Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የህዳሴው ግድብ – ጥራት አሳሳቢ አይደለም

0 1,038

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኢንጅነር አዜብ አስናቀ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ዳይሬክተር ናቸው።የግቤ ሦስት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብን ሥራ መርተው ለምረቃ ያበቁ ብርቱ ሴትም ናቸው። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት ስድስተኛ ዓመት  ምክንያት በማድረግ ያደግነው ቃለ ምልልስ  በሚከተለው መልኩ  አቅርበነዋል።

አዲስ ዘመን ፦ ግድቡ  ምን ደረጃ ላይ ደረሰ?

ኢንጅነር አዜብ፡-  ግድቡ ትልልቅ የግንባታ ሂደቶችን አልፎ ከግማሽ በላይ 57 በመቶ የሚሆነው ተጠናቋል፡፡ ይህ በስድስት ዓመት ውስጥ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ ምክንያቱም ዋናኛዎቹ ከመሬት በታች የሚሰሩት የመሰረትና የጂኦሎጂ ሥራዎች በሙሉ ተደማምረው ተሰርተው ነው፤ ግንባታው 57 በመቶ ላይ ደርሷል የተባለው፡፡

ምንም እንኳ ዋና ዋና የመሬት ላይ ሥራዎች በከፍተኛ መጠን ተሰርተዋል ቢባልም ቀሪ ሥራዎቹ ቀላል ናቸው ማለት አይደለም፡፡ የበለጠ ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው ሥራዎች ይቀራሉ፡፡ የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራዎችም ሆኑ ሌሎቹ ተቀናጅተው በከፍተኛ ጥንቃቄ መሰራት ያለባቸው ሥራዎች መቅረታቸው መዘንጋት የለበትም፡፡

አዲስ ዘመን ፦ በታቀደው መሰረት እ.አ.አ በ2014 እና በ2015  የሁለቱ ዩኒቶች ኃይል ሙከራ ለምን አልጀመሩም?

ኢንጅነር አዜብ፡- አንድ ዩኒትም ሆነ አስር ዩኒት ሥራ እንዲጀምር ለማስቻል ቀድመው መሰራት ያለባቸው በጣም ብዙ መሰረታዊ ሥራዎች አሉ፡፡ በፍፁም ውሃ ሳይጠራቀም ኃይል ማመንጨት አይታሰብም፡፡ ውሃው ተጠራቅሞ ወደ ተርባይኖቹ መግባት አለበት፡፡ የተጠራቀመው ውሃ ተርባይኖቹ ጋር ለመግባት መድረስ ያለበት ደረጃ ላይ መድረስ ይኖርበታል፤ ይህ የግድ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ከኋላ መሰራት ያለባቸው ብዙ ሥራዎች አሉ፡፡ የቁፋሮ ሥራው በጣም ጊዜ ወስዷል፡፡ ማንኛውም ፕሮጀክት ሲሰራ በቅድሚያ ጥናት ይጠናል፡፡ ነገር ግን መሬት ላይ ሥራው ሲከናወን የሚያጋጥሙ የተለያዩ ጉዳዮች ይኖራሉ፡፡ ከገፀ ምድር በታች ያሉት ነገሮች ላይ ከግንባታ በፊት የሚደረጉት ጥናቶች ግምታዊ ናቸው፡፡ ቅድመ ጥናት ላይ ፍፁኑት የሚባል ነገር የለም፡፡ ሲቆፈር ብዙ ጊዜ በጣም የተለየና ወጣ ያለ ነገር ያጋጥማል፡፡ ያንን ለማስተካከል የሚሰራው ሥራ ደግሞ ጊዜ ይበላል፡፡

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይም ጥብቅ መሬት መገኘት ስላለበት በጣም ብዙ ቁፋሮ ተካሂዷል፡፡ ከ10 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የሆነ ኮንክሪት ለመሙላት ያንን መሰረት ሊሸከም የሚችል ጠንካራ መሬት መገኘት አለበት፡፡ ጥብቅ መሬት ሲፈለግ ልል የሆኑ መሬቶች በሙሉ መውጣት አለባቸው፡፡ ልል የሆኑት በሙሉ ተቆፍረው ወጥተዋል፡፡ የተቆፈረው ሁሉ ደግሞ በኮንክሪት የሚሞላ ነው፡፡ ኮንክሪቱም ጊዜ ወስዷል፡፡

የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ የኒቶች ማመንጨት የሚችሉት ሥራው ወደ ማለቅ ሲደርስ ነው፡፡ መሰረቱ አልቆ ውሃ መያዝ ሳይጀመር ሁለቱ ዩኒቶች ኃይል ማመንጨት አይችሉም፡፡ ስለዚህ ሁለቱ ዩኒቶች ሥራ እንዲጀምሩ ውሃው እንዲያዝ ግድቡ ተገንብቶ የሚፈለግበት ደረጃ ላይ መድረስ አለበት፡፡ ግድቡ የሚፈለግበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ደግሞ የመሰረት ሥራው መጠናቀቅ ይኖርበታል፡፡ ሁሉም ግንባታ ተያያዥ ነው፡፡ ግድቡ ትልቅ እንደመሆኑ መጠን አሰራሩም እጅግ ውስብስብ ነው፡፡ ስለዚህ በታቀደው ጊዜ የሁለቱ ዩኒቶች ኃይል ሙከራ ሊታይ ያልቻለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡

አዲስ ዘመን ፡- በግንባታ ላይ የተለየ አጋጠመ የሚባለው ችግር ምንድን ነው?

ኢንጅነር  አዜብ፡- እንኳን የታላቁ ህዳሴ ግድብን የሚያህል ግዙፍ ፕሮጀክት ይቅርና አነስተኛ ቤት ሲገነባ የሚያጋጥሙ ያልታሰቡ ችግሮች ይኖራሉ፡፡ታላቁ ህዳሴ ግድብ ብዙ ችግር አለበት፡፡ እንደሚታወቀው የውሃ ፖለቲካው በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ከታችኛው የተፋሰሱ አገራት ጋር ያለው ሁኔታ ራሱን የቻለ ችግርና መፍትሄ እየተሰጠው የቀጠለ ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን በምንም መልኩ ግድቡ አልተቋረጠም፡፡ ለሁሉም በየራሱ አግባብ ምላሽ እየተሰጠ ነው፡፡

የግንባታ ሥራውም ራሱን ችሎ እየሄደ ነው፡፡ በቴክኒክም ጠንካራ ግድብ ከመስራት አኳያ የተደረገው ጥረት የመሰረት ቁፋሮ ከተጠበቀው በላይ ጊዜ እንዲወስድ አድርጓል፡፡ በየቀኑ የሚያጋጥመው ጉዳይ እንደችግር መገለፅ የለበትም፡፡ ምክንያቱም እንኳን ይህን የሚያህል ፕሮጀክት ይቅርና ማንኛውም ትንንሽ ፕሮጀክቶች ላይ ችግር ያጋጥማል፡፡ እንደዛ ዓይነት ጥቃቅን ችግሮች ያጋጥማሉ፡፡ ከዛ ውጪ ይህን የሚያህል ፕሮጀክቱን ሊጎዳና ሊያስቆም የሚያስችል ምንም ዓይነት ችግር አልነበረም፡፡

አዲስ ዘመን ፦ የግድቡ የግንባታ ጥራት  እንዴት ነው?

ኢንጅነር አዜብ፡- የግድቡ ጥራት በምንም መልኩ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡ እኛ ባለቤቶቹ ብቻ ሳንሆን እኛን የሚያግዙ ብዙ አማካሪዎች ሁሉ ቁጥጥር እያደረጉበት የሚሰራ ፕሮጀክት ነው፡፡ የግንባታው ተቋራጮችም ቁጥጥር ያደርጋሉ፡፡ የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራውን የሚሰራው አገር በቀሉ የብረታብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽንም (ሜቴክ) ሆነ የሲቪል ሥራውን የሚያከናውነው ሳሊኒ የተሰኘው የውጭ ኩባንያ ሲገነባ ሁለቱም በየራሳቸው ጥራቱን የሚቆጣጠር አማካሪ አላቸው፡፡ ኮንትራክተሮቹም ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በዋናነት እኛም እንደባለቤት እንቆጣጠራለን፡፡

ኮንትራቱ ጂሲ የሚባል ሲሆን አጠቃላይ ኢንጂነሪንጉ ውስጥ ዲዛይኑንና ሌሎችም የሚገዙ ዕቃዎች እና በአጠቃላይ ግንባታው ሙሉ ለሙሉ የሚሰራው በእነርሱ ኃላፊነት ነው፡፡ ጥራቱ በምንም መልኩ ድርድር ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡ ራሳቸው ገንቢዎቹም ጥራቱን አስጠብቆ የመስራት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ እነሱ ሙሉ ለሙሉ ኃላፊነት ቢኖርባቸውም፤ እኛም በራሳችን የቁጥጥር ሥራውን እየሰራን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ የሆነው ታላቁ የህዳሴውን ግድብ አስመልክቶ ጥራት በምንም መልኩ አሳሳቢ መሆን የለበትም፡፡

አዲስ ዘመን ፦ እንደ አሰሪ ሜቴክ  አቅሙ ምን ላይ ደርሷል ይላሉ?

ኢንጅነር አዜብ፡- የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽንን (ሜቴክ) አስመልክቶ የአገርን አቅም ከመገንባት አኳያ የሜይቴክ ጉዳይ እንደምሳሌ የሚጠቀስ ነው፡፡ ምን ጊዜም አንድ ፕሮጀክት ሲጀመርና እየተሰራ ሲኬድ የሚገኘው የሥራ ልምድ የተለየ ነው፡፡ አሁን የሜቴክ ሥራ መታየት ያለበት በአንድ ጊዜ አቅም ያምጣ ከሚል አኳያ አይደለም፡፡ ሜይቴክ ገብቶ እየሰራ ነው፡፡ ነገር ግን በሚጎድለው ቦታ የሌሎችንም አቅም እየተጠቀመ የሚሰራበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ዋናው ቁምነገር በዚህ ሂደት ውስጥ መማሩ ነው፡፡ አብሮ እየተማሩ ማደጉ  ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን መታየት አለበት፡፡ በግድቡ የሥራ ሂደት ላይም እየታየ ያለው ይኸው ነው፡፡

ሜይቴክ እየተማረ ነው፡፡ የመማር እና የመሻሻል  ሂደቶች እየታዩ ናቸው፡፡ መንግሥትም ሜይቴክ እንዲገባ የወሰነው ‹‹መቶ በመቶ ሙሉ አቅም አለው ይችለዋል›› ብሎ አይደለም፡፡ ወደ ሥራ እንዲገባ የተደረገው አቅሙን እየገነባ እንደሚሄድ ታሳቢ ተደርጎ ነው፡፡አሁንም እየሆነ ያለው እንደታሰበው ነው፡፡

አዲስ ዘመን ፦ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለ በኋላ ከ14ቱ ዩኒቶች ነበሩ። ኋላ ሁለት ተጨምረዋል። ይህ ግንባታውን እንደሚያጓትተው ይገለፃል፡፡ይህን እንዴት ይመለከቱታል?

ኢንጅነር አዜብ፡- የህዳሴ ግድብ ዩኒቶች ከ14 ወደ 16  አድገዋል፡፡ የዩኒቶቹ መጨመር የሚመነጨውን የኃይል መጠን አሳድጓል፡፡ የቁጥር መጨመር ብቻ ሳይሆን የተርባይኖቹ የኃይል ማመንጨት መጠናቸውን የመጨመር ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡ አንዱ ዩኒት ያመነጫል ተብሎ ከታሰበው 375 ሜጋ ዋት እያንዳንዳቸው 400 አካባቢ እንዲያመነጩ እየታቀደ ነው፡፡ ይህ የብረታብረት ሥራው እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል፡፡

የተርባይኖቹ ቁጥር መጨመር በእርግጥ የብረታብረት ሥራውን ሊጨምር ይችላል፡፡ የዋጋ ጭማሪም ይኖረዋል፡፡ ነገር ግን መጨመሩ የሚፈጀው ጊዜና ገንዘብ ከሚያስገኘው ጠቀሜታ አኳያ ምንም ማለት አይደለም፡፡  የሚገኘው የኃይል መጠን መጨመር በአጠቃላይ ፕሮጀክቱን የሚያዘገይበት ሁኔታ አለ ለማለት የሚያስደፍር አይደለም፡፡

አዲስ ዘመን ፦ የኃይል ማመንጨት መጠኑ ሊጨምር እንደሚችል ይነገራል፡፡በእርግጥ መጨመር ይቻላልን ወይስ ግምት ነው?

ኢንጅነር አዜብ፡- የሚመነጨውን የኃይል መጠን መጨመር ይቻላል የሚባለው እንዲሁ ዝም ብሎ አይደለም፤ ያለጥናት የሚከናወን ነገር የለም፡፡ ከግድቡ ጋር ተያይዞ ሁሉም ነገር ላይ ጥናት ይከናወናል፡፡ ብዙም ወጪ ሳያስጨምር የሚመነጨውን የኃይል መጠን መጨመር የሚቻለው እንዴት ነው? የሚል ጥናት በቅድሚያ ይካሄዳል፡፡ እናም ከዚህም በላይ ሊጨምር ይችላል የተባለው እውነት ነው፡፡ ነገሩ እየተጠና የሚቀጥል ነው፡፡

መዋቅሩ (ስትራክቸሩ) በቦታው ላይ አለ፡፡ ስለዚህ እዛው ላይ አነስተኛ ማስተካከያዎችን በማድረግ የኃይል መጠንን መጨመር ብቻ በመሆኑ በየጊዜው የሚመነጨው የኃይል መጠን መጨመር ግር ሊያሰኝ አይገባም፡፡ እስከ አሁን እየተደረገ ያለው በዚህ መልኩ ነው፡፡ መጀመሪያም ከነበረው አቅም ከፍ እንዲል የተደረገው በዚህ መልኩ ነው፡፡

በቅድሚያ ጥናት ሲሰራ ወይም ዲዛይኑ ሲዘጋጅ የማሻሻል ሥራዎች ብዙ ጊዜና ገንዘብ ሳይወስዱ የሚገኙ ጥቅሞችን ከማየት አኳያ የሚታይበት ሁኔታ አለ፡፡ ስለዚህ ግምቱ ትክክል ሊሆን ይችላል፡፡ ዝም ብሎ ግምት አይደለም፡፡

አዲስ ዘመን ፦ በየዓመቱ በዓሉ ሲከበር  ግድብን አስመልክቶ የሚከወኑ አዳዲስ ነገሮች ብቅ ይሉ ነበር፡፡ ዘንድሮ ምን አዲስ ነገር አለ?

ኢንጅነር አዜብ፡-  አሁን ዋነኛ ሥራው እና አዲሱ ነገር የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራው በብዛት መሰራቱ ነው፡፡ ቀድሞ የሚጀመረው እንደሚታወቀው የሲቪል ሥራው ነው፡፡ ግድቡ ውስጥ ተቀባሪ ብረታብረቶች አሉ፡፡ አብረው እያደጉ የሚመጡት እነርሱ ሁሉ ናቸው፡፡

ዋነኛዎቹ አዲስ ነገሮች በሜቴክ የሚሰሩት የውሃ ማስተላለፊያዎች የብረታ ብረት ሥራዎች ናቸው፡፡ በብዛት እየተሰሩና (ቤን ስቶኮች) በሚታይ ሁኔታ እየተከወኑ ናቸው፡፡ በፊት እንደማንኛውም ግድብ አሰራር ቀድመው የሚሰሩት የሲቪል ሥራዎች ናቸው፡፡ የሚታዩትም እነርሱ ናቸው፡፡ ቀደም ብሎ ኮንክሪት መዋቅሩ ብቻ ይታይ ነበር፡፡ አሁን ግን የብረታ ብረት ሥራዎች እየተሰሩ እየታዩና ለውጦችም ጎልተዋል፡፡ ብዙ የፋብሪካ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡ ተርባይኖች እና ጀኔሬተሮች ተሰርተዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ሂደት ስለሆነ የደረሰበት ደረጃ ይሄ ነው ብሎ ቁርጥ አድርጎ ማስቀመጥ አይቻልም፡፡

አዲስ ዘመን ፦ ለሚመነጨውን ኃይል  ስርጭት ምን እየተሰራ ነው?

ኢንጅነር አዜብ፡- አንድ ማመንጫ ጣቢያ ሲሰራ ምንጊዜም የሚወጣው ኃይል እንዴት ይተላለፋል የሚለው አብሮ ይታሰብበታል፡፡ የሚመነጨውን ኃይል ወደ ኃይል ቋት ለማስገባት መስመሮች የግድ ያስፈልጋሉ፡፡ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይም በተመሳሳይ መልኩ በኢትዮጵያ የኃይል ታሪክ ትልቁ እስከ አራት መቶ ኪሎ ቮልት የነበረውን የማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ምክንያት ባለአምስት መቶ ኪሎ ቮልት አቅም ያለው መስመር እየተዘረጋ የማከፋፈያ ጣቢያውም ተሰርቷል፡፡

ኃይል ማመንጨት እንደጀመረ ሁሉም ዝግጁ ስለሚሆን ኃይል የማስተላለፉ ሂደቱ ይቀጥላል፡፡ በዚህ በኩል ምንም የሚያሳስብ ነገር አይኖርም፡፡ የኃይል ማመንጫ ግንባታውን ከማከናወን ጎን ለጎን ኃይሉ የት እንደሚደርስ ከወዲሁ ማስተላለፊያው ላይ እየተሰራ ነው፡፡ እንደውም ከበለስ ኃይል ማመንጫ ለግድቡ 400 ኪሎ ቮልት አቅም ያለው መስመር ተሰርቷል፡፡ እና ለግድቡ ለእያንዳንዱ ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶት የሚኬድበት ነው፡፡ የመስመር ዝርጋታውም አልተዘነጋም፡፡

አዲስ ዘመን ፦  ኃይል በመጠቀምና በመሸጥ በኩል የህዳሴ ግድቡ ፋይዳ ምንድን ነው?

ኢንጅነር አዜብ፡- የህዳሴው ግድብ ውሃው ሙሉ ለሙሉ ሲሞላ የሚያመነጨው የኃይል መጠን 6 ሺ450 ሜጋ ዋት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህ ልክ እንደ ግልገል ጊቤ ሦስት  ባለው ውሃ ልክ ኃይል እየሰጠ የሚቀጥል እንጂ ሁል ጊዜ ስድስት ሺ ያመነጫል ማለት አይደለም፡፡ ግልገል ጊቤ ሦስት አንድ ሺ አንዳንዴ 800፣ 600 ሜጋ ዋት እያመነጨ  ነው፡፡ የሚመነጨው ኃይል የተያዘውን ውሃ መሰረት አድርጎ ነው፡፡ 16ቱም ዩኒት መስራት የሚጀምረውም በሂደት ነው፡፡ ወደ ብሔራዊ ቋት ይገባል፡፡

አሁን ልማቱ እየተስፋፋ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተገነቡ አግሮ ኢንዱስትሪ እያደገ ነው፡፡ ስለዚህ ኃይል ያስፈልጋል፡፡ ባቡር ኤሌክትሪክ ኃይል የሚፈልግ ሆኗል፡፡ የህዝቡም የኃይል ፍላጎት አድጓል፡፡ እነዚህን ሁሉ በማርካት የሚተርፍ ይኖራል ተብሎ ይገመታል፡፡ ኃይል የመሸጥ አላማ የተያዘው አገሬውን በሚጠቅምና የአገር ውስጥ ፍላጎትን ካረካን በኋላ ነው፡፡

አሁን ለጂቡቲና ለሱዳን ኃይል እየተሸጠ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ ኃይል ለመውሰድ 500 ኪሎ ቮልት ማስተላለፊያ መስመር እየተገነባ ነው፡፡ ከኬንያ አልፎም ወደ ታንዛኒያ ይቀጥላል፡፡ስለዚህ ለሽያጩ የሚያገለግለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡-  ምን ያህል ቦንድ ገዝተዋል?

ኢንጅነር አዜብ፡- እኔማ ባለቤት በመሆኔ ምሳሌ መሆን ስላለብኝ በደንብ ቦንድ ገዝቼያለሁ፡፡ ከሠራተኞቹ ጋር በደመወዜ ቦንድ እየገዛሁ ነው፡፡ በተጨማሪ በሌሎች አጋጣሚዎችም የምገዛ ሲሆን፤ የመስሪያ ቤቱ ሠራተኞች በሙሉ በደመወዛችን ቦንድ እየገዛን ነው። ቁጠባም  ነው፡፡

 

ምህረት ሞገስ

– See more at: http://ethpress.gov.et/addiszemen/index.php/technology/item/12008-2017-04-02-18-56-53#sthash.vHQugdqP.QHVD4nMz.dpuf

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy