Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አዲሱ የኢትዮ-ኳታር ግንኙነት

0 984

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አዲሱ የኢትዮ-ኳታር ግንኙነት/ ዘአማን በላይ/

     የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ነው። ይህ ፖሊሲ ሰጥቶ የመቀበል አካሄድን ይከተላል። ፖሊሲው ሀገራችን በሁለትዮሽ መንገድ ከየትኛውም ሀገር ጋር የምታደርገው ግንኙነት ተባብሮ በማደግ፣ ያላትን የተፈጥሮ ሐብት እጅ ለእጅ ታይዞ በመጠቀም በጋራ ለማደግ ያለመም ነው። ማንኛውም የዚህ ፅሑፍ አንባቢ እንደሚያውቀው ሀገራችን የእርስ በርስ ግጭትና ስር የሰደደ ድህነት ተምሳሌት ተደርጋ ትታወቅ ነበር።

ታዲያ በዚህ አሳፋሪና መጥፎ ምሳሌነት የተሳለችው ኢትዮጵያ፤ ካለፉት 26 ዓመታት ወዲህ ገፅታዋን በመለወጥ ላይ ትገኛለች። የኢፌዴሪ መንግስትና መላው ህዝቦቿ አንድነት ፈጥረው በእነዚህ ዓመታት ባከናወኗቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት በዓለም አቀፉ መድረክ በአዲስ ገፅታ መታየት ጀምራለች።

በተለይም ላለፉት 15 ዓመታት በኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ያላሰለሰ ጥረት ሀገራችን ውስጥ ጠንካራ፣ ፈጣንና ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት እየተመዘገበ ከመሆኑም በላይ፤ ሀገራችን በዓለም አቀፍ የፖለቲካና ዲፕሎማሲ መድረኮች ተሰሚነቷ እየጎለበተ መጥቷል። ታዲያ ሀገሪቱ እነዚህን ስኬታማ ድሎች ለመቀዳጀት የቻለችው በተለያዩ ዘርፎች ተቀርፀው ተግባራዊ በተደረጉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች አማካኝነት መሆኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም።

በሀገሪቱ ውጤታማ ከሆኑት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ውስጥ የውጭ ጉዳይና የሀገራዊ የደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ አንዱ ሲሆን፤ በእኔ እምነት በዚህ ፖሊሲና ስትራቴጂ ውስጥ የተመለከተውና ከሀገራት ጋር የሚደረገው የሁለትዮሽ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ዘርፍ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው። ይህ ዘርፍ የሀገራችንን ተፈላጊነት ያጠናከረና ልማታዊ ዲፕሎማሲውን ከፍ በማድረግ ላይ ይገኛል።

ይህን ዕውነታ ለማረጋገጥም ያለፉትን ድሎች ሳንጠቅስ፤ በቅርቡ ሀገራችን ከግብፅ፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከሶማሊያና ከሱዳን ሪፐብሊክ እንዲሁም ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካኝነት ከሞዛምቢክና ከታንዛኒያ ብሎም ከሌሎች ሀገራት ጋር እያደረገች ያለችው በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ግንኙነት መጥቀስ የሚቻል ይመስለኛል።

የዚህ ፅሑፍ ዓላማ ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት ጋር የምታደርገውን የሁለትዮሽ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ግንኙነት ተግባራትን መተንተን አይደለም። ይልቁንም ሰሞኑን የኳታሩ አሚር ሼክ ታሚም ቢን ሐሚድ አልታኒ በሀገራችን ለሁለት ቀናት ያደረጉትን ጉብኝት አስመልክቶ ሀገራችን በዚህ የዲፕሎማሲ መስክ የተቀዳጀችውን ድል ማሳየት ነው። ታዲያ እዚህ ላይ የኢትዮ-ኳታር ግንኙነት ሀገራችን ከሌሎች ሀገራት ከምታደርገው የሁለትዮሽ ግንኙነት የተለየ ነው እያልኩ አይደለም። ምንም ዓይነት ልዩነት የለውም።

ሆኖም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለየት የሚያደርገው ከዚህ በፊት እ.ኤ.አ በ2008 ዓ.ም የኢትዮ-ኳታር ግንኙነት ተቋርጦ ስለነበር የተለየ የሚያደርገው ይመስለኛል። እናም የተቋረጠ ግንኙነትን ለመቀጠል ከማሰብ ባሻገር፣ የአንድ ሀገር መሪ ግንኙነቱን ወዳቋረጠው ወደ ሌላኛው ሀገር በማቅናት ግንኙነቱን ለማደስ መፈለጋቸው የኢትዮጵያን ተፈላጊነት ስለሚያረጋግጥ ይህን ዕውነታ ማውሳት የግድ የሚል ይመስለኛል። ይህን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በርዕሰ ጉዳይነት ያነሳሁትም ለዚህ ነው።

ምንም እንኳን ኢትዮጵያና ኳታር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.ኤ.አ በ1995 ዓ.ም ቢሆንም፤ ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው ከ13 ዓመታት በኋላ እ.ኤ.አ በ2008 ዓ.ም ተቋርጧል። ለመቋረጡ ምክንያት የሆነው ደግሞ የኳታር መንግስት የኳታር መንግስት ንብረት እንደሆነው የሚነገረው አልጀዚራ ቴሌቪዥንና በሀገራችን በኢፌዴሪ መንግስት በአሸባሪነት የተሰየሙ ድርጅቶችን በቀጥታ ይሁን በተዘዋዋሪ እንደሚደግፍ በኢትዮጵያ በኩል ተቃውሞ ማስነሳቱ ነው። ታዲያ የኢትዮጵያ መንግስት ድርጊቱን በመቃወም ለኳታር መንግስት በተደጋጋሚ ቢያስታውቅም፤ የዶሃው አስተዳደር ተገቢ የሆነ ምላሽ ባለመስጠቱ የኢትዮጵያ መንግስት ሳይወድ በግድ የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ እንዲቋረጥ አድርጓል።

ይህ የኢፌዴሪ መንግስት ውሳኔ ከየትኛውም ሀገር ጋር በጋራ ተጠቃሚነትና የሌሎችን ጥቅሞች ባለመንካት የውጭ ግንኙነት መርህን ለምትከተለው ሀገራችን ከባድ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይመስለኝም። ምክንያቱም የኢፌዴሪ መንግስት ከሚከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ሰላማዊ እንዲሁም ከሁሉም ሀገራት ጋር የተጠናከረና በወዳጅነት መንፈስ የታጀበ ግንኙነት እንዲኖረው ፅኑ እምነት ስላለው ነው። እናም ውሳኔው ምን ያህል ከባድና ከሀገራችን ሰላማዊና በወዳጅነት ላይ የተመሰረተ የግንኙነት መርህን የሚፈታተን እንደነበር ለማንም ግልፅ ይመስኛል።     

ያም ሆኖ ግን ምናልባትም የዶሃው አስተዳደር የሀገራችንን ትክክለኛ የዲፕሎማሲ መርህ በመረዳቱ፤ የዛሬ ሶስት ዓመት በፊት ግንኙነቱ ወደነበረበት እንዲመለስ ማድረግ ተችሏል። እናም በዚያን ወቅት የኳታሩ አሚር ሼክ ሐማድ ቢን ካሊፋ አልታኒ በኢትዮጵያ ያደረጉት ይፋዊ ጉብኝት ሁለቱ ሀገራት ግንኙነታቸውን ዳግም እንዲያድሱ በር ሊከፍት ችሏል። በጉብኝቱ ወቅትም ሀገራቱ ተደጋጋሚ ቀረጥን በማስቀረት፣ በአየር ትራንስፖርት፣ በኢንቨስትመንት ከለላ፣ በባህልና ንግድ ላይ ተባብረው ለመስራት የሚያስችሏቸውን ጨምሮ ሌሎች 11 የመግባቢያ ስምምነቶችን ተፈራርመዋል። ስምምነቶቹን ወደ ተግባር ለመለወጥም ብዙ ጥረት ተደርጓል።

የኳታሩ አሚር ሰሞኑን ባደረጉት ጉብኝትም ከኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር ተወያይተዋል። በውይይቱም የሁለቱን ሀገራት የኢኮኖሚና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ይበልጥ ማሳደግ እንዲሁም ፖለቲካዊ ትስስርን ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክረዋል። ከዚህ በተጨማሪም አሚሩ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ሀገራችን እየተጫወተች የምትገኘውን ሚና ከማድነቅ ባሻገር፤ ይህን ተግባርም እንደምትደግፍ ገልፀዋል። ኢትዮጵያም በበኩሏ የሀገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር፤ የኳታር ባለ ሃብቶች በኢትዮጵያ በግብርና፣ በማዕድንና በአገልግሎት ዘርፎች እንዲሰማሩ ጠይቃለች።

ከዚህ የውይይት መንፈስ የምንረዳው አንድ ነገር አለ። እርሱም ውይይቱ ሀገራችን እንደምትፈልገውና ከማንኛውም ሀገር ጋር ለማድረግ የምትሻውን በሰጥቶ መቀበልና በጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ ያተኮረ መሆኑ ነው። ይህም ኢትዮጵያ ላለፉት ዓመታት ስትከተለው የነበረው ፖሊሲ ውጤት ይመስለኛል።

ውይይቱ ኢትዮጵያ የትኛውም ሀገር ጋር ለጋራ ተጠቃሚነት የምትሰራና ይህን ወሳኝ መርህ ተፃርሮ እስካለቆመ ድረስ ከማንኛውም ሀገር ጋር በአጋርነት መንፈስ እንደምትተባበር ያረጋገጠ ክንዋኔም ነው ማለት ይቻላል። ርግጥ የኳታሩ አሚር እንዳሉት ሀገራችን ከምትከተለው የሰላም ፖሊሲ አኳያ ቀጣናዊ ጥረት እያደረገች ነው። በተለይም በሱዳን-ዳርፉርና አብዬ እንዲሁም በሶማሊያ መስዕዋትነት በመክፈል ጭምር ሰላምን የማስከበር ተግባር እያከናወነች ትገኛለች። ይህ የሰላም ማስከበር ተግባር እንደ ኳታር ዓይነት ሀገራት ቢደገፍ ደግሞ ሀገራችን የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንድትቀጥል ያስችላታል። እናም በእኔ እምነት ኳታር ሀገራችን በምታከናውነው የሰላም ማስከበር ሂደት ላይ የበኩሏን ድጋፍ ማድረግ የምትችል ከሆነ፤ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት የበኩሏን ሚና ልትጫወት ትችላለች።

ምንም እንኳ ሀገራችን በተባበሩት መንግስታት ድርጅትና በአፍሪካ ህብረት ብሎም በራሷ የሰላም መርህ በመመራት እስካሁን ድረስ ውጤታማ ተግባር ያከናወነች ቢሆንም፤ በእያንዳንዷ የሀገሪቱ የሰላምና የልማት ተግባር ትንሽም ቢሆን አስተዋፅኦ ማድረግ የሚችል አካል ካለ ውጤታማነቱን ይበልጥ ያግዘዋል። ይህም ላለፉት ዘመናት በጦርነትና በእርስ በርስ ግጭት ሲታመስ የኖረውን ምስራቅ አፍሪካንና ህዝቦቿን ከሰላም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።

ከሰላም ወጣ ብለን ወደ ልማቱ ስንመለስ እንደ ኳታር ዓይነት ሀገራት ኢትዮጵያ ውስጥ በግብርናው ኢንቨስትመንት ዘርፍ ቢሳተፉ ራሳቸውን ጠቅመው ኢትዮጵያንም ሊጠቅሙ ይችላሉ። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በቆላማው የሀገራችን አካባቢዎች ለግብርና ስራ ምቹ የሆነ እጅግ ሰፊ ያልለማ መሬት አለ። ይህ መሬት ደግሞ ጥቅም መስጠት አለበት። እናም መሬቱን በአግባቡ በመጠቀም የግብርና ኢንቨስትመንትን ማስፋት ይገባል።

ያም ሆኖ ግን ይህን መሬት አርሶ ለመጠቀም ካፒታል ያስፈልጋል። የኳታር ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን በዚህ ዘርፍ ላይ ማዋል ከቻሉ፤ ከግብርና ሊገኝ የሚችለውን የጋራ ተጠቃሚነት ማጎልበት ይቻላል። የኳታር ባለሃብቶች በግብርናው ዘርፍ ተሳትፈው ከሚያመርቱት ምርት ትርፍ ማግኘታቸው አይቀሬ ነው። ኢትዮጵያም ከመሬቷ ተጠቃሚ የምትሆን ሲሆን፤ በርካታ ዜጎቿም የስራ ዕድል ያገኛሉ። ይህም ሁለቱም ወገኖች ተጠቃሚነታቸው እንዲጎለብት ዕድል የሚሰጥ ነው። በመሆኑም ከሶስት ዓመት በፊት የተጀመረው አዲሱ የኢትየ-ኳታር ግንኙነት እነዚህ ሁሉ የጋራ ተጠቃሚነት ዕድሎች ያሉት በመሆኑ ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል እላለሁ።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy