Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ትርፍ ለማግበስበስ ጀሶና ሰጋቱራን እንጀራ

0 5,440

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ወይዘሮ አለምነሽ ተሰማ  የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ ነዋሪ ናቸው። ወትሮም እንደሚያደርጉት ከወረዳው የሸማቾች ማህበር  ሸቀጣ ሸቀጦችን ለመግዛት ያመራሉ። በዕለቱ  በቦታው  የጠበቃቸው  የስኳር ወረፋ ሰልፍ  አይደለም። ሰዎች  አንድ ላይ ሰብሰብ ብለው «ጉድ ጉድ» ሲሉ ያዩና እሳቸውም የምን ጉድ ነው ሲሉ  ወደተሰባሰቡት  ሰዎች ያመራሉ። በኤግዚቢትነት የተያዘ ጀሶና ሰጋቱራ ተደባልቆ  የተቦካበት  ብዛት ያለው ሰማያዊ ትላልቅ የፕላስቲክ በርሜሎች ተሰልፈው ይመለከታሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት « በቃ ከነጋዴ ጋር መተማመን ከባድ እየሆነ ነው። አስቡት፤ መብራት ሲጠፋ  በሌላም ምክንያት በቤት ውስጥ እንጀራ በማይኖርበት ወቅት  ከተለያየ ቦታ እንጀራ ይገዛል። በቋሚነት የግዢ እንጀራ የሚጠቀሙም አሉ። ሆቴል ቤቶችም ምግብ የሚያቀርቡት  እንጀራ ገዝተው ነው። ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ  የጀሶ እንጀራ እየተመገበ ነው የሚል እምነት አላቸው።

ከዚህ ቀደም በቴሌቪዥን ይህን ዓይነት ወንጀል የፈፀሙ ሰዎች ተይዘው  አይተናል።አሁንም በተመሳሳይ ወንጀል እየተሰራ ነው።ይሄ ደግሞ ለጤና ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ማንም ሰው ሊገምት ይችላል። ስለዚህ ይህንን ዓይነት ወንጀል በሚፈጽሙት ላይ ጠበቅ ያለ ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል ይላሉ።

የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኘ  ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ካህሳይ እንዳሉት፣ የአካባቢው ነዋሪ የሆኑ አምስት ግለሰቦች  ጤፉን ከጀሶ ጋር ቀላቅለው 29 በርሜል ሊጥ ፣ አስር ኩንታል ሰጋ ቱራ  እንጀራ ጋግረው ለመሸጥ ሲሉ ተደርሶባቸዋል፡፡

ግለሰቦቹ  እንጀራውን  ለሆቴሎች፣ ለግሮሰሪዎች፣ ለግለሰቦች፣ ለሱቆች  እንደሚያከፋፍሉ መታወቁን ጠቅሰው፣ እነዚህም ቦታዎች በርካታ ሰዎች የሚጠቀሙበት  በመሆናቸው  ህብረተሰቡ ላይ የሚያደርሰው የጤና ጉዳት የከፋ ሊሆን እንደሚችል  ይናገራሉ፡፡

«ግለሰቦቹ   ሳጋቱራውን የሚፈጩት የት እንደሆነ ለማወቅ ጥረት ቢደረግም መለየት  አልተቻለም»  ያሉት አቶ ተወልደ ጉዳዩ  ህብረተሰቡ ላይ ከሚያደርሰው የጤና ጉዳት አንፃር  ጠለቅ ያለ ጥናት ያስፈልገዋል፡፡ እስካሁን ድረስም ጉዳዩ በህግ ተይዞ  የተወሰኑ ግለሰቦች ለህግ  እንዲቀርቡ  የተደረገ ሲሆን፣  ከቀረቡት መካከልም በዋስ የተለቀቁ  መኖራቸውን ይጠቅሳሉ። እስካሁንም  ያልተያዙና የተሰወሩ ሰዎች   እንዳሉም   ያብራራሉ፡፡

ግለሰቦቹ ሊያዙ የቻሉትም  የአካባቢው ማህበረሰብ በተደጋጋሚ በሚያነሳው የመልካም አስተዳደር ጥያቄ መሰረት  ለወረዳ አስተዳደሩ በሰጠው ጥቆማ እንደሆነ  ታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ  የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና እንክብካቤ  አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ወረቲም  በምግብና በመጠጥ ላይ የሚቀላቀሉ ባዕድ ነገሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ነው ያስታወቁት፡፡  ይሄም የሚደረገው የምግቡን ክብደት ለመጨመር እንዲሁም መልኩን  በማሳመር  ያልተገባ ትርፍ ለመሰብሰብ ነው፡፡ የህብረ ተሰቡን ጤና  ለጉዳት የሚያጋልጥን ንጥር ነገር ቀላቅሎ መሸጥ በህግና  በአዋጁም  የተከለከለ  መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ በከተማዋ በስፋት  የሚስተዋለው ችግር ከጤፍ ጋር ባዕድ ነገርን አቀላቅሎ  እንጀራ  መሸጥ ነው፡፡ ይህ ድርጊት ከጊዜ  ወደ ጊዜ ቁጥሩም መጠኑም እየጨመረ የመጣበት ሁኔታ አለ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታም መጠኑ ቢለያይም  በአሥሩም  ክፍለ ከተሞች ችግሩ መኖሩን የሚያሳዩ  ምልክቶች  መታየታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከባዕድ ነገር ጋር የተቀላቀሉ ምግቦች  በህብረተሰቡ ጤና ላይ ከፍተኛ የሆነ  ችግር ያደርሳሉ የሚሉት አቶ ጌታቸው፣ አንድ በንግድ ዘርፍ የተሰማራ ግለሰብ ወይም ድርጅት ጥራቱን የጠበቀ ንፁህ ነገር ለህብረተሰቡ ማቅረብ አለበት፡፡ ይሄን እንዲያደርግ ህጉ ያስገድዳል፡፡ ይህን የሚያደርጉ አካላት በአንድ በኩል የማህበረሰቡን ጤና የሚጎዱ በመሆናቸውና  በሌላ በኩል ደግሞ በህገወጥ መንገድ  ትርፍ ለማግኘት የሚሯሯጡ ኪራይ ሰብሳቢ ኃይሎች ስለሆኑ በህግ የሚጠየቁ ይሆናሉ ፡፡

ጤፍ ውስጥ ከሚቀላቀሉት ባዕድ ነገሮች አንዱና በስፋት የሚስተዋለው  ጄሶ  መሆኑን ጠቅሰው፤ ጄሶ    ጠንካራ የሆነ ንጥረ ነገር በመሆኑ ወደ ሰውነት ሲገባ የተለያዩ  የጤና ችግርን ሊያስከትል እንደሚችል አብራርተዋል፡፡

«ይህን  ህገ ወጥ ተግባር እያከናወኑ ያሉ  ግለሰቦች ንግድ ፈቃድና የብቃት ማረጋገጫ የሌላቸው ናቸው» ያሉት አቶ ጌታቸው፣ ግለሰቦቹ ተደብቀው  በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ስለሚያዘጋጁ ለቁጥጥር ችግር እየፈጠረ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በህብረተሰቡ ጥቆማ እነዚህን አካላት  ለህግ የማቅረቡ ጉዳይ ትኩረት ተሠጥቶት የሚሰራ ነው።

ከዚህ በፊት በእንደእዚህ ያለ ህገ ወጥ ንግድ  ላይ ተሰማርተው የተገኙ አካላት  ከሁለት እስከ 10 ዓመት  እስራት የተፈረደባቸው ሲሆን፣ ባለስልጣኑ ህገወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩትን ግለሰቦች  አስተዳደራዊ እርምጃ የመውሰዱና ለፍትህ  የማቅረብ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም  ተናግረዋል፡፡  ከዚህም ባሻገር ችግሩን ለመቅረፍ ባለስልጣኑ ከክፍለ ከተማ እስከ ቀጣና አሰራር ዘርግቶ ህብረተሰቡ ድረስ በመውረድ ተቀናጅቶ እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡

‹‹ባእድ ነገር ቀላቅሎ ለህብረተሰቡ  የሚያቀርቡ ግለሰቦች ጤና ላይ ጉዳት ከማድረሳቸውም ባሻገር ሀገሪቱ  በውጭ ገበያ በምታቀርበው ምርት ላይም ጉዳት የሚያስከት ይሆናል። እንዲሁም የሀገሪቱን ኢኮኖሚም የሚጎዳ  መሆኑን አስረድተዋል። ህብረተሰቡ ወንጀለኞችን አጋልጦ ለህግ በማቅረብ በኩል ትብብር ማድረጉን መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መረጃ ለማግኘት በተደጋጋሚ  ስልክ በመደወል፣ በቢሮአቸው በመሄድ እንዲሁም ከተቋማችን የትብብር ደብዳቤ በመውሰድ ጭምር ጠይቀን አልተሳካልንም።

ሰብስቤ ኃይሉ

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy