Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አክሱምን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ መንግስት የሚጠበቅበትን ድጋፍ ያደርጋል- ጠ/ሚ ኃይለማርያም

0 304

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የአክሱም ከተማን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ መንግስት የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአክሱም ከተማ ነዋሪዎች ጋር ዛሬ የተወያዩ ሲሆን፥ ከነዋሪዎቹ ለተነሱት የልማት ጥያቄዎችም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ከነዋሪዎቹ ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል በቂ የመሰረተ ልማት ባለመኖሩ ቱሪስቶች የሚቆዩበት ጊዜ አጭር ነው፤ ከተማዋ ካላት እምቅ የቅርስ ሃብት ክምችት አንጻር በሚፈለገው ደረጃ ጥቅም ላይ አልዋለምና መንግስት በዘርፉ ምን እየሰራ ነው የሚሉ ይገኙበታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ፥ የከተማዋ የቱሪዝም ዘርፍ ገጽታ ለማስተዋወቅ የመሰረተ ልማት ጥያቄ ማሟላት ይገባል ብለዋል፡፡

“መንግስትና የግል ባለሃብቶች የየራሳቸው ድርሻ በመውሰድ መስራት አለባቸው” ሲሉም አስታውቀዋል።

“ቱሪስቶች ብቁና አስተማማኝ የሆነ አገልግሎት ማግኘት ይፈልጋሉ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፥ ትልቁ ጉዳይ መልካም አቀባበልና የተሳለጠ አገልግሎት ከሌለ የቱሪስት ፍሰት ሊቀንስ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

ይህንን ለማስተካከል መንግስትም የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

“በከተማዋ የሚገኘው የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ይህንን በኃላፊነት መሰራት እንዳለበትና የቅርስ ጥናትና ልማት መዋቅራዊ ለውጥ በማምጣት የድርሻውን ሊወጣ ይገባል” ብለዋል።

ከቅርስ ጥናት ልማት ባለፈ አስጎብኚዎች ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኙ በኢትዮጰያ ስምንት የሚሆኑ ዩኒቨርስቲዎች በቱሪዝም ልማት ዘርፍና በእንግዳ አቀባበል ላይ ያተኮሩ ትምህርቶች እንደሚሰጡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡

ዩኒቨርስቲዎቹ ከዲግሪ መርሃ ግብር በተጨማሪ ህዝቡን በዘርፉ ላይ ግንዛቤውን እንዲያሳድግ አጫጭር ስልጠናዎችን በመስጠት ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

የከተማዋ የእድገት ማነቆ የሆነውን ንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር በዘላቂነት ሊፈታ የሚችል ግድብ እንደሚገነባ ተነግሮ ነበር እስካሁን ግን አልተጀመረም ለምን የሚል ጥያቄም ከነዋሪዎች ተነስቷል፡፡

የግድቡ ግንባታ ወደ ተግባር እንዲሸጋገር ክትትል እንደሚያደርጉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ ገልጸዋል፡፡

“በእኔ እምነት አክሱም ከተማ መነቃቃት ጀምራለች፣ ለመነቃቀትዋ መነሻ የሚሆነው ነገር በአግባቡ ተለይቶ መታወቅ አለበት”ብለዋል።

ቢሆንም ከተማዋ ከእድሜ ጠገብነቷዋ አንጻር ሲታይ የሚመጥናት እድገት ግን እንዳላሳየችም ጠቅሰዋል።

ነዋሪዎቹ ለከተማ እድገት የፌዴራል መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግ በጠየቁት መሰረት የተመረጡና መሰረታዊ የሆኑ ጥያቄዎችን ለመመለስ ድጋፍ እንደሚደረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ ላይ አረጋግጠዋል፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በተደረገው ውይይት ላይ ከተሳተፉት ነዋሪዎች መካከል የሃይማኖት አባቶች፣ምሁራን፣የንግድ ማህበረሰብና የወጣቶች ተወካዮች ይገኙበታል፡፡

ምንጭ፦ ኢዜአ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy