Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በአዳማ 350 የልማት ተነሺ አባወራዎች ቃል የተገባላቸውን የቤት መስሪያ መሬት አላገኙም

0 1,110

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በአዳማ ከተማ 350 የልማት ተነሺ አባወራዎች የካሳ ክፍያ ቢሰጣቸውም ቃል የተገባላቸው የቤት መስሪያ መሬት ባለማግኘታቸው መቸገራቸውን ተናግረዋል።

የአዳማ ከተማ ቦኩ ሸነን ቀበሌ ነዋሪዎች አካባቢያቸው በከተማዋ ለሚከናወን የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ በመመረጡ እንዲነሱ ተደርጓል፡፡

1 ሺህ 800 ቤተሰብ ያላቸው 500 አባወራዎች የካሳ ከፍያ ሲሰጣቸው ምትክ የመስሪያ ቦታ የተሰጣቸው አባወራዎች ደግሞ 150 ብቻ ናቸው፡፡

ቀሪዎቹ 350 አባወራዎች ግን ለአባወራዎቹ 500 ካሬ ሜትር ለልጆቻቸው ደግሞ 200 ካሬ ሜትር መሬት ምትክ የቤት መስሪያው ቃል በተገባላቸው መሰረት አልተሰጣቸውም፡፡

የልማት ተነሺዎቹ የቤት መስሪያ ቦታ ለመስጠት የተገባው ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ወደ ከተማዋ የመሬት ልማት እና ማኔጅመንት ኤጀንሲ ቢመላለሱም መፍትሄ አለማግኘታቸውን ይናገራሉ።

ምትክ ቦታውን ባለማግኘታቸውም የተሰጣቸው የካሳ ገንዘብ ቤት ሳይሰሩበት መመናመኑን ነው የገለጹት።

አባወራዎቹ ከሚኖሩበት ስፍራ ከተነሱ ጀምሮ ወደ ኤጀንሲው ቢመላለሱም መሬቱ ይሰጣችኋል ከሚል ተስፋ ባለፈ ላለፉት ዘጠኝ ወራት ተጨባጭ መፍትሔ አላገኘንም ነው ያሉት።

ከዚህም ባለፈ ሰርገው የገቡ መሬቱ የማይገባቸው ግለሰቦች ተቀላቅለዋል የሚል ቅሬታንም አቅርበዋል፡፡

የልማት ተነሺዎቹ ጉዳይ በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ዙር በተገቢው መንገድ ተከናውኖ ሶስተኛ ዙር ላይ ሲደርስ ግን የአርሶ አደሩን ቤተሰብ በማጣራት ሂደት ክፍተት መፈጠሩን የአዳማ ከተማ የመሬት ልማት እና ማኔጅመንት ኤጀንሲ አምኗል፡፡

ለችግሩ መፈጠርም ቀድሞ የነበረው ብልሹ አሰራር መሆኑን ገልጿል፡፡

የኤጀንሲው ሃላፊ አቶ ተሻለ በቃና የቤት መስሪያው መሬት ሳይገባቸው ተቀላቅለው የተገኙት ግለሰቦች በሁለቱም አካላት በኩል በተፈጠረ ችግር ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ችግር ፈጥረዋል ተብለው የተጠረጠሩ ዘጠኝ የኤጀንሲው ባልደረቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቅሰው፥ የልማት ተነሺዎች ችግር አፋጣኝ መፍትሄ የሚሻ በመሆኑ አርሶ አደሮችን ካካተተው አጣሪ ኮሚቴ ጋር በመሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ ችግሩ ይፈታል ነው ያሉት ሃላፊው፡፡

ኤጀንሲው በኢንዱስትሪ ፓርኩም ሆነ በሌሎች የልማት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ችግሮችን ተከታትሎ ከመፍታት ጎን ለጎን፥ መሰል ችግሮች እንዳይደገሙ የማድረግ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy