Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር የተከሰሱት በእስራትና በገንዘብ ተቀጡ

0 588

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ህጋዊ ፈቃድ ሳይኖራቸው ኢትዮጵያውያንን በህገ ወጥ መንገድ ወደ ውጭ ሀገር የላኩና የመላክ ሙከራ ያደረጉ ግለ ሰቦች በገንዘብና በእስራት ተቀጥተዋል፡፡

ተከሳሽ ሊራንሶ ጫሚሶ ሱሞሮ በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ሀዲያ ዞን ሸሸጎ ወረዳ የሆሳዕና ከተማ ነዋሪ ነው፡፡

ከኢፌዲሪ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢትዮጵያውያንን ለስራ ወደ ውጭ ሀገራ የመላክ ፈቃድ ባይኖረውም ዜጎችን ወደ ተለያዩ ሀገራት ለስራ እልካችኋለሁ በማለት ወንጀል ሲሰራ መቆየቱን በፍርድ ቤቱ ተጣርቶ ከተሰጠው ውሳኔ መረዳት ተችሏል ፡፡

ደመቀች ላምቦሮ፣ልብነሽ ሞሎሮና አሚር ጫኬቦ የተባሉትን የሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች ለስራ ቤሩት ሊልካቸው ተስማምቶ ሻሸመኔ ከተማ  የህክምና ምርመራ እንዲያከናውኑ ካደረገ በኋላ ከሁለቱ ከእያንዳንዳቸው 5000 ብር ከሌላኛዋ ደግሞ 5400 ብር ተቀብሏቸው የጉዞ ቀነ ቀጠሮ አስቀምጠው ተለያዩ፡፡

ተከሳሹ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እንዳጠናቀቀ ተበዳዮቹ በድጋሜ ሻሸመኔ እንዲመጡ አድርጎ ቦሌ ዓለም ዓቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ አደረሳቸው፡፡

ተከሳሹ ከተጓዦች ከእያንዳንዳቸው ተጨማሪ ስድስት መቶ ብር ሲጠይቃቸው የተፈጠረው አንባጓሮ  ግለሰቡን በአካባቢው ስምሪት ላይ በነበሩ የጸጥታ አካላት እጅ ውስጥ አስገባው፡፡

ጉዳዩን የተመለከተው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን መርምሮ በተከሳሹ ላይ የዘጠኝ ዓመት ጽኑ አስራትና የሁለት ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ ወስኖበታል፡፡

አበበ ቦንጃ ደግሞ የአዲስ አበባ ነዋሪ ሲሆን በህገ ወጥ መንገድ ገንዘብ ተቀብሎ ሰዎችን ወደ ውጪ ሀገር ለስራ በመላኩና በመሞከሩ በህግ ቁጥጥር ስር ውሎ ለፍርድ ቀርቧል፡፡

ግለሰቡ የኢፌዲሪ ወንጀል ህግ አንቀጽ 598/1/ን ተላልፎ ህጋዊ ፈቃድ ሳይኖረው ከትርሃስ መሃሪ ስምንት ሺህ ብር ተቀብሎ በሱዳን አድርጋ  ኩዌት እንድትገባ ወደ ሱዳን መላኩ ተረጋግጧል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ምጽላል ተስፋየም በሱዳን በኩል ወደ ቤሩት ለመጓዝ 4000 ብር ከፍላ አውሮፕላን ጣቢያ ስትገባ ሰነዶቹ ሀሰተኛ በመሆናቸው ጉዞዋ ተስተጓጉሏል፡፡

ተከሳሹ ተጨማሪ 4000 ብር ከከፈለችው ድጋሚ እንደሚልካት ተስማምተው በተገናኙበት ጊዜ አስቀድማ ለፖሊስ በሰጠችው ጥቆማ ተይዞ ለህግ ቀርቧል፡፡

ጉዳዩን የተመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን መርምሮ በተከሳሹ ላይ የሁለት ዓመት ጽኑ እስራት ወስኖበታል፡፡

ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ከአደገኛ እጽዋትና ሀገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ቀጥሎ በሶስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ዓለም ዓቀፍ ወንጀል ነው፡፡

ከዘርፉ በየዓመቱ 32 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ እንደሚገኝበትም በተባበሩት መንግስታት የአደንዛዥ እጽና ወንጀል ቢሮ (UNODC) ይፋ ያደረገው መረጃ ይጠቁማል፡፡

የኢፌዲሪ ወንጀል ህግ አንቀጽ 596-98 በህገ ወጥ መንገድ ወደ ውጪ መውጣት፣ እንዲወጣ ማነሳሳትና እንዲሰደድ ማድረግ ወንጀል መሆኑን በግልጽ አስፍሯል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy