Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ቅንነት ማጣት እንደ መሰረታዊ ችግር

0 1,260

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ቅንነት ማጣት እንደ መሰረታዊ ችግር

(ሰለሞን ሽፈራው)

በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ጥቂት ነጥቦችን አንስተን እንድንነጋገር የፈለግኩት ያለምክንያት አይደለም፡፡ ይልቅስ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደፈሊጥ የተያዘ የሚመሰለው ከትምክህተኝነትና ከጠባብ ብሔርተኛ ፖለሪካዊ አመለካከት በመነጨ ጭፍን ስሜታዊነት ላይ የተመሰረተ ተቃውሞን የሙጥኝ ማለት፤ ቀና አስተሳሰብን ገድሎ የሚቀርብ ክፉ ወረርሽኝ እያዛመተብን ስለመሆኑ የሚሰማኝን ስጋት ለመግለፅ ነው ጉዳዩን ማንሳቴ፡፡ ስለዚህም እኛ ኢትዮጵያውያን ህዝቦች ቅንነት ከማጣት በሚመነጭ መሰረታዊ ችግር ምክንያት የጎሪጥ እንድንተያይና እርስ በርሳችን እየተጠላለፍን አብረን እንድንወድቅ ለማድረግ የሚሹ ሃይሎች መኖራቸውን ለመጠቆም ያህል አንዳንድ ነጥቦችን እያነሳሁ ትዝብቴን ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡

እንግዲያውስ አሁን በቀጥታ ወደዋነኛው ርዕሰ ጉዳያችን እናልፍና ለመሆኑ ቅንነት የማጣት ችግር እንዴት ነው የሚገለፀው? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ በሚያስችለን መሰረተ ሃሳብ ዙሪያ መመልከት ያለብንን ነጥቦች እናነሳለን፡፡ እናም ከዚህ አኳያ በቅድሚያ ግልፅ መሆን የሚገባው ጉዳይ ቢኖር፤ ቀና አስተሳሰብ የሰው ልጆችን ከተራው የቤት እንሰሳ የተለየንና እንዲሁም ደግሞ የተሻልን ከሚያደርጉን ተፈጥሯዊ ፀጋዎቻችን ምናልባትም ዋነኛው ጠቃሚ ዕሴት ነው ተብሎ እንደሚታመንነው፡፡

ምክንያቱም፤ የሰብዓዊው ፍጡር ዓይነተኛ መገለጫዊች ተደርገው ከሚወሰዱት በጎ ጎኖቹ ቀዳሚ ስፍራ ሊይዝ የሚችለው በተለይም፤ ለሕገህሊና የመገዛት ወይም ደግሞ የመዳኘት ፍቃደ-ልቦናን የታደለበት ተፈጥሯዊ ባህሪው ነው ማለት ይቻላልና ነው፡፡ ይህን መሰረተ ሃሳብ ይበልጥ ግልፅ ለማድረግ እንዲረዳንም፤ በሰው ልጆች ማህበራዊ መስተጋብር ውስጥ ብቻ አስፈላጊነቱ የሚታመንበትንና ለሌላው ፍጡር ግን የማይሰራውን የሞራል ብቃት መለኪያ ዕሴት ማንሳት ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ በግልፅ አነጋገር፤ ቅንነት ማጣት እንደመሰረታዊ ችግር ከሚገለፅባቸው መንገዶች መካከል አንዱ፤ የሞራል ኪሳራ ሊያስከትል በሚችለው ማህበራዊ ቀውስ፤ ወይም ስነምግባራዊ ዝቅጠት ምክንያት የሚመጣ የአስተሳሰብ ድህነት ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ በሌላ አባባል፤ ጉዳዩ ለቡድናዊ ፍላጎታቸው መሟላት ሲሉ ከገዛ ራሳቸው ህሊና ጋር ጭምር እስከመጣላት የሚደርሱ ሰዎች ቁጥር እየተበራከተ ሲመጣና ነገሮችን በምክንያታዊነት አገናዝቦ ከመረዳት ይልቅ በጅምላ የመፈራረጅን እንሰሳዊ ባህሪ የማስቀደም አዝማሚያ የበላይነት እንዲያዝ የሚፈቅድ ማህበረሰብ ሲፈጠር ነው ቅንነት የማጣት ችግር እንደወረርሽኝ ሊዛመት የሚችለው፡፡

ስለዚህም እንደኔ ግንዛቤ ከሆነ፤ ከላይ ለማመልከት በተሞከረው መልኩ የሚገለፅ የቅንነት ማጣት ችግር የዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ስር እየሰደደ ስለመምጣቱ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ከኢሞራላዊ ሰብዕና የሚመነጭ ሆነ ብሎ ቀናውን ነገር የማጣመም አባዜ እንድንጋለጥ ያደረገን ምክንያትም ደግሞ፤ በተለይም “የበቁ የነቁ” ተደርገው የሚቆጠሩ አንዳንድ ምሁራን ዜጎቻችን፤ የፖለቲካዊ ስልጣን ፍለጋ ከሚፈጥረው የዕርስ በርስ ሽኩቻ በሚመነጭ ጭፍን ጥላቻ ተነሳስተው የሚያውጠነጥኑትን የበቀል ሴራ ለሀገርና ለወገን የሚበጅ የስርዓት ለውጥን ለማምጣት ሲባል የሚደረግ “የነፃነት ትግል” አስመስለው የሚያቀርቡበት አግባብ መኖሩ ነው፡፡

ለዚህ አስተያየቴ የተሻለ ማሳያ ሊሆን የሚችል ተጨባጭ ምሳሌ ማቅረብ ካለብኝም፤ የወቅቱ አገር አቀፋዊ አሳሳቢ ችግር ተደርጎ የሚወስደውን የትምክህትና የጠባብ ብሔርተኝነት አመለካት ፅንፍ ወክለው፤ የመሪ ተዋናይነቸትን ሚና ሲጫወቱ ከምናውቃቸው የተቃውሞው ጎራ ፖለቲካ ልሂቃን መካከል ዋነኞቹን ብቻ አነስተን እንደ አብነት መመልከት ይቻላል፡፡ ስለሆነም ከዚሁ የመጣጥፌ ማጠንጠኛ መሰረተሃሳብ ጋር በተያያዘ መልኩ ስማቸው ተደጋግሞ የሚነሳውን ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማሪያምንና እንዲሁም የእርሳቸው የቅርብ ወዳጅ እንደሆኑ የሚነገርላቸውን ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳን ነው የማስቀድመው፡፡

እንግዲህ ስለነዚህ ሁለት ጎምቱ ምሁራን ማንነት ጉዳይ የማያውቅ አንባቢ ይኖራል የሚል እምነት ስለሌለኝ በቀጥታ ወደፍሬ ነገሩ ልለፍና ተጠቃሾቹ ግለሰቦች ዕውቀታቸውን ሁሉ አሟጥጠው በመጠቀም የቅንነት ማጣት ችግር ሰለባ ሊያደርጉን ሲጥሩ የሚስተዋሉበት አግባብ ምን እንደሚመስል ከብዙ በጥቂቱ ለማስታወስ ልሞክር፡፡ ስለዚህም ላለፉት 25 ዓመታት የወደቀውን የአገዛዝ ስርዓት ለጋሲዮን ለማስቀጠል ያለመ የተቃውሞ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ከምናውቃቸው የትምህክት ኃይሎች ጎን በመቆም ረገድ፤ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙት ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማሪያም፤ በስር ነቀል የስርዓጥ ለውጥ ሂደቱ ላይ ያላቸውን እጅጉን የመረረና የከረረ ጥላቻ ከመቸውም ጊዜ ይልቅ የገለፁበትን “መክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ” የሚል ርዕስ ያልን መፀሐፋቸውን ያነበብን ሰዎች አሳምረን የተገነዘብነው ይመስለኛል፡፡

እናም ፕሮፌሰሩ በዚያው የአፄውን ዘመን ኢትዮጵያ ከአሁኑ ስርዓት ይልቅ ለህዝቧ የምትመች ሀገር እንደነበረች አድርገው በተረኩበት ጨለምተኛ ድርሳናቸው ላይ “ትክክለኛውን የኦሮሞ ታክ ሊፅፍልን የሚችለው ዶክተር ፍቅሬ ቶሎሳ ብቻ ነው የሚል እምነት አለኝ” ሲሉ አንድ አስገራሚ “ትንቢት” ፅፈው እንደነበርም ጭምር አንባቢያን የምንዘነጋው ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ የፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማሪያም “ትንቢት” ይፈፀም ዘንድም ተጠቃሹ ምሁር ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ብዙም ሳይቆዩ “የኦሮሞና የአማራ ትክክለኛ የዘር አመጣጥ” በሚል ርዕስ የፃፉትን የታሪክ ድርሳን አሳትመው ገበያ ላይ ስለማዋላቸው ሰማን፡፡ የፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ መፀሐፍ ታትሞ ገበያ ላይ የዋለው ባሳለፍነው 2008 ዓ.ም መጨረሻ ግድም እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፤ ልክ በዚያው ሰሞን በተለይም የኦሮሚያንና የአማራን ብሔራዊ ክልሎች ለማተራመስ የሞከሩ ሃይሎች ያቀነባበሩት ሀገር አውዳሚ የሁከት ተግባር መቀስቀሱም ብዙዎችን ያነጋገረ ጉዳይ ነው ማለት ይቻላል፡፡

እኔን እንደ አንድ የዚህች አገር ዜጋ እጅግ በጣም ያስገረመኝ ተያያዥ ጉዳይ ግን “የኦሮሞና የአማራ ትክክለኛ የዘር አመጣጥ” የሚል ርዕስ የተሰጠውን መፀሐፍ ያዘጋጁት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ፤ ባሳለፍነው መስከረም ወር 2009 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ታትሞ ከወጣ ሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የተናገሩት መርዘኛ መልዕክት ያዘለ ንግግር እንደሆነ ልብ ይባልልኝ፡፡ ስለዚህም ፕሮፌሰሩ የተጠቃሹን መፀሐፋቸውን አጠቃላይ ይዘት አስመልክተው ለሰንደቅ ጋዜጣ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ “ለመሆኑ በአማራና በኦሮሞ ብሔር ተወላጆች መካከል የሚስተዋለውን አለመግባባት የፈጠረው መሰረታዊ ምክንያት ምን ይመስልዎታል? ይሄ በአንዳንድ የገዥው ፓርቲ ሰዎች ሲነገር የምንሰማው ትምክህተኝነትና ጠባብ ብሔርተኛ የሚባለው የአመለካከት ችግርስ በእርግጥ አለወይ?” የሚለውን የጋዜጠኛ ይርጋ አበበ ጥያቄ የመለሱበት አግባብ ምን ይመስል እንደነበር ማስታወስ ጉዳዩን በተሻለ መልኩ ግልፅ የሚያደርግልን ይመስለኛል፡፡

ምክንያቱም፤ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ከላይ በትምህርተ ጥቅስ ውስጥ የተቀመጠውን መሰረተ ሃሳብ ያዘለ ጥያቄ ቀርቦላቸው ሲመልሱ የተናገሩትን ነገር ይዘት አሁንም ደግሞ ማንበብና ማረጋገጥ እንደሚቻለው፤ በአማራና በኦሮሞ ብሔር ተወላጆች መካከል አለ የሚባለውን ቅራኔ፤ የትግራይ ምድር ፖለቲከኞች ወይም የህወሐት ሰዎች የፈጠሩት የቅርብ ጊዜ ሰው ሰራሽ ክስተት እንደሆነ አድርገው የገለፁበት እጅግ መሰሪነትን የተላበሰ ቅኚት በራሱ የታሪክ ቀመስ መፀሐፋቸው ዓላማ ምን እንደሆነ እንረዳ ዘንድ ያስችላልና ነው፡፡

ይህን ስል ግን፤ ከላይ የተጠቀሰውን “የኦሮሞና የአማራ ትክክለኛው የዘር አመጣጥ” የተሰኘ ታሪክ ቀመስ ድርሳን የፃፉት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳም ሆኑ ሌላ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ምሁር፤ በሁለቱ ብሔሮቻችን ወንድማማች ህዝቦች መካከል ምንም አይነት መሰረታዊ የጥቅም ቅራኔ አለመኖሩን የሚያስረዳ ታሪካዊ ዳራ እያጣቀሰ ነገር ለማርገብ የሚያስችል የፅሁፍ መረጃ በማቅረብ ረገድ የሚጠበቅበትን ጥረት ማድረግ የለበትም ማለቴ እንዳመስልብኝ፡፡ እኔን እንደ አንድ የዚች አገር ዜጋ ያሳሰበኝ ጉዳይ፤ በአማራና በኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ልሂቃን መካከል ብዙውን ጊዜ የሚስተዋለው የአመለካከት ልዩነትን መሰረት ያደረገ ፍጥጫ እንዲረግብ፤ ትግርኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያንን በጠላትነት መፈረጅ ያስፈልጋል ብሎ እንደማመን የሚቆጠር አንድምታ ያዘለ አዝማሚያ ጎልቶ የተንፀባረቀበት የፕሮፌሰሩ ቃለ ምልልስ ነው እንጂ ጭራሽ መፃፍ አልነበረባቸውም ማለቴ አይደለም፡፡

ምንም እንኳን መፀሐፋቸው ላይ የኢትዮጵያን ታሪክ በሚመለከት የተነሱት አብዛኛዎቹ ነጥቦች አንባቢያንን ለሌላ ተጨማሪ ብዥታ የሚዳርግ የተረት-ተረት ባህሪ ጎልቶ በሚታይበት ኢ.ተአማኒ አቀራረብ ታግዘው መተረካቸው በራሱ ጥያቄ ማስነሳቱን ባውቅም፤ ግን ደግሞ ፕሮፌሰሩ “ጠባብ ብሔርተኝነትና ትምህክተኝነት ወዘተ የሚባለው ነገር ሆነ ተብሎ ሁለቱን ትልልቅ ብሔሮች በጠላትነት ዓይን እንዲተያዩና በመካከላቸው ዕርስ በርስ ያለመተማመንን የሚያሰፍን መሰጋጋት እንዲኖር በሚፈልጉ የፖለቲካ ሃይሎች የተፈጠረ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲያቸው አካል ነው፤ በእርግጥም ደግሞ ያን ማድረግ ባይችሉ ኖሮ አሸንፈው ስልጣኑን አይቆጣጠሩትም ነበር” ሲሉ “የሁሉም ችግሮቻችን ምንጭ ወያኔ (ኢህአዴግ ነው” እንደማለት በሚቃጣው የተቃዋሚ ፖለቲከኞች ጭፍን የጥላቻ ስሜት ሰንደቅ ጋዜጣ ላይ የተናገሩት ይበልጥ አስገርሞኛል፡፡

ሰውየው “የኦሮሞና አማራ ትክክለኛ የዘር አመጣጥ” በሚል ርዕስ የፃፉት ታሪክ ቀመስ ድርሳን ታትሞ መውጣቱን ተከትሎ ስለጉዳዩ ሌላ ሰፋ ያለ ቃለምልልስ ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ ሰጥተው እንደነበር ባይዘነጋም፤ እኔ የፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማሪያም ሌላው ገፅታ መሆናቸውን የተረዳሁት ግን፤ ሁዋላ ላይ ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር መሰል ያደረጉበትን ቃለምልልስ ሳነብ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ያምሆነ ይህ ግን እኚሁ ፍቅሬ ቶሎሳ የተባሉ ግለሰብ ያሳተሙትን መፀሐፍ አስመልክተው በየ የግሉ ፕሬስ ሚዲያ ላይ ያስተላለፉት መልዕክት ለትምክህትና ለጠባብ ብሔርተኛ አስተሳሰብ አቀንቃኝ ተቃዋሚ ቡድኖች የአንድ ሰሞን ፕሮፖጋንዳ እንደዋነኛ ግብዓት ሳይወሰድ እንዳሰልቀረ ነው የገባኝ፡፡

ለዚህ ጥሩ ማሳያ ሊሆን የሚችለው ደግሞ ሀገራችንን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ ለማድረግ ያስገደዳት የሁከትና ብጥብጥ እንቅስቃሴ የተስተዋለበት የጊዜና የቦታ ክልል ነው፡፡ ሌላው ሰውየው ከደሙ ንፁህ እንዳልሆኑ የሚያረጋግጥልን ምክንያት፤ በውጭ የሚኖሩት የትምክህትና የጠባብ ብሔርተኝነት ፖለቲካዊ አቋምን አቀንቃኝ ቡድኖች ኢትዮጵያን ለማተራመስ ያለመ ውዥንብራቸውን የሚያዛምቱባቸው፤ የመረጃ አውታሮች በሙሉ፤ ወደለየለት ፀረ የትግራይ ተወላጆች ዘረኛ ፕሮፖጋንዳ ጠቅልለው የገቡት ከዚያን ጊዜ ወዲህ የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡

ከዚህ አኳያ በተለይም ጁውሐር መሐመድ በሚባለው ፅንፈኛ ግለሰብ ፊታውራሪነት የሚንቀሳቀሱት ዲያስፖራ የጠባብ ብሔርተኝነት ፖለቲካዊ አቋም አራማጅ ቡኖድች ከመቸውም ጊዜ ይልቅ ባፈጠጠና ባገጠጠ ቅንነት ማጣት ያቀነባበሩትን መስከረም 22 ቀን 2009 ዓ.ም የተከበረውን የኢሬቻ በዓል የማወክ ተግባር ተከትሎ ምን የሚል አሉቧልታ እንዳሰራጩ ማስታወስ የተሻለ አብነት የሚሆን ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም የኦሮሞ ህዝብ በየዓመቱ መስከረም 22 ቀን ቢሾፍቱ ላይ የሚያከብረውን የኢሬቻ በዓል ምክንያት በማድረግ ወደስፍራው የመጣውን በሚሊዮን የሚቆጠር የዘንድሮው በዓል ታዳሚ ተተግነው የራሳቸውን ድብቅ ፖለቲካዊ አጀንዳ ለማሳካት የሞከሩት የኦ.ነ.ግ ጀሌዎች፤ በፈጠሩት ትርምስ ውስጥ ለከፋ ጉዳት ተዳርገው የሞቱትን በርካታ ንፁሃን ወገኖቻችንን፤ “መንግስት ራሱ ነው በጦር አውሮፕላን የጨፈጨፋቸው” የሚል የበሬ ወለደ ዓይነት ውንጀላ ፈጥረው በማራገብ ህብረተሰቡን ግራ ለማጋባትና በስርዓቱ ላይ ለማሳመፅ ያለመ መርዘኛ ፕሮፖጋንዳቸውን ሲያዛምቱ የተስተዋሉበትን አስነዋሪ ዘገባ ማስታወስ ተገቢ ሆኖ ይሰማኛል፡፡

እናም እንደኔ እንደኔ፤ ይሄ መንግስት ያን ያህል የሚሊዮኖች የሚቆጠር ሰላማዊ ህዝብ ላይ ጥቃት እንዲፈፅሙ የጦር አውሮፕላኖችን አሰማራ ብሎ በመወንጀል ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ከመሞከር የተሻለ፤ ቅንነት የማጣትን መሰረታዊ ችግር አሳምሮ ሊገልፀው የሚችል ተጨባጭ እውነታ አይገኝም የሚል ፅኑ እምነት አለኝ፡፡ እንዲሁም ደግሞ ከዚያን ጊዜው አሳዛኝ ክስተት ወዲህ፤ የምስራቅ ኦሮሚያ ዞኖችን ከኢትዮጵያ ሶማሌ ብሔራዊ ክልል ጋር በሚያዋስኗቸው አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ በአቶ ጅሁዋር መሐመድ የሚመሩት ጠባብ ብሔርተኞቹ ዲያስፖራ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፤ የግጭቱን ምንጭ የትግራይ ተወላጅ የኢፌዴሪ መንግስት ባለስልጣናት እንደሆኑ አድርገው ሲቀሰቅሱ መሰንበታቸውንም ታዝበናል፡፡

ስለሆነም፤ እነዚህ – እነዚህን የመሳሰሉ ምንም ዓይነት ተጨባጭ የመረጃ ምንጭ መጥቀስ ሳያስፈልጋቸው፤ አንዱን ኢትዮጵያዊ ህዝብ ከሌላኛው ወገኑ ጋር ለማቃቃርና ከተቻለም ወደለየለት የብሔር ጦርነት ገብተን እቺን ሀገር ሌላዋ ሶማሊያ እንድናደርጋት የሚያደርግ ዕርስ በርስ የመጠፋፋት አደጋን ሊያስከትሉብን በሚሞክሩት ፅንፈኛ ቡድኖች የሚቀነባበሩ መርዘኛ ቅስቀሳዎች፤ የተባባሱበት ዋነኛ ምክንያት ቀና አስተሳሰብን እንደ “ያለመሰልጠን መገለጫ” የመቁጠር አዝማሚያ ስር እየሰደደ የመጣበት አጠቃላይ እውነታ በመኖሩ ነው ብሎ መደምደም የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ይህን መሰሉ ከለየለት የጥላቻ ፖለቲካ በሚመነጭ ጭፍን ስሜታዊነት ወደ አንደኛው የአስተሳሰብ ፅንፍ ብቻ ጭልጥ ብሎ የመነዳት አዝማሚያ እንደ መልካም ፖለቲካዊ ባህል ተቆጥሮ ከትውልድ ወደትውልድ ሊተላለፍ የሚገባው እንዳልሆነ ለመረዳት ያንያህልም ዕውቀት የሚጠይቅ ጉዳይ ባይሆንም፤ ግን ደግሞ ከላይ ለአብነት የተጠቀሱትን ሁለት ፕሮፌሰሮች ጨምሮ ሌሎችም ጥቂት የማይባሉ አንጋፋ ምሁራን ዜጎቻችን የሙጥኝ ሲሉት መስተዋላቸው በወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ የማይናቅ አሉታዊ ተፅእኖ እያሳደረ ይገኛል፡፡

ይሄው የብሔር፤ ወይም ደግሞ የሃይማኖት ልዩነት ላይ የተመሰረተን ቡድናዊ ፍላጎት ለማሳካት ከመሻት ከሚመነጭ ፅንፈኛ አቋም ጋር በተያያዘ መልኩ የሚገለፅ የቅንነት ማጣት ችግር፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ህዝቦች በረጅሙ የጋራ አሊያም ደግሞ የተናጠል ታሪካችን ሒደት ውስጥ ያዳበርናቸውን እጅግ ጠቃሚ ባህላዊ፣ ስነልቦናዊና እንዲሁም መንፈሳዊ ዕሴቶች፤ ረብየለሽ ተደርገው እንዲቆጠሩ የሚያደርግ ኢ-ምክንያታዊ ተቃውሞን፤ ወይም ደግሞ ድጋፍን የሚያረታታ አሉታዊ ሚና እየተጫወተ ስለመሆኑ ለመገንዘብም የፖለቲካ ሳይንስ ማጥናትን አይጠይቅም፡፡ ስለዚህ ቅንነት ከማጣት የሚመነጭ መሰረታዊ ችግር ከፖለቲካዊ ርዕሰ ጉዳይነት አልፎ፤ የተራ ተርታውን ኢትዮጵያዊ ዜጋ ጥሮ ግሮ የመኖር ዕጣ ፈንታ በእጅጉ የሚያወሳሰአብ ፈርጀ ብዙ ፈተና እየፈጠረ ስለመሆኑ በርካታ ማሳያዎችን እያነሳን መተማመን እንደምንችል ሊሰመርበት ይገባል ባይ ነኝ እኔ፡፡ ስለሆነም፤ በተለይ ትውልድ የመቅረፅ ኃላፊነትን የመወጣት ግዴታ የተጣለባቸው መንግስታዊ፤ ማህበራዊና ሃይማኖታዊ ተቋማቶቻችን፤ ቀና ቀናውን ነገር ከማሰብ ስለሚገኝ ፈርጀ ብዙ ጠቀሜታ በቅጡ የማስተማርን አስፈላጊነት ከመቸውም ጊዜ ይልቅ ትኩረት ይሰጡት ዘንድ ይሰማኛል፡፡ መዓሰላማት!

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy