Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በሙሰኞች ላይ ተገቢ እርምጃ እንደሚወሰድ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ ገለጹ

0 732

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በሙስና ድርጊቱ ተሳታፊ ሆነው በተገኙ አካላት ላይ ተገቢ እርምጃ እንደሚወሰድ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ ገለጹ።

የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ 59 ወረዳዎችና 12 ዋና ዋና ከተሞች በሙስናና በሕብረተሰቡ ግንዛቤ ላይ አተኩሮ ያካሄደውን ጥናት ይፋ አድርጓል።

የጥናቱ ውጤት በአዳማ ከተማ ይፋ በተደረገበት ወቅት የተገኙት የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ እንደገለጹት በክልሉም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ ሙስና መልኩን እየቀየረና እየተስፋፋ መጥቷል።

በተለያዩ ወረዳዎች የተካሄደው የዩኒቨርሲቲው ጥናትም ሙስና በክልሉ ለሕብረተሰቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትና ዕድገት ማነቆ መሆኑን በግልጽ ያሳየ እንደሆነ ተናግረዋል።

ሙስና በክልሉ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ ከመሆኑ በተጨማሪ ህዝብን ለምሬትና ለቅሬታ እየዳረገ በመምጣቱ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት ጥናቱ ጠቃሚ መሆኑን ነው የገለጹት።

“የጥናቱ ውጤት በዋናነት ችግሩ የት ላይ እንደሆነ አሳይቶናል” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ የፍትህ አካላት በሙስና ውስጥ ተዘፍቀው ፍትህ በማጓደል በሕብረተሰቡ ላይ ተደራራቢ ወንጀል እየፈጸሙ ስለመሆኑ ጥናቱ ማመላከቱን አስታውቀዋል።

ችግሩን ለማስወገድ የጥናቱን ውጤት መሰረት በማድረግ በየደረጃው ከሚገኙ አመራሮች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የሃይማኖት አባቶችና መላውን ሕብረተሰብ ያሳተፈ ሥራ እንደሚከናወን አስረድተዋል።

ሙስና ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማነቆ ከመሆን ባለፈ የመልካም አስተዳደር እጦት መንስኤ እየሆነ በመምጣቱ በድርጊቱ ተሳታፊ ሆነው በተገኙ አካላት ላይ ተገቢ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ፕሬዚዳንቱ አሳስበዋል።

እንደ አቶ ለማ ገለጻ በፍትህ ተቋማት፣ በገቢዎች፣ በግብርና ታክስ፣ በግዥ አስተዳድር፣ በመሬት፣ በመንግስት የልማት ድርጅቶች፣ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማትና በሌሎች ተያያዥ ሴክተሮች ላይ ሕብረተሰቡ አገልግሎትን በገንዘብ እየገዛ ስለመሆኑ ጥናቱ አመልክቷል።

በተጨማሪም “ጥናቱ ሙስናን የማይሸከም ተተኪ ትውልድ ማፍራት እንደሚገባ የጠቆመ ጥናት ነው ሲሉም ” ተናግረዋል።

የጥናቱን ውጤት ያቀረቡት የዩኒቨርሲቲው የምርምር ቢሮ ዲን ዶክተር አለሙ ዲሳሳ፣ ጥናቱ ሙስና በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የማወቅና ለቀጣይ መፍትሄ የማፈላለግ ዓላማ አንዳለው አመልክተዋል።

በአመለካከትና በተግባር  ችግሩ በስፋት የሚታይባቸው አካባቢዎች ላይ ሕብረተሰቡ ያለውን ዕውቀት፣ ግንዛቤና አመለካከትን በመለየት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለመፍታትም ጠቀሜታ እንዳለውም ገልጸዋል።

ዶክተር አለሙ እንዳሉት፣ ጥናቱ ለሙስና ተጋላጭ የሆኑ ዘርፎች፣ የችግሩን ምንጭ እንዲሁም ሙስና የሚያስከትለው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ  ጉዳቶችን  አመላክቷል።

በዚህም የፍትህ፣ የገቢዎች፣ የመሬት አስተዳድር፣ የግዥ ዘርፍ፣ የማዘጋጃ ቤት አገልግሎት፣ የጤና ተቋም፣ የልማት ድርጅቶችና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሙስና በስፋት የሚታይባቸው ተቋማት እንደሆኑ መለየታቸውንና በመንግስት ልዩ ትኩረት የሚያስፈልጋቸው ሴክተሮች መሆናቸው ተረጋግጧል።

ሕብረተሰቡም በሙሰኞች ላይ አስተማሪ እርምጃ ሲወሰድ አለማየቱ “ለውጥ አይመጣም” የሚል ተስፋ የመቁረጥ አዝማሚያ በስፋት እየያዘ መምጣቱ በጥናቱ በግልጽ መለየቱንም ጠቁመዋል።

የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ለሚ ጉታ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ሥራ ጎን ለጎን የሥርአቱ አደጋ የሆነውን ሙስናን ለማስወገድ በሚደረግው ጥረት ውስጥ ከክልሉ መንግስት ጋር በመሆን በጥናት የተደገፉ ምርምሮችን እያካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

ጥናቱ በራሱ ግብ እንዳልሆነ የተናገሩት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሁሴን ኡስማን ናቸው።

“በጥናቱ ሙስና ይስተዋልባቸዋል ተብለው በተለዩ ዘርፎች ላይ በአሰራርና አደረጃጀት የተደገፉ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥና ጠንካራ ህጋዊ እርምጃዎች መወሰድ ይገባል” ብለዋል ።

ጥናቱ የክልሉ መንግስት በመደበው አምስት ሚሊዮን ብር የተካሄደ ሲሆን የጥናቱ ውጤት በአዳማ ከተማ ይፋ ሲደረግ ከ800 በላይ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

በመድረኩ ላይ የክልሉ መንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ተወካዮች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የዞንና የከተማ አስተዳድርና ከንቲባዎች ተገኝተዋል።

ምንጭ፡- ኢዜአ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy