Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ቃላችንን የምንጠብቅበት ፕሮጀክት

0 492

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ቃላችንን የምንጠብቅበት ፕሮጀክት/ዳዊት ምትኩ/

  ኢትዮጵያውያን ለሰንደቅ ዓላማችን የምንሰጠው ክብር ከማንም በላይ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ሰንደቅ ዓላማችን ሁሉም ነገራችን መሆኑን እንኳንስ ወዳጅ ጠላትም የሚመሰክርልን ሃቅ ነውና፡፡ ለምን ቢባል የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር ቀፎው እንደተነካ ንብ የተመሙበት የትናንት በስቲያው አድዋ፣ የትናንቱ የፀረ- ሻዕቢያው ትግል፣ በየስፖርት አደባባዩ የሚደምቀው ሰንደቅ ዓላማ የዚህ እውነታ አስረጅ ስለሆነ ነው፡፡ የዘመናት ቁጭትን ለሻረው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ብስራት ዜና ማጀቢያነት በግምባር ቀደምትነት መዋሉ ሳይዘነጋ ማለቴ ነው፡፡

ታዲያ “የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ” ፕሮጀክት ብለው የሰየሙት ይሁኑ “የዘመኑ ስጦታ” ያሉት ወገኖች ፕሮጀክቱ የመላው ኢትዮጵያውያን አሻራቸውን ያሳረፉበት የማንነታቸው መገለጫ እንደሆነ ጠንቅቀው የሚያውቁና ይገልፅልናል ባሉት ስያሜ መጥራታቸው የሚያኮራ ነው፡፡ ለማንኛውም ግን በዋና መጠሪያው “ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ” የሀገራችን ህዳሴ ማብሰሪያ የማንነታችን አሻራ መገለጫ ሆኖ ዛሬ ስድስተኛ ዓመቱ ላይ ደርሷል፡፡ እኔም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አሁን የሚገኝበትን ሁኔታ ላስቃኛችሁ ወደድኩ። እናም ትናንትን በስሱ እየዳሰስኩ ዛሬ የሚገኝበትን ሁኔታ እነሆ እላለሁ፡፡

“ዛሬ የትናንት ውጤት ነው” እንዲሉ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ስናነሳ ወደ አእምሯችን የሚመጣው “ባለቤቶቹ እኛ፣ መሃንዲሱ እኛው፣ ግንበኞች እኛው…” የሚለው የታላቁ መሪያችን አቶ መለስ ዜናዊ ንግግር ነው ቢባል ሁሉን የሚያስማማ ይመስለኛል፡፡ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጋቢት 24 ቀን 2004 ዓ.ም የመሠረት ድንጋይ የማኖር ሥነ- ሥርዓትን ተከትሎ በኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዘንድ የተንጸባረቀው ስሜትም እንዲሁ፡፡

ቀስቃሽና ቆስቋሽ ሳያስፈልገው፣ ዘር፣ ሃይማኖት፣ ጾታና ዕድሜ ሳይገድበው የምንጊዜውም የማንነቱ መገለጫ በሆነው ሰንደቅ ዓላማው ደምቆ ወደየአደባባዩ የተመመው መላው ኢትዮጵያዊ “ባለቤቱ እሱ፣ መሃንዲሱ ራሱ፣ ግምበኛው እርሱ…” የመሆኑን እውነታ ምላሽ የሰጠበት ሂደትም መቼም የሚዘነጋ አይሆንም፡፡ በዚህም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ለመገንባት ያለውን ቁርጠኝነት የ“ይቻላል” ምላሹን በመስጠት ታሪክ የማይዘነጋው ተግባር አከናውኗል፡፡

እንደሚታወቀው የግድቡ ግንባታ በበርካታ ክስተቶች የተሞላ ነው። በተለይም ለዘመናት አብሮን የዘለቀው ዓባይን የመገደብ አይሞከሬነት አስተሳሰብ ያከተመበትና የ“ይቻላል” አስተሳሰብ ለውጥ የተፈጠረበት፣ በየትኛውም የዓለማችን ክፍል የሚገኝ ኢትዮጵያዊ የዜግነት ድርሻውን ለመወጣት ቃል የገባበት እንዲሁም ምላሹን የሰጠበት ፕሮጀክት መሆኑ በዓለማችን በዜጎች ገንዘብና ባለቤትነት የሚገነባ ብቸኛው ፕሮጀክት መሆኑ ከፕሮጀክቱ ክስተቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

አዎ! ዛሬ የግድቡ መሰረተ ድንጋይ ከተጣለ ስድስተኛ ዓመቱ ነው፡፡ ታዲያ የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ስራው በተፈለገው ሁኔታና ፍጥነት በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ስድስት ሺህ አራት መቶ ሃምሳ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ግንባታው የተጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለዘመናት ጥቅም ሳይሰጥ የቆየው የዓባይ ወንዝ ኢትዮጵያን ለቆ ከሚወጣበት ከሃያ እስከ አርባ ኪሎ ሜትር መካከል ላይ እየተገነባ ይገኛል፡፡

ግንባታው በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ባካበተው የሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኩባንያና በሀገር በቀሉ የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፓሬሽን አማካኝነት እየተከናወነ ሲሆን፤ የመጀመሪያው ምዕራፍ ተጠናቆ ዋነኛ የግንባታ ሥራው በመፋጠን ላይ ነው፡፡ የግንባታ ሥራው ሲጠናቀቅ አንድ ሺህ 780 ሜትር ርዝመትና 145 ሜትር ከፍታ እንደሚኖረው የሚነገርለት የህዳሴው ግድብ ግንባታ፤ የሲቪል ሥራ የሚከናወነው በሳሊኒ ኮንስትራክሽን፣ የኤሌክትሮ እና የሃይድሮ ሜካኒካል ሥራው በብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፓሬሽን፣ የማማከሩ ተግባር ደግሞ የጣልያንና የፈረንሳይ መሃንዲሶች ጥምር ኩባንያ አማካኝነት እየተካሄደ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ታዲያ “ነገርን ነገር ያነሳዋል” እንዲሉ የግድብ ግንባታን ስናነሳ የዓላማችን ሃያሏ ሀገር አሜሪካ በ1930ዎቹ ያስገነባቸው የሁቨር ግድብ ይጠቀሳል፡፡ በኮሎራዶ ወንዝ ላይ የተገነባው የሁቨር ግድብ አሜሪካውያኑ ግሬት ዲፕረሽን ብለው በሚጠሩት አስቸጋሪ ወቅት ከተገነቡት ግድቦች መካከል አንዱ ነው፡፡ በወቅቱ የግድቡ ግንባታ የዕድገታቸው ዋነኛ መሰረት እንደሆነ በማሰብ በዜጎች ከፍተኛ መነሳሳትን የፈጠረ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡ የግድቡ ግንባታ ሥራ ለዜጎች ከፍተኛ የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉም እንዲሁ፡፡ በዚህም ለግድቡ የአርማታ ሥራ ብቻ 5000 ሺህ የሀገሪቱ ዜጎች ተሰማርተው ኑሯቸውን ለመግፋት አስችሏቸዋል፡፡ የሁቨር ግድብ ግንባታ ሥራ የከሎራዶ ወንዝን ተፈጥሯዊ የፍሰት አቅጣጫ ለማስቀየር ከአንድ ዓመት በላይ መፍጀቱንም ማስረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ታዲያ በዚህ እውነታ የምንረዳው ነገር ቢኖር የሁቨር ግድብ በበርካታ ጉዳዮች ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ  ግድብ ግንባታ ጋር የሚያመሳስለው ቢሆንም የሚለይበት ሁኔታ መኖሩንም ጭምር ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የወንዙን የፍሰት አቅጣጫ ለመቀየር የፈጀው ጊዜና ፍጥነት ከወንዙ መጠን ጋር ተዳምሮ ግድቡ በተፋጠነ መልክ እንዲከናወን ማድረጉ ተጠቃሽ ሲሆን፤ ይህም የስኬታማነቱን ደረጃ ፈጣንነት የሚያመላክት ነው፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም ሃያ አራት ሰዓታት ያለማቋረጥ እየተገነባ ነው። ከ10 ሺህ የሚበልጡ ሰራተኞችም በሥራው ላይ ተሰማርተው በከፍተኛ ሀገራዊ ስሜትና ኃላፊነት ተግባራቸውን በሀገራዊ ፍቅር ስሜት በማከናወን ላይ ናቸው፡፡ በዚህም የግንባታ ሥራው በመለዋወጫና ግብዓት ረገድ አንዳች ችግር ሳይገጥመው በተፈለገው ፍጥነት እንዲጓዝ አስችሎታል፡፡

ሀገር በቀሉ የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፓሬሽን በበኩሉ የኤሌክትሮ ሚካኒካልና የሃይድሮ ሜካኒካል እንዲሁም ተዛማጅ የመቆጣጠሪያ መሣሪያዎች ዲዛይን የማድረግ፣ የመፈብረክ፣ የማምረት፣ የመትከልና ፈትሾ የማስረከብ ስራውን በተገቢው ሁኔታ በመፈጸም አመርቂ ውጤት በማስመዝገብ ላይ ይገኛል፡፡ ይህም ሀገራዊ አቅምን በማጠናከር ረገድ ትልቅ አቅም እየፈጠረ በመምጣቱ፤ በዘርፉ ለሚካሄድ የግንባታ ሥራ ራስን በመቻል ረገድ ከፍተኛ ዕድል እየፈጠረ መሆኑ በገሃድ ያሳያል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተለያዩ ሁነቶችን ተሻግሮ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ በዚህም የግንባታ ሥራውን ከጋራ ተጠቃሚነት አኳያ በመመዘን ድጋፋቸውን ያንጸባረቁ ሀገሮች የተስተዋሉበት እንዲሁም ፍትሃዊ የውኃ አጠቃቀም ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት እንዲስብ አስችሏል።

በተቃራኒው ደግሞ ሥራውን ከመቃወም እስከ የማደናቀፍ ሴራ ጥንስስም ታይቶበታል፡፡ ነገር ግን መንግስትና ህዝብ በሰጡት ትኩረት የግንባታ ሥራው ላፍታም ሳይደናቀፍ በታለመለት መንገድ እየተፈጸመ አሁን በሚገኝበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ለዚህም በመላው ኢትዮጵያዊ የተፈጠረው መነሳሳትና የመንግስት የፀረ- ድህነት ትግል ቁርጠኝነት ለግንባታ ሥራው የእሰካሁኑ ጉዞ ስኬታማነት በምክንያት የሚጠቀሱ ዋና ዋና ጉዳዮች ናቸው፡፡

ሀገራዊው ቀደሚ አጀንዳ የሆነው የግድቡ ሥራ በአሁኑ ጊዜም የቅርብ ክትትል አልተለየውም፡፡ መላው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንደ “ዓይን ብሌናቸው” የሚንከባከቡት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በየዕለቱ በርካታ ዜጎች ይጎበኙታል፡፡ ይህም በሥራው ለተሰማሩ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ዜጎች ትልቅ የሞራል ስንቅ በመሆኑ ለሥራው መፋጠን ሚናው የላቀ ሆኗል፡፡

ግድቡ ለተለያዩ ዜጎችና ሀገር በቀል ተቋራጮች የዕውቀት መቅሰሚያ መንገድ በመሆኑ የነገን ብሩህነት ማመላከት ያስችላል፡፡ በተለይም የዓለማችን ከተፈጥሮ ጋር የሚሰማማ የኃይል ፍላጎትን የሚያሟላው የሃይድሮ ኃይል ማመንጫ ግንባታ ሥራ መስፋፋት ጋር ተያይዞ በዘርፉ ተሰማርቶ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችል በመሆኑ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው፡፡

በሌላም በኩል በሀገራችን በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ለሚገኘው የመሠረተ ልማት ግንባታ ምላሽ የሚሰጥ የሰው ኃይል መፈጠሩ ሀገራዊ ፋይዳው የላቀ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለማመን በሚያዳግት ሁኔታ እያስገመገመ ለመጣው የኢንቨስትመንት ፍሰት በቂ ምላሽ መስጠት የሚችል የኃይል አቅርቦት የሚያጎናጽፍ በመሆኑ፤ ለሀገራዊው ዕድገት ቀጣይነት ታላቅ ዋስትና እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡

የግድቡ ጠቀሜታ በዚህ ብቻ የተወሰነ አይደለም። ከጎረቤት ሀገሮች ጋርም ኢኮኖሚያዊ ትስስራችንን ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራል፡፡ ይህም ለአካባቢው ሀገራት የጋራ ዕድገትና አስተማማኝ ሠላም መስፈን አስተዋጽኦው የጎላ ነው፡፡

በመሆኑም በጀርባችን ላይ የተፈናጠጠው ድህነትን አሽቀንጥረን ለመጣል ለጀመርነው የፀረ-ድህነት ትግል ከግብ መድረስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል። እርግጥም የግድቡ ግንባታ ሥራ ፅናትና ቁርጠኝነት በተሞላበት ሁኔታ በመካሄድ ላይ መሆኑን ለሚመለከተው ሰው የሚያጎናፅፈው ሀገራዊ ኩራት ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል ከማንም የሚሰወር አይመስልኝም፡፡

አዎ! የነገዋን ኢትዮጵያ የሚያመላክተው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሥራ መሠረተ ድንጋይ ከማኖር ጀምሮ መላው ኢትዮጵያዊ የሰጠው ምላሽ ለስኬታማነቱ በር መከፈት ከፍተኛ ድርሻ እንደነበረው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ በወቅቱ በመላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የተፈጠረው መነሳሳት በተለይ ለግድቡ ግንባታ መጀመር ከፍተኛ ድርሻ የነበራቸው ታላቁ መሪያችን አቶ መለስ ዜናዊ ህልፈተ- ህይወት በኋላም “እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን” የሚል ቃል በመግባት ግለቱን ጠብቆ በመጓዝ ላይ ይገኛል፡፡ እርሳቸው እንዳሉትም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ “ባለቤቱ እኛው፣ ግንበኛውም እኛ፣ መሃንዲሱም እኛው…” በመሆን ዛሬ 57 በመቶ ደርሷል። ነገ ደግሞ እንጨርሰዋለን። ይህም ለሀገራዊው ልማታችን ምላሽ የሚሰጠውን ግድብ ማፋጠን መቻላችን ለፀረ – ድህነት ትግሉ ከግብ መድረስ ያለንን ቁርጠኝነት የሚያመላክት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ቃላችንን የምንጠብቅበት ሀገራዊ ፕሮጀከታችን መሆኑን ልንዘነጋ አይገባም፡፡ ሰላም!

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy