Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የልደት ቀኔን ፍለጋ

0 1,936

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ልደት የሚባል ነገር መኖሩን ያወቅኩት ከተማ ከገባሁ በኋላ ነው፡፡ ከከተማ አደግ ጓደኞቼ ጋር መተዋወቅ እንደጀመርኩ ከሚያወሩኝ ነገሮች አንዱ የልደታቸውን አከባበር ነው፡፡ ‹‹ለልደቴ እንዲህ አድርጌ፤ እንዲህ ተደርጎልኝ›› እያሉ ያወራሉ፡፡ ጭራሽ አንዳንዶቹማ ልደት ጠርተንሃል ማለት ሁሉ ጀመሩ፡፡ ይቺን ይወዳል! ማን ከማን ያንሳል ታዲያ አልኩና የኔንም ላከብር ተነሳሁ፡፡

ያው እንግዲህ ለልደት ምን እንደሚያስፈልግ ታውቃላችሁ (አቤት ወደሚበላ ነገር መቸኮል)፡፡ ለልደቴ ኬክ ሻማ….. ምናምን እንዳይመስላችሁ የቸገረኝ፡፡ እና ታዲያ ምንድነው? እኔን የቸገረኝ የልደቴ ቀን መቼ እንደሆነ አለመታወቁ ነው(ምነው ያኔ ወሳኝ ኩነቶች በነበረ)፡፡ ከተማ አደግ ጓደኞቼ ልደት ሲያከብሩ አይቼ ባደረብኝ ድንገተኛ ቅናት እኔም ማክበር ፈለኩ፡፡ ለልደት የሚያስፈልጉ ቁሳቁስ ከመግዛቴ በፊት ቀኑን ማወቅ አለብኝና እናቴን ጠየቅኳት(ምን እናቴን ብቻ የቀረ ዘመድ አዝማድ የለም እንጂ)፡፡ ቢሆንም ግን የመጀመሪያው ጥያቄ ለእናቴ ነበር፡፡

ኧረ እማመይ መቼ ነው የተወለድኩ? አልኳት አንድ ቀን ድንገት ተነስቼ፡፡ ‹‹ኧረግ የገብሬል ያለህ በስንት ግዜው ነው የምትጠይቀኝ ልጄ?›› «አይ ለምን መሰለሽ እማመይ፤ እስካሁን ልደት አክብሬ አላውቅም፡፡ ቢያንስ ከአሁን በኋላ እንኳን ማክበር ስላለብኝ ንገሪኝ» ‹‹ምንድንነው ደግሞ ልደት?›› «ልደት ማለት ምን መሰለሽ? የተወለድኩበትን ቀን ማክበር ማለት ነው፡፡ በዕለቱም ጓደኞቼ ይመጡና ኬክ ይቆረሳል፡፡ ኬክ ማለት ከተለያዩ ከወተትና እንቁላል መሰል ነገሮች የሚዘጋጅ ጣፋጭና ውድ የሆነ ነገር ነው … » እያልኩ ማስረዳት ስጀምር አቋረጠችኝና ‹‹ከእንቁላልና ከወተት ብቻ ነው የሚዘጋጅ?›› አለችኝ፡፡

ከእንቁላልና ከወተት ብቻ አይደለም ሌላም ነገር አለው፡፡ እኔ ሲበሉት እንጂ ሲያዘጋጁት አይቼ አላውቅም፡፡ ግን ዋጋው ውድ ስለሆነ ሀብታም የሆኑ ሰዎች ወይም እንደ ሀብታም የሚቃጣቸው ሰዎች ናቸው የሚመገቡት አልኳት፡፡ ‹‹አይ! ሁሉ አማራሽን ገበያ አታውጧት አሉ፤ ሀብታም ሲያደርግ ያየኸውን ሁሉ አድርገህ ትዘልቀዋለህ? ለመሆኑ ምን ዓይነት ምግብ ነው?›› አለችኝ፡፡ «አንቺ የምትሰሪውን አነባበሮ የመሰለ ደረቅ ኬክ አለ፡፡ አንቺ የምትሰሪውን ገንፎ የመሰለ ክሬም ኬክ አለ» ‹‹ታዲያ ለምን እርጥብ ኬክ አትሉትም?›› «አይ! ክሬም የሚል ስም ስላለው እርጥብ ኬክ አይባልም።»

‹‹ታዲያ ይሄን ነው የሀብታም ምግብ ያልከኝ? ወተትና እንቁላሉስ ቢሆን ከየት የሄደ መስሎህ ነው? ከዚሁ ከእኛው እኮ ነው፡፡ በል አሁን በውድ ዋጋ እንዳትገዛ አነባበሮ ከፈለክ እርሾ ጣል አድርጌ፣ ገንፎም ከፈለክ አሁኑኑ ላዘጋጅልህ›› አለችኝ፡፡ «ቆይ ግን ልደቱ መቼ መስሎሽ ነው?» ‹‹እኔ ምን አውቅልሃለሁ፡፡ በፈለክ ቀን ማድረግ ትችላለህ፡፡ ዘመድ አዝማድ ይጠራ ካልክ ደሞ አዝመራ ሲሰበሰብ ማድረግ ትችላለህ።››

«ሃሃሃሃ! አይ እማማይ ስነግርሽ ቆይቼ! ልደት የሚከበረው እንደዚህ አይደለም፤ የተወለድኩበት ቀን ነው የሚከበረው፡፡ አሁን የጠየቅኩሽ እኮ መቼ ነው የተወለድኩት የሚለውን ነው» ‹‹እና አሁን ስንት ዓመት እንደሆነህ ነው እምነግርህ?›› እሱን ብቻ አይደለም፡፡ የተወለድኩበትን ቀን ከቻልሽ ዕለቱንም ጭምር፣ ወሩንና ዓመተ ምህረቱን ነው የምፈልገው፡፡

‹‹ሆሆሆሆሆ! ወደው አይስቁ አሉ፡፡ በስንት ዓመቱ ነው ደሞ ይሄን የማስታውሰው?›› « ይሄን ያህል ብዙ ዓመት ሆኖኛል ማለት ነው?» ‹‹እስቲ ጋሼ ደምሴ ነው እንዲህ ዓይነት ነገር የሚያስታውስ እሱን ሂድና ጠይቀው››

«አንቺ ያላወቅሽውን እሱ እንዴት ያውቀዋል? ተይው እኔው ስንት ዓመት እንደሆነኝ አሰላዋለሁ። እስኪ ቀኑንና ወሩን ንገሪኝ?» ‹‹የአያ ደምሴ ልጅ የመጀመሪያ ባሏን ስታገባ ነው የተወለድክ፡፡ ልብ እለዋለሁ አንተን ነፍሰ ጡር ሆኜ ለሰርጉ እንኳን ሥራ አላገዝኳቸውም ነበር፡፡ አይ ሰርግ ነበር! ዳሱ አልበቃ ብሎ ቀዬው ሁላ ሰው ነበር›› «አይ እማማይ እኔ ስለሰርጉ ድምቀት መቼ ንገሪኝ አልኩሽ? እና ለሷ ሰርግ ነፍሰ ጡር ሆንሽ እንጂ መቼ ተወለድኩ?» ‹‹አይ ምልክቱን ልንገርህ ብዬ ነው፡፡ ደሞም ብዙም አልቆየም እሷ ተጫጉላ ስትወጣ ነው የተወለድክ››

«አሁንም እኮ መቼ እንደተወለድኩ አልነገርሽኝም እማመይአልኩ በስጨት ብዬ፡፡ እሷ እቴ መቼ ይሄ ይገባትና አሁንም እንደገና በምልክት ነገረችኝ፡፡ ‹‹ውይ! እሷ ስታገባማ ምልክት ያለው ዘበን እኮ ነው፡፡ ዝናቡ ከመጋቢት ጀምሮ ሲረግጠው ሲረግጠው ከርሞ በልግ በበልግ የሆነበት ዘበን ነው፡፡ አይ! ዘበን አሁን ምን አለ ያ ዘበን ተመልሶ ቢመጣ›› አለች፡፡ ወይኔ! ከስሮ የቀረው ልደቴ! እንግዲህ ወቅት እየጠበቀ ብዙ ጊዜ ከባድ ዝናብ ይዘንባል፤ የትኛውን ልያዘው? እስኪ ከሰርግ፣ ከዝናብ፣ ከድርቅ ውጪና ሌላ ምልክት ንገሪኝ አልኳት ተስፋ ባለመቁረጥ፡፡

‹‹አይ! እንግዲህ አትነዝንዘኝ፤ አንተን ወልጄ ተኝቼ የሚያዝያ ጆርጊስ የዓመት ስለነበር እነ እትየ አስረስ እንኳን ማርያም ማረችሽ ያሉኝ ለክብሩ እንደመጡ ነበር፡፡ አይ እትየ አስረስ እንዲያው አሁንስ ምን ሆና ይሆን እንዲህ ጥፍት ያለች?›› አሁን እኔ ስለእትየ አስረስ ምን አገባኝ እንግዲህ! ኧረ እማመይ እባክሽ እኔ እማላውቃቸውን ሰዎች ምልክት አትንገሪኝ፡፡ እስኪ እዚሁ እኛ ቤት ያለ ነገር ለምን አትነግሪኝም? አልኳት ተስፋ ወደመቁረጥ እየተቃረብኩ፡፡

‹‹ወይኔ! እንደዛ ተሆነ ደሞ ምን ሽግር አለው እነግርሃለሁ፡፡ እንዲያውም እስተምልክቱ አንተን አራስ ሆኜ ለማሽ ማለፍን ወልዳ ገና እየታለበች ነበር፡፡ ማለፍ እንቦሳ ሆኖ ቤት ውስጥ ታስሮ ነበር የሚውል፡፡ አይ! ማለፍ አይ ሞያ ነበር፡፡ አብሮት ተጠምዶ የሚውል በሬ እኮ አልነበረም፡፡ ወላ ሰርዶ ነሽ፣ ወላ ጭቃ ነሽ አይፈራም ነበር፡፡ እንዲያው መችም ማርጀት አይቀርም እሱም አረጀና ዙሪያሽወርቅ ስታገባ ታረደ›› እና ከኔ ጋ የተወለደ በሬ አርጅቶ ሞቷል ማለት ነው? አልኩ እኔም የእርጅና ስሜት እየተሰማኝ፡፡

‹‹የሰውና የከብት ዕድሜ አንድ አይደለም፡፡ ማለፍ ስንት ዓመት እንደቆየ ማወቅ ተፈለክ አባትህን ጠይቀው›› አለችኝ ደግሞህ እንዳጠይቀኝ በሚል ስሜት፡፡

አሁን ያለኝ ተስፋ አባቴን መጠየቅ ነበር፡፡ እሱ ደግሞ ጥሎበት እያንዳንዱን ነገር ከፖለቲካ ጋር ማገናኘት ይወዳል፡፡ አያቴ ራሱ እንደዚሁ ነበር፡፡ ስለጎረቤት ባልና ሚስት መጣላት ከነገሩት ከእስራኤልና ፍልስጤም ጋር ያገናኘዋል፡፡ አባቴም በአባቱ ወጥቶ ነው መሰለኝ የነገሩትን ሁሉ እንደምንም ጠምዞ ወደፖለቲካ ይወስደዋል፡፡ እንግዲህ ያለውን ይበል ብዬ ዕድሜዬን ጠየቅኩት፡፡ ‹‹ይሃዴግ ተገባ ስንት ዓመት ሆኖት ይሆን?›› አለኝ ጥያቄውን በጥያቄ፡፡ እሰይ! አሁን ፍንጭ ተገኘ፡፡ ኢህአዴግ የገባበትን በዓመተ ምህረት አባቴ ባያውቀው እንኳን የታሪክ መምህሬን እጠይቀዋለሁ፡፡ «ኢህአዴግ ሲገባ ነው የተወለድኩአልኩት ፍንጭ ያገኘሁ መስሎኝ፡፡ ‹‹ይሃዴግና ደርግ እየተዋጉ እናትህ አንተን ነፍሰ ጡር ነበረች፤ በዚያ ነው የማውቀው›› ሲለኝ እንደገና ተስፋ ወደመቁረጥ ተጠጋሁ፡፡ ደርግና ኢህአዴግ የተዋጉት 17 ዓመት ነው፡፡ ይህኔ እኮ 40 ሞልቶኝ ይሆናል ብዬ በመስጋት «እንዴ ምን እያልክ ነው አባበይ ደርግና ኢህአዴግ እኮ የተዋጉት 17 ዓመት ነው፡፡ በየትኛው ጦርነት እንደሆነ በምን ይታወቃልቆጣ አለና ‹‹ምናባቱ ይላል፤ ይሃዴግ ደርግን አሸንፎ መሬት ሲከፈል እናትህ አንተን ወልዳ አልጋ ላይ ነበረች›› አለኝ፡፡

እንግዲህ ዕድሜዬን የማሰላው በዚህ መልኩ ነው፡፡ እንኳን ትክክለኛ ቀኑ ትክክለኛ ዓመተ ምህረቱም አይታወቅም፡፡ ምናባቱ ስንት ዓመት ሆነኝ እያልኩ ከማሰብ ግልግል!

ዋለልኝ አየለ

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy