Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ንቁ!

0 474

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ንቁ!

ኢብሳ ነመራ

በቅርቡ በመልካም አስተዳደርና መጓደልና በኪራይ ሰብሳቢነት ይታሙ ከነበሩ የአገሪቱ አካባቢዎች በቀዳሚነት ሲጠቀስ ወደነበረው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥተ የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ሰበታ ከተማ ሄጄ ነበር። የሰበታ ከተማ ባለፈው ዓመት ተቀስቅሶ በነበረው ሁከት በመቶ ሚሊዬን የሚገመት የግለሰቦች ሃብት የወደመበት እንደነበረ ይታወሳል። ታዲያ በአጋጣሚ ያገኘኋቸውን ሰዎች፣ በተለይ ወጣቶች አገር እንዴት ነው? ስል ጠይቄ ነበር። አንዳንዶቹ በጥርጣሬ እየተመለከቱ ለጊዜው ከጥያቄዬ ለመገላገል ያህል ጥሩ ነው ምንም አይልም የሚል ምላሽ ሲሰጡኝ፤ ሌሎቹ ደግሞ በድፍረት እንግዲህ የመልካም አስተዳደር ችግር ይቀረፋል ተብሏል፣ ሙስናም ይጠፋል ተብሏል፤ ወጣቱም ባለሥራ ይሆናል ተብሏል፤ የሚመጣውን በትዕግሥት እያየን ነው የሚል ምላሽ ሰጥተውኛል። ምንም የተሻሻለ ነገር የለም፤ መንግሥት ጊዜ ለመግዛት የፈጠረው እንጂ የሚሻሻል ነገር ይኖራል ብለን አንጠብቅም፣ አሁን ህዝቡ ዝም ያለ እንዳይመስልሀ አድፍጦ ነው፤ መንግሥትም አድፍጧል ህዝቡም እንዲሁ ያሉኝም አጋጥመውኛል።

እንዳለመታደል ሆኖ የአገራችን የግል ሚዲያዎች የህዝብን ተጨባጭ የመልካም አስተዳደር፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች የተመለከቱ ዘገባዎች የማቅረብ ልምድ ስለሌላቸው ከእነርሱ ብዙ ባይሰማም፣ የህዝብ ሚዲያዎች ግን ከዚህ ቀደም ከነበረው በተለየ ሁኔታ የህዝብን ቅሬታ እያስደመጡን ነው። በተለይ የክልል መገናኛ ብዙሃን፤ በተለይም የኦሮሚያ ቴሌቪዥን።

የህዝብ የመገናኛ ብዙሃኑ ተጀምረው ግንባታቸው ማብቃት አቅቶት መድረሻቸው መገንባት ይመስል ሁሌ ስለሚገነቡት የመሠረተ ልማት ፕሮጀከቶች፣ ተጀምረው ስለተቋረጡትና አባ ካና የሚላቸው ስላጡት ፕሮጀክቶች፣ ግንባታቸው ተጀምሮ ተቋርጠው ስለፈራረሱት የማህበራዊ ልማት ተቋማት፣ መንግሥት ለህዝቡ በድጎማ በተመጠጣኝ ዋጋ የሚያቀርባቸው የፍጆታ ሸቀጦች ለህዝቡ ከመድረስ ይልቅ ወደነጋዴ መጋዘን የሚጋዙ ስለመሆናቸው፣ ስለየኤሌትሪክ ኃይልና ውኃ መቆራረጥ፣ በአንዳንድ ቦታ ደግሞ ጭራሽ ለወራት ጠፍቶ ስለመቅረት ወዘተ…በየእለቱ ይዘግባሉ።

የፌዴራል መንግሥቱ መቀመጫ በሆነውና የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት በሚያስተዳድራት አዲስ አበባ፣ ከያዝነው ወር መግቢያ አንስቶ በብዙ አካባቢዎች የኤሌትሪክ ኃይል ለቀናት የሚቋረጥበት ሁኔታ የተለመደ እየሆነ መጥቷል። የኤሌትሪከ ኃይል ለቀናት እንደሚቋረጥ አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ አይሰጥም። የትንሣዔ በዓል ሰሞን ኤሌክትሪክ በመቋረጡ ሪፍሪጀሬተር ውስጥ ያስቀመጡት ሥጋ ተበላሸቶባቸው የጣሉ ቤተሰቦቸ ብዙ ናቸው። ኤሌክትሪክ የተቋረጠባቸው አካባቢ ነዋሪዎች ወደሚመለከተው ኃላፊ መሥሪያ ቤት ስልክ ይደውላሉ። ይሁን እንጂ ተመዝግቧል ተራችሁን ጠብቁ ከሚል ውጭ ምላሽ ሳያገኙ ለቀናት ይቆያሉ። ውኃም እንዲሁ ያለቅድመ ማስጠንቀቂያ ለቀናት ይቋረጣል። በውድቅት ሌሊት ለጥቂት ሰዓታት ፈስሶ መልሶ ይጠፋል። ሰው እንቅልፍ አጥቶ ውኃ ሲጠብቅ የሚያድርበት ሁኔታ የተለመደ ሆኗል።

5ኛው ዙር የመንግሥት የሥልጣን ዘመን ሲጀምር ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግና መንግሥት የመልካም አስተዳደር ችግርና የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ድርጊት መስፋፋት የሥርዓቱ አደጋ መሆኑን አሳውቆ ህዝባዊ ንቅናቄ ማቀጣጠሉን ሲያውጅ፣ ህዝቡ ችግሮቹ ይስተካከላሉ የሚል ተስፋ ሰንቆ ነበር። በተለይ በአገሪቱ ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግርና የኪራይ ሰብሳቢነት ድርጊት በተመለከተ በፖሊሲ ምርምርና ጥናት ማዕከል ተዘጋጅቶ የቀረበውና የአገሪቱ ጉምቱ ጉምቱ ባለሥልጣናት በተሳተፉበት በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ የመድረክ መሪነት ውይይት የተካሄደበትን የአገሪቱን የመልካም አስተዳደር ችግር ነቅሶ ያጋለጠ ሰነድ የተመለከቱ ዜጎች መንግሥት ችግሩን ለማቃለል ቁርጠኛ ነው የሚል ተሰፋ አደረባቸው።

ይህ የህዝባዊ ንቅናቄ ማቀጣጠያ የተባለ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመራ ውይይት በተካሄደ ማግሥት ችግሩ እስኪፈነዳ አብጦ ኖሮ፣ ድንገት ፈንድቶ የአደባባይ ተቃውሞ ሆኖ ወጣ። አገሪቱን ለማፍረስ ለሚፈልጉ ቡድኖችም መልካም አጋጣሚ ፈጥሮ አገሪቱ ዓመቱን በሁከት አሳለፈች፤ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ማወጅ እስኪያስፈልግ ድረስ። ይህን ሁከት ተከትሎ መንግሥትና ገዢው ፓርቲ በጥልቀት መታደስ የሚል ንቅናቄ መጀመራቸውን አወጁ። በጥልቀስ የመታደሱ ዓላማ ከአስፈጻሚው ውስጥ የነጠፈውን የህዝብ አገልጋይነት መንፈስ መሙላት፣ የአስፈጻሚውን ብቃት ማሻሻል፣ ኪራይ ሰብሳቢነትን ማራገፍ ወዘተ… ነው።

ይህ በጥልቀት የመታደስ ርምጃ ቢያንስ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አስፈጻሚዎችን ሞቋቸው ከተኙበት ዳተኝነትና ኪራይ ሰብሳቢነት ውስጥ አባንኖ ቀስቅሷቸዋል። መንግሥት የተረከቡትን ኃላፊነት ይመጥናል በሚል የሚከፍላቸውን ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም እያጣጣሙ ህዝብን ሳያገለግሉ ማንቀላፋት፣ ሥልጣንን የማይገባ ጥቅም መሰብሰቢያ መሣሪያነት ማዋል፣ ወዘተ…እንደማያዛልቅ እንዲገነዘቡ አድርጓል። በተወሰነ ደረጃ መደንገጥ የፈጠረው የሚመስል የመልካም አስተዳደር መሻሻል የታየበት ሁኔታ መኖሩም አየካድም።

በተለይ ወጣቶችን የልማት ተሳታፊ በማድረግ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የወጣቶች ተሳተፎና ተጠቃሚነት ፓኬጅ በመቅረጽ እንዲሁም በወጣቶች የሥራ ፈጠራ በኩል በመደረግ ላይ ያለው እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪና አበረታች ነው። ለወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ መንግሥት የመደበው የ10 ቢሊዬን ብር ተንቀሳቃሽ ፈንድ በብድር ለወጣቶች ለመስጠት የዝግጅት ሥራ ተጠናቋል። በኦሮሚያ ክልል ፈንዱን ለወጣቶች መስጠት የተጀመረበት ሁኔታም አለ።  በአገሪቱ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን እድሜያቸው ከ18 እስከ 34 ዓመት የሆኑ ሥራ አጥ ወጣቶች እንደሚገኙ የመለየት ሥራ ተከናወኗል። እነዚህ ወጣቶች አዋጭ የፕሮጀክት ጥናቶችን እንዲያቀርቡና ለፕሮጀከቶቻቻው ማስፈፀሚያ የሚያስፈልጋቸውን ካፒታል 10 በመቶ እንዲቆጥቡ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ ነው። በተለይ በኦሮሚያ ክልል በቅርቡ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶች ሥራ ላይ እንዲሰማሩ ማድረግ ተችሏል። በሌሎች ክልሎችም በቅርቡ በርካታ ወጣቶች ወደሥራ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ይሁን እንጂ በተለይ በተንቀሳቃሽ ፈንድ አጠቃቀም በኩል ግልጽነት የጎደላቸው ነገሮች ይስተዋላሉ። ለየክልሎች የተመደበው ተንቀሳቃሽ ፈንድ ክልሎቹ ቀደም ሲል በአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት ለሥራ እድል ፈጠራ ከሚጠቀሙበት ፈንድ ጋር በተመሳሳይ የወለድና የአጠቃቀም ሥርዓት ከመስጠት አኳያ፣ ብድሩን ለመስጠት የ10 በመቶ ቁጠባ አስፈላጊ መሆኑ፣ ይህ አሠራር በገጠርና በከተማ ተመሳሳይ ያልሆነበት ሁኔታ መኖሩ ወዘተ… በተለይ በወጣቶች ዘንድ ግርታን ፈጥሯል። ይህ ጠርቶ ሊታወቅ ይገባል። አለበለዚያ ፈንዱ እውነት ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ሳይሆን፣ ግርግር ለማብረድ እንደተመደበ በመቁጠር ወጣቶች በቁርጠኘነት ለሥራ ፈጠራ እንዳይነሳሱ ሊያደርግ የሚችልበት ሁኔታ መፈጠሩ አይቀሬ ነው።  

እንግዲህ ቀደም ሲል የተጠቀሱት ችግሮች አሁንም ህዝቡን እያማረሩት ነው። በተለይ ከወጣቶች የሥራ ፈጠራ ፕሮግራም ጋር በተያያዘ የሚታዩት ግልጽነት የጎደላቸው ነገሮች በወጣቱ ዘንድ ጥሩ ስሜት እየፈጠሩ አይደለም። በጽሁፌ መግቢያ ላይ የጠቀስኩት የሰበታ ከተማ ነዋሪዎቸ ሁኔታዎችን በጥርጣሬ የማየት መንፈስ ምንጭም ይኸው ነው።

በተለይ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተያያዙት ችግሮች ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሱ የመጡበት ሁኔታም አለ። በጥልቀት የመታደሰ እንቅስቃሴ እንደታወጀ ተስፋ አድሮበት የነበረው ህዝብ አሁን ተስፋው እየተሸረሸረ ይመስላል። ድሮም የመንግሥትን ርምጃ ባለማመን በጥርጣሬ ሲመለከት የነበረው ህዝብ ደግሞ ድሮም ብለናል ወደማለት እየሄደ ነው። አሁን አሁን በጥልቀት መታደስ የሚለው ሃሳብ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የሚናገሩት ባዶ ቃል ወደመሆን እየሄደ ነው። በጥልቀት መታደስ የሚለው ሐረግ ተስፋ ከመጫር ይልቅ አሰልቺ ወደመሆን እየሄደ ነው። ይህ ያልተጋነነ ህዝብ ውስጥ የሚታይ እውነት ነው።

እንግዲህ ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው ችግሮች መኖራቸው እውነት ነው። በተለይ በዚሀ ጽሁፍ ላይ ያልተጠቀሱ፣ መገናኛ ብዙሃንም ያልዘገቧቸው ህዝቡ የሚያወቃቸው በርካታ ችግሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይገመታል። በመሆኑም በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አስፈጻሚዎችና የህዝብ የልማት ተቋማት ኃላፊዎች በሁከቱ ሰሞን እንደነበረው ሊነቁ ይገባል። ህዝብ እንደሚታዘባቸውም ማወቅ አለባቸው፤ በሁከት ኃይል የሚንቀሳቀሱ ማሽኖች እያለ። እናም ንቁ።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy