Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከኢትዮጵያ…. በስተቀር !!

0 378

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከኢትዮጵያ…. በስተቀር  !! / ይነበብ ይግለጡ/

የአፍሪካ  እድገትና መነሳት በስፋት ለሚገኘው አፍሪካዊ ወጣት ተደራሽ መሆን አብሮ ይዞት መጓዝም አልቻለም፡፡የወጣቱ የስራ አጥነት ችግር  በመላው አፍሪካ የሚታይ ችግር ሲሆን አንዲት ከአፍሪካ ውስጥ ብቸኛ ሀገር ኢትዮጵያ የወጣቱን ችግር ለመፍታት የምትችለውን ሁሉ እያደረገች ነው ሲል የኢብራሂ ሞ ፋወንዴሽንን ዘገባ መነሻ በማድረግ ኩዋርትዝ አፍሪካ ዘግቦአል፡፡

በሀገር አቅም በሀገር ገንዘብ ወጣቱን የራሱ ስራ ባለቤት ለማድረግ ሰርቶም እራሱን እንዲለውጥ በተራውም የስራና የፈጠራ ችሎታውን ተጠቅሞ አዳዲስ የስራ መስኮችን ለዜጎች እንዲፈጥር ኢትዮጵያ ለወጣቶችዋ ቅድሚያ በመስጠት የምትችለውን ሁሉ እያደረገች ነው፡፡ በመሬት ላይ ያለ ተጨባጭ እውነት ነው ዘገባው ያሰፈረው፡፡ምስክርነቱ ራሱን ችሎ መሰጠቱ የሚያበረታታ ነው፡፡ከድፍን አፍሪካ ሀገራት ኢትዮጵያ በምሳሌነት መጠቀስዋ ለበለጠ ውጤት የሚያነሳሳ ነው፡፡

በአለፉት አስርት አመታት ኢኮኖሚያቸው አድጎና ተንሰራፍቶ የነበሩት የአፍሪካ ሀገራት ጭምር የወጣቶቻቸውን ችግር በማጤንና በመረዳት መፍታት አልቻሉም፡፡አፍሪካ እያደገች እየተነሳች፤እያሻቀበች ነው የሚለው አባባል ለአፍሪካ ወጣቶች በተጨባጭ ያደረገው ወይም የሰራው ነገር ትንሽ ነው፡፡አህጉሪቱን በመላው ጉልበቱ ሊለውጣት የሚችለው የወጣቱ ኃይል በአፍሪካ ውስጥ እንደ አደጋ እየተቆጠረ ነው ሲል ኩዋርትዝ አፍሪካ ይገልጻል፡፡

በሞ ኢብራሂም ፋወንዴሽን የወጣው አዲስ ሪፖርት የአፍሪካን አህጉር ወጣቶች ተጨባጭ ሁኔታ በሚያሳይ ዳታ የታጨቀ ነው፡፡ሪፖርቱ መለየት የቻለው በአንድ ወቅት በአህጉሪቱ ብልጭ ብሎ የነበረው ተስፋ ወደ ተስፋ ማጣትና ጨለማነት መቀየሩን ነው፡፡ፖለቲካዊ ቅዠት፤ከችሎታ ጋር ያልተመጣጠነ ትምህርትና ከጀርባ ማምለጥ እንዲሁም አሸባሪነት የአፍሪካን አህጉር ወጣቶች ሕልም እየነጠቁ ነው ብሎአል፡፡

በአፍሪካ ውስጥ ሀምሳ ሀገራት ሲፈተሹ የሞ ኢብራሂም ፋወንዴሽን ሪፖርት የደረሰበት ግኝት እድገቶች ቢኖሩም በአፍሪካ ስራ አጥነት በቋሚነት የቀጠለ ሲሆን አሁንም ከፍተኛ ነው፡፡ የተለያየ ብሔራዊ ገቢ ባላቸው ሀገራትም የወጣቱ ስራ አጥነት ተመሳሳይ ነው፡፡ ለምሳሌም በኬንያና በሱዳን የወጣቱ ስራ አጥነት ቁጥር  22 በመቶ ሲሆን በ2016 የኬንያ ብሔራዊ ገቢ 6 በመቶ ያደገ ሲሆን የሱዳን ደግሞ በግማሽ ወደ 3. 1 በመቶ ነበር፡፡

የወጣቱን ስራ አጥነት ችግር ለመፍታት ለረዥም ግዜ ትምህርት እንደ መፍትሄ ተወስዶ ቆይቶአል፡፡ቢሆንም ሪፖርቱ የሚጠየቀው ችሎታና የሚገኘው ስራ ያለመገጣጠማቸውን ያሰምርበታል፡፡በቱኒዚያና ግብጽ ወጣቶች እጅግ በጣም ከተማሩት ውሰጥ የሚገኙ ቢሆንም የወጣት ስራ አጥነት ቁጥር  ከ60 በመቶ በላይ ነው፡፡የዩኒቨርሲቲ ዲግሪ ስራ እንደማያስገኝ አረጋግጦአል ሲል ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡

ሪፖርቱ ይቀጥላል፡፡አሁንም ቢሆን በአህጉሪቱ ብሩህ ተስፋ ሰጪ ነጥብ አለ፡፡እንደሌሎች የተለየየ ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ እንደሚታገሉት ሁሉ ኢትዮጵያ ወደመሬት በመመለስ የተለየች ሁና ብቅ ብላለች፡፡ግብርና ግዙፉ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ነው፡፡80 በመቶውን የሠራተኛ ኃይልና ከብሔራዊ ገቢውም 40 በመቶ ይሸፍናል በማለት ይገልጻል፡፡  

ይህም ማለት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኢኮኖሚ በ2015 ከነበረው በ2016(እኤአ) ዝቅ ሲል የወጣት ስራ አጡ ቁጥር ከነበረበት ወደ ላይ አልተወነጨፈም ሲሉ ሪቻርድ ሙሬይ የፋወንዴሽኑ ተጠባባቂ የምርምር ኃላፊ ለኩዋርትዝ አፍሪካ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ስራአጥነት በአጠቃላይና በተለይም የወጣቱ ስራ አጥነት ባለፉት አስርት አመታት አንጻራዊ በሆነ ሁኔታ አልተለወጠም፡፡የተረጋጋና በነበረበት የነበረ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አጠቃላይ የስራ አጥ ቁጥር 5.7 ፐርሰንት ሲሆን የወጣት ስራ አጡ ቁጥር ደግሞ 8.1 ፐርሰንት ነው፡፡በቀሪው የአፍሪካ ክፍል በአህጉሪቱ እነዚህ ቁጥሮች በአማካይ ከ8 ፐርሰንት እስከ 13 ፐርሰንት ይደርሳሉ፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ችግሮች የሌሉበት አይደለም በማለት ችግሮቹን የጠቀሰው ሪፖረት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ቀውስ ራሱን ያገኘው ስር በሰደደው የመሬት ጉዳይ ላይ የገቢ ምንጭና የማንነት መለያ አድርጎ ነው ሲል ይገልጻል፡፡

ፖሊሲዎችዋ በግብርና እድገት የሚመራ ኢንደስትራላይዜሽን የሚለው ሀገሪትዋ ሀብቶችዋንና የግብርናውን ክፍል እንድታሳድግ ረድቶአታል  ይላል ሪፖርቱ፡፡የፖሊሲውን ስኬታማነት እስከአሁን በተጨባጭ ያረጋገጠው ሳይሸረሸር አነስተኛ የእርሻ ይዞታ ባለቤቶች መብታቸው ተጠብቆ እንዲቀጥሉ ማድረጉ ነው፡፡የሕዝብ እድገትን አስከትሎአል፡፡ እድሎችን በከተማና በገጠርም አስፋፍቶአል በማለት ሪፖርቱ ኢትዮጵያን ያወድሳል፡፡

በግብርና ላይ ማተኮር ማለት አፍሪካ ምናልባት በትውልዶች ውስጥ ራስዋን መቀለብ ትችላለች ማለት ነው፡፡ ከውጭ የምታስገባውንና እርዳታን ታስወግዳለች ማለት ነው፡፡ በቴክኒዮሎጂ ውስጥ ለቴክኒሎጂ ፈጠራዎች ቦታ በመስጠት አዲሱ የአርሶአደሮች ትውልድ ቀድሞ ከነበሩት በላይ አዲስ አይነት የተለያዩ ሰብሎችን በማምረት በጣም በተስፋፋ ሁኔታ በመጨረሻም ሰፊ ስራዎችን ይፈጥራል ሲል ኩዋርትዝ አፍሪካ ዊክሊ አስነብቦል፡፡

በአፍሪካ ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት ቁጥሩ እየጨመረ የመጣውን ወጣት ትውልድ በየሀገራቱ የኢኮኖሚ አቅም ወደስራ ለማስገባት በአብዛኛው መንግስታት ትኩረት ሰጥተው እየሰሩበት አይደለም፡፡የወጣቱ ስራ አጥነት ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነትና ደረጃ በማደጉ ለአህጉሪቱ ልማትና እድገት የሚጠቅም ኃይል ተደርጎ ሊወሰድ ሲገባው  የሚታየው  ለመንግስታቱ እንደ ስጋትና አደጋ ተደርጎ የሚቆጠርበት ደረጃ ላይ ደርሶአል፡፡

ይህ ምስክርነት በመስኩ ጥናት አድርጎ በቅርቡ ይፋ ያወጣው  የሞ ኢብራሂም ፋወንዴሽን  የጥናትና የምርምር ግኝት ሪፖርት ነው፡፡ሀገራት ኢኮኖሚያቸው ቢያድግም የወጣቱን ስራ አጥቁጥር ለመቀነስ ያደረጉት ነገር እምብዛም ነው፡፡ ቁጥሩ ከግዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ ይገኛል፡፡ኢትዮጵያ ብሔራዊ የኢኮኖሚ አቅምዋ በፈቀደ መጠን ለወጣቶችዋ የተለያየ የስራ እድሎችን በመክፈት ሰርተው አግኝተው እንዲለወጡ ለማድረግ አቅምዋ የፈቀደውን ሁሉ አድርጋለች፡፡ በማድረግም ላይ ትገኛለች፡፡

ቀደም ባሉት አመታት በብሔራዊ ደረጃ በሁሉም ክልሎች የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማትን በማደራጀት ወጣቱ በአቅሙ ብድር ወስዶ የሚሰራበትን መንገድ በማመቻቸት በርካታ ወጣት ዜጎች በአገኙት ብድር ተጠቅመው ስራም ፈጥረው በመስራት በብዙ ተጠቃሽ መስኮች ውጤታማ መሆን ችለዋል፡፡

በእንጨት ስራ፤ በብረት ስራ፤ በንብ ማነብ፤በቤት ግንባታ፤በሸክላና በጡብ ምርት፤በምግብ ቤት፤በመዝናኛ አገልግሎት መስጫ ወዘተ ስራዎች በመሰማራት ውጤት አስመዝግበዋል፡፡ ከወጣቶቹ መካከል ደረጃቸውን አሳድገው ከነበሩበት ወደተሻለ አደረጃጀት የተለወጡ ሰፊ የስራ መስክ የከፈቱም ይገኙባቸዋል፡፡

ዛሬ ደግሞ ለወጣቱ የበለጠ የስራ እድል ለመክፈትና የራሱም የስራ ባለቤት እንዲሆን መንግስት 10 ቢሊዮን ብር የወጣቶች ፈንድ በጀት መድቦ በሁሉም ክልሎች እንዲዳረስ ወደስራ እንዲገቡም በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

ወጣቱ ተደራጅቶ በመረጠው የስራ መስክ መሰማራት መስራት የፈጠራ ችሎታውን ተጠቅም አዳዲስ ስራዎችን መክፈት የበለጠም ማስፋፋት ይችላል፡፡ለወጣቱ የተሰጠው ገንዘብ ሰርቶ በሚመለስ ብድር ነው፡፡ሰርቶ አግኝቶ ራሱን እንዲለወጥ ውጤታማና ትርፋማ ሁኖ የብድር ገንዘቡን ወደ መንግስት ይመልሳል፡፡ይሀው ገንዘብ ተመልሶ ለሌላ አስፈላጊ የሀገሪቱ ልማትና እድገት ይውላል፡፡

የዚህን ስራ ሂደትና አፈጻጸም በብሄራዊ ደረጃ የሚከታተል ራሱን የቻለ አካል ያለው ሲሆን ውጤቱ የሚመዘነው በወጣቶቹ የስራ ብቃትና በሚያስገኙት ውጤት ነው፡፡ሀገርን በማልማትና በማሳደግ ረገድ የወጣቱ ድርሻ ጉልህ ነው፡፡ወጣቱን ያላሳተፈና በወጣቱ እውቀትና ትኩስ አእምሮ እንዲሁም ጉልበት መጠቀም ያልቻለ ሀገርና ሕዝብ የማደግ ተስፋው የመነመነ ነው፡፡

ይህ እውነት ስለሚታወቅ ነው በኢትዮጵያ ውስጥ ለወጣቱ የተለየ ትኩረት የተሰጠው፡፡ ወጣቱ ስራ ፈጣሪና ስራ አክባሪ በመሆን የስራ ቦታንም ሳይመርጥ ለመስራት የሚችል ሲሆን ለውጡን እራሱ በራሱ ያየዋል፡፡ ተቀምጦ ስራን ከመጠበቅ የተገኘውን ማንኛውንም አይነት ስራ መስራት ከሰው እጅ ጠባቂነት አውጥቶ በራስ መተማመንን ያዳብራል፡፡የስራ ፍቅርንም ያሳድጋል፡፡

ዛሬ በአነስተኛ ደረጃ ወጣቱ በየቦታው የጀመረውና እየሰራ ያለው ስራ ነገ በከፍተኛ ደረጃ ወደ ካምፓኒዎችን ኢንዱስትሪዎች ሊያድግና ሊሰፋ ይችላል፡፡ በርካታ ሰራተኞችን ቀጥረው መስራት የሚችሉበት አቅምና ጉልበትም ያገኛሉ፡፡ በሌላውም አለም አንድ ስራ ሲጀመር መነሻው ትንሽ ነው፡፡ እያደገና እየሰፋ የሚሄደው በሂደት ነው፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy