Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢትዮጲያ ሲባል ማን ዝም ይላል ሰምቶ፡፡

0 325

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኢትዮጲያን እንደሀሳብ መዝፈን ማለት ይህ ነው

ቴዎድሮስ ጸጋዬ

ቴዎድሮስ ካሳሁን በአዲሱ አልበሙ ላይ ኢትዮጲያን ከየትኛውም ቀድሞ ከሚታወቅ ግለሰብ ጋር ሳያዛምድ፣ ቀድሞ ከገነነ ልዩ ክስተት ጋር ሳያገናኝ እንደጽንሰ ሀሳብ ቢዘፍናት እወዳለሁ ብዬ ነበር፡፡ እነሆ ኢትዮጲያ የተሰኘውን ዘፈን አደመጥኩ፡፡ እናም፣ የሻትኩትን አገኘሁ፡፡

ኢትዮጲያ በዚህ የቴዎድሮስ ካሳሁን ዘፈን ላይ እንደማንነት፣ እንደአገርነት ተዘፍና በመስማቴ ደስ ተሰኝቻለሁ፡፡ ኢትዮጲያ በዚህ የቴዎድሮስ ግጥም ውስጥ ከዚህ ቀደም ቴዎድሮስ ካሳሁን ከሚያደርገው በተለየ መልኩ ከግለሰቦችና ክስተቶች በላይ ልቃ፣ በረቂቅ ሀሳብነት፣ በሁለንተና ጥላነት ተገልጻለች፡፡ በብዙሀን ቤዛነት፣ በልጆቿ መስዋእትነት የተዋጀች አገር መሆኗ ተዚሟል፡፡ ኢትዮጲያ በልባችንና በነፍሳችን ያላትን ጥልቅ ትርጓሜና ተሻጋሪ አንድምታ ያነሳል ይህ የቴዎድሮስ ካሳሁን የዘፈን ግጥም፡፡

እንኳን ሰማይ ላይ ባንዲራዋን አይቶ፣

ኢትዮጲያ ሲባል ማን ዝም ይላል ሰምቶ፡፡

በእነኚህም ስንኞች ይህ ክቡር ባንዲራ ከሌሎች ባንዲራዎች ጋር እኩል የሚተካከል ሳይሆን፣ ከሁሉ ከፍ ብሎ፣ ሁሉ በሚያየው ስፍራ በሰማይ ሳይቀር በደመና ሸራነት የተሳለ፣ ሰማይ ላይ የሚውለበለብ እጹብ ባንዲራ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ ኢትዮጲያ ከግለሰብ ጋር ሳትተሳሰር፣ በልዩ ክስተት ልክ ሳትጠብ፣ በረቂቅነቷ የተወደሰችበት አንድ ተጨማሪ ዘፈን ማግኘታችን ለኢትዮጲያውያን ሁሉ መልካም በረከት ነው፡፡

ይበልጥ የወደድኩትን መንቶ ላጋራችሁ፡፡

የሰለሞን ዕጽነሽ የቅዱሳን እንባ ያበቀለሽ ቅጠል፣

ዛሬ አዲስ አይደለም በለኮሰው እሳት የነካሽ ሲቃጠል፡፡

እውነት ነው፣ ኢትዮጲያ በብዙ ፈተና ብታልፍም በአምላኳ ጥበቃ፣ በህዝቧ ምህላና ደም የኖረችና የምትኖር አገር ናት፡፡

ሳይወሰን ዝናሽ በቅርሶችሽ ድርሳን በአድባራት ታሪኩ፣

ነብይ አይተው ከሩቅ ያሉልሽ በመጽሀፍ ኢትዮጲያን አትንኩ፡፡

እነኚህም ስንኞች የኢትዮጲያን ድንበር ከድንበሯ በላይ መስፋት፣ የዝናዋን ከአጽናፍ አጽናፍ መስተጋባት መስክረዋል፡፡ ግሩም ነው፡፡ ከዚህ በኋላ አልበም የምታወጡ ድምጻውያንም ኢትዮጲያን የመቀኘቱን ነገር እንደውዴታ ግዴታ ብትቆጥሩልንና ነፍሳችንን ብታክሙት እንዴት በወደድን?

ኢትዮጲያን እንደሀሳብ መዝፈን ማለት ይህ ነው፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy