Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ባለቤቱን ያላጠራው የውጭ ማስታወቂያ

0 649

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ሥፍራዎች ሲንቀሳቀሱ በርካታ ውጭ ማስታወቂያዎች ማስተዋል አይቀርም። ሥርዓት ባጣ መልኩ የሚሰቀሉት ማስታወቂያዎች የከተማውን ውበት ከማበ ላሸታቸው ባሻገር በአዋጅ ቁጥር 759/2005 የተደነገጉትን ገደቦች የሚጥሱ ናቸው። በማስ ታወቂያ አዋጁ አንቀፅ 26 ንዑስ አንቀጽ አራት ላይ «ማንኛውም የአልኮል መጠጥ የውጭ ማስታወቂያ ከልጆች መዋያ ማዕከል፣ ከትምህርት ቤት፣ ከህክምና ወይም ታሪካዊ ተቋም፣ ከሲኒማ ቤት፣ ከቴአትር ቤት ወይም ከስታዲየም በመቶ ሜትር ራዲየስ ውስጥ እንዲቀመጥ መደረግ የለበትም›› ይላል። ይህ ስለመጣሱ ግን በአዲስ አበባ ስታዲየም ዙሪያ በብዛት የሚታዩት የአልኮል ማስታወቂያዎች ምስክር ናቸው።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የውጭ ማስታወቂያ ሥራን ለመደንገግ የወጣ ደንብ ቁጥር 35/2003 አንቀፅ ሁለት ንኡስ አንቀፅ ሁለት ላይ የደንቡ ባለስልጣን የከተማው የመሬት አስተዳደርና ግንባታ ፈቃድ ባለስልጣን እንደሆነ ይገልፃል። ይሁንና የውጭ ማስታወቂያዎች የሚሰቀሉበትን ቦታ፣ የሚተላለፉትን ይዘቶች እና ሌሎችም ጉዳዮች በተመለከተ የጠራ ባለቤትና አሰራር ባለመኖሩ ህገ ወጥ ተግባራት ተበራክተዋል።

የአራዳ ክፍለ ከተማ ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር የሥራ ሂደት ባለሙያ የሆኑት አቶ ዘነበ የትኖሩ በጉዳዩ የሚሰጡት አስተያየት በዘርፉ የጠራ ነገር አለመኖሩን ያመለክታል። እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ በደንቡ መሰረት የውጭ ማስታወቂያ ፈቃድ አሰጣጥ በክፍለ ከተማው ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር የሥራ ሂደት በኩል ይከናወናል። የማስታወቂያ ይዘትን በተመለከተ አልፎ አልፎ የክፍለ ከተማው የኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ይገመግማል። በተረፈ ማስታወቂያውን በደፈናው በማየትም የተዘጋጀ መጠይቅን እንዲሞሉ በማድረግ ይፈቀዳል።

የውጭ ማስታወቂያ ፈቃድ አሰጣጥ ለሁለት ዓመት ያህል ተቋርጦ እንደነበር በማስረዳት የቆመበትም ምክንያት የራሱ የሆነ መመሪያ ይወጣለታል በሚል እንደሆነና ነገር ግን በተቋረጠበት ወቅት ፈቃድ ያላገኙ አዳዲስ ማስታወቂያዎች ይወጡ እንደነበርም ያስታውሳሉ።

በአዋጅ ቁጥር 759/ 2005 መጠናቸው ከ12 በመቶ በላይ የሆኑ አልኮሎች በውጭ ማስታወቂያ እንዳይተዋወቁ ቢደነግግም ይህ መጣሱን በአዲስ አበባ ከተማ በሚሰቀሉ ማስታወቂያዎች መገንዘብ ይቻላል። አቶ ዘነበ ይህን በተመለከተ «ይዘቱን የመቆጣጠሩን እና የመመዘኑን ኃላፊነት በትክክል የሚያሳይ ግልፅ የሆነ መመሪያና አሰራር ባለመኖሩ ትልቅ ክፍተት ፈጥሯል፤ ወደ ቢሮው ሳይመጡ ማስታወቂያዎቹ የሚለጠፉበት ሁኔታም አለ» ይላሉ።

በውጭ ማስታወቂያ በኩል በክፍለ ከተሞች በኮሙኒኬሽን ቢሮዎችና በግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር የሥራ ሂደት ቢሮዎች መካከል ያልጠራ አሰራር እና የጉዳዩ ባለቤትነትና ኃላፊነትን በተመለከተ ግልፅ ያልሆነ ጉዳይ መኖሩን ይጠቁማሉ። በእዚህ የተነሳ «ባለቤት የለውም» ማለት ይቻላል ይላሉ። ይህም በትክክል ያልተፈተሹ ማስታወቂያዎች እንዲሰራጩ ዕድል እንደሚከፍት ይጠቁማሉ። በሌላ በኩልም የኃላፊነት ቅብብሎሽ የበዛበት አሰራር በመሆኑ በገቢ አሰባሰቡም ረገድ እክል እንደሚያጋጥመው ያስረዳሉ።

የክፍለ ከተማው ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር የሥራ ሂደት በአሁኑ ወቅት በአዋጁ መሰረት የሚሰቀሉት ማስታወቂያዎች የህብረተሰቡን እንቅስቃሴ የማይረብሹና የመሰረተ ልማት ሥራዎችን የማያደናቅፉ መሆኑን ይከታተላል። ይሁንና ይህም ቢሆን በአግባቡ እየተሰራበት አለመሆኑን በማመልከት የይዘቱ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የውጭ ማስታወቂያ ፈቃድ አሰጣጥ በኩል ያለው ሥራ በአግባቡ እየተመራ አለመሆኑን ይናገራሉ።

የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ላይሰንስ ኬዝ ቲም የሥራ ሂደት መሪ ወይዘሮ አትክልት ተክሉ የውጭ ማስታወቂያ የአስተዳደሩን የኮሙኒኬሽን ቢሮ እንደማይመለከተው ይናገራሉ። ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት ደብዳቤ ተፅፎ የውጭ ማስታወቂያ በግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን እንዲተዳደር ተደርጓል ይላሉ። ነገር ግን እስካሁንም የውጭ ማስታወቂያን ጉዳይ በግልፅ በባለቤትነት የያዘው ባለመኖሩ በከንቲባ ጽሕፈት ቤት በኩል ከኮሙኒኬሽን ቢሮ፣ ፍትህ ቢሮ እና ከሥራ አስኪያጅ ጽሕፈት ቤት ባለሙያዎች ተወጣጥተው ጥናት በማዘጋጀት ለካቢኔ እንዲቀርብ እንደተደረገ ይገልፃሉ።

የጥናቱን ዋና ዓላማ ሲያስረዱም የውጭ ማስታወቂያን ማን በኃላፊነት ይያዘው እና ገቢውን ማን ያስተዳድረው፣ ማን ይምራው ? የሚል ነው። ነገር ግን የግንባታ ቁጥጥርና ፈቃድ ቢሮ የውጭ ማስታወቂያዎችን የይዘት ግምገማ የሚመለከተው የኮሙኒኬሽን ቢሮን ነው በማለት ኃላፊነቱን እየወሰዱ አለመሆኑን ይገልፃሉ።

እንደ ወይዘሮ አትክልት ገለፃ በደንቡ በግልፅ የማን ኃላፊነት እንደሆነ የሚያሳይ ቢሆንም በአግባቡ የሚከታተለው ባለመኖሩና እስካሁንም በግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን በኃላፊነቱ መሰረት እየሰራ ባለመሆኑ እና ከህጉ ውጪ ማስታወቂያዎቹም እየወጡ በመሆኑ ተጨማሪ ጥናት እንደተደረገም ይናገራሉ።

አቶ ንጉስ ተሾመ የአዲስ አበባ መስተዳድር የመሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ የኮሙኒኬሽን ደጋፊ የሥራ ሂደት አስተባባሪ ደንቡ ከወጣበት ከ2003 .ም ጀምሮ የማስታወቂያ ፈቃድ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን ይገልፃሉ። የውጭ ማስታወቂያ ፈቃድ ማግኘት የሚፈልግ ሥፍራውን በማስታወቅ በጠየቀው መሰረት ይፈቀድለታል። በወቅቱ የነበረው ጥያቄም ትንሽ ነበር። የውጭ ማስታወቂያ ፈላጊው ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ አገልግሎቱን ለመስጠት ያስቸግራል በሚል በግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ለሁለት ዓመት ያህል አገልግሎቱን ማቋረጡን ይጠቅሳሉ።

በደንቡ መሰረት በግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን የማስታወቂያውን ፈቃድ የመስጠት ኃላፊነት አለበት። ነገር ግን ማስታወቂያዎች የሚተከሉበትን መሬት ማዘጋጀት ስለሚገባ፣ በምን ዓይነት መንገድ መዘጋጀት እንዳለበት ግልፅ የሆነ አሰራር መቀመጥ ስላለበት ለአሰራር አመቺ አይደለም በሚል ደንቡ እንዲሻሻል ጥያቄ ቀርቦ፤ ‹‹ለጊዜው ባለቤት እስኪበጅለት ድረስ በግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን በኩል አገልግሎቱ እንዲሰጥ በከንቲባው ታዟል›› ይላሉ።

እንደ አቶ ንጉስ ገለፃ፤ አሁን በግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን በኩል ለውጭ ማስታወቂያ ፈቃድ ሲሰጥ የውጭ ማስታወቂያዎቹ የት ቦታ እንደሚቆሙ፣ እንደሚለጠፉ፣ የቁመት፣ ስፋትና መጠን፣ የማስታወቂያ ቢልቦርድ ጥራት በሚመለከት ባለው መስፈርት መሰረት ይሰራል። ይሁን እንጂ አስፈላጊ ማጣሪያ እየተደረገ አይደለም። ምክንያቱም ይላሉ አቶ ንጉስ ‹‹ባለቤቱ እስካልጠራ ድረስ ማንም እንደፈለገ ማስታወቂያውን የሚያቆምበት ሁኔታ አለ፤ ገደብ የተደረገባቸው ማስታወቂያዎችንም ህጉን በጣሰ መልኩ በትምህርት ቤቶችና፣ ከስፖርት ማዘውተሪያ አካባቢዎች መራቅ ቢኖርባቸውም በህጉ መሰረት እየተተገበረ አይደለም። የውጭ ማስታወቂያ እየተሰራጨ ያለው በህገ ወጥ መንገድ ነው። ህግን የሚተላለፉትን የውጭ ማስታወቂያዎችንም የሚቆጣጠር የለም። በዚህ መሰረት ደንቡ በድጋሚ መስተካከል ይፈልጋል» ይላሉ።

በጉዳዩ ላይ የከተማ አስተዳደር በግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን አስተያየት ለማካተት ሞክረን መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።

ሰላማዊት ንጉሴ

– See more at: http://ethpress.gov.et/addiszemen/index.php/news/national-news/item/12372-2017-04-27-17-47-23#sthash.cZpRahjj.dpuf

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy