Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የመንግስት ኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙሃን የሚዛናዊነት ችግር አለባቸው-ጥናት

0 606

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የመንግስት ኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙሃን ሚዛናዊ ዘገባ የማቅረብ ጉድለት እንዳለባቸው በመስኩ የተደረገ ጥናት አመለከተ።

የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት በአገራዊ የመገናኛ ብዙሃን ልማትና ብዝሃነትን ማረጋገጥ፣ የአሰራር ስርዓቶችን መቅረፅና መተግበር እንዲሁም በመገናኛ ብዙሃን ልማት ዘርፍ በሚስተዋሉ ክፍተቶች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል።

የህዝብና የመንግስት ብሮድካስት መገናኛ ብዙሃን ተደማጭነት ደረጃ ላይ ያተኮረው ጥናት እንደጠቆመው የመንግስት ኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙሃን ሚዛናዊ ዘገባ የማቅረብ ጉድለት ይታይባቸዋል።

መገናኛ ብዙሃኑ ተደራሽነታቸውን ከማስፋት ባሻገር ሚዛናዊ ዘገባዎች ላይ ሊያተኩሩ እንደሚገባ ነው ጥናቱ በመፍትሄ ሃሳብ ያቀረበው።

የመንግስት ሬድዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች በቋንቋና ሽፋን ተደራሽነት መሻሻል፣ የወቅታዊ ጉዳዮች አቀራረብና የመዝናኛና የስፖርት ዝግጅቶች በተሻለ ነጻነት የሚቀርቡባቸው ናቸው ሲል ጥናቱ በጠንካራ ጎን ጠቅሷቸዋል።

ከምርመራ ጋዜጠኝነትና ከሚዛናዊነት፣ ከማስታወቂያ መብዛትና ከይዘት ድግግሞሽ ጋር በተያያዘ ጣቢያዎቹ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንዳሉም ነው ያመለከተው።

በተጨማሪም የመንግስት ሬድዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ስኬት ላይ እንጂ በችግሮችና መፍትሔዎቻቸው ላይ አለማተኮራቸውን ጠቁሞ ፕሮግራሞችን ለመሸፈን እንጂ ከሳቢነትና ከአሳታፊነት አንጻር ትኩረት አይሰጣቸውም ሲል በድክመት አቅርቧል።

ለችግሮቹ ከቀረቡ መፍትሄዎች መካከል የአቀራረብ ስልቶችን ማስተካከል ቢችሉ የአየር ሰዓትን ለመሸፈን ከሚደረገው ጥረት ባላነሰ ለፕሮግራሞች ጥራትም ትኩረት ቢሰጡና በህብረተሰቡ ዘንድ ተወዳጅ የሆኑ ፕሮግራሞችን ተጠናክረው ቢቀጥሉ የሚሉት ይገኙበታል።

በተመሳሳይ የምርመራ ጋዜጠኝነት በሰፊው ቢሰራበት፣ ሚዛናዊ የአቀራረብ ስልት እየተለመደ ቢመጣ፣ መገናኛ ብዙሃንና ጋዜጠኞች በነፃነትና ተጠያቂነት መንፈስ እንዲሰሩ ቢበረታቱ የሚሉ የመፍትሄ ሀሳቦችንም ጥናቱ ጠቁሟል።

የአማራ ክልል ቴሌቪዥን ከተለመደው የህዝብና የመንግስት ብሮድካስተሮች ለየት ያለ የአቀራረብ ስልትና ግልጽነት ይዞ በመምጣቱ ሌሎች ጣቢያዎችም አርአያነቱን ሊከተሉ እንደሚገባም በጥናቱ ተጠቅሷል።

በመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የሚዲያ አብዝሃነት ጄኔራል ዳይሬክተር አቶ ታምራት ደጀኔ መገናኛ ብዙሃን በምርመራ ጋዜጠኝነት የህዝቡን የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ ጋዜጠኞች ችግሮችን ፈልፍለው ማውጣት ይጠበቅባቸዋል፤ መንግስትም ውሳኔ እንዲሰጥበት የማድረግ ኃላፊነት አለበት ብለዋል።

ጋዜጠኞች “የህዝቡ አይንና ጆሮ ሆነው ማገልገል ይገባቸዋል” ያሉት አቶ ታምራት፤ በዚሁ ዓላማ የሚከናወኑ ማናቸውም የምርመራ ጋዜጠኝነት ሥራዎች በመንግሥት በኩል እንደሚደገፉ ተናግረዋል።

ጋዜጠኞች አንዳንድ ችግሮችና ውስንነቶችን መሠረት አድርገው ለመሥራት በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ጥረቱን ለማደናቀፍ የሚሞክሩ አመራሮች “ህገ-ወጦች ናቸው” በማለት “እያንዳንዱ የመንግሥት አካል ለህብረተሰቡ መረጃ የመሥጠት ግዴታ አለበት” ብለዋል።

ጋዜጠኞች ችግር የሚፈጥሩ አካላት ሲያጋጥሟቸው “በየአካባቢው ላሉ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን መስሪያ ቤቶችና ለሚመለከታቸው አካላት ማመልከት ይችላሉ” ነው ያሉት።

እንደ አቶ ታምራት ገለጻ፤ ጋዜጠኞች ሙያዊ ሥነ-ምግባራቸውን ጠብቀው የህዝቡን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት በሚከናወኑ ተግባራት ላይ በትኩረት መሥራት ይጠበቅባቸዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ ሁሉንም የመንግስትና የህዝብ መገናኛ ብዙሃን የሚዳስስ ጥናት ሲካሄድ ይህ የመጀመሪያው መሆኑ ተጠቁሟል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy