Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከዝንጋኤ እንውጣ

0 361

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከዝንጋኤ እንውጣ   /አሜን ተፊሪ  /

                                                                        

 

ከሰሞኑ የኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናት እና ምርምር ማዕከል ባቀረበው አንድ ጥናት ላይ መሠረት ያደረገ ውይይት ተካሄዶጎ ነበር፡፡ ይህ ውይይት በመልካም አስተዳደር ዘርፍ ያለው ችግር ሥር የሰደደ መሆኑን፤ እንዲሁም የዲሞክራሲ ተቋማት ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑን የሚያሳይ እና ይህ ችግር በተጠናከረ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ባሳተፈ መልኩ መፈታት እንደሚገባው ያሳሰበ ጥናት ነበር፡፡

የፖሊሲ ጥናት እና ምርምር ማዕከሉ ኃላፊ አቶ አባይ ፀሐይ እንደተናገሩት የጥናት ሰነዱ የአንዳንድ የፍላጎት ቡድኖችን ጥቅም ሊነካ የሚችል (እንዲነካም የታሰበ) የጥናት ሰነድ ነው፡፡ በጥናት ሰነዱ የተጠቀሱት ሥር የሰደዱ ችግሮች፤ ኢህአዴግ ባካሄደው ግምገማ ተለይተው ከወጡት ችግሮች ጋር ተመሳሳይ ናቸው፡፡ እንዲያውም ችግሮቹ ከጥናት ሰነዱ ይልቅ፤ በኢህአዴግ የግምገማ ሰነድ ከረር ባለ አገላለጽ እንደተቀመጡ አመልክተዋል፡፡

ህግ የማክበር እና የማስከበር ህገ መንግስታዊ ኃላፊነት የተጣለበት የሥራ አስፈጻሚ፤ ህግ የማክበር እና የማስከበር ኃላፊነቱን መወጣቱ ቀርቶ፤ ራሱ ያወጣውን ህግ የሚጥስ መሆኑን በምሬት የተናገሩት አቶ አባይ፤ በድርጅቱ ግምገማ ተለይተው የወጡትን ችግሮች፤ የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር አካሄድ ለማስወገድ አስቦ ወደ ሥራ የተገባ ቢሆንም፤ በዚህ ረገድ የተሳካ ሥራ ተሰርቷል ለማለት እንደማይቻል ገለፀዋል፡፡

ይህ ሰነድ የትግል ሰነድ እንዲሆን ያስፈልጋል ያሉት አቶ አባይ፤ ችግሮቹ ከተወሰኑ ሰዎች ጋር ውይይት በማድረግ ሊወገዱ እንደማይችሉና የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ሰነዱን የራሳቸው አድርገው በመውሰድ ለትግል እንዲሰለፉ ጥሪ አድርገዋል፡፡ የዲሞክራሲ ተቋማት የሚባሉት ምክር ቤቶች፣ የህዝብ እና የሙያ ማህበራት እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃን፤ ከአድርባይነት መንፈስ ተላቅቀው፤ ተቋማዊ ኃላፊነታቸውን በውል ተገንዝበው፤ ህገ መንግስታዊ እና ዴሞካራሲያዊ የሆነ የተፈጥሮ ሚናቸውን እንዲጫወቱ አሳስበዋል፡፡

‹‹ይህን ሰንድ ህዝቡ ይፈልገዋል፡፡ ሐገሪቱ ትፈልገዋለች፡፡ የዚህ ጉባዔ ተሳታፊዎች የሆናችሁት እናንተ ትፈልጉታላችሁ›› ያሉት ኃላፊው፤ በሰነዱ የተጠቀሱትን ችግሮች ማስወገድ አለመቻል ሐገርን ለጥፋት መዳረግ መሆኑን ገልጸው፤ የአደጋውን አስከፊነት ከወራት በፊት በታየው ቀውስ ተገልጦ የታየ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

ታዲያ ይህ የፖሊሲ ጥናት እና ምርምር ማዕከል ‹‹መርዶ›› የተሰማው፤ በቅርቡ የስድስት ወራት አፈጻጸሙን የገመገመው የኢህአዴግ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፤ ‹‹የጥልቅ ተሐድሶ እንቅስቃሴው በታለመለት መንገድ እየተከናወነ መሆኑን ተረድተናል›› የሚል መግለጫ ባወጣበት ሰሞን ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ይበልጥ ትኩረት ሳቢ የሚሆነው፤ የሁለቱ አካላት የተጨባጭ ሁኔታ ንባብ እንዲህ ተቃራኒ ሆኖ በመታየቱ ጭምር ነው፡፡

ያሬድ ዲያመንድ (Jared Diamond)፤ የሚሉት አንድ ጸሐፊ፤ ‹‹Collapse: How Societies Choose to Fail or Succeed›› በተሰኘ አንድ መጽሐፉ እንደሚለው፤ አንድ ህብረተሰብ የውድቀት ወይም የስኬት ጎዳና የሚከተለው በምርጫ ነው፡፡ እንደ ጸሐፊው እምነት ወደ ውድቀት የሚያመራ ‹‹ጅል›› ማህበራዊ ውሳኔ የሚመነጨው፤ ቀጥሎ ከተዘረዘሩት ነገሮች በአንዱ ወይም ከአንድ በላይ በሆኑ ምክንያቶች የተነሳ መሆኑን ያስረዳል፡፡

 

 

  • ችግሩ በተጨባጭ ከመፈጠሩ በፊት አስቀድሞ ለማየት ካለመቻል፤
  • ችግሩም ከመጣ በኋላ የችግሩን ምንጭ ለይቶ እርምጃ ለመውስድ ካለመቻል፤
  • ችግሩ ተለይቶ ቢታወቅም መፍትሔ ለመሻት ለመንቀሳቀስ ካለመቻል፤ ውድቀት ሊመጣ እንደሚችል ያትታል፡፡

 

 

ታዲያ እነዚህን ውድቀቶች ከጀርባ ሆነው የሚገፉ ሌሎች ነገሮች ይኖራሉ፡፡ በአብዛኛው፤ (1) ልዩ ጥቅም በሚያሳድዱ ወገኖች ስግብግብነት (special- interest selfishness)፤ (2) የለውጥን አስፈለጊነት የሚያውጁ ድምጾች በዙሪያው ሲንጫጩ እየሰማ፤ ‹‹የያዝከውን መስመር እንዳትለቅ›› ብሎ ድርቅ በሚል ግትር የእምነት ስርዓት (rigid belief system)፤ (3) እንዲሁም የሰው ልጆች ከእንግዳ ከሆነ ክስተት ጋር ሲጋፈጡ ዘወትር እንደ ጋሻ በሚያነሱት እውነታን የመካድ ዝንባሌ (denial with which humans confront unfamiliar conditions) እየተነዱ የሚመጡ ውድቀቶች ናቸው፡፡

የፀሐፊው ትንታኔ በፖለቲካ ድርጅት ውሳኔ እና ተግባር ላይ ያተኮረ ሳይሆን፤ በሰውልጅ የሥልጣኔ ታሪክ እና ባህል ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ፀሐሪው አሁን በዓለማችን ያለው ስልጣኔ (ባህል) ከቀደምት ስልጣኔዎች ውድቀት ብዙ መማር የሚችል ቢሆንም፤ በኒውክሌር መሣሪያ የሚታመን ጉልበተኝነት፣ አሸባሪነት፣ የሐይማኖት አክራሪነት፣ የአየር ብክለት፣ ዘላቂ ያልሆነ የተፈጥሮ ሐብት አጠቃቀም፣ ያልተመጣጠነ የሐብት ስርጭት ወዘተ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ለማስወገድ ከልብ የሆነ ጥረት እያደረገ አይደለም፡፡ እናም ይህ ስልጣኔ ዘላቂ ለመሆን አይችልም ይላል፡፡ ‹‹የሚጠፋ ከተማ፤ ነጋሪት ቢጎሰም አይሰማም›› እንዲሉ፤ ዓለም በአስቀያሚ የዘረኝነት መንፈስ እና በአሸባሪዎች አረመኔያዊ ድርጊት እየታመሰች ትገኛለች፡፡

እናም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማህበራዊ ጉዳዮች ዓለም አቀፍ ገጽታ እየያዙ በመምጣቸው የተነሳ፤ ስህተቱ የሚያስከፍለው ዋጋም በዛው ልክ ከፍተኛ ሆኗል፡፡ ድሮ ድሮ ከመንድር ያለፈ አደጋ የማያስከትሉ የነበሩት ባህላዊ ውድቀቶች፤ ዛሬ ጠቅላላ የሰውን ልጅ ወይም ጠቅላላ ሥነ ፍጥረትን ወደ መቃብር ሊያወርድ የሚችል (ኬሚካል እና ባዮሎጂካዊ የጦር መሳሪያን አስቡ) አደጋ ሆኖ ይታያል፡፡

አንድ ማለፊያ ብሂል አለ፡፡ ‹‹ባህል ከሰው ልጆች የሚጠይቀው ዋጋ፤ ዝንታለም በርን ለለውጥ ከፍቶ አድርጎ መኖርን ነው›› ይባላል፡፡ ብሂሉ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተመቸ ለዛ አለው፤ The price of culture is eternal openness to change ይላል፡፡ የሰው ልጅ በአሁኑ ሰዓት ከባድ ፈተናዎች ተጋፍጠውታል፡፡ ሆኖም ፈተናዎቹን ተጋፍጦ ለማለፍ እና እንቆቅልሸቹን ለመፍታት፤ ስኬታማ የሆኑ ባህሎች ከዚህ ቀደም ያደረጉትን ነገር ለማድርግ መነሳት ይኖርበታል፡፡ መጭው ጊዜ ወቅታዊ ፈተናዎችን ለማለፍ የሚያስችሉ የፈጠራ ብቃት እና ራስን ከሁኔታዎች ጋር አስማምቶ የመገኘት ብቃትን ይጠይቀናል፡፡ ሆኖም አሁን የሚታየው ነገር የወደቁ ባህሎች ባህርያት ነው፡፡ ዓለም ነጋሪት ሲጎሰም የማሰማ ከተማ ሆናለች፡፡

ሆኖም እነዚህ ውድቀቶች፤ ምንም ቢደረግ ሊቀሩ የማይችሉ ውድቀቶች አይደሉም፡፡ ውድቀቶቹ እየዳሁ ወይም እየተንደረደሩ የሚመጡት፤ ከላይ የተጠቀሱት ቅድመ ሁኔታዎች ሲሟሉ ብቻ ነው፡፡ ታዲያ የውድቀት ቅድመ ሁኔታዎች ተሟልተው፤ ወደ ገደል እንዳይገፉን፤ አሁን የምንገኝበትን ተጨባጭ ሁኔታ በደንብ ፈትሸን ለችግሩ የሚመጥን እና እርምጃ መውሰድ ያስፈልገናል፡፡

ከታሪክ ለመማር ፊትን ወደ ኋላ አዙሮ ማየት ነው፡፡ ተመልከቱ፤ የኢትየጵያን የአክሱም ሥልጣኔ፡፡ ደግሞም የታላቋ ዝምባቡዌን የታሪክ ቅርስ መጎብኘት ይችላል፡፡ እንደዚህ ያሉ የፍርስራሽ ክምር እና የእንቆቅልሽ መደብር ሆነው የቆሙ፤ የዓለም ህዝቦችን ቀልብ የገዙ በርካታ የሥልጣኔ አሻራዎች በተለያዩ የዓለማችን አካባቢዎች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ የጠፉ ሥልጣኔዎች ናቸው፡፡ ለእነዚህ ሥልጣኔዎች መውደቅ የወዲያው (ግብታዊ)  ምክንያት ሆነው የሚጠቀሱ በርካታ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ከላይ እንደ ጠቀስኩት ጸሐፊ እምነት ለሥልጣኔዎቹ መውደቅ የራሱ የህብረተሰቡ ባህል ወሳኝ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ ህብረተሰቡ የራሱን ውድቀት በማጋፈር ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት መዘንጋት የለብንም የሚለው ያሬድ ዲያመንድ፤ ይህም ክስተት በታሪክ ውስጥ በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ‹‹ባህል ከሰው ልጆች የሚጠይቀው ዋጋ፤ ዝንታለም በርን ለለውጥ ከፍቶ አድርጎ መኖርን›› የማያውቅበት ሥልጣኔ ይወድቃል፡፡

ለምሣሌ፤ ስለ አክሱም ሥልጣኔ ውድቀት ሲነሳ፤ ‹‹የአክሱም ስልጣኔ የወደቀው በዮዲት ጉዲት ነው፡፡ በእስልምና መስፋፋት ነው›› ወዘተ የሚሉ ግብታዊ ምክንያቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ ሆኖም እነዚህ የውድቀቱ ግብታዊ ምክንያቶች እንጂ መሠረታዊ ምክንያቶች አይደሉም፡፡ አክሱማውያን ችግሩ ከመምጣቱ በፊት ለማየት፣ ከመጣ በኋላም ምንጩን ለመለየት፣ ለይተውትም ከሆነ መፍትሔ ለመሻት አለመቻላቸው ነው የውድቀታቸው መነሻ፡፡

ስለዚህ ሰሞኑን በፖሊሲ ጥናት ማዕከል የቀረበው ጥናት በትኩረት ሊታይ ይገባል፡፡ ውድቀት የጋሪ ፈረስ አድርጎ እንዳሻው እንዳይጋልበን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ችግሩ ከእጃችን እንዲወጣ እና እንደ ፈቀደው እንዲጋልብ ዕድል ልንሰጠውም አይገባም፡፡ ከዝንጋኤ እንውጣ፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy