Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በጎንደር ከተማ በሁለት ቢሊየን ብር የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካ ሊገነባ ነው

0 599

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በጎንደር ከተማ በሁለት ቢሊየን ብር ወጪ ለሚገነባው የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የመሰረት ድንጋይ ለማስቀመጥ በተዘጋጀው ሥነስርአት ላይ እንደገለጹት፣ በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዓመታት የነበረውን ዝቅተኛ የኢንዱስትሪ ልማት አፈጻጸም ለመቀየር የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።

አፈጻጸሙን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስም የባለሀብቶችን ተሳትፎ ከማጠናከር ባለፈ አባይ ኢንዱስትሪ ልማት አክሲዮን ማህበር ተቋቁሞ ወደስራ እንዲገባ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

ሰሜን ጎንደር ሰፊ የልማት መሬት፣ ውሃና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት መሆኑን ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በተለይ ለፋብሪካው ግብአትነት የሚውለውን ጥጥ አርሶ አደሩና ባለሃብቱ አምርቶ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችል አመልክተዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ጌታቸው በበኩላቸው፣ የፋብሪካው የኢንቨስትመንት ወጪ ከሁለት ቢሊየን ብር በላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ፋብሪካው በ56 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚገነባ ሲሆን፥ ከስድስት ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወገኖች ቋሚ የስራ ዕድል ይፈጥራል።

በግንባታው የመጀመሪያ ምዕራፍ የሚገነባው የፋብሪካው አልባሳት ማምረቻ ክፍል በመጪው ዓመት ተጠናቆ ሥራ ይጀምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ከሌሎች ዘርፎች የተሻለ ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠሩና ለፋብሪካው የሚወጣውን የኢንቨስትመንት ወጪም በሰባት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሊመልስ የሚችል መሆኑ ቅድሚያ እንዲሰጠው አድርጎታል።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ተቀባ ተባባል፥ ፋብሪካው በከተማዋ መቋቋሙ ለበርካታ ወገኖች የስራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ የከተማዋን የኢንቨስትመንትና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በማነቃቃት በኩል የሚኖረው ሚና የጎላ ነው ብለዋል።

ከተማ አስተዳደሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች በከተማው በብዛት እንዲኖሩ የሚያስችል ቀልጣፋ አገልግሎት እንደሚሰጥ ጠቁመው፣ ባለሀብቶችም መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ በአካባቢው አዋጭ በሆኑ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሰማሩ ጥሪ አድርገዋል፡፡

በሰሜን ጎንደር ዞን ቆላማ ወረዳዎች በየዓመቱ ከ20 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በጥጥ የሚለማ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ከ500 ሺህ ኩንታል በላይ ጥጥ ተመርቶ ለገበያ እንደሚቀርብ መረጃዎችን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy