Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እህት አገር ወንድም ህዝብ!

0 344

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኢትዮጵያና የሱዳን ግንኙነት ከአክሱም ዘመነ መንግሥት ጀምሮ እንደተመሰረተ የሚገልጹ ጸሀፍት አሉ። የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ይህን እውነታ ይጋራል። ቁም ነገሩ ያለው ግንኙነት መቼ ተጀመረ? የሚለው ሳይሆን፤ በዚህ እድሜ ጠገብ በሆነው ግንኙነት ውስጥ አገራቱ ምን አተረፉ? ምንስ ከሰሩ? የሚለው ነው።

ከዚህ እውነታ ተነስተን የሁለቱን አገራት ግንኙነት ስንመለከት በየዘመኑ የየራሱን አሻራ ትቶ ማለፉን እንረዳለን። ሱዳን ለኢትዮጵያ ስጋት የነበረችበት፤ ኢትዮጵያም ለሱዳን ሰላምና ፀጥታ አስጊ ሆና ትታይ የነበረበት ዘመን መኖሩን ታሪክ ይነግረናል። አንዳቸው የሌላውን መንግሥት ለመጣልም መስራታቸው የአገራቱ የታሪክ ምዕራፍ ሲገለጥ የሚያስረዳው ሀቅ ነው።

ይህ አለመተማመን የፈጠረው በስጋት የተወጠረ ግንኙነት የተወገደውና ዛሬ ላይ ለሚታየው ፍሬያማ ደረጃ የበቃው በኢትዮጵያ የተደረገውን የስርዓትና የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ ነው። በኢትዮጵያ የደርግ መንግሥት ከወደቀ በኋላ የኢፌዲሪ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቅኝቱን ከውስጥ ወደ ውጭ በመቀየርና፤ ጎረቤት አገራትንም እንደ የስጋት ምንጭ ሳይሆን፤ ለአገራችን ልማትና ዴሞክራሲ ግንባታ ካላቸው ፋይዳ አንጻር መመልከት መጀመሩ ሱዳንንም ብቻ ሳይሆን የተቀሩትን ጎረቤት አገራትንም መልካም አጋር ማድረግ አስችሏል። ከኤርትራ በስተቀር።

በዚህ ፖሊሲ መሰረት ሱዳን ዛሬ እህት አገር ሆናለች። ሱዳናዊያንም ወንድም ህዝብ። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያንም ለሱዳንና ሱዳናዊያን እንደዚያው ናቸው። ዛሬ ስለሱዳን ሰላምና ፀጥታ የምትጨነቀው ሱዳን ብቻ አይደለችም፤ ኢትዮጵያም ጭምር እንጂ። ምክንያቱም የሱዳን ሰላም ለኢትዮጵያም እረፍት ነው። የሱዳን ሰላም ማጣት ለኢትዮጵያ የጎን ውጋቷ ነው። ብሂሉም እኔ ሰላም እንድሆን ጎረቤቴን ሰላም አድርገውነውና ስለሱዳን ሰላም አብዝተን መጨነቃችን በብዙ መልኩ ተገቢ ነው። ስለምንጨነቅና ስለሚገባንም ጭምር ነው ሰላም አስከባሪ ሰራዊት በመላክ ለሱዳን ሰላም ዘብ የቆምነው።

የተረጋጋ ጎረቤት የብልጽግና ዋስትና ነው። ኢትዮጵያና ሱዳንም በተረጋጋው የውስጥ ሰላማቸው ዛሬ አንዳቸው ለሌላኛው በአያሌው የሚያስፈልጉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ሱዳናዊያን ከኢትዮጵያ ልማት መጎንጨት መጀመራቸው የኢትዮጵያን ሰላምና መረጋጋት የራሳቸው ያህል የሚጠብቁትና የሚንከባከቡት ሆኗል።

ኢትዮጵያ የተከዜ ወንዝን በመገደብ ለሃይል ማመንጫ በማዋሏ ሱዳኖች ከደለል ነፃ የሆነ ውሃ በማግኘታቸው ተጨማሪ ግድብ መገንባት ሳይጠበቅባቸው የመስኖ ልማታቸውን ማስፋፋት ችለዋል። የአሌክትሪክ ሃይልም በአነስተኛ ዋጋ ማግኘት ችለዋል። ስለሆነም የኢትዮጵያ ልማት ለሱዳናዊያን መብራትም እራትም ሆኖላቸዋል ቢባል ስህተት አይሆንም።

ኢትዮጵያም ቢሆን ከሱዳን የምታገኘው ጥቅም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ከአማራጭ የወደብ አገልግሎት ጀምሮ በተመጣጣኝ ዋጋ ነዳጅ፣ ለምርቶቿ ደግሞ ገበያና መሰል ጥቅሞችን እያጣጣመች ናት። በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው የንግድ ልውውጥም 300 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል። በኢትዮጵያ ካሉ የውጭ ባለሀብቶች መካከልም የሱዳን ባለሀብቶች በብዛታቸው ተጠቃሽ ናቸው። ይህ ብዙ ለሚደከምለት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የሱዳን ኢንቨስትመንት በዚህ ደረጃ መምጣቱ ትልቅ ጥቅም ነው።

በሀገራቱ መካከል ያለው የጉርብትናና የወንድማማችነት ግንኙነት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፎች ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠሉን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። የህዝብ ለህዝብ ትስስሩና ግንኙነቱን ያህል በኢኮኖሚውና በፖለቲካው መስክ መድገም ይገባል። በተለይም ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ግራ ቀኙን አይታና እውነታውን ተረድታ የያዘችው አቋም፤ በኢትዮጵያ ዘንድ ምክንያታዊ አገር እውነተኛ አጋርም አድርጓታል። ይህንን አጋርነትም የናይል ወንዝ የትብብር ማዕቀፍን በመፈረምም እንዲደገም ኢትዮጵያ መስራት አለባት።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy