የሠላም ኖቤል ሽልማት አሸናፊ የሆኑትን ደቡብ አፍሪካዊ ቄስ ዴዝሞንድ ቱቱን ይጠቅሳል። ዴዝሞንድ ቱቱ “በዓለም ላይ ላይ ሰዎችን ተስፋ ቢስ የሚያደርጉ ድህነት፣ በሽታና መኃይምነት እስካሉ ድረስ በፀረ ሽብርተኝነት ላይ የተከፈተው ጦርነት ድል መቀዳጀት አይችልም።” ብለዋል። ይህን ሃሳብ ሌሎች ምሁራንና ዓለም አቀፍ ተቋማትም ይጋሩታል።

ከድህነት በተጨማሪ የፖለቲካ ነጻነት እጦትም የሽብርተኝነት መንስዔ መሆኑ ይታመናል። ሰዎች የአመለካከት፣ ሃሳብን የመግለጽ፣ አመለካከትን በግልና ከመሰሎች ጋር ተደራጅቶ የማራመድ፣ ለፖለቲካ ሥልጣን የመፎካከርና የመወከል፣ የመደመጥ ወዘተ… ዴሞክራሲያዊ መበቶች ሊረጋገጥላቸው ይገባል። እነዚህ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሲታፈኑ ወይም ታፍነዋል ተብለው ሲገምቱ ሰዎች ወደ የኃይል ርምጃ ይገባሉ።

በመሆኑም፣ የኃይል ተቃውሞንና ሁከትን፣ አክራሪነትንና አሸባሪነትን ለመከላከል የሚደረገው ትግል በቀጥታ እነዚህ ወጤቶች ላይ ከማተኮር ይልቅ ምክንያቱ የሆነው ሥር የሰደደ ድህነት ላይ ማተኮር ይኖርበታል። በተለይ ሥር የሰደደ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ወጣቶች በቀላሉ ወደ ኃይል ተቃውሞና ሽብርተኝነት ለመግባት የተጋለጡ ናቸው።

ድህነትና የኃይል ተቃውሞ እንቅስቃሴዎችና ሽብርተኝነት ሥር ከሰደደ ድህነት ጋር ያለውን ቁርኝት ያነሳሁት በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፊ ትንታኔ ለመስጠት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በተለይ ከወጣቶች ሥራ አጥነት አኳያ ምን ገጽታ እንዳለውና በዚህ ጉዳይ ዙሪያ በመንግሥት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን መዳሰስ ነው።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሚያስታውሰው ባለፈው ዓመት ሠላም ርቆን ነበር የከረምነው። በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በተለይ ወጣቶች የተሳተፉባቸው የአደባባይ ተቃውሞዎች ተካሂደዋል። የአደባባይ ተቃውሞዎቹ ህግና ሥርዓት የተከተሉ ሳይሆኑ በመንግሥት ላይ የመረረ ቅሬታ ያደረባቸው ወጣቶች በድንገት ገንፍለው ያካሄዱት ነበር። ወጣቶቹ ላይ የመረረ ቅሬታ ያሳደረው ቀዳሚው ጉዳይ ሥራ አጥነት የፈጠረው ድህነትና ጥገኝነት ነው። ወጣቶቹን ለጥገኝነት የዳረገው ሥራ አጥነት ከጊዜ ወደጊዜ እየተሻሻለ ከመሄድ ይልቅ እየተባባሰ ከተሞች የሥራ አጥ ወጣቶች መናኸሪያ መሆን፣ በወጣቶቹ ዘንድ የተስፋ መቁረጥ ስሜት አሳደረ። እናም ቆስቋሽ አጋጣሚ ሲፈጠር ገንፍለው ለተቃውሞ አደባባይ ወጡ።

እርግጥ ሥራ አጥነት በፈጠረው የመረረ ቅሬታ ገንፍለው ለተቃውሞ የወጡ ወጣቶች የሌሎች ኃይሎች ሲሳይ ሆነዋል። ለወጣቶቹ ዘላቂ የተሻለ ህይወት የሚበጅ አንድም አማራጭ የሌላቸው በውጭ አገራት ያደፈጡ ጽንፈኛ ተቃዋሚዎችና የኢትዮጵያ ጠላቶች የትርምስ ስትራቴጂ አስፈጻሚዎች የወጣቶቹን ተቃውሞ ጠልፈው የራሳቸውን ዓላማ ለማሳካት ወደአውዳሚ ሁከትነት ቀይረውታል። ወጣቶቹ የጽንፈኛ ተቀዋሚዎቹ መጠቀሚያ ለመሆን የተጋለጡት ተስፋ የመቁረጥ ሰሜት ስላደረባቸው ነው። ሁከት ውስጥ ቢገቡ ምንም የሚያጡት በእጃቸው ያለ ነገር የላቸውም። ይህ የድህነትንና ሥራ አጥነትን አደገኝነት በተጨባጭ የሚያሳይ ገና ግለቱ ያልበረደ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው። ይህን ተከትሎ መንግሥት አጠቃላይ ከሚታዩት የመልካም አስተዳደር መጓደልና ኪራይ ሰብሳቢነት ጋር አያይዞ የወጣቶች የሥራ አጥነት ችግር በመቅረፍ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ የማድረግ እንዲሁም ፖለቲካዊ ተሳትፏቸውን የማሻሻል ርምጃ ወስዷል። ቀዳሚው ርምጃ ከዚህ ቀደም በሥራ ላይ የነበረውን የወጣቶች የልማትና ተጠቃሚነት ፓኬጅ አሁን ካለው ችግር አኳያ ከልሶ የማሻሻል ርምጃ ነው።

ይህ የወጣቶች የለውጥና የእድገት ፓኬጅ በሚል የተሻሻለው የወጣቶች ፖሊሲ የወጣቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ያረጋግጣል ተብሎ ታምኖበታል። ከዚህ የወጣቶች የለውጥና የእድገት ተጠቃሚነት ፓኬጅ ጋር ተያይዞ፣ ልዩ የወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ ፕሮግራም ተነድፏል። ለዚህ ዓላማ መንግሥት አሥር ቢሊዬን ብር ተንቀሳቃሽ ፈንድ መድቦ ወጣቶች በሥራ ፈጠራ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ እንቅስቃሴ ተጀምሯል።

የወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ሚኒስቴር ሰሞኑን እንዳስታወቀው በሁሉም የአገሪቱ ክፍል የሚገኙ ሥራ አጥ ወጣቶች መንግሥት በብድር ለመስጠት ከመደበው የአሥር ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ ተጠቃሚ ለመሆን በማንኛውም ጊዜ መመዝገብ ይችላሉ። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሆኑ ሥራ አጥ ወጣቶች ቢያንስ አምስት ሆነው በመረጡት የሥራ መስክ መደራጀት ይችላሉ።

ሚኒስቴሩ እስካሁን በመላ አገሪቱ እድሜያቸው ከ18 እስከ 34 የሆኑ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሥራ አጥ ወጣቶችን ለይቶ ከተዘዋዋሪ ፈንዱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል እየሰራ መሆኑንም አስታውቋል። ወጣቶቹ በአሁኑ ወቅት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና በመውሰድ ላይ ይገኛሉ። ወጣቶቹ ያሰራናል፤ ውጤትም ያስገኝልናል ባሉት የሥራ መስክ ላይ የፕሮጀክት ፕሮፖዛል መቅረፅ ይኖርባቸዋል። ፕሮፖዛሉን ለማዘጋጀት በየወረዳው የሚገኙ የወጣቶችና ስፖርት ባለሙያዎች አስፈላጊውን እገዛ ያደርጋሉ።

ወጣቶቹ ያዘጋጁት ፕሮፖዛል አዋጭነቱ ተረጋግጦ ሲፀድቅ ወጣቶቹ ለመረጡት የሥራ መስክ የብርድ አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል። ወጣቶቹ በየአካባቢው ከሚገኝ አነስተኛ የብድር ተቋም ከሚጠይቁት አጠቃላይ ብድር አሥር በመቶ የሚሆነውን አስቀድመው በመቆጠብ ገንዘቡን እንዲያገኙ ይደረጋል። በአካባቢያቸው የአነስተኛ የብድር ተቋም ከሌለ በንግድ ባንክ በኩል አገልግሎቱን እንዲያገኙ ይደረጋል። ወጣቶቹ አንድ ዓመት የብድር መመለሻ የእፎይታ ጊዜ የሚሰጣቸው ሲሆን ስምንት በመቶ ወለድ እንዲከፍሉም ይጠበቅባቸዋል። ለሚበደሩት ገንዘብ የንብረት ማስያዣ አይጠየቁም። ለወጣቶች የተመደበውን ፈንድ በመጠቀምና በአጠቃላይ ሥራ አጥ ወጣቶችን ሥራ ላይ እንዲሰማሩ በማድረግ ረገድ የኦሮሚያ ክልል ተጠቃሽ ሊሆን የሚችል እንቅስቃሴ እያደረገ ነው። በመሆኑም በአጠቃላይ በአገሪቱ የሚደረገውንና ሊደረግ የታሰበውን የሥራ ፈጠራ እንቅስቃሴ ለማሣያነት ልጠቅሰው ወድጃለሁ።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ተንቀሳቃሽ ፈንዱን ለወጣቶች በብድር መስጠት ጀምሯል። ፈንዱን መጠቀም በመጀመር ከሁሉም ክልሎች ቀዳሚ ነው። በዚህ መሠረት የክልሉ ሥራ አጥ ወጣቶች ከባለፈው ሣምንት ጀምሮ የተዘዋዋሪ ፈንዱ ተጠቃሚ መሆን ጀምረዋል። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሥራ አጥ ወጣቶች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የክልሉ የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል።

የኦሮሚያ ክልል የፌዴራል መንግሥት ከመደበው ተንቀሳቃሽ ፈንድ 3 ነጥብ 5 ቢሊዬን ብር አግኝቷል። የክልሉ መንግሥትም ለዚሁ ዓላማ አንድ ቢሊዬን ብር በጀት መድቧል። ከዚህ በተጨማሪ  የኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ተቋም ለሥራ ዕድል ፈጠራ ብድር 1 ነጥብ 5 ቢሊዬን ብር በጀት ይዟል። ከክልሉ የልማት ድርጅቶችና አጋር አካላት የተገኘ ከ600 ሚሊዬን ብር ለሥራ እድል ፈጠራ ለማዋል ተዘጋጅቷል። ክልሉ በዚህ ዓመት በአጠቃላይ 6 ነጥብ 6 ቢሊዬን ብር ለሥራ ዕድል ፈጠራ አዘጋጅቷል። ለወጣቶች የሥራ እድል በመፍጠር ሂደት፣ በክልሉ ከተሞች በህገ ወጥ መንገድ የታየዙ ሼዶች፣ የመሥሪያና የመሸጫ ቦታዎች ላይ በተደረገ ማጣራት 824 ሼዶች በህገ ወጥ መንገድ ተይዘው ተገኝተዋል።

እነዚህን ሼዶች ተመላሽ በማድረግ ከ429 በላይ ሼዶች በህዝብ ፊት ለሥራ አጥ የገጠር እና የከተማ ወጣቶች በዕጣ እንዲተላለፉ ተደርገዋል። የተቀሩት ሼዶችም በቅርቡ ለተደራጁ ሥራ አጥ ወጣቶች ይሰጣሉ። የኦሮሚያ ክልል በወጣቶች የሥራ ፈጠራ እንቅስቃሴ ለሌሎች ክልሎች አብነት ሊሆን ይችላል የሚችል የሥራ ፈጠራ ተግባር አከናውኗል። ይህም በተለይ በማዕድን ማምረት የሥራ ዘርፍ የተከናወነ ነው። የማዕድን ማውጣት ሥራን  በተመለከተ ያለአግባብ የተያዙ 14,301 ሄክታር የማዕድን ማውጫ ቦታዎችን  ከህገ ወጦች በማስመለስ ለሥራ አጥ ወጣቶች እንዲተላለፉ ተደርጓል። በማዕድን ዘርፍ እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴ  በ1978 ማህበራት ለተደራጁ 44,869 ሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል።

 

ለሲሚንቶ ፋብሪካ ግብዓት ሊሆን የሚችል ማዕድን የማምረት ሥራ ላይ የተሰማሩ ወጣቶች ከሲሚንቶ ፋብሪካዎች ጋር  አስተማማኝና ዘላቂ የገበያ ትስስር ለመፍጠር በክልሉ ከሚገኙ ትላልቅ የሲሚንቶ አምራች ኩባንያዎች ጋር በተደረገ ውይይት፣ ደርባ ሜድሮክና ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከተረደራጁ ወጣቶች የሲሚንቶ ግብዓት ማዕድናትን ለመግዛት ከወጣቶቹ ጋር ስምምነት ተፈራርመዋል። ኢስት ሲሜንት፣ ናሽናል ሲሜንትና ሙገር ሲሚንት ፋብሪካዎችም በቅርቡ ከወጣቶቹ ጋር ውል ይፈራረማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በአጠቃላይ የኢፌዴሪ መንግሥትና ክልላዊ መንግሥታት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሶ የነበረውን የወጣቶች የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ በማሻሻል የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ ኃይል የሚሆኑበትን ሁኔታ ለመፍጠር ተጨባጭ እንቅስቃሴ እያከናወኑ ነው።

ለአብነት የተነሳው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እንቅስቃሴ ይህን ያሳያል። በጥቂት ዓመታት ውስጥ ወጣቱን የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ በማሳተፍ ተጠቃሚ እንዲሆን ከማድረግ ባሻገር የዕድገቱ ሞተር ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ እንደሚፈጠር በተጨባጭ ያሉት ሁኔታዎች ያመለክታሉ። አዲስ የተዘጋጀው የወጣቶች የለውጥና የዕድገትና ፓኬጅ ወጣቶች ተደራጅተው መብትና ነጻነታቸውን፣ ልዩ ፍላጎታቸውን የሚያስጠብቁበትና በመንግሥት ውስጥ ድምጻቸው የሚሰማበት እድል ያስገኝላቸዋል ተብሎ ይገመታል። ለዚህ እውን መሆን በመንግሥት በኩል በርትቶ መሥራት ይጠበቃል። የወጣቶች የዕድገትና የለውጥ ፓኬጅ ተግባራዊነት ወጣቱን የኢኮኖሚ አቅም በማድረግ ከትርምስ የሥጋት ምንጭነት ወደ የልማት መልካም አጋጣሚነት እንደሚያሸጋግረው ተስፋ እናደርጋለን።    

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy