Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በአንዳንድ የአገሪቷ አካባቢዎች የተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ “እንዳይባባስ ተገቢው ጥረት አልተደረገም” ተባለ

0 305

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በአንዳንድ የአገሪቷ አካባቢዎች የተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ እንዳይባባስ ተገቢውን ጥረት አለመደረጉን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ገለጸ።

በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎችና በጌዲኦ ዞን በተካሄዱት ሁከትና ብጥብጦች የ669 ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን፤ ወደ 20 ሺ የሚጠጉ ሰዎች ከመኖሪያ አካባቢያቸው መፈናቀላቸውንም ኮሚሽኑ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በሶስቱ ክልሎች ከሰኔ 2008 ዓ.ም እስከ መስከረም 2009 ዓ.ም የተከሰተውን ሁከትና ብጥበጥ አስመልክቶ ያደረገውን የምርመራ ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል።

ቀደም ብሎ በኦሮሚያ 15 ዞኖችና 91 ወረዳዎች፣ በአማራ 5 ዞኖችና 55 ወረዳዎች እንዲሁም በደቡብ ክልል ጌዲኦ ዞን 4 ወረዳዎች ሁከትና ብጥብጥ  መከሰቱ ይታወሳል።

በዚሁ መሠረት ኮሚሽኑ በተጠቀሱት አካባቢዎች ከሁከትና ብጥብጡ ጋር ተያይዞ በዜጎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ማጋጠሙንና አለማጋጠሙን ለማረጋገጥ ምርመራ አካሂዷል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ዶክተር አዲሱ ገብረእግዚአብሔር ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፤ በአንዳንድ የአገሪቷ አካባቢዎች በተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ የመንግሥትና የጸጥታ አካላት ጉዳዩን በቅርበት ቢያውቁትም ችግሩ እንዳይባባስ ተገቢውን ጥረት አላደረጉም።

በሪፖርቱ ላይ ለአብነት እንደተመለከተው፤ በኢሬቻ በዓል ወቅት ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር ከዋዜማው ምሽት ሁለት ሰዓት ጀምሮ ሙከራዎች ተደርገዋል።

በተጨማሪም ከሌሊቱ 8 ሰዓት ጀምሮ ከሌሎች አካባቢዎች በአይሱዙ ተጭነው የገቡ አካላት መኖራቸው በተደረገው ምርመራ ታውቋል።

ይህ እየታወቀ የመከላከል ጥረት ካለመከናወኑም በተጨማሪ “ችግሩ እንዳይከሰት ለማድረግ የጸጥታ አካላት ሚናቸውን በአግባቡ አልተወጡም” ተብሏል።

በተጨማሪም በበዓሉ ላይ “ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች እንደሚገኙ እየታወቀ አደጋው የተፈጠረበትን ቦታ የበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴ መፍትሄ ሊያበጅለት አልቻለም” ብለዋል።

በመሆኑም በጉዳዩ ዙሪያ ያሉ የጸጥታ አካላትና የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በህግ ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚገባም አመልክተዋል።

በሌላ በኩል ሁከትና ብጥብጡን ለመቆጣጠር በተሞከረበት ወቅትም በአንዳንድ የክልል ዞኖች ሁከት ፈጣሪዎቹ የታጠቁና ከጸጥታ አካላት ጋር የተፋለሙ በመሆኑ “የሀይል እርምጃ መወሰዱ አግባብነት አለው” ብለዋል።

ይሁን እንጂ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ከድንጋይ ያለፈ ምንም የጦር መሳሪያ ያልታጠቀሙ ህገወጥ ሰለፈኞች በጸጥታ አካላት ህይወታቸው እንዲያልፍ መደረጉ “የመብት ጥሰት መሆኑ ተረጋግጧል” ብለዋል።

በኦሮሚያ ክልል በመልካም አሰተዳደር እጦት ምክንያት የተነሳውን ጥያቄ ኦነግ፣ ኦፌኮና ሌሎች ዓላማ ያነገቡ አካላት ችግሩን ለማባባስ እንደተጠቀሙበት አውስተዋል።

በ2008 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ብጥብጥና ሁከት እንዳለ ሆኖ መስከረም 2009 ዓ.ም በኢሬቻ በዓል ላይ የተፈጠረው ክስተትና እርሱን ተከትሎ “በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጩ የሀሰት ወሬዎች ሁከቱን አባብሰዋል” ብለዋል።

በተመሳሳይ በአማራ ክልልም የአገልግሎት አሰጣጥን መነሻ በማድረግ በክልሉ የአንድ ብሔር የበላይነት እንዳለ በማስመሰል መረጃዎች በማሰራጨት፣ የትግራይና የአማራን ወሰን በመጥቀስ ሁከት እንዲፈጠር ምክንያት መሆናቸውም ነው  የተገለጸው።

በጌዲኦ ዞንም በዲላ ከተማ የሚገኝ ቦታ የፍርድ ውሳኔን መነሻ በማድረግ በመንግስት መዋቅር ውስጥ የሚሰሩ ኃላፊዎች ያላቸውን የዘርና የብሔር ጥላቻ ለብጥብጡ ማባባሸነት እንደተጠቀሙበት ነው የገለጹት።

በአጠቃላይ በብጥብጡና በሁከቱ በአማራ ክልል 140 ዜጎች ህይወት ያለፈ ሲሆን፤ 237 ደግሞ ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል። በኦሮሚያም 495 ዜጎች ህይወት አልፎ 464 ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።

በጌዲኦ ዞንም 34 ሰዎች ሞተው 178 ዜጎች ደግሞ ለአካል ጉዳት መዳረጋቸው ታውቋል። በሁከትና ብጥብጡ ምክንያት ከዞኑ ከ8 ሺ 450 በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል።

በአማራ ክልል ደግሞ “11 ሺ በላይ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል” ብለዋል- ዶክተር አዲሱ።

ኮሚሽኑ በክልሎቹ በግለሰቦችና በመንግስት ንብረት ላይ በሚሊዮን የሚቆጠር ንብረት መውደሙንና ዜጎች ለከፍተኛ የስነ ልቦና ችግር መዳረጋቸውን ገልጿል።

ኮሚሽኑ ምርምራውን ያካሄደው በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችን፣ አባገዳዎችን፣ የአገር ሽማግሌዎችን፣ የኃይማኖት አባቶችንና የመከላከያ ሠራዊት አባላትን በማናገር ነው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy