Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በቡና ወጪ ንግድ የተንሰራፉ ችግሮችን ለመፍታት 11 ጉዳዮች ተለይተው የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጀላቸው

0 861

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

  • ላኪዎችና አቅራቢዎች የጎንዮሽ ግንኙነት መፍጠር እንዲችሉ ይፈቅዳል

ከአሥር ዓመታት ወዲህ በበርካታ ችግሮች ተተብትቦ የኢኮኖሚ ዋልታነቱ እያሽቆለቆለ የሚገኘውን የቡና ዘርፍ ለመታደግ፣ 11 መሠረታዊ ጉዳዮች ተለይተው የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጀላቸው፡፡

በቡና ዘርፍ የተንሠራፋውን መጠነ ሰፊ ችግር ከመሠረቱ ለመፍታት ተነቅሰው የወጡ ጉዳዮች ላይ ማሻሻያ ለማድረግ አዋጅ፣ ደንብና መመርያዎች ተዘጋጅተው ከዘርፉ ዋነኛ ተዋናዮች ጋር ውይይት እየተካሄደባቸው ነው፡፡

የሕግ ማዕቀፍ ከተዘጋጀላቸው ጉዳዮች መካከል የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የቡና ዋጋ ተገማችና የተረጋጋ አለመሆን፣ ወደ ውጭ ከተላከ ቡና ተመጣጣኝ ዋጋ አለማግኘት፣ ቡና ላኪ ኩባንያዎችና የኅብረት ሥራ ዩኒየኖች እያደጉ አለመምጣት፣ የተቆላና የተወቀጠ ቡና ኤክስፖርት ለሚያደርጉ ተቋማት ተገቢውን ድጋፍ አለማድረግ፣ የግብዓትና የሎጂስቲክስ ዋጋ ንረት፣ ለቡና ዘርፍ ዕድገት ራሱን የቻለ የማበረታቻ ማዕቀፍ አለመኖር፣ በአገሪቱ የሚገኙ የቡና ተቋማት ተጠሪነታቸው የተበታተነ መሆን፣ የቡና ጥራት መጓደልና ሕገወጥ ንግድ መስፋፋት የሚሉት ይገኙበታል፡፡

በተለይ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተመሠረተ በኋላ በቡና ዘርፍ በርካታ ችግሮች እየተከሰቱ በመሆኑና መፍትሔ የሚሰጥ አካል በመጥፋቱ፣ ችግሩን ለመፍታት ‹‹የቡና ህዳሴ›› በሚል ስያሜ ንቅናቄ ተጀምሯል፡፡ ሐሙስ መጋቢት 28 ቀን 2009 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ግብይት ባለሥልጣን ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር ለመመካከር በጠራው ስብሰባ፣ የንግድ ሚኒስትሩ በቀለ ቡላዶ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ከዛሬ 16 ዓመታት በፊት የቡና ዘርፍ በደረቅ ቼክ ምክንያት ከፍተኛ ችግር ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡

በአሁኑ ወቅት የችግሩ ስፋትና ጥልቀት ይለያይ እንጂ ችግሩ እንዳለ በመታመኑ ራሳቸው የንግድ ሚኒስትሩ፣ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትሩ እያሱ አብርሃ (ዶ/ር) እና የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽነር ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ጉዳዩን እየተከታተሉት መሆኑን  አስረድተዋል፡፡ የማስተባበሩን ሥራም የንግድ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አያና ዘውዴና የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ግብይት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳኒ ረዲ መቀጠላቸውን ጠቁመዋል፡፡

በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት 140 ገጾች ጥናት መሠራቱን፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሚመራው የብሔራዊ ኤክስፖርት ኮሚቴም ጉዳዩን ተከታትሎታል ብለዋል፡፡

‹‹ቡናን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የኤክስፖርት ምርቶች በድምር እያየን ነበር፤›› በማለት የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ‹‹ነገር ግን የቡና ንግድ እያሽቆለቆለ መጥቷል፤›› ብለዋል፡፡

በዚህ ምክንያት ይኼን ጉዳይ ለያይቶ ማየት ያስፈልጋል ተብሎ ጉዳዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ወደሚገኘው የኢኮኖሚ ዩኒት ተወስዷል በማለት አክለዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የኢኮኖሚ ዕቅድ ውጤታማነት ክትትል ዘርፍ አስተባባሪ አርከበ ዕቁባይ (ዶ/ር) ቡናን ጨምሮ ከመቶ ሚሊዮን ዶላር በላይ የኤክስፖርት ገቢ የሚያስገቡ የግብርና ምርቶች ላይ የተንሰራፉትን ችግሮች እንዲፈቱ፣ አገሪቱም ከዘርፉ የምታገኘው ገቢ እንዲጨምር ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፡፡

በዚህ መሠረት በተለይ በቡና ዘርፍ ከኤክስፖርተሮችና ከአቅራቢዎች፣ ቀደም ሲል ጉዳዩን ሲከታተሉ ከቆዩት ሚኒስትሮች፣ ከምርት ገበያ ባለሥልጣናትና ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ባለሙያዎች ጋር በተካሄደ ተደጋጋሚ ውይይት በቡና ዘርፍ የተንሰራፋው ችግር ተለይቶ የመጨረሻ ውይይትና ውሳኔ እየጠበቀ ይገኛል፡፡

የችግሩ ሰለባ የሆኑት የኢትዮጵያ ቡና ኤክስፖርተሮች በማኅበራችው አማካይነት ተደጋጋሚ ውይይት አካሂደው በዘርፉ ውስጥ ያጋጠሙ 13 መሠረታዊ ችግሮችንና የመፍትሔ ሐሳቦችን፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት አቅርበው መፍትሔ እንዲካተት ተደርጓል፡፡

በቀድሞ አሠራር እሸት ቡና ወደ ማጠቢያ ተልኮ ታጥቦ ለገበያ ይቀርብ ነበር፡፡ አሁን ባለው አሠራር ግን እሸት ቡና ለቅድመ ገበያ ከቀረበ በኋላ ወደ ማጠቢያ ይላካል፡፡ በመጀመሪያ ግብይትና በማጠቢያ ማዕከላት በቂ ክትትል አለመኖር በቡና ጥራት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ መከሰቱ ተመልክቷል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ በቡና ጨረታ ወቅት ገዢዎች ስለሚጫረቱት ቡና ዝርዝር መረጃና ናሙና እንዲኖራቸው የሚፈቅድ አሠራር አለመኖር፣ ሦስተኛ በመጋዘኖች ከደረጃ ውጪ የሆነ አሠራር መኖር፣ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሚዛን በትክክል መሥራት አለመሠራቱ በየወቅቱ አለመፈተሽና ትክክለኛነቱን በቅርብ አለመከታተል ከፍተኛ የክብደት ጉድለት በማስከተሉ፣ ኤክስፖርተሮችን ለኪሳራ እየዳረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡

አራተኛው ችግር የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሚያገበያየው ቡና ከገፈቱ ጋር በመሆኑ፣ ኤክስፖርተሮች ላልተገባ ወጪ መዳረጋቸው ተገልጿል፡፡

አምስተኛው በምርት ገበያ መጋዘኖች ቡናዎች በተገዙበት የጥራት ደረጃ ሳይሆን በጣም ዝቅ ብለው መገኘታቸው፣ ለምሳሌ ጅማ ደረጃ ሦስት ተብሎ የተገዛ ቡና ደረጃ አራትና አምስት ተብሎ አገራዊ ደረጃ ሆኖ መገኘቱ ተመልክቷል፡፡

ይህ አሠራር ለኪሳራ የዳረገ ከመሆኑም በላይ ቡና ላኪዎች ከደንበኞቻችው ጋር በተስማሙት የቡና ጥራት ደረጃ መሠረት መላክ ባለመቻሉ የቡና ዘርፍን ተዓማኒነት እያሳጣ ነው ተብሏል፡፡ በአገሪቱ የቡና ነጋዴዎች ገጽታ ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በስድስተኛ ደረጃ የተቀመጠው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የቡና መጫረቻ ዋጋ የዓለም አቀፍ ዋጋን ያገናዘበ አለመሆን፣ በዚህና በሌሎች ምክንያቶች የቡና ኤክስፖርት ትርፋማ ባለመሆኑ ምክንያት ኤክስፖርተሮች በኤክስፖርት የሚያጡትን በገቢ ንግድ መደገፋቸው ችግር እያስተከለ መሆኑ፣ ከዚህ በተጨማሪም አንዳንድ ላኪዎች ከማጠቢያ ጀምሮ እስከ ምርት ገበያ ድረስ የሚፈልጉትን ቡና ለማግኘት የሚያደርጉት ያልተገባ ግንኙነት በግብይቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ ተመልክቷል፡፡

በሰባተኛ ደረጃ ለረዥም ዓመታት የቆየው የኮንትሮባንድ ንግድ በዘላቂነት ባለመፈታቱ በዘርፉ በሕጋዊ መንገድ በሚሠሩ ነጋዴዎች ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ ጤናማ የግብይት ሥራዎች እንዳይኖር ከማድረግ ባሻገር ሕገወጥ ነጋዴዎች እንዲበራከቱ ምክንያት መሆኑ ተመልክቷል፡፡

አሥረኛ ቡናን በሚመለከት መመርያዎች፣ ደንቦችና ፖለሲዎች ሲዘጋጁ የዘርፉን ተዋናዮች አለማሳተፍ፣ ይኼ ባለመሆኑም ሕግጋቱን ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ ችግሮች እያጋጠሙ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

አሥራ አንደኛው የምርት ገበያ ወንበር በአሁኑ ወቅት ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ በመሆኑ፣ አዳዲስ ቡና ላኪዎችን የማያበረታታና በቡና ግብይት ላይ አጠቃላይ የወጪ ንረት ማስከተሉ ተመልክቷል፡፡

አሥራ ሁለተኛ በደረጃው መሠረት ለኤክስፖርት የሚቀርበው ቡና የሚጣለው መጠን በአማካይ ከ12 እስከ 15 በመቶ መሆን ሲገባው፣ በአሁኑ ወቅት እስከ 30 በመቶና ከዚያ በላይ መሆኑ ጥራት ያለው ቡና ማግኘት እንዳይቻል አድርጓል፡፡

በመጨረሻ የመንግሥት አካል የሆነው የመጋዘን ድርጅት ያረጋገጠው የጥራት ደረጃ በሌላው የመንግሥት አካል ተቀባይነት አለማግኘቱ የደረጃ አሳንሶ መመደብን አስከትሏል፡፡ ይህም ቡና ላኪውን ላልተፈለገ ወጪ ሲዳርግ፣ የቡና ግብይትን ሰንሰለት ደግሞ ማርዘሙ ተመልክቷል፡፡

እነዚህን ተግዳሮቶች መፍትሔ አፈላላጊው የመንግሥት ተቋም የተቀበለ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ግብይት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳኒ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የሕግ ማዕቀፍ መዘጋጀቱን፣ በዚህም አቅራቢዎችና ላኪዎች የጎንዮሽ እህት ኩባንያ አቋቁመው እንዲሠሩ እንደሚፈቅድ፣ የኪሳራ ማካካሻ ሥርዓት እንደሚፈጠር፣ የቡና ፈንድ እንደሚቋቋም፣ የመጀመሪያ ደረጃ ግብይት ፈጻሚዎች አሠራር እንደሚወሰን፣ ለቡና ዘርፍ ራሱን የቻለ የማበረታቻ ሥርዓት እንደሚዘረጋ፣ የቡና ደረጃ ክለሳ እንደሚደረግ፣ አቅራቢዎች ራሳቸውን ችለው ወደ ውጭ ኤክስፖርት እንደሚያደርጉና የትራንስፖርትና ቀረጥ ዋጋ እንደሚወሰን አስታውቀዋል፡፡

ባለሥልጣኑም በድጋሚ የተቋቋመበት ደንብ እንደሚሻሻልና ሁሉንም የቡና ዘርፍ ተዋናዮች እንደሚመራም አቶ ሳኒ አስታውቀዋል፡፡

በቡና ምርትና ንግድ ላይ የረዥም ጊዜ ልምድ ያላቸው አቶ ኃይለ ገብርኤል ውቤ፣ ‹‹ቡና ከመሞቱ በፊት መንግሥት መድረሱ መልካም ነው፤›› ብለዋል፡፡ አቶ ኃይለ ገብርኤል የቡና ቅምሻ አሠራር በሙስና የተዘፈቀ በመሆኑ ተጠሪነቱ ለሚቋቋመው የቡና ዘርፍ ፎረም ቢሆን መልካም እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የቡና ምርታማነት ለመጨመር የሚሠራው ምርምር ሁሉንም የአግሮ ኢኮሎጂ ዞኖች የማያጠቃልል በመሆኑ ሊታሰብበት እንደሚገባ አቶ ኃይለ ገብርኤል አሳስበዋል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy