ከኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ያለአግባብ 11 ሚሊየን ብር ካሳ እንዲከፈል ያደረጉና የወሰዱ ግለሰቦች በጽኑ እስራት በገንዘብ መቀጮ ተቀጥተዋል።
ተከሳሾቹ በዳዋ ጨፋ ወረዳ ግንባታው በመካሄድ ላይ በሚገኘው የአዋሽ ወልዲያ የባቡር መስመር ግንባታ ወቅት ያለአግባብ 11 ሚሊየን ብር ካሳ እንዲከፈል በማድረጋቸውና በመውሰዳቸው ነው ክስ የተመሰረተባቸው።
ከተከሳሾቹ ውስጥ አምስቱ የካሳ ኮሚቴ ገማች ኮሚቴ አባላት ሲሆኑ፥ አንዱ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የመንገድ መብት ጥበቃ ተወካይ እንዲሁም ቀሪዎቹ ደግሞ የአካባቢው ነዋሪዎች እና የወንጀሉ ተሳታፊዎች መሆናቸው በአቃቤ ህግ ክስ ላይ ተብራርቷል።
ተከሳሾቹ በጋራ በመሆን ለ7ኛ ተከሳሽ አቶ ሰኢድ የሱፍ ምንም አይነት መሬት ሳይኖረው በባቡር ግንባታ ፕሮጀክቱ መሬቱን አጥቷል በሚል 1 ነጥብ 8 ሚሊየን እንዲከፈለው አድርገዋል።
እንዲሁም ለ8ኛ ተከሳሽ አርሶ አደር አደም ሁሴን የሸንኮራ እርሻ መሬት ሳይኖረው የአትክልት መሬት ሲሆን ግምቱ ይጨምራል በሚል ለባዶ መሬት ከ180 ሺህ 843 ብር በላይ ገምተው ሰጥተዋል የሚለውም በክሱ ላይ ሰፍሯል።
በተጨማሪም ለ9ኛ ተከሳሽ አቶ አደም አርጋው ምንም አይነት መሬት ሳይኖረው መሬቱ ተወስዷል በሚል 3 ነጥብ 263 ሚሊየን ብር የሰጡት ሲሆን፥ ለ10ኛ ተከሳሽ ወይዘሮ ጀማዬ አሊ ባለቤቷ የሆነው 9ኛ ተከሳሽ የሆነው የወሰደውን ካሳ በድጋሚ እንትወስድ መደረጉም በክሱ ላይ ተገልጿል።
ተከሳሾቹ በአጠቃላይ በዚህ መልኩ ከኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን 11 ሚሊየን ብር ያለ አግባብ እንዲከፈል ያደረጉ ሲሆን፥ ለዘጠኝ ግለሰቦችም የማይገባቸውን ካሳ እንዲከፈላቸው አድርገዋል ይላል የአቃቤ ህግ ክስ።
ከ1ኛ እስከ 5ኛ ተከሳሽ የተዘረዘሩት የካሳ ገማች ኮሚቴ አባላት ስልጣናቸውን ያለ አግባብ በመጠቀም ክስ ቀርቦባቸዋል።
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የመንገድ መብት ጥበቃ ተወካይ የሆነው 6ኛ ተከሳሽ አቶ ወንዴ ወይሳ በተሰራው ግምት ላይ ክፍያ እንዲፈፀም በፊርማቸው አረጋግጠዋል የተባለ ሲሆን፥ ከ7ኛ እስከ 10ኛ ያሉት ደግሞ ያለአግባብ እና በሌላቸው መሬት ግምት ተሰርቶ የተሰጣቸውን ገንዘብ ተቀብለዋል በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
የክስ መዝገቡም ለአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀርቦ ለተከሳሾች የተነበበ ሲሆን፥ ተከሳሾችም የቀረበባቸውን ክስ አላስተባበሉም።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ደሴ ምድብ ችሎትም አስሩንም ተከሳሾች ጥፋተኛ ብሏቸዋል።
በዚህም መሰረት 1ኛ ተከሳሽ ጋሮማ ንጉሴ፣ 3ኛ ተከሳሽ ተስፋዬ ከበደ እና 7ኛ ተከሳሽ ሰኢድ የሱፍ በ4 ዓመት ከ5 ወር ጽኑ እስራት እና በ7 ሺህ በር፤ 4ኛ ተከሳሽ አቶ ደረጄ ዲንሳ በ1 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት እና 400 ብር፤ 6ኛ ተከሳሽ አቶ ወልዱ ወዬሳ በ5 ዓመት ፅኑ እስራት እና በ7ሺህ ብር፤ 8ኛ ተከሳሽ አቶ አደም ሁሴን በ4 ዓመት ጽኑ እስራት እና በ7 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል።
ባል እና ሚስት የሆኑት 9ኛ እና 10ኛ ተከሳሽ እያንዳንዳቸው በ3 ዓመት ከ3 ወር ጽኑ እስራት እና በ3 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ተወስኗል።
2ኛ ተከሳሽ ማርቆስ ኮርሜ በከፍተኛ ህመም ላይ በመሆኑ ከበሽታው እስኪያገግም የክስ ሂደቱ ተቋርጧል።
በካሳ ክፍያው ስም ሊሰጥ ከታሰበው ከ11 ሚሊየን ብር በላይም ሳንቀሳቀስ በባንክ የተያዘ በመሆኑ ለመንግስት ተመላሽ እንዲሆን ትእዛዝ ተላልፏል።