Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የህዝቡን የመልማት ፍላጎት ለማርካት ሃገሪቱ የጀመረችው የህዳሴ ጉዞ ተጠናክሮ ይቀጥላል–ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

0 298

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የህዝቡን የመልማት ፍላጎት ለማርካትና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ለማሳደግ ሃገሪቱ የጀመረችው የህዳሴ ጉዞ የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠሉን የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።

በባህር ዳር ከተማ ከሁለት ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ለሚገነባው የጣና ብረታ ብረት ፋብሪካ የመሰረት ድንጋይ ዛሬ ተቀምጧል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የፋብሪካውን የመሰረት ድንጋይ ባስቀመጡበት ወቅት እንዳስታወቁት ሃገሪቱን ከድህነት ማላቀቅ የሚያስችሉ ስትራቴጂዎች ተነድፈው እየተተገበሩ ይገኛል።

“ባለፉት ዓመታት አስከፊውን የድህነት ገጽታ ለመቀየር በተደረገው ብርቱ ጥረት በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል” ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለውጡ በትክክልም ከድህነት መላቀቅ እንደሚቻል በተግባር ማረጋጋጥ ያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም አገሪቱን በፍጥነት ወደ ስልጣኔ ማማ ማድረስ የሚችሉ የልማት አቅጣጫዎችን በመተግበር ህዝቡ ከቱሩፋቱ ተጠቃሚ መሆን መጀመሩን አብራርተዋል።

“የተመዘገበው ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚያበረታታ ቢሆንም በተሰራው ስራ ከተሰበረው የድህነት ምሽግ የባሰ ያልተሰበረ የድህነት ምሽግ በመኖሩ አሁንም ድህነትን ለማሸነፍ ከመቸውም ጊዜ በተሻለ ጠንካራ የልማት ስራ እየተከናወነ ይገኛል።”ብለዋል።

“የህዝቡን የመልማት ፍላጎት መሰረት ያደረጉ ስራዎችን በማከናወን በእርምጃ ደረጃ የተገኘውን ኢኮኖሚያዊ እድገት ወደ ሩጫ ለመቀየር የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ይጠይቃል” ብለዋል።

በአማራ ክልል በአባይ ኢንዱስትሪ ልማት አክሲዮን ማህበር የሚገነቡት ኢንዱስትዎች መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት መሆኑን ጠቁመው፤ ለውጤታማነቱም መንግስት፣ የግል ባለሃብቱና የህዝቡ ቅንጅታዊ አሰራር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ንግድ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ቢሮ ሃላፊና የአባይ ኢንዱስትሪ ልማት አክሲዮን ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ጌታቸው በበኩላቸው የክልሉን አዝጋሚ የኢንዱስትሪ እድገት በተሻለ ፍጥነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአክሲዮን ማህበሩ 22 የሚደርሱ ኢንዱስትሪዎችን 16 ቢሊዮን ብር በሚደርስ ወጪ ለመገንባት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸው በተለይም ሰባት ታላላቅ ፋብሪካዎችን በቅድሚያ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ እየተጣለ መሆኑን አመልክተዋል።

ከሁለት ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የሚገነባው ጣና ብረታ ብረት ፋብሪካ ግንባታው በሁለት ዓመት ውስጥ ተጠናቆ ስራ ሲጀምር በዓመት 300 ሺህ ቶን ብረት የማምረት አቅም እንደሚኖረውም ተናግረዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy