Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ራሱን በራሱ የሚያርም ስርዓት መገለጫ የሆነው የኮሚሽኑ ሪፖርት

0 880

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ራሱን በራሱ የሚያርም ስርዓት መገለጫ የሆነው የኮሚሽኑ ሪፖርት /ዘአማን በላይ/

    የኢትዮጵያ መንግስት ሀገራችን ውስጥ እየገነባው ያለው ስርዓት ብዙውን ጊዜ ራሱን በራሱ የሚያርም መሆኑ ይገለፃል። መገለጫዎቹም መንግስት በተለያዩ ወቅቶች መልካም አስተዳደርን፣ ከሙስናን አሊያም ሌሎች ሀገራዊ ችግሮችን የህግ የበላይነትን መሰረት በማድረግ የወስዳቸውና የሚወስዳቸው ርምጃዎች ተጠቃሽ ናቸው። ይህም በመንግስት ውስጥ የሚፈጠሩት ችግሮች እንዲፈቱ ስርዓቱ የራሱ የሆነ የማረሚያ መንገድ ያለው መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።

እንዲህ ዓይነቱ ራስን በራስ የማረም አሰራር (Self Corrective Mechanism) በየትኛውም ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን በሚከተል ሀገር ውስጥ ተግባራዊ የሚሆን ነው። በሀገራችንም ቢሆን ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው ራስን በራስ የማረም አሰራሮችና በቅርቡ የተካሄደውና በመካሄድ ላይ ያለው የጥልቅ ተሃድሶ ርምጃዎች የዚሁ አሰራር መገለጫዎች ናቸው። በአሰራሮቹም ማንኛውም የመንግስት አካል ይሁን ዜጋ አሊያም የፖለቲካ ፓርቲ ከህግ በላይ ሊሆን እንደማይችል እየተረጋገጠ መጥቷል።

የቅርብ ጊዜውን ብናስታውስ እንኳን፤ በኢህአዴግና በአጋር ድርጅቶቹ አማካኝነት ህዝቡ ግንባር ቀደም ተሳታፊ ሆኖ በመላው ሀገሪቱ በተካሄደው ጥልቅ ተሃድሶ በሺህዎች የሚቆጠሩ የመንግስት ባለስልጣናት እንደ ጥፋታቸው ደረጃ በህግ እንዲጠየቁ፣ ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ፣ ከደረጃቸው ዝቅ እንዲሉ፣ ወደ ሌላ ቦታ እንዲሸጋሸጉ፣ ከስራቸው እንዲባረሩ ወይም በተግሳፅ እንዲታለፉ…ወዘተ. ተደርጓል።

በህዝቡ የነቃ ተሳትፎ በተካሄደው በዚህ ጥልቅ ተሃድሶ ከላይ እስከታች የህዝቡን እርካታ ሲያጓድሉና በመንግስት ስልጣን ሲገለገሉ የነበሩ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተደረገው በግምገማ ጥልቅ ተሃድሶው በታለመለት አቅጣጫ እየተጓዘ መሆኑን አረጋግጧል። ይህ በምሳሌነት ያነሳሁት የተጠያቂነት ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግስት የሚከተለው ስርዓት ራሱን በራሱ የሚያርም እንዲሁም ማንኛውም ሰው ከህግ በላይ መሆን እንደማይችል ያሳየም ነው። ይህን መሰሉ የመንግስት ጥረት የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ የሚያደርግ ነው። ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል መሆኑንና የትኛውም አካል በፈጠረው ችግር ተጠያቂ ከመሆን የማይድን መሆኑን የሚያሳይም ጭምር ነው።

ይህ የስርዓቱ ራስን በራስ የማረም አካሄድም ለዚሁ ተግባር ስርዓቱ ራሱ ካቋቋማቸው የዴሞክራሲ ማሳለጫ ተቋማት ውስጥ አንዱ በሆነው በኢፌዴሪ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አማካኝነት ከመሰንበቻው ገቢራዊ ሆኗል። ኮሚሽኑ ከሐምሌ 2008 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መስከረም 2009 ዓ.ም ድረስ በአንዳንድ የኦሮሚያና የአማራ አካባቢዎች በተከሰተ ሁከት እንዲሁም በደቡብ ክልል ጌዴኦ ዞን ብሔርን መነሻ ባደረገ ግጭት አማካኝነት የተፈጠሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን አስመልክቶ ሰሞኑን ለህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት በጥናት ላይ የተመሰረተ ሪፖርት አቅርቧል። በኮሚሽኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዲሱ ገብረእግዚሐብሔር አማካኝነት የቀረበው ሪፖርት፤ በተጠቀሱት አካባቢዎች የ669 ሲቪሎችና የፀጥታ አስከባሪዎች ህይወት ለህልፈት መዳረጉን አስረድቷል።

በኮሚሽኑ የምርመራ ውጤት መሰረት ከሟቾቹ ውስጥ 495ቱ ህይወታቸው ያለፈው በኦሮሚያ ክልል በተነሳው ብጥብጥና ግጭት ሲሆን፤ የቀሪዎቹ ህይወት ያለፈው በአማራና በደቡብ ክልሎች ውስጥ ነው። ኮሚሽኑ በኦሮሚያ ክልል 15 ዞኖችና 91 ወረዳዎች ውስጥ ተገኝቶ ባደረገው ምርመራ፤ የግጭት አዘል ተቃውሞዎቹን መንስኤዎችንና አባባሽ ምክንያቶችን ዘርዝሯል። በመሆኑም ስር የሰደደ የመልካም አስተዳደር ችግርና የመብት ጥሰት፣ የሥራ አጥነት ችግር ሰፊ መሆን፣ የልማት ፕሮግራሞች መዘግየትና መታጠፍ፣ ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ያላት ጥቅም በሕግ ተደንግጎ ተግባራዊ አለመደረግ በመንስኤነት የተጠቀሱ ናቸው። በአባባሽ ምክንያትነት ደግሞ በሀገራችን በአሸባሪነት የተፈረጀው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (OLF)፣ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (OMN) እና ሌሎች የሚዲያ አውታሮች የህዝቡን ምሬት አስታከው፣ ፖለቲካዊ ፍላጎታቸውን እውን ለማድረግ ከፍተኛ አሉታዊ ሚና እንደተጫወቱ በሪፖርቱ ላይ ተመልክቷል።

በምሥራቅ አርሲ፣ በባሌ፣ በምዕራብ ጉጂና በጉጂ ዞኖች በጦር መሣሪያ የተደገፈ ውጊያ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ በደቡብ ምዕራብና በምዕራብ ሸዋ ዞኖች፣ በሶዶ፣ በአዳአ በርጋ፣ በሜታ ሮቢ፣ በደንቢ የሙሉ ቀን ውጊያ የነበረ በመሆኑ የፀጥታ ኃይሎች የወሰዱት ዕርምጃ ሕግን የተከተለ፣ ተመጣጣኝና ተገቢ እንደነበር በሪፖርቱ ላይ ተመልክቷል። በምዕራብ አርሲ፣ በሻሸመኔና በአርሲ ነገሌ ተመሳሳይ ውጊያ የተካሄደባቸው በመሆናቸው የተወሰደው ዕርምጃ ተገቢ ነው ሲልም አክሏል። በሌላ በኩል በአዳሚ ቱሉ ማረሚያ ቤት 14 እስረኞች ሊያመልጡ ሲሞክሩ በጥበቃ ኃላፊዎች መገደላቸው ህግን ያልተከተለ፣ አላስፈላጊና ተመጣጣኝ አይደለም ብሏል። በባሌ ዞን ሮቤ ከተማና በራይቱ ወረዳ የተካሄደው ሰልፍ በጦር መሣሪያ ያልተደገፈ በመሆኑ፣ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት ርምጃ የሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተመጣጣኝ አለመሆኑን ገልጿል።

በምሥራቅና በምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች በአወዳይ ከተማ በተወሰደው ርምጃ 28 ሰዎች መሞታቸውንም የተወሰደው ርምጃ ህግን ያልተከተለና ተመጣጣኝ ያልሆነ መሆኑም ተመልክቷል። ከአዚህ በተጨማሪም በምስራቅ ወለጋ በነቀምቴ ከተማ 12 ሰዎች ህግን ባልተከተለና ተመጣጣኝ ባልሆነ መንገድ መገደላቸውም ተገቢ አለመሆኑን አመልክቷል።

በአጠቃላይ በኦሮሚያ ሁከትና ብጥብጥ እንደሚነሳ እየታወቀ፤ ርምጃ ባልወሰዱ በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት አመራር አካላት በህግ እንዲጠየቁ ኮሚሽኑ ሃሳብ ያቀረበ ሲሆን፤ በአዳሚ ቱሉ ማረሚያ ቤት 14 ታራሚዎችን የገደሉ የጥበቃ ሠራተኞች በወንጀል ክስ ሊመሰረትባቸው ይገባል ብሏል። ኦነግና ተባባሪዎቹ እንዲሁም የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ አመራርና አባላት ሊጠየቁ እንደሚገባም ኮሚሽኑ ለምክር ቤቱ ሃሳብ አቅርቧል።

በአማራ ክልል የተለያዩ ዞኖች በነበረው ተቃውሞና ግጭት 110 ሲቪሎች ሲገደሉ 30 የፀጥታ ኃይሎች ተመሳሳይ ዕጣ ገጥሟቸዋል ብሏል—ኮሚሽኑ። 276 ሲቪሎችና 100 የፀጥታ አስከባሪዎች የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸውም ተመልክቷል። በክልሉ የተከሰተው ግጭትና ተቃውሞ መንስኤዎች ስር የሰደደ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ፍትህ ማጣት፣ የቦታ አሰጣጥ ችግር፣ ኢ-ፍትሐዊ ግብር አጣጣልና የኑሮ ውድነት መሆናቸው ተገልጿል።

የወልቃይት ጉዳይ በጊዜ መልስ ሊያገኝ አለመቻሉ፣ የአማራ መሬት ለሱዳን ተሰጥቷል የሚል ቅስቀሳ መኖሩ፣ በሲቪክ የትምህርት መጽሐፍ ላይ ያልታረመው የክልሎች ካርታ በአባባሽ ሁኔታዎች የተጠቀሱ ናቸው። ተመጣጣኝ ያልሆኑ ግድያዎች በአማራ ክልል መፈጸመቸውን ያስታወቀው ኮሚሽኑ፤ በጎንደር አዘዞ፣ በደንቢያ፣ በወንበራ፣ በደባርቅ፣ በደብረ ታቦር፣ በስማዳ፣ በእንጅባራ እንዲሁም በዳንግላ ተመጣጣኝ ያልሆኑ ግድያዎች ተፈፅመዋል።

በጎንደር ከተማ ማራኪ በሚባለው ቦታ የፌዴራል ፀረ ሽብር ግብረ ኃይል ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ በወሰደው ዕርምጃ 12 የፀጥታ ኃላፊዎችና አራት ሲቪሎች መገደላቸውን በምርመራ መረጋገጡን ያስታወቀው ኮሚሽኑ፤ በማረሚያ ቤት የተወሰደው እርምጃ ሕግን የተከተለ ነው ብሏል። በአማራ ክልል ብሔር ተኮር ጥቃት በመካሄዱ 11 ሺህ 678 የትግራይ ተወላጆች መፈናቀላቸውንም በሪፖርቱ ላይ ተመልክቷል። በመሆኑም በተፈጠረው ረብሻና ብጥብጥ ለተከሰተው ሞት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት መውደም አጥፊዎች ተለይተው ለህግ እንዲቀርቡ ኮሚሽኑ ሃሳብ አቅርቧል።

በተመሳሳይ ሁኔታም በጌዴኦ ዞን አራት ወረዳዎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች በተቀሰቀሰ ብሔር ተኮር ግጭት 34 ሰዎች መገደላቸውን በምርመራ ማረጋገጡን ያወሳው ኮሚሽኑ፤ የግጭቱ መንስዔ የመልካም አስተዳደር እጦትና የእኩል ተጠቃሚነት አለመኖር፣ በዲላ ከተማ በሚገኘው ጊምቦ የገበያ ማዕከል ለሳሪንደን አክሲዮን ማኅበር እንዲሰጥ ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠውን ብይን የዞኑ አስተዳደር ለመቀበል አለመፈለጉና ዞኑ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀው ከጌዴኦ ውጪ ያሉ ብሔሮችን ዞኑን ለቀው እንዲወጡ ሲካሄድ የነበረ ቅስቀሳ ውጤት ነውም ብሏል።

ከሞቱት በተጨማሪ 178 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱንና ከጌዴኦ ብሔር ወጪ ያሉ 8 ሺህ 450 የተለያዩ ብሔሮች አባላት መፈናቀላቸውም ተመልክቷል። ለዚህ ግጭትና ሕይወት መጥፋት እንዲሁም አካል መጉደል በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት አካላት በህግ እንዲጠየቁ ኮሚሽኑ ሃሳብ አቅርቧል። የጌዴኦ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ጌህዴድ)፣ የዞኑ የአመራር አካላትና ፖሊሶች በነበራቸው የመቀስቀስና የማደራጀት ሚና በህግ ፊት መቅረብ እንደሚገባቸው ኮሚሽኑ ለህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ሃሳብ አቅርቧል። ምክር ቤቱም ሪፖርቱን አዳምጦ በጥልቀት ከተወያየበት በኋላ ሚያዚያ 12 ቀን 2009 ዓ.ም ሪፖርቱን በማፅደቅ ውሳኔ አሳልፏል።

እንግዲህ ማንኛውም ይህን በጥቅል ያቀረብኩትን የኮሚሽኑን ሪፖርትና የፓርላማውን ውሳኔ የሚያነብ ሰው ሁለት ጉዳዩችን ለመገንዘብ የሚችል ይመስለኛል። አንደኛው ከሪፖርቱ በመነሳት የኢፌዴሪ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ከጊዜ ወደ ጊዜ አቅሙን እያጎለበተ መምጣቱን ይገነዘባል። የተቋሙ ሪፖርት  በጥናት ላይ የተመረኮዘ፣ የተጠቀሱት ቦታዎች ድረስ በመንቀሳቀስ የችግሩን መንስኤ ነቅሶ ያወጣ፣ ገለልተኛና ሚዛናዊ የሆነ ብሎም ሁሉንም አካላት ተጠያቂ ያደረገ ስለሆነ ይህንኑ ለመገንዘብ የሚከብድ አይመስለኝም። ሁለተኛው ደግሞ ኮሚሽኑ እንደ ዴሞክራሲ ማሳለጫ ተቋምነቱ ስርዓቱ ራሱን በራሱ የሚያርምና የትኛውም አካል ከህግ በላይ መሆን እንደማይችል ያሳየ መሆኑን ነው።

እናም በእኔ እምነት ይህን መሰሉ ተቋም የሀገራችንን ዴሞክራሲ በማስፋት የህግ የበላይነትን የሚያረጋግጥ በመሆኑ በየትኛውም የውጭ ሃይል ሊተካ አይገባም። ይልቁንም አቅሙን ይበልጥ በመገንባት አሁን እያከናወነ ካለው በላይ ተግባር እንዲወጣ ሊታገዝ ይገባል። እንደ ማንኛውም ሀገር ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮች መጣራት የሚገባቸው ሀገሪቱ ይህን ጉዳይ እንዲከውን ባቋቋመችው ተቋም እንጂ በውጭ ሃይል አይደለም።

እዚህ ሀገር ውስጥ እንደ ሂዮማን ራይትስ ዎችና አምንስቲ ኢንተርናሽናልን የመሳሰሉ ራሳቸውን በሰብዓዊ መብት ስያሜ ጆብነው የሚንቀሳቀሱ የርዕዩተ-ዓለም ሲራራ ነጋዴዎች በምንም ዓይነት መንገድ ቦታ ሊኖራቸው አይችልም፤ አይገባምም። ምክንያቱም የዚህ ሀገር ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንጂ የውጭ ሃይሎች አይደሉም። የራሳችንን ችግር መፍታት የሚገባን በራሳችን ዴሞክራሲን ማሳለጫ መነገድ እንጂ በውጭ ሃይሎች ችሮታና ፈቃድ ላይ በሚመሰረት የዴሞክራሲ መዘውር አይደለም።

በመሆኑም የኢፌዴሪ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋምን የመሳሰሉ የዴሞክራሲ ማሳለጫ ተቋሞች ምንም እንኳን ከአቅም ጋር በተያያዘ የራሳቸው ችግር ቢኖርባቸውም በገለልተኝነት ስሜት ተግባራቸውን ለህዝቡ በመወገን እየተወጡ ያሉ ተቋማት በመሆናቸው ስራቸው “ይበል” የሚያሰኝ ነው። ወገንተኝነታቸውም ለህዝብና ለህዝብ ብቻ በመሆኑም፤ እንደ እነ ሂማን ራይትስ ዎች በውሸት ስም የሰብዓዊ መብት ጠባቂ ሆነው የተደራጁ አይደሉም።

ስለሆነም እነዚህ ሃይሎች ለከፈላቸው ሁሉ ይሰራሉ እንጂ፤ እንደ ኮሚሽኑ ሪፖርት ዓይነት የመንግስት አካላትን፣ አሸባሪዎችን፣ ተቃዋሚዎችንና ግለሰቦችን በልኬታቸው ተጠያቂ በማድረግ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ አይችሉም። ለነገሩ ከእኛ በላይ ስለ እኛ እነርሱ ሊያውቁ አይችሉም። እኛን ተክተው ስለ እኛ ሊሰሩም አይገባቸውም። የኮሚሽኑ ሪፖርት ከተዓማኒነት በዘለለ፣ ስርዓቱ ራሱን በራሱ የሚያርምነት አንዱ መንገድ በመሆኑ ከእነዚህ የኒዮ ሊበራል ርዕዩተ ዓለም አራማጆች ጋር እኩል ሚዛን ላይ ሊቀመጥ የሚችል አይደለም። ይቀመጥ ቢባልም፤ የኮሚሽኑ ስራ ሙሉ ለሙሉ ወደ ህዝብ ጎን የሚያጋድል ሲሆን፤ የአክራሪ ኒዮ ሊበራል ርዕዩተ-ዓለም አራማጆቹ ደግሞ ለሚከፍላቸው ቀኖና በመቆም የችግሩን ሐጢያት በአንድ ወገን ላይ ከመደፍደፍ ወደ ኋላ አይልም። እንዲህ ዓይነቱ ፍርደ ገምድልነት ደግሞ ዴሞክራሲን ከማቀጨጭ በስተቀር ምንም ዓይነት ፋይዳ የለውም። ስለሆነም ስርዓቱ ራሱን በራሱ ለማረም የሚያደርገው ጥረት በፅንፈኛ ኒዮ-ሊበራሎች የቅጥፈት አጀንዳ እንዳይዋጥ ብርቱ ጥረት ማድረግ የሚያስፈልግ ይመስለኛል።

እርግጥ ስርዓቱ ራሱን በራሱ የሚያርመው ለማንም ብሎ አየደለም። የሚፈጠሩ ችግሮች ፍላፃቸው መልሶ ወደ እርሱ ስለሚወረወሩ እንዲሁም የህዝቡን ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች እውን ካላደረገ የሚጎዳው ራሱ ስለሆነ ነው። እናም በሰብዓዊ መብት ስም የሚነግዱ የውጭ ርዕዩተ-ዓለም አራማጅ ሃይሎች ‘የእኛ እናውቅላችኋላን’ ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት በምንም ዓይነት ሁኔታ ስርዓቱ ራሱን በራሱ ለማረም የሚያደርገውን ቁርጠኛ አቋም ሊተኩ አይችሉም። ስለሆነም የዚህ ተግባር ባለቤት የሆነው የኢፌዴሪ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ስራዎች ሊበረታቱ፣ ሊጠናከሩና ወደፊትም ከዚህ በላይ ተግባራቸውን እንዲወጡ ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል እላለሁ።          

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy