Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በቅናት ዛር የታወረ የከሸፈ ፖለቲካ

0 595

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በቅናት ዛር የታወረ የከሸፈ ፖለቲካ
ሰለሞን ሽፈራው
እንደኔ እምነት ከሆነ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች አጠቃላይ ሁኔታለዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ማበብ የሚያመች አይደለም ፡፡ ይህን ስል የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራንን በጥናት ላይ የተመሰረተ ሰፊ ሙያዊ ትንታኔ የሚጠይቅ ጉዳዩእንጂ ትዝብት አዘል በተራ የግለሰብ ግርድፍ ምልከታ የሚበየን ሊሆን እንደማይችል መገንዘብ አቅቶኝ አይደለም፡፡ የሀገራችን የፖለቲካ ኃይሎችአጠቃላይ እንቅስቃሴ ከአንድ ትውልድ ዕድሜ እምብዛም የማይበልጥ ታሪክ ያለው ፤ ከትናንትእስከ ዛሬ ፈተና የሚስተዋለው፤ ከመሳፍንታዊ አስተሳሰብ በሚመነጭ የቡድን ሴራ ዱለታ ጎራ እየለዩ እርስ በእርስ የመጠላለፍ ችግር ለትችት የሚጋብዝ ገጽታ ተላብሶ ይታይልና ነው፡፡
ከዚሁ በኢትዮጵያ በተደራጀ መልኩ የሚደረግ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ከተጠናወተው የሴረኝነት አባዜ ጋር በተያያዘ ብዕር ያነሳሁባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት እንዳልነበሩ ማስታወስ ይቻላል፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ፤ ዛሬም ሌላ ርዕሰ ጉዳዩን አንስቼ የሀገራችን ህዝቦች ዘለቄታዊ የጋራ ዕጣ ፈንታ አይበጅምየምለውንየፖለቲካ አቀንቃኞች፤ በዜሮ ድምር አስተሳሰብ ላይ ተመሰረተ አቋም ለመንቀፍ የምሞክርበትን መጣጥፍ አዘጋጅ ዘንድ የገፋፋኝን ነባራዊ እውነታ መታዘቤ አልቀረምና በእንዲህ መልኩ መንደርደርን መረጥኩ፡፡
አሁንም ድረስ የኢትዮጵያን ሀገር አቀፋዊ የፖለቲካ ድርጅቶች እንቅስቃሴ በሚደጋገም ውስጣዊ ችግር እንዲታመስና አልፎም እንዲፈራርሱ ጭምር እያደረገ ያለ ክፉ ሴራ ባህል ሆኗል፡፡ ከመጋረጃው በስተጀርባ ጎራ ለይቶ የሚዶለት ቡድናዊ ሴራ ሲነሳ የችግሩ አመጣጥ ማጋለጫ ታሪካዊ ዳራዎችም ማስታወስ ይጠበቅብናል፡፡ ስለሆነም የሀገራችንን መድበለ ፖርቲየፖለቲካ ስርዓት እንቅስቃሴ በማቀጨጭ ረገድ የማይናቅ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ስለመሆኑ ከሚታመንበት እየተቧደኑ ከሚዶለት ሴራ በሚመነጭ የጭፍን ጥላቻ ስሜት ምክንያት እርስ በርስ እየተጠላለፉ ከመውደቅ ጋር በተያያዘ፤ ስማቸው ተደጋግሞ ይነሳል፡፡ የዘመነ “ነጭ-ሽብር ቀይ-ሽብር” አሳዛኝ ታሪካችን መሪ ተዋናዮች የነበሩት ኢ.ህ.አ.ፓ. እና መ.ኢ.ሰ.ን. ናቸው ማለት ይቻላል፡፡
በተለይም ደግሞ ግማሽ ሚሊዮን ያህል ቀለም ቀመስ ወጣት ዜጎች ለዕልቂት የተዳረጉበትን የደርግ “ነፃ እርምጃ” ያስከተለ አጉል ትንኮሳ እንደነበር ተደርጎ የሚወሰደው “ነጭ-ሽብር” ተሰኘ የከተማ ውስጥ ውጊያ በመጀመር ታሪክ ይቅር የማይባለውን ስህተት ስለመፈፀሙ የሚነገርለት ኢ.ህ.አ.ፓ ሴራ የሙጥኝ ከማለት ጋር ተያይዞ እርስ በእርስ እየተጠላለፉ የመውደቅን ክፉ ፖለቲካዊ ባህል ወልዶ ስለማሳደጉ በበርካታ ፀሐፍት የተሰናዱ ድርሰትም ጭምር የሚያመላክቱት ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ፤ ከደርግ ውድቀት በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ የተከፈተውን አዲስ የፖለቲካ ታሪክ ምዕራፍ ገና ከመነሻው ጀምሮ ለቅልበሳ አደጋ በሚያጋልጥ መልኩ ሲፈታተኑት የምናውቃቸው የትምክህት አስተሳሰብን የሚያቀነቅኑ ተቃዋሚ የፖለቲካ ሃይሎች በህቡዕ እየተቧደኑ ፀረ ሕገመንግስት የአመፅ ሴራ የመዶለት ፈሊጥ የቀድሞ ኢ.ህ.አ.ፓ ርዝራዦች እጅ እንዳለበት የሚናገሩ አስተያየት ሰጪዎች ጥቂት እንዳልሆኑ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡
በእርግጥም ደግሞ ኢህአዴግ መራሹ የኢትዮጵያ ህዝቦች ፀረ ጭቆና የትጥቅ ትግል የደርግን ወታደራዊ አምባገነን የአገዛዝ ስርዓት አስወግዶ አዲሱን የታሪክ ምዕራፍ የከፈተበት የግንቦት 20ው ድል ክፉኛ ካስደነገጣቸውና ወሽመጥ ሚቆርጥ መርዶ ከሆነባቸው መካከል፤ በደርግ ቀይ-ሽብር እሳት ከመሞት የማምለጥ ዕድል የገጠማቸው የቀድሞው ኢ.ህ.አ.ፓ. አመራር አካላት ዋነኞቹ እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ እናም “ተራራን በገመድ ጎትቶ ለመጣል ከመሞከር ከንቱ ድካም” ጋር እልህ አስጨራሽ የትጥቅ ትግል ሂደት የደርግ ኢ.ስ.ፓ.ን እጅግ ግዙፍና ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀ ሰራዊት አሸንፎ ወታደራዊውን አምባገነን ስርኣት የገነባውን የአፈና መዋቅር ማፈራረስ እንደሚቻል ሲረዱ፤ በድል አድራጊዎቹ ኢህአዴጎች ላይ የመረረ ጥላቻ ያደረባቸው ዲያስፖራ የኢ.ህ.አ.ፓ ርዝራዦች፤ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ስር ነቀል ለውጡን ለማኮላሸት ያለመ ሴራቸውን ማውጠንጠን የያዙት ወዲያውኑ እንደነበር የሚዘነጋ ጉዳይ አይደለም፡፡
ከዚህ አኳያ ባለፉት 25 ዓመታት ስር ነቀል የስርዓት ለውጥ ጉዞ፤ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የመቀልበስና የወደቀውን የአገዛዝ ስርዓት ለመመለስ ከመፈለግ የመነጨ አቋም ላይ ተመሰረተ ፅንፈኛ ፖለቲካዊ አመለካከትን ከማቀንቀን ቦዝነው የማያውቁት ተቃዋሚ የትምክህት ሃይሎች “ሲፋቁ ኢ.ህ.አ.ፓ ሆነው የሚገኙ” ጸረ ኢህአዴግ ሴራ በማውጠንጠን ተግባር ተጠምደው ያልተስተዋሉበት አጋጣሚ እንዳልነበር ይታመናል፡፡ ይልቁንም ደግሞ ከአራቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄና (ብአዴን) የቀድሞው ኢ.ህ.አ.ፓ ውስጥ የአመራር ሰጭነት ሚና እንደነበራቸው በሚነገርላቸውና ከዚሁ የተነሳም “ወያኔዎቹ የተቀዳጁት ድል ለኛ ነበር የሚገባን” የሚል ብርቱ የቅናት ስሜት ሳያድርባቸው እንዳልቀረ የሚታሙት ዲያስፖራ የተቃውሞው ጎራ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ስትቴጂስቶች፤ ከባህር ማዶእስከ አገር ቤት በተዘረጋው መረባቸው አማካኝነት የሚያውጠነጥኑት ሴራ ግንባር ቀደም ኢላማ ስለመደረጉ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡
በተለይም ብአዴን ከሌሎቹ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የበለጠ የቀድሞ ኢ.ህ.አ.ፓ ርዝራዦች የመሪ ተዋናይነትን ሚና ይጫወቱበታል ተብሎ ስለሚታመንበትየዚህ የአመፅ ሴራ የማውጠንጠን ፖለቲካዊ የድብብቆሽ ጨዋታ ተጋላጭ እንዲሆን የሚያደርጉት ጉዳዮች እንደሚከተለው ሊገለፁ ይችላሉ፡፡ የመጀመሪያውና ዋነኛ ምክንያት እንደሚሆን የሚገመተው ነጥብ፤ የአሁኑን ብአዴንን የመሰረቱት የቀድሞው ኢ.ህ.አ.ፓ ውስጥ ይፈፀም የነበረውን ኢ.ዲሞክራሲያዊ ተግባር ተቃውመው የወጡ ጥቂት የፖርቲው አባላት ከመሆናቸው ጋር ከተያያዘ ተራ ምቀኝነትም ጭምር በሚመነጭ ክፋት ተነሳስተው ድርጅቱን ተቀባይነት ለማሳጣት ሲሞክሩ የሚስተዋሉበት ፖለቲካዊ ደባ ነው ቢባል ከእውነት መራቅ አይሆንም፡፡
ከዚሁ መሰረተ ሃሳብ ጋር ተያያዥነት ባለው መልኩ ሲገለጽ የሚስተዋለው ሌላ ሁለተኛ ነጥብ ደግሞ፤ አብዛኛዎቹ የቀድሞው ኢ.ህ.አ.ፓ ርዝራዦች፤ የአማራ ብሔር ተወላጆች በመሆናቸው ምክንያት፤ ብአዴንን የራሱ ድርጅታዊ ነፃነት የሌለው የህወሐት “ተለጣፊ” ለማስመሰል ከሚሞክሩበት ፍረጃቸው በሚመነጭ ትምክህታዊ የተቃውሞ ጎራ ፖለቲካ ጭፍን የማጥላላት ዘመቻ አማካኝነት እያሳደሩ ያሉት አሉታዊ ጫና ቀላል ግምት የሚሰጠው አለመሆኑ ነው፡፡ ለዚህ ሀሳቤ ተጨባጭ ማረጋገጫ የራሱ የብአዴን ድርጅታዊ ልሳን የሆነው፤ “አብዮታዊ ዴሞክራሲ መጽሔት፤ በየካቲት 2009 ዓ.ም እትሙ ሌላው ከዚህ መሰረተ ሃሳብ ጋር ተያያዥነት ባለው መልኩ የወጣው ፅሁፍ ነው፡፡ የቀድሞው ኢ.ህ.አ.ፓ ርዝራዦች፤ ብአዴን (ኢህአዴግ) ላይ ሆን ብለው ሲፈጽሙት የሚስተዋል ፖለቲካዊ ደባ ደግሞ፤ እነርሱ እራሳቸውን ለአማራ ብሔረሰብ ከኢህአዴጎች ይልቅ የሚቆረቆሩ አማሮች አድርገው በመቁጠር ገዥውን ፓርቲ የሚያብጠለጥሉበት ያፈጠጠና ያገጠጠ ትምክህታዊ ፕሮፖጋንዳ ነው፡፡ እናም ከዚህ የተነሳ መላው የተቃውሞው ጎራ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ከትናንት እስከ ዛሬ ለሚታወቅበት፤ ሶስቱን የኢህዴግ አባል ድርጅቶች በ”ህወሐት ተለጣፊነት” ፈርጆ የማብጠልጠን ዘመቻ ፈር ቀዳጆቹ በተለይም የቀድሞው ኢ.ህ.አ.ፓ ውስጥ ተሳትፎ እንደነበራቸው የሚናገሩት የሴራ ፖለቲካ መሪ ተዋንያኖች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡
ይልቁንም ደግሞ የአማራነትን ጭምብል አጥልቀው የሚተውኑበት አግባብ ሲታይ፤ ብአዴን /ኢህአዴግ የአማራን ህዝብ ለመወከል የሚያስችል ምንም ዓይነት ማህበራዊና ፖለቲካዊ መሰረት የሌለው እንደሆነ አድርጎ ከመቁጠር በሚመነጭ የለየለት ትምክህተኛ አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ዘረኝነትን በክልሉ ተወላጅ ወጣቶች ዘንድ ማስፋፋቱ እንዳልቀረ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ለዚህ የተሻለ የመረጃ ምንጭ ሊሆነኝ ይችላል፤ራሱ ብአዴን/ኢህአዴግ በየወሩ የሚያሳትመው አብዮታዊ ዴሞክራሲ መጽሔት የየካቲት 2009 ዓ.ም እትሙ ላይ “ሁለት ስለት ባለው ቢላዋ ድርጅታችንን ለማረድ ሴራው ተጠናክሮ ቀጥሏል” በሚል ዓብይ ርዕስ ስር ያቀረበው ወቅታዊ ችግሮቹን በስፋት ያተተበት ጽሁፍ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም፤ መጽሔቱ የብአዴን ድርጅታዊ ልሳን እንደመሆኑ መጠን፤ በስድስት ንዑሳን ርዕሶች ከፋፍሎ የየካቲት ወር እትሙ ላይ ያወጣውንና የሴራ ፖለቲካ ሰለባ የመሆን አደጋ እንደተጋረጠበት በማያሻማ መልኩ አምኖ መቀበሉን የገለፀበትን ተጠቃሹን ትንታኔ ለዚህ ርዕሰ ጉዳያችን የተሻለ ማረጋገጫ አድርገን ብንወስደው ተገቢነት ይኖረዋልና ነው፡፡ ስለሆነም በጉዳዩ ዙሪያ መፅሔቱ ላይ የተሰጠው ድርጅታዊ ማብራሪያ ሲታይ፤ ብአዴን /ኢህአዴግ ስርዓቱንም ጭምር ላልተጠበቀ የቅልበሳ አደጋ ሊያጋልጡ የሚችሉ እጅጉን አሳሳቢ የአመለካከት ችግሮችን፤ በቅጡ ለይቶ የማወቅ ስራ ሰርቷል ብለን ተስፋ እንድናሳድር የሚያደርግ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡
ይህን ስልም ደግሞ፤ ምንም እንኳን የድርጅቱን ውስጣዊ መዋቅር ለትምክተኞቹ የተቃውሞው ጎራ ፖለቲከኞች ሴራ እንዲጋለጥ የማድረግ አፍራሽ ሚና የሚጫወቱ አባላት ጭምር መኖራቸውን አምኖ እስከ መቀበል መድረስ በራሱ ሊደነቅ የሚገባው የአመራሩ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት መገለጫ ሆኖ ቢሰማኝም፤ ግን ደግሞ ችግሮቹን ለይቶ በማወቅ ብቻ አደገኛውን አዝማሚያ መቀልበስ እንደማይቻል የጋራ ግንዛቤ ይወስድበት ለማለት ነው፡፡ አለበለዚያ ግን፤ በተለይም ለአማራ ክልል ህዝብ መብትና ጥቅም መከበር፤ ከብአዴን/ኢህአዴግ ይልቅ የሚቆረቆሩ መስለው ለመታየት የሚሞክሩበትን ከዘመነ “ነጭ-ሽብር – ቀይ-ሽብር” ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ መሳፍንታዊ የሴራ ፖለቲካቸውን በመተወን ረገድ የተካኑ ትምክህተኛ ተቃዋሚ ሃይሎች፤ ወደለየለት የ“እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” ዓይነት አጥፍቶ መጥፋት እያመሩ ስለመሆናቸው ለመናገር ነቢይ መሆን አይጠበቅብንም፡፡
ከዚህ አኳያ የሚስተዋለውን በተለይም ብአዴንን ለማንበርከክና ከሚመራው የአማራ ክልል ህዝብ ለመነጠል ሲባል የትምክህተኞቹ ተቃዋሚ የፖለቲካ ሃይሎች ሴራ በተደጋጋሚ የታዘብኩባቸውን ክስተቶች እያነሳሁ ላስታውስ ብል አንባቢን ማሰልቸት ይሆንብኛል፡፡ በ2006 ዓ.ም መገባደጃ ግድም፤ አንድ ምንጩ ያልታወቀና የኢትዮጵያ መንግስት ከአማራ ክልል መሬት ቆርሶ ለጎረቤት ሀገር ሱዳን እንደሰጠ የሚያወሳ መሰረተቢስ ወሬ ከወደ ባህርማዶ በመናፈሱ ምክንያት የክልሉን ህዝብና መንግስት ለማቃቃር ሲሞክር የታዘብንበትን አደገኛ ፕሮፖጋንዳዊ ዘመቻ ማስታወስ ብቻ በቂ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ይመስለኛል፡፡
በወቅቱ በክልላዊ መንግስቱ ርዕሰ ከተማ ባህር ዳር የሚኖሩ የሀገር ውስጥ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፤ ምናልባት “ፍኖተ ዴሞክራሲ” የተሰኘውን የኢ.ህ.አ.ፓ ሬዲዮ እንደዋነኛ ኢትዮጵያን ለማተራመስ ያለመ የውዥንብር ፈጠራ ፕሮፖጋንዳቸው ማዛመቻ አድርጎ ተጠቅሞበታል፡፡ አቶ ክፍሉ ታደሰ ሳያቀነባብረው እንዳልቀረ የሚገመተውን የ“መሬታችንን ወያኔ ኢህአዴግ ቆርሶ ሸጦብናል” ሴራ ተግባራዊ የማድረግ ተልዕኮ ወስደው ለአንድ ሰሞን በጉዳይ አስፈፃሚነት የተንቀሳቀሱበትን የአመፃ አዝማሚ የነበረውን የትምክህት ሃይሎች አቋም ሳስታውስ ብዙ ስጋት ተሰምቶኝ እንደነበር ሳላወሳው ማለፍ አልፈልግም ፡፡ በተለይ የክልላዊ መንግስቱ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አቶ ዓለምነው መኮንን የ“መሬታችን ተቆርሶ ለሱዳን ተሰጠብን” ሰበብ ፈጥረው ለተቃውሞ ሰልፍ የወጡ ወገኖች ላቀረቡት ጥያቄ ትክክለኛውን ምላሽ ለመስጠት ሲሞክሩ የተናገሩት “የአማራን ህዝብ ክብር የሚያንቋሽሽ ስድብ ነው” በሚል ተተርጉሞባቸውና ከቶውንም በእርሳቸው ላይ ሌላ መጠነ ሰፊ የተቃውሞ ሰልፎ ተጠርቶ ከስልጣን እንዲወርዱ የተደረገበትን እጅ ጥምዘዛ ማስታወስ ይቻላል፡፡
ከዚያን ጊዜው በተቃዋሚ የሴራ ፖለቲካ መሪ ተዋናዮች የተቀነባበረ ብአዴንን የማንበርከክ ሙከራ ጀምሮ፤ በ2008 ዓ.ም የወልቃይትን ጉዳይ ሰበብ በማድረግ ለሌላ ዙር እጅ ጥምዘዛ ሲረባረቡ እስከተስተዋሉበት የትምክህተኞቹ ተቃዋሚ ቡድኖች ፖለቲካዊ ደባ ድረስ ጉዳዩን እንደጉድ የማራገብና በቀላሉ የማይጠፋ ሀገር አውዳሚ የአመጽ እሳት ለመጫር የሚያስችላቸውን መርዘኛ ፕሮፖጋንዳ በማዛመት ረገድ እንዴት ባለ የተጠና ቅንብር ታግዘው እንደተንቀሳቀሱ ልብ ብሎ ለታዘበ ሰው ብዙ ጥያቄዎችን እንድናነሳ የሚያስገድድ ስጋት ያጭራል፡፡ ምክንያቱም የሴራ ፖለቲካ ስትራቴጂስቶች ተደርገው ለሚወሰዱት ዲያስፖራዎቹ ጽንፈኛ ተቃዋሚዎች፤ በልሳንነት እንዲያገለግሉ ሲባል በምዕራቡ ዓለም ተቋቋሙት እነ “ኢሳት” እና “ፍኖተ-ዲሞክራሲ” የሚደግሱልን ሀገራዊ ጥፋት አልበቃ ያለ ይመስል፤ የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ (ቪ.ኦ.ኤ.) ጭምር፤ ብአዴንን ለማንበርከክ የሚውጠነጠነው ፖለቲካዊ ሴራ አካል ሲሆን የታዘብንባቸውን ተደጋጋሚ እውነታዎች መጥቀስ ይቻላልና ነው፡፡
እኔ እንደዚህ አምርሬ እንድፅፍ የተገደድኩት በተለይም ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የአማራ ክልልን ህዝብ መንግስት ለማተራመስ ያለመ የሁከት ተግባር ስትራቴጂ ነድፈው እንደሚንቀሳቀሱ ተደጋግሞ የተነገረላቸው የኤርትራው ግፈኛ አገዛዝ ጉዳይ አስፈፃሚ ቡድኖች የሚታወቁበትን “የአማራ ህዝብ ራሱን በራሱ እያስተዳደረ አይደለም” የሚል ኢ.ምክንያታዊ የተቃውሞ ፖለቲካ መከራከሪያ እያነሱ ነባራዊውን ጥሬ ሀቅ ለማፋለስ ሲቃጣቸው የሚደመጡ ትምክህተኛ ግለሰቦችን እዚሁ አገር ቤት ውስጥ እያፈላለጉ የሚያነጋግሩት ጋዜጠኞች ከጊዜ ወደጊዜ መበራከታቸውን በመታዘቤ ነው፡፡ ለእንደዚህ ዓይነቱ ሆነ ተብሎ በተጠና የሴራ ፖለቲከኞች ህቡዕ እንቅስቃሴ እየተቀነባበረ የሚሰነዘር መርዘኛ ፕሮፖጋንዳ ፈጣንና ህዝቡን ካላስፈላጊ ውዥንብር ሊታደግ የሚችል ታማኝ የመረጃ ምንጭ የተደገፈ አፀፋዊ ምላሽ የሚሰጥ አካል መኖር እንዳለበትይሰማኛል፡፡
ደግነቱ ግን፤ ብአዴን በዚህ ዓይነት የሴራ ፖለቲከኞች እንደሙያ ሲቆጥሩት በሚስተዋል ሆን ብሎ ነገር ማወሳስብ ደባ ምክንያት ሊያጋጥም የሚችል መሰል ፈተናን ተጋፍጦ በማለፍ ረገድ የረጅም ጊዜ ልምድ ያለው ድርጅት እንደሆነ ይታመናል፡፡ ለአብነት ያህልም የቀድሞውን ኢ.ህ.አዴ.ን የአሁኑን ብአዴን ከዛሬ 36 ዓመት በፊት ከመሰረቱት ጥቂት የትጥቅ ትግሉ ዘመን አንጋፋ ታጋዮች መካከል አንዱ የነበሩት አቶ ህላዊ ዮሴፍ ስለዚሁ ከሴራ ፖለቲካ የሚመነጭን ደባ ተጋፍጦ ስለማለፍ የድርጅታቸው ተደጋጋሚ ፈተና ጉዳይ ሲናገሩ የሰማሁትን ማስታወስ ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡
በ2008 ዓ.ም የተከበረውን የብአዴን 35ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ምክንያት በማድረግ ከፋና ፕሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ኤፍ ኤም 98.1 ሬዲዮ ጣቢያ ጋዜጠኛ ከአቶ ብሩክ ከበደ ጋር ቆይታ ባደረጉበት ቃለ ምልልስ ላይ ሲናገሩ ካደመጥኩት የትጥቅ ትግሉ ዘመን ታሪክ ትዝታቸው መካከል ለዛሬው መጣጥፌ የሚያስፈልጉኝን ጥቂት ነጥቦች ነቅሼ ላውጣና በማውጣት ሃሳቤን እቋጫለሁ፡፡
በገጣሚነታቸውም ጭምር የሚታወቁት አቶ ህላዊ፤ ብአዴንን ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ በዘለቀው ረጅም የትግል ጉዞ ስላጋጠሙት ውስብስብ ፈተናዎች ተጠይቀው ሲመልሱ “ብዙውን ጊዜ የድርጅታችንን ህልውና የሚፈታተኑ ችግሮች የሚያጋጥሙን በተለይም ክህደት ለመፈፀም በሚነሳ ውስጥ አዋቂ ግለሰቦች ከሚሸርቡብን ፖለቲካዊ ሴራና እንዲሁም ከሚፈፅሙት ደባ ጋር በተያያዘ ምክንያት ነው ማለት ይቻላል” የሚል ሃሳብ መሰንዘራቸውን አስታውሳለሁ፡፡ ድርጅታቸውን ገና በእንጭጩ ለመቅጨት የተሞከረባቸውን ሁለት ያህል የትጥቅ ትግሉ ዘመን የክህደት ተግባራት አውስተው ፈተናዎቹ ስለታለፉበት የዓላማ ጽናት መተረካቸውን ማስታወስ ይቻላል፡፡
ስለዚህ እኔም ሃተታዬን የማጠቃልለው ራሳቸው አቶ ህላዊ ዮሴፍ ከፃፉትና በትጥቅ ትግሉ ዘመን የኢ.ህ.ዴን (ብአዴን) ድርጅታዊ መዝሙር ከነበረው “ያልተንበረከክነው” የሚል ርዕስ ያለው ተወዳጅ ግጥም ላይ ተከታዮቹን ስንኞች በመጋበዝ ይሆናል፡፡ እነሆ ካልተንበረከኩት የብአዴን ታጋዮች ጋር አብረን እንዘምር…..
ስንቶች ተቸንፈው፤ ከጎዳናው ወጡ
ስንቶች ተኮላሽተው፤ ካረንቋው ዘቀጡ
ጥቂቶች ቆራጦች፤ ያልተንበረከክነው
ነገ ዕልፍ እንሆናለን፤ ታሪክ ምስክር ነው፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy