ኢትዮጵያ በሁለተኛው ዕቅድና ትራንስፎርሜሽን ጊዜ 7 ሚልዮን ሄክታር መሬት እንዲያገግም በማድረግ ለአለም አየር ንብረት ለውጥ አዎንታዊ ሚና እየተጫወተች መሆኗን የአከባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚንስቴር ገለጸ፡፡
እኤአ በየአመቱ ሚያዝያ 22 በመንግስታቱ ድርጅት የሚከበረውን የመሬት ቀን አስመልክቶ የአከባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚንስቴር ህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ነጋሽ ማብራት በተለይ ለኢቢሲ እንደገለጹት ኢትዮጵያ የቀረጸችውን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ መሰረት በማድረግ የተጎዱ መሬቶችን ከሰውና እንስሳ ንኪኪ ነጻ በማድረግ እንዲሁም ዛፎች በመትከል እንዲያገግም እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
የመሬት ብክለትንም ለመከላከል የብክለት ቁጥጥር አዋጅ በተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁን አቶ ነጋሽ ገልጸዋል፡፡
የአከባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚንስቴር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጋር በጋራ በመሆን ያደረጉት ጥናት በአዲስ አበባ የሙቀት አማቂ ጋዞች መጠን መጨመሩን ያሳያል ብለዋል ህዝብ ግንኙነት ባለሙያው፡፡
ወደ አገር ውስጥ የሚገባ የነዳጅ ጥራትና ያገለገሉ መኪናዎች ለአማቂ ጋዝ መጠን መጨመር ምክንያት መሆናቸውን የተደረገው ጥናት ማረጋገጡንም ተናግረዋል አቶ ነጋሽ፡፡
የሙቀት አማቂ ጋዞችን መጠን መቆጣጣር እንዲያስችል ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ከሚገኘው የአየር ብክለት መቆጣጠሪያ በተጨማሪ በአደማና በሀዋሳ መተከሉን የገለጹት አቶ ነጋሽ ከዚህ በተጨማሪ የአየር ጥራትን መጠበቅ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ እየተዘጋጀ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ለብክለት ዋነኛ መንስዔ ከሆኑትን ከፋብሪካዎችና አበባ እርሻዎች የሚወጡ ፈሳሾችን ላይ የላብራቶሪ ናሙና እየተወሰደ ክትትል እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በዚህም አጋጣሚ ብክለትን ለመቀነስ ህብረተሰቡ ቆሻሻን በተገቢው ቦታ እንዲጥልና ባለሃብቶችም ለአጭር ጊዜ ትርፍት መሰረት አድርገው አከባቢን ከመበከል እንዲቆጠቡ ህዝብ ግንኙነቱ አቶ ነጋሽ ማብራት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የዘንድሮ የመሬት ቀን የአከባቢና የአየር ንብረት ለውጥ ግንዛቤ ማሳደግ “Environmental & Climate Literacy” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ይገኛል፡፡