Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አርፋጅነትና ቀሪነት

0 531

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በሚያሰሟቸው ዜናዎችና ሀተታዎች ውስጥ አብዛኞቹ ቃላት ከፊት ለፊታቸው «የውሸት» በፈረንጆቹ (Fake) የሚል ቃል የለጠፉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ «የውሸት ሠራተኞች» /Fake employees/ በናይጄሪያ የተከሰተ ጉዳይ ነው «የውሸት ሥራ» /Fake Jobs/ በፈረንሣይ በወይዘሮ ፔኔሎፕ ጌት የተነሳ የተፈጠረ ቃል ነው፡፡ «የውሸት ወሬ» /Fake News/ ባሳለፍነው ወር በዶናልድ ትራምፕና በአሜሪካ ጋዜጠኞች መካከል ተፈጥሮ በነበረው አለመግባባት የተሰነዘረ ቃል ነው ( ቃሉ ዘንድሮ ተነሳ እንጂ ከ2ኛው የዓለም ጦርነት ጀምሮ የነበረ ነው ) «የውሸት ገንዘብ» /Fake Notes/ በዓለም ሁሉ ያለና በእኛም አገር የሚገኝና አሁን ደግሞ እያንሰራራ ያለ ሀሰተኛ ገንዘብን ከእውነተኛ የብር ኖት ጋር ደባልቆ የማይገባ ጥቅም ለማግኘት የሚሰራበት የሻጥር ቃል ነው፡፡

አሁን እጅግ በጣም ትኩስ ሆኖ በመናፈስ ላይ የሚገኘው ሌላው ቃል ደግሞ «የውሸት አሻራ» /Fake –Finger/ የሚባለው ነው፡፡ ሀሰተኛ ወይም የተጨበረበረ የጣት አሻራ እንደማለት ነው፡፡ የውሸት አሻራ ከታሪካዊ ደፓሪ ጽንሰ ሀሳብ ጋር አንዳችም ግንኙነት የለውም፡፡ ቃሉ በቀጥታ የሚያመለክተው ወስላታ የመንግስት ሠራተኞች በሰዓት መቆጣጠሪያ ቅጽ /አቴንዳንስ ሺት/ ላይ የሚያደርጉትን የሰዓት ማጭበርበር ነው፡፡ቦታው ኩዌት ነው፡፡በዚህ አይነቱ ማጭበርበር ቀደምትነት የሚጠቀሱትም የኩዌት የመንግስት ሠራተኞች ናቸው፡፡ የኩዌት የመንግስት ሠራተኞች ግማሽ በግማሽ /50 በመቶው/ ሥራ ገበታቸው ላይ አይገኙም፡፡ ለሰዓታት ማርፈድ ወይም ለቀናት መቅረት ብቻ ሳይሆን ለወራትና ለዓመታት ሥራ አይገቡም፡፡ ሥራ ማግኘት ከሚፈልገው ህዝብ ሀያ /20/ በመቶው ያህሉ የሚፈልገው የመንግሥት ሠራተኛ መሆን ነው፡፡ ምክንያቱም የመንግሥት ሥራ መቀለጃ ነው፡፡ በየት ወጣህ በየት ገባህ የሚለው የለም። የግል ኩባንያ ግን የአመረተውን መጠንና ጥራት ጭምር የሚቆጥር ሥራ ላይ መገኘትን የግድ የሚል የውጭ አገር ሰዎች ያሉበትና ጥብቅ ዲስፒሊን የሚጠይቅ ሥራ በመሆኑ ይህን የሚፈልግ የለም፡፡

የመንግስት ሥራ ያገኘ ሰው የታደለ ነው ሲፈልግ ያረፍዳል፣ ሲፈልግ ግማሽ ወይም ሙሉ ቀን ይቀራል፡፡ ሳምንትም ወርም እርስ በርሱ እየተሸፋፈነ ሥራ መግባት ትቶ የግል ጉዳዩን ሲከውን ይከርማል፡፡ የሚሸፋፈኑት በሰዓት መቆጣጠሪያ ቅጽ /አቴንዳንስ ሺት / ላይ አንዱ ለአንዱ በመፈረም ነው፡፡ይህ የአቴንዳንስ መቆጣጠሪያ ዘዴ በጣም ያረጀው አንጋፋው ዘዴ ነው፡፡ የሰራተኛው ስም በታይፕ ተተይቦለታል፣ በቀኑ አንፃር ብቻ መፈረም ነው፡፡ ስሙን ስለማይፅፍ የፊደል አጣጣሉን አይቶ የእከሌ ፊርማ ነው አይደለም ለማለት አያስችልም፡፡ ፊርማ ማለት የሆነ ያልሆነ ነገር መሞነጫጨር ሳይሆን የራስን ስም በራስ እጅ መፃፍ ማለት ነው፡፡ፈርማ ምለት ሌላ ትርጉም የለውም፡፡ስምን በእጅ መፃፍ ብቻ ነው፡፡ይህ መሞነጫጨር ግን «ፊርማ» ነው እየተባለ ብዙ የወስላታነት ሥራ ሲሰራበት ኖሯል፡፡ ዛሬም እየተሰራበት ነው፡፡ አንዳንዱ መስሪያ ቤት ሰራተኛው በስሙ የተዘጋጀለትን ካርድ የቀን መምቻ ማሽን ውስጥ እያስገባ የሚመታበት አሰራር አለ፡፡ ይህም ቢሆን ዋጋ የለውም ፡፡ ጓደኛው ያስመታለታል፡፡ ሰራተኛው ሥራ ሳይገባ እንደገባ ይቆጠርለታል፡፡ እስካሁን ያሉት የመቆጣጠሪያ ዘዴዎች አልሰሩም፡፡

ከዚህ በኋላ «ሌላ የጣት አሻራ» ዘዴ መጣ የሰራተኛው የሥራ መግባት ባህርይ አጠራጣሪ ሆኖ ሲገኝ በስሙ አንፃር ያሳረፈውን አሻራ ከጣቱ ጋር በማነፃፀር በመመርመር ማጣራት የሚቻልበት ሁኔታ ነበር፡፡ ይህም አላዋጣም ኩዌት ተግባራዊ አድርጋው ነበር፡፡ የመንግስት ሰራተኛው ተንኮል ግን የሚቻል አልሆነም 38 የመንግስት ሰራተኞች በርካታ ጓደኞቻቸውን ሥራ የገቡ ለማስመሰል የውሸት አሻራቸውን ሲሊኮን ከሚባል ንጥረ ነገር የተሰራ ቀጭን ፕላስቲክ ላይ ጣታቸውን እየተጫኑ አሻራ እንዲቀመጥ ማድረግ ጀመሩ አሻራው ግን በሲሊኮን ውስጥ ያለፈ በመሆኑ የማን እንደሆነ አይታወቅም 38 ወስላቶች በብዙ መቶ ለሚቆጠሩ ሰራተኞች በዚህ ዓይነት ሲሰሩ በመቆየታቸው በወንጀለኝነት ህግ ፊት ቀርበዋል፡፡

የጣት አሻራ ብቻውን አላዋጣ ሲል አሻራው ሲደረግ የባለአሻራው የፊት ገጽታ ፎቶ የሚያነሳ አዲስ ማሽን ተሰራ ‹‹ባዮሜትሪክ የመቆጣጠሪያ ስርዓት›› /Biometric attendance system/ የሚባል መሳሪያ መጣ ለሌላ ሰው የሚፈርሙ ወስላቶች ግን ፎቶአቸው መነሳቱን ስላልፈለጉ / ስለፈሩ/ ፊታቸው እንዳይታይ እያደረጉ አሻራቸውን ማስቀመጥ ቀጠሉ፤ ቢታይ ፎቶአቸው የለም! መሳሪያው ሲፈተሽ የተበላሸ ነገር ወይም የቴክኒክ ችግር የለበትም፤ ጥናት ተካሄደ፤ ጉዳዩ ተመረመረ ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ የተካሄደው ጥናት አንዳረጋገጠው ከላይ በተጠቀሱት የወስላታነት ተግባራት ውስጥ በተገኙ 900 ሠራተኞች ላይ የኩዌት መንግስት የደመወዝ እገዳ አድርጓል። የሚገርመው ከነዚህ ሠራተኞች ውስጥ አንዳንዶቹ ለአስር ( 10 ) ዓመት ሥራ ላይ ሳይገኙ ደመወዝ የበሉ ነበሩ፡፡ ሌሎች ደግሞ ለአስራ ስምንት (18) ወራት ውጭ አገር የነበሩ እንኳንስ በሥራ ላይ ሊገኙ በአገርም ውስጥ የሌሉ ሰራተኞች ደመወዝ ሲበሉ ከርመዋል፡፡ ለአለቃቸው ያሳወቁት ነገር የለም፡፡ ፈቃድ አልጠየቁም። የሀኪም ዕረፍት አላቀረቡም፡፡ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ተነጋግረውና ተስማምተው ተዋውለው «ፈርምልኝ ፣አሻራ በሲሊከን አርግልኝ» ተባብለው ሥራ ላይ ሳይገኙ ደመወዛቸው በየአካውንታቸው ሲገባላቸው የኖሩ ናቸው፡፡ ጉዳዩ ብርቅ ላይሆን ይችላል፡፡ አንድ የህንድ አስተማሪ 23 ዓመት ሥራ ላይ ሳይገኝ ደመወዝ ሲበላ በመኖሩ ሪከርድ ይዟል፡፡ ስለዚህ የ10 ዓመቱ ያለሥራ ደመወዝ መብላት ላይደንቅ ይችላል፡፡ የኩዌት መንግሥት ከሥራ ገበታ እየቀሩ በሥራ ባልደረቦቻቸው በሚያስፈርሙና በዚህ ህገወጥ ተግበር ለሚተባበሩ ሁሉ «ወዮላችሁ» እያለ ነው፡፡

እኛ ሥራን የሚያስተጓጉልብን «ስብሰባ» ነው እያልን ጣታችንን እንቀስርበታለን እንጂ ሥራን በማስተጓጎል የአገሪቱን ሀብት /ገንዘብ/ በማባከን ረገድ ዋናው በመንግስት ሠራተኞች ላይ ያለው የአርፋጅነትና የቀሪነት በሽታ ነው፡፡ አርፋጅነት / Lateness/፡፡ ሁለት ገጽታ አለው፤አርፋጅነት ማለት ከሥራ መግቢያ ሰዓት በኋላ አርፍዶ /ዘግይቶ/ መግባትና ከሥራ መውጫ ሰዓት በፊት ቀድሞ መውጣት ማለት ነው፡፡ ፈረንጆቹ /tardiness/ ይሉታል፡፡ መጥፎ በሽታ ነው፡፡ ቀሪነት ግማሽ ወይም ሙሉ ቀን ከዚያም በላይ ሥራ ላይ አለመገኘት ነው፡፡ ላልተሰራ ሥራ በደመወዝ መልክ የሚከፈለው ገንዘብ የህዝብ ገንዘብ ነው፡፡ በጣም ብዙ ገንዘብም ነው፡፡ የሥራ መግቢያ መቆጣጠሪያ ቅፁን የአንድ ወሩን ወስዶ ስንት ሰው ስንት ሰዓት ወይም ቀን እንደቀረ ማየትና ላሉት ሰራተኞች ቁጥር በማካፈል አማካይ የሥራ ጊዜ ብክነት መጠንን ማወቅና ይህንን ወደ ደመወዝ መጠን በመቀየር የሚጠፋውን ብር ግዝፈት ማወቅ ይቻላል፡፡

አርፋጅነትና ቀሪነት በሌሎች ሰራተኞች ላይ የሥራ ጫናን ይፈጥራል፡፡ የራሱን ኃላፊነት ለመወጣት የተቀጠረው ሰራተኛ የሌላ ሰውን ሥራ ደርቦ እንዲሰራ ሲደረግ ችግር ይገጥመዋል፡፡ የሥራው መጠን ጥራትና ፍጥነት ይቀንሳል፡፡ የአርፋጅነትና የቀሪነት ምክንያቶች ብዙ ናቸው፡፡ ግምባር ቀደሙ የቤት ውስጥ ችግር ነው ፡፡ ኑሮ አይመችም ፣ ህይወት አትሞላም ፣ እንዳሰቡት የሚሆን ነገር የለም፡፡ እንቅልፍ ድካም በራሱ ተግዳሮት ነው፤ ጠዋት በ12 ሰዓት ተነስቼ ብለው ያቀዱ ሰዎች ካረፋዱ ሁለት ሰዓት የሚነሱበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ ሰዓት ያጥራቸዋል፡፡ ሌላኛው ምክንያት የትራንስፖርት ችግር ነው፡፡ መኪና እንደልብ አይገኝም፣ በመንገድ መጨናነቅ የተነሳም መኪናው የሚሄደው እንደ ኤሊ እየተንፏቀቀ ነው፡፡

የጤና ችግር አለ ያልታሰበ አደጋ/ ሀዘን/ በራስና በቤተሰብ ላይ ይደርሳል፡፡ የአየሩ ሁኔታ ወደ ሥራ ለመሄድ የሚያበረታታ አይሆንም የሥራ ቦታውም ቢሆን «ኑልኝ ኑልኝ» የሚል ዓይነት ሳቢና ማራኪ ሳይሆን «ሂዱ ፣ጥፉ፣ብረሩ» የሚያሰኝ የሚሆንበት ክስተት ሞልቷል፡፡ አንዳንዱ ቢሮ እንደ አልቤርጎ ተከርችሞ ፣ የሚዋልበት ከሰው ጋር መገናኘት የማይቻልበት ዓይነት ነው፡፡ አንዳንዱ መስሪያ ቤት ደግሞ ከልክ በላይ ሰፍቶ የሰው መቀመጫ ሳይሆን የእህል ማከማቻ መጋዘን የመሰለ፣ የመስታወት ሽንሽን/ ፓርትሽን/ የሌለው አንዱ ድምጽ የሌላውን ሥራ የሚያውክበት ወይም ቀልብ የሚሰርቅበት ፣ በመስመርም ሆነ በሞባይል ስልክ እንደልብ መነጋገር የማይቻልበት ቀፋፊ የሆኑ ስፍራዎች በመሆናቸው ሰራተኞቹ ሥራቸውን እያቋረጡ ወጣወጣ ማለት እንዲያበዙ የሚገደዱበት ሁኔታ ያለባቸው የሥራ ቦታዎች ብዙ ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ የአርፋጅነት እና የቀሪነት መሰረታዊ ችግሮች የሰራተኞች ቸልተኝነትና የአስተዳደሩ የቁጥጥር ብቃት ማነስ ናቸው፡፡ አስተዳደሩ የመቆጣጠሪያ ቅጹን /አቴንዳንሱን/ በጊዜ አያነሳም /አያስነሳም/ የቅፁን የዕለቱ ፊርማ መሟላት አይመለከትም፣በሰራተኞች በራሳቸው መፈረሙን አያረጋግጥም፣ ድንገተኛ ጉብኝት በየሥራ ዘርፉ እያደረገ የመጣና ያልመጣውን አይለይም፡፡ ከአርፋጅና ቀሪዎች ጋር እየተሞዳሞደ ዛሬ ላይ ሆነው የትናንቱን አቴንዳስ እንዲፈርሙ ዕድል ይሰጣል፡፡ ተገቢውን አስተዳደራዊ ርምጃ ማለትም የደመወዝ መቁረጥ የቃልና የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ መስጠት ከማገድ እስከ ማሰናበት ያሉ በሠራተኛ አዋጅ ላይ የተቀመጡ ህጋዊ እርምጃዎችን አይወስድም፡፡

በሥራ ሰዓት (ሲሆን ቀደም ብሎ ካልሆነም በሰዓቱ አናቱ ላይ) አለመገኘት ማርፈድ ወይም መቅረት ለሰውየው ለራሱ፣ ቀጥሎም ለሥራ ባልደረቦቹ እንዲሁም ለድርጅቱ ኪሣራ ትልቅ የራስ ምታት ነው፡፡ ከላይ ከተዘረዘሩት ምክንያቶች አንፃር ሲታይ ሰው ያልታሰበ መሰናክል አያጋጥመውም ማለት ባይሆንም ተገቢ ባልሆነ የርስ በርስ መሸፋፈን (መፈራረም) ላይ ተመክቶ የሚታይ ደንታቢስነት ህገወጥነት ነው፡፡ መልካም ስነምግባር አይደለም፤ መታረም አለበት፡፡ አርፋጅነትና ቀሪነትን የሚጠየፍ ትውልድ ለመፍጠር ጊዜ ሊወስድ ይችላል፡፡ እዚያ ደረጃ ላይ ለመድረስና አሁን ያለውን ችግር ለመፍታት የችግሩ ደረጃ ተጠንቶ ሁኔታው አሳሳቢ ሆኖ ከተገኘ በባዮሜትሪክ መቆጣጠሪያ ስርአት /Biometric attendance system/ ለሙከራ መጠቀም ሳይሻል አይቀርም፡፡

– See more at: http://ethpress.gov.et/addiszemen/index.php/editorial-view-point/item/11914-2017-03-27-17-48-48#sthash.OhWyMk48.dpuf

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy