Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሣኔዎች ይተግበሩ

0 376

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሣኔዎች ይተግበሩ

ኢብሳ ነመራ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሰሞኑን ከሰኔ 2008 እስከ መስከረም 2009 ዓ.ም መጨረሻ በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግሥታት የተወሰኑ አካባቢዎች ተፈጥረው በነበሩ ሁከቶች የደረሰውን ጉዳት መርምሮ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት አቅርቧል።

ኮሚሽኑ ምርመራውን ማካሄድ የጀመረው ህዳር 2009 ዓ.ም ላይ ነበር። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባለፈው ዓመት ተቀስቅሶ ከነበረው ሁከት ጋር በተያያዘ ሪፖርት ሲያቀርብ የሰሞኑ ሁለተኛው ነው። ኮሚሽኑ ሰኔ 2008 ዓ.ም በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ተቀስቅሶ የነበረውን ሁከት መነሻ በማድረግ መንስዔውንና ያስከተለውን ጉዳት ከምክረ ሃሳብ ጋር ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረቡ ይታወሣል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሰሞኑን ያቀረበውን ሪፖርት ከመመልከታችን በፊት ባለፈው ዓመት ያቀረበውን የመጀመሪያ ሪፖርት እናስታውስ። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በ2008 ዓ/ም ህዳር ወር በኦሮሚያ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎች፣ በኋላም በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ተከስቶ የነበሩ ግጭቶችን በተመለከተ ያካሄደውን የምርመራ ሪፖርት ሰኔ 3፣ 2008 ዓ/ም ላይ ነበር ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበው። 

ኮሚሽኑ ምርመራውን ሲያካሂድ ተጎጂና የተጎጂ ቤተሰቦችን፣ በየደረጃው ያሉ አመራሮችንና ፈጻሚዎችን፣ የሃገር ሽማግሌዎችን፣ የሃይማኖት አባቶችን፣ የህብረተሰብ ተወካዮችን፣ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን በጋራና በተናጠል በማነጋገር እንዲሁም የተለያዩ ሰነዶችን መመርመሩን አስታውቋል።

ይህ ሪፖርት እንዳመለከተው በኦሮሚያ ክልል በአጠቃላይ 173 ሰዎች ሞተዋል። 956 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሷል። ከሞቱት ሰዎች 14ቱ የጸጥታ ሃይል አባላት፣ 14ቱ ደግሞ የመስተዳደሩ አመራሮች ነበሩ።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ባደረገው ምርመራ በኦሮሚያ ክልል ለተፈጠረው ሁከት ዋነኛ መንስኤ የመልካም አስተዳደር ችግር መሆኑን እንደደረሰበት በሪፖርቱ አሰታውቆ ነበር።

ሪፖርቱ የህብረተሰቡን ጥያቄ በየደረጃው ምላሽ አለማትግኘት፣ የአመራሮች የጥቅም ትስስር፣ የመሬት አስተዳደር ችግር፣ የአዲስ አበባና ፊንፊኔ የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን ላይ የተሳሳተ መረጃ መሰራጨት እንዲሁም የፍትህ አካላት ኪራይ ሰብሳቢነትና መሰል ችግሮችንም በመንስኤነት ዘርዝሯል። ለተነሱ ችግሮች ከላይ የተጠቀሱት ምክንያቶች መነሻ ይሁኑ እንጂ፣ ሌሎች የህብረተሰቡን ሰላም ለመበጥበጥ ዓልመው የሚጠባበቁ አካላት ልዩ እቅድ በመያዝ የህብረተሰቡን ሰላማዊ ጥያቄ ወደ ሁከት መቀየራቸውን ሪፖርቱ አመልክቷል።

በክልሉ መንግስት ጥያቄ መሰረት መከላከያ ሰራዊትና የፌደራል ፖሊስ ግጭቱን ለማብረድ ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን በሰሩት የተቀናጀ ስራ ችግሩ ከነበረበት እንዳይብስ ማድረጉንም ሪፖርቱ አመልክቶ እንደ ነበር ይታዋሰል።

የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በአማራ ክልል ተቀስቅሶ የነበረው ሁከት ሰሜን ጎንደር ላይ የተወሰነ እንደነበረ፣ የቅማንት ብሄረሰብ የማንነት ጥያቄ ለክልሉ ምክር ቤት ቀርቦ የተሰጠውን ምላሽ ተከትሎ የተቀሰቀሰ እንደነበር በሪፖርቱ አስታውቋል። ለጥያቄው ምላሽ መስጠት ላይ የተስተዋለው መጓተት ዋነኛው የሁከቱ ቀስቃሽ ሁኔታ እንደነበርም አመልክቷል።

በዚህም 97 ሰዎች መሞታቸውንና 86 ሰዎች ላይ ደግሞ ቀላልና ከባድ ጉዳት መድረሱን አስታውቋል። ግጭቱን ለማስቆም በተወሰደ እርምጃ የጸጥታ ሀይሉ የብሄርተኝነት ስሜት በማንጸባረቅ የችግሩ አካል የነበረበት ሁኔታ መኖሩን፣ በተጨማሪ ተመጣጣኝ ያልሆነ ወይም ከፍተኛ የሀይል እርምጃ መወሰዱን በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል። ግጭቱን በማባባስ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ በማስኬድ የሞትና የንብረት ውድመት እንዲደርስ ያደረጉ አካላት ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚገባም ኮሚሽኑ ባስቀመጠው ምክረ ሃሳብ ጠቁሟል።

ሪፖርቱ የቀረበለት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በበኩሉ፣  የቀረበውን ሪፖርት በመመርመር በምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ በተሰጠው መመሪያ መሰረት በህግ፣ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አማካኝነት  የውሳኔ ሃሳብ አቅርቦ አጽደቋል። በዚህም በተለይ በኦሮሚያ የተወሰደው እርምጃም ከተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ ጋር ሲነጻጸር ተመጣጣኝ እንደነበረ ከቀረበው ሪፖርት ለማረጋገጥ መቻሉ ተገልጿል። በኦሮሚያ ክልል ፖሊስና ሚሊሻ፣ የፌደራል ፖሊስ እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊት በከፈሉት መስዋዕትነት፣ በክልሉ ተፈጥሮ የነበረዉ ሁከትና ብጥብጥ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር መቻሉን የሚያሳይ ነው ብሏል። የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የተጀመረው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ምክር ቤቱ በውሳኔ ሃሳቡ አመልክቷል።

በሌላ በኩል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርቱን መነሻ በማደረግ ያጸደቀው የወሳኔ ሃሳብ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን፣ በማውራና አይከል በተፈጠረው ግጭት የፖሊስ አባላትና አመራሮች ተመጣጣኝ ያልሆነ ሃይል መጠቀማቸውን ኮሚሽኑ ባቀረበው ሪፖርት መረጋገጡን አስታውሷል።

በተፈጸመው የህግ ጥሰት የክልሉ መንግስት ትዕዛዝ ወይም እጅ አለመኖሩም መረጋገጡንም አመልክቷል። የቅማንትን ህዝብ ጥያቄ ተመርኩዞ የሃገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት መሪዎች ግጭቱ ወደ መጥፎ ደረጃ እንዳይሸጋገር የእርቅና የሰላም ተግባራት ማከናወናቸውን የኮሚሽኑ ሪፖርት እንደሚያሳይ የውሳኔ ሃሳቡ ገልጿል።

እንግዲህ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርትን መነሻ በማድረግ ሰኔ 2008 ዓ/ም ላይ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች በምን ደረጃ ተግባራዊ እንደተደረገ የሚያሳይ መረጃ ግን እስካሁን ይፋ የተደረገ አይመስለኝም።

በጽሁፉ መግቢያ ላይ እነደተነሳው፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከሰኔ 2008 ዓ/ም በኋላ ሁከቱ አገርሽቶ፣ ከኦሮሚያና አማራ ክልሎች በተጨማሪ የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልልንም ጨምሮ መስከረም መጨረሻ ላይ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ለማወጅ ያስገደደ ሁኔታ እስኪፈጠር ተባብሶ የነበረውንም ሁከት መርምሮ ሚያዚያ 10፣ 2009 ዓ/ም  ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት አቅርቧል።

በዚህ ሪፖርት መሰረት ምርመራ የተደረገው በኦሮሚያ ክልል 15 ዞኖችና 91 ከተሞች፣ በአማራ ክልል 5 ዞኖች እና 55 ወረዳዎች እንዲሁም በደቡብ ክልል ጌዲዮ ዞን በሚገኙ 6 ከተሞች ነው። ሁከቱ ተቀስቅሶባቸው የነበሩት አካባቢዎች በሙሉ በምርመራው ውስጥ ተካተተዋል። በዚህ የምርመራ ወጤት ሪፖርት መሰረት በአጠቃላይ በሶስቱ ክልሎች  ዳግም ባገረሸው ሁከት ሳቢያ ብቻ የ669 ሰዎች ሕይወት አልፏል። ወደ 20 ሺ የሚጠጉ ሰዎች ተፈናቅለዋል። በመቀጠል የኢትዮጵያ ሰበአዊ መብት ኮሚሽን ያቀረበውን ሪፖርተ በሶስቱ ክልሎች ከፋፍለን እንመልከተ።

ኦሮሚያ

በኦሮሚያ ክልል ከሰኔ በኋላ ባገረሸው ሁከት ለ462 ሰላማዊ ሰዎችና 33 የፀጥታ ኃይሎች በአጠቃላይ ለ495 ሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት መሆኑን የኮሚሽኑ ሪፖርት አሰታውቋል።  በኦሮሚያ ክልል የተከሰተው ሁከት መንስኤ በመጀመሪያው ዙር ሁከት እንደነበረው ሁሉ፣ ስር የሰደደ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ማግኘት ያለበትን ጥቅም ህገመንግስቱ በሚደነግገው መሰረት ተግባራዊ አለመደረጉና የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን በተመለከተ የተሰራጨው የተዛባ መረጃ መሆኑን ሪፖርቱ አመልክቷል።

የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (ኦ ኤም ኤን) እና ማህበራዊ ድረገጹ ሃምሌ 30 እና ነሃሴ 30 ቀን 2008 ዓ.ም ሰፊ የአመፅ ጥሪ ማድረጋቸውም በሪፖርቱ ቀርቧል። የኢሬቻ በዓል በቢሾፍቱ በሚከበርበት ወቅት አነዚሁ ሚዲያዎች የሁከት ጥሪ ተላልፈው እንደነበረም ተመልክቷል። በኢሬቻ በዓል ላይ ለተፈጠረው አመፅ የፀጥታ ኃይሉ ከአስለቃሽ ጋዝ ውጭ የጠቀመው የሃይል እርምጃ እንደሌለ፣ የተወሰደው እርምጃም ተመጣጣኝ እንደነበረ ሪፖርቱ ይገልጻል።

በምዕራብ አርሲ፣ ባሌ እና ጉጂ በመሳሪያ የታገዘ ሁከት መፈፀሙን የሚገልጸው ሪፖርቱ፣ የፀጥታ ሃይሉ የሰላማዊ ሰዎችን ህይወት ለማዳን የወሰደው እርምጃ ተመጣጣኝና አስፈላጊ እንደነበር አመልከቷል። በሌላ በኩል በባሌ ሮቤና በምስራቅ ሃረርጌ 28 ሰዎች የሞቱበት እንዲሁም በዲዴሳ ከተማ የተወሰደው ለሰው ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆነ እርምጃ ተመጣጣኝ አለመሆኑን ሪፖርቱ አመልክቷል። በአዳሚ ቱሉ 14 ሰዎች ለሞቱበት፣ በአወዳይ እና ዲዴሳ ለ38 ሰዎች ሞትና ለ62 ሰዎች መጎዳት ምክንያት የሆኑ አካላት በህግ ሊጠየቁ እንደሚገባም ሪፖርቱ አሳስቧል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው የኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባር (ኦነግ)፣ ህጋዊ ሆኖ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) እና ከውጭ ሃገር የሚሰራጨው ኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ የተባለ ሚዲያ ህገወጥ ሰልፎች መጥራታቸውን ያመለከተው የኮሚሽኑ ሪፖርት፣ አነዚህ ህገወጥ ሰልፎች የብሔር ጥቃት እንዲፈጸም፣ የሃይማኖት እኩልነት እንዳይከበር፣ የሰዎችን በሕይወት የመኖር መብት እንዲጣስና የአካል ጉዳት እንዲደርስ ያደረገ ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውን ገልጿል።

ሪፖርቱ በኢሬቻ በዓል ላይ ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር ከዋዜማ ምሽት 2 ሰዓት ጀምሮ ሙከራዎች ተደርገው እንደነበረ፣ በተጨማሪም ከሌሊቱ 8 ሰዓት ጀምሮ ከሌሎች አካባቢዎች በአይሱዙ ተጭነው ወደቢሾፍቱ የገቡ አካላት መኖራቸው በተደረገው ምርመራ መታወቁን ገልጿል።

ይሁን እንጂ ችግሩ እንዳይከሰት ለማድረግ የጸጥታ አካላት ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዳልተወጡ ሪፖርቱ አመልክቷል። የኢሬቻ በዓል በዚያ ወቅት መከበሩ ሃላፊነት የጎደለው መሆኑን ያመለከተው ሪፖርቱ፣ ሆኖም የፀጥታ ሃይሉ በበዓሉ ወቅት ያሳየው ትዕግስት የሚስመሰግን ነው ብሏል። በማግስቱ በቢሾፍቱ የነበረውን ብጥብጥ መቆጣጣር ባለመቻሉ ግን ሊጠየቅ እንደሚገባው አመልክቷል።

አማራ

በአማራ ክልል ተቀስቅሶ በነበረው ሁከት የ110 ዜጎች ህይወት ማለፉን  237 ደግሞ ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን፣ ከ11 ሺህ በላይ ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት አስታውቋል። የሁከቱ መንስኤ፣ የወልቃይት የማንነት ጥያቄ አልተመለሰም የሚሉ ጥያቄዎች፣ የትግራይ የበላይነት አለ የሚሉ ቅሬታዎች፣ የዳሽን ተራራ በመማሪያ መፅሐፍ ውስጥ በትግራይ ክልል ስር እንዲካተት መደረጉ፣ የጠገዴ ወሰን ድንበር ምላሽ ያግኝ የሚል እንዲሁም የአማራ መሬት ለሱዳን ተሰጥቷል የሚሉት ምክንያቶች መሆናቸውን የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በሪፖርቱ አስታውቋል።

ሃምሌ 4 ቀን 2008 ዓ.ም ፖሊስ በሽብር የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ለመያዝ ሲነቀሳቀስ፣ ሁኔታውን የወልቃይት የማንነት ጥያቄን ለማዳፈን የተደረገ ነው በሚል ኢሳትን በመሳሰሉ ሚዲያዎች መልዕክቶች ተላልፈው እንደነበረም ሪፖርቱ ይገልጻል። በክልሉ የተደረጉ ሰልፎችም ህጋዊ ፍቃድን ያላገኙ እንደነበሩ ያመለከተው የኮሚሽኑ ሪፖርት፣ የሀገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ የማቃጠል እና የብሔር ጥቃት ተፈፅሞባቸዋል ብሏል። በሁከት እና ብጥብጡ ወቅት የፀጥታ ሃይሎች የወሰዱትን እርምጃ መመርመሩን ያመለከተው ኮሚሽኑ፣ ሃምሌ 18 ቀን 2008 ዓ/ም በጎንደር የተወሰደው እርምጃ ህጋዊና ተመጣጣኝ መሆኑን ጠቅሷል።

በባህርዳር ማረሚያ ቤት፣ በጅጋና በሊቦ ከምከም እንዲሁም ሌሎች አካባቢዎች የተወሰዱት እርምጃዎችም ተመጣጣኝ እንደነበሩ አመልክቷል። በደምቢያ መንገድ በዘጉ፤ በደባርቅ፣ በወገራ፣ በደብረታቦር መኪና ላይ ድንጋይ በወረወሩ፤ በስማዳ፣ እብናት፣ እንዲሁም በወረታ ሁለት ሰዎች የሞቱበት እርምጃ የፀጥታ ሃይሉ አላስፈላጊ የሃይል እርምጃ የወሰደባቸው መሆናቸውንም ሪፖርቱ አመልክቷል።

የደቡብ፣ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች

በደቡብ ክልል ጌዲዮ ዞን የተፈጠረውን  ብጥብጥ አስመልክቶ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የኢፍትሐዊ ተጠቃሚነት መንስኤ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት አስታውቋል። በተቀሰቀሰው ሁከት የ34 ሰዎች ህይወት ማለፉን 139 ሰዎች ላይ ደግሞ ጉዳት መድረሱን አመልክቷል።

የጌዲዮ ዞን አስተዳደር፣ የፖሊስ አካላት፣ እንዲሁም የጌዲዮ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሁከቱ እንዲቀሰቀስ ማድረጋቸውን ሪፖርቱ አመልክታል። ሁከቱን በመቀስቀስ በሌሎች በሄሮች አባላት ላይ ጥቃት እንዲሰነዘረ ያደረጉት እነዚህ አካላት በህግ ሊጠየቁ እንደሚገባ አሳስቧል።

እንግዲህ ከላይ ይዘቱን ለማየት ያህል ቀንጭበን የተመለከትነው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ያቀረበውን ሪፖርት ያዳመጠው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርቱን አጽድቋል።ምክር ቤቱ በየደረጃው ባሉ የመንግስት አካላትና ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ በወሰዱ የፀጥታ ሃይሎች ላይ ማጣራት ተደርጎ ለህግ እንዲቀርቡ በኮሚሽኑ የተሰጠውን ምክረ ሃሳብም ደግፏል። በብሄር ተኮር ጥቃት ከአካባቢያቸዉ የተፈናቀሉ ዜጎችም በአስቸኳይ እንዲቋቋሙ አሳስቧል።

በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል፣ በጌዲኦ ዞን ብሄርን መሰረት ባደረገ ጥቃት ላይ ተሳትፎ ያደረጉ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የጸጥታ አካላትና የጌዲኦ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት በህግ እንዲጠየቁም ወስኗል። በአማራ ክልል በባህርዳር ከተማ ተቀስቅሶ በነበረW ሁከት ሰላማዊ ሰልፍ ጠርቶ ህዝቡ ሊያውቀው በማይችልበት ሁኔታ ሰልፉን መተዉን አሳውቆ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ሰልፍ ተካሂዶ ወንጀል እንዲፈጸም ምክንያት የሆነው ሰማያዊ ፓርቲ እንዲሁም በኦሮሚያ ለተፈጠረው ቀውሰ የአባባሽ ሚና የተጫወተው የአሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፊኮ) አባላት በህግ እንዲጠየቁ ሲልም ውሳኔ አሳልፏል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በህገመንግስቱ መሰረት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቋቋመ ተጠሪቱም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆነ ተቋም ነው። ይህ ተቋም ከአስፈጻሚው አካል ፍጹም ገለልተኛ ነው። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በህገመንግሰቱ አንቀጽ 55 (የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባር) ንኡስ አንቀጽ 14 “የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ያቋቁማል፤ የኮሚሽኑ ሥልጣንና ተግባር በህግ ይወሰናል ተብሎ በተደነገገው መሰረት የተቋቋመ ተቋም ነው።

ኮሚሽኑ በአዋጅ ቁጥር 210/1992 መሰረት የተቋቋመ ሲሆን፣ ዓላማውም ሕዝቡ ስለሰብአዊ መብቶች ግንዛቤ እንዲኖረው ማስተማር፣ መብቶቹ እንዳይጣሱ መጠበቅ፣ መብቶች ሳይሸራረፉ ሥራ ላይ እንዲውሉና ተጥሰው ሲገኙ አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ነው። ኮሚሽኑ የሰብአዊ መብት መጣስ ቅሬታዎች ሲቀርቡለት ወይም በራሱ አነሳሽነት ምርመራ የማካሄድ ስልጣን ተሰጥቶታል። የባለፈውን ዓመት ሁከቶች ሁለት ጊዜ መርምሮ ሪፖርት ያቀረበው በዚህ ስልጣኑ ነው።

የኢፌዴሪ ሀገመንግስት አንድ ሶስተኛ ድንጋጌዎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚመለከቱ ናቸው። በመሆኑም የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበራቸውን የሚያረጋግጥና ስለመበቶቹና ነጻነቶቹ በህዝቡ ውስጥ ግንዛቤ የሚያሰርጽ ገለልተኛ ተቋም ማዋቀር አማራጭ የሌለው ነው። የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ይህን ተልዕኮ እየተወጣ ነው። ከላይ የተጠቀሱት ሁለት ሪፖርቶች ተቋሙ ምን ያህል በገለልተኝነት እንደሚሰራ ያሳያል። በሰብአዊ መብት ጥሰት ድርጊት ላይ የተሳተፉ አስፈጻሚ አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ የማሳሰብ  ስልጣን ያለው መሆኑንና ይህንንም ተግባራዊ እያደረገ መሆኑንም ያረጋግጣል። በኢትዮጵያ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በማጣራትና እርምጃ አንዲወሰድ በማሳሰብ ረገድ ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የተሻለ ተቋም የለም። ሆኖም መንግስት ኮሚሽኑ ያቀረበውን ሪፖርት መነሻ በማድረግ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያሳለፋቸውን ወሳኔዎችና ምክረሃሳቦች ተግባራዊ ማደረግ ይጠበቅበታል። ይህ ሲሆን ብቻ ነው መንግስት በሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ላይ ሃላፊነት የሚሰማው መሆኑንና ራሱን የማረም ዝግጁነትና ፍቃደኝነት ያለው መሆኑን በተግባር የሚያሳየው። እናም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወሳኔዎች የመተግበሩና እርምጃውን ለህዝብ የማሳወቅ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy