Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የመደራጀትና ሃሳብን የመግለፅ መብት

0 370

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የመደራጀትና ሃሳብን የመግለፅ መብት/ታዬ ከበደ/

  የተለያዩ ፅንፈኛ ሃይሎች በሀገራችን ላይ ከሚያነሷቸው ጉዳዩች ውስጥ እየደጋገሙ የሚገልጿቸው ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ የመደራጀትና የመሰብሰብ መብቶች ዋነኛዎቹ ናቸው። እነዚህ መብቶች በህግ ካልተደገቡ በስተቀር፣ በሀገራችን ህገ መንግስት ዕውቅና እና ከለላ የተሰጣቸው ናቸው። ሆኖም ሂዩማን ራይትስ ዎች የተሰኘው ዕንፈኛ ተቋም እነዚህ መብቶች የተጣሱ በማስመሰል እየደጋገመ ለውንጀላ ሲጠቀምባቸው ይስተዋላል።

ይሁን እንጂ ፅንፈኛው ኒዮ-ሊበራል ድርጅት ባህር ማዶ ተቀምጦ በነሲብ እንዳለው ሀገራችን ውስጥ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ፣ የመደራጀትና የመሰብሰብ መብቶች የሌሉ አይደሉም። እንዲያውም ከመኖር በላይ ህገ-መንግስታዊ ዕውቅና እና ከለላ ያላቸው ብሎም በተግባር ገቢራዊ እየሆኑ ያሉ የማይገሰሱ መብቶች ሆነው ሀገራችን ውስጥ እየተሰራባቸው ናቸው።

እንደ እውነቱ ከሆነ ሀገራችን ውስጥ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ባይኖር ኖሮ፤ እንኳንስ ስርዓቱ የፈጠራቸው የግል መገናኛ ብዙሃን ሊኖሩ ቀርቶ ተግባራቸውንም በነፃነት ባልተወጡ ነበር። የፕሬስ ነፃነትን የሚያትተውና ጋዜጠኛው ይበልጥ ነፃ ሆኖ እንዲሰራ ለማድረግ የተረቀቀው የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅም ባልኖረ ነበር።

ግና ዛሬ በሀገራችን ውስጥ እንደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን ጀማሪነት ይበል የሚያሰኙ በርካታ የፕሬስ ውጤቶች በገበያ ላይ ናቸው። ህገ-መንግስቱን ተመርኩዞ የወጣው የሀገራችን የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅም ማንኛውም ጋዜጠኛ በፃፈው ፅሐፍ ምክንያት ከፍርድ ሂደት በፊት መታሰር እንደሌለበት ስለሚደነግግ፤ እነሆ የሙያውን ስነ-ምግባር ተከትለው የሚሰሩ ጋዜጠኞች ሀገራችን ውስጥ በሂደት በመፈጠር ላይ ናቸው።

በዚህም ምክንያት ዛሬ ከወንጀል ጋር በተያያዘ ሁኔታ ካልሆነ በስተቀር በፃፈው ፅሁፍ ምክንያት የሚታሰር ጋዜጠኛ ኢትዮጵያ ውስጥ የለም። ይሁንና ሂዮማን ራይትስ ዎች እንዲህ ዓይነቱ ምድር ላይ ያለ ተጨባጭ ሃቅ እንደለመደው መንግስትን ለማጥላላት ስለማያመቸው ለመስማትም ይሁን ለማውራት አይፈልግም። ከዚህ ይልቅ ባልተጨበጠ ዕውነታ ተመርቶ እነ እገሌ ታሰሩ እያለ አሉባልታ መንዛትን ስራዬ ብሎ ተያይዞታል።

የመደራጀትና የመሰብሰብ መብቶችም ቢሆኑ ሀገራችን ውስጥ ህገ-መንግስታዊ እውቅና እና ከለላ የተሰጣቸው እንጂ አክራሪው ኒዮ-ሊበራል ተቋም እንደሚያስወራው የሌሉ አይደሉም። ሌላው ቀርቶ ሀገራችን ውስጥ የመደራጀትና የመሰብሰብ መብት ለመኖሩ በተናጠል፣ በግንባር፣ በቅንጅትና በውህደት ተሰባስበው በመደራጀትና በምርጫ ቦርድ ዕውቅና አግኝተው በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙት የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖራቸው በአክራሪው ተቋም ፖለቲካዊ ቀመር እንደሌሉ የተቆጠሩ ናቸው።

እነዚህ ፓርቲዎች በሂዮማን ራይትስ ዎች ዕውቅና ይሰጣቸው ዘንድ እርሱ የሚፈልገውን የቀለም አብዮት በጎዳና ላይ ነውጥ ማሳየት አለባቸውን?— እጅግ ያስገርማል። በሀገሪቱ ህግ መሰረት የሚንቀሳቀሱ ሲቪክ ማህበራትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችስ ከቶ ለፅንፈኛው ተቋም ምን መስለው ይሆን የታዩት?…እርግጥ ምላሹን የሚያውቀው ተቋሙ ነው።

ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ህገ-መንግስቱ ባጎናፀፋቸው የመደራጀት መብት መሰረት በርካታ የመንግስት ተቃዋሚዎች መኖራቸውን ማወቅ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ እነዚህ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዓላማቸውን ለማሳካት በሚያካሄዱት ማናቸውም እንቅስቃሴ ጣልቃ የሚገባ አንድም የመንግስት አካል የለም፡፡ ፓርቲዎችቹ በሀገራዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ይሰጣሉ፤ አቋማቸውንም ያንጸባርቃሉ፡፡

ተደራሽነታቸውን ለማስፋትም በመገናኛ ብዙሃን ተጠቅመው ዓላማቸውን ለህዝቡ ሲያደርሱ ማየት የተለመደ ነገር ነው፡፡ ታዲያ ለምን ይህን አቋም አንጸባረቅክ ተብሎ የታገደ ፓርቲም ይሁን የታሰረ ግለሰብ እንደማይገኝ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ከዚህ ባሻገር ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚ ድርጅቶችን የሚያቀራርብና በወቅታዊ ጉዳዮች ያላቸውን አቋም የሚያንጸባርቁበት የክርክር መድረኮች እየተበራከቱ መምጣታቸው ሀገራዊው የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት እየዳበረ መሄዱን የሚያመላክት ነው፡፡

የኢፌዴሪ ህገ -መንግስት ለዜጎች ካጎናፀፋቸው ዴሞክራሲያዊ መብቶች መካከል የቡድንና የግለሰብ መብቶች ይገኙበታል፡፡ ከእዚህም ውስጥ የአመለካከትና ሃሳብን በነጻ የመያዝና የመግለጽ፣ የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነት እንዲሁም አቤቱታን የማቅረብ መብት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ እነዚህ መብቶች በህግ ካልሆነ በስተቀር በማንኛውም መልኩ ሊገደቡ የሚችሉ አይደለም።

ዜጎች በፈለጉት ከመደራጀት መብት አኳያ ባሻቸው ሃይማኖት ውስጥ ሊሳተፉ ይችላሉ—ያለ አንዳች ጣልቃ ገብነት። የኢትዮጵያ መንግስት በሃይማኖት ጉዳዮች ላይ ጣልቃ በመግባት የዜጎችን መብት ጥሷል የሚል ክስ አይሉት ወቀሳ አቅርበዋል፡፡ ይሁንና ሁላችንም እንደምናውቀው የኢፌዴሪ ህገ – መንግስት የመንግስትና የሃይማኖት መለያየትን በግልፅ ደንግጓል።

በዚህም ድንጋጌ መሰረትም እስከ አሁን ድረስ መንግስት በማንኛውም ሃይማኖት ጣልቃ ገብቶ ‘ይህን አድርግ ያንኛውን ደግሞ ተው’ ያለበት ሁኔታ የለም። የሃይማኖት መሪዎችን ሲሾምና ሲሽርም አልተመለከትንም፡፡ ታዲያ እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ፤ መንግስት የሃይማኖት ነጻነት መብትን እየጣሰ እንደሚገኝ ለማስመሰል የሚካሄደው የስም ማጥፋት ዘመቻ መንስዔ ለእንደራሴውና ለእማኞቻቸው ካልሆነ በሰተቀር ለማንም ግልፅ አይደለም።

የኢፌዴሪ መንግስት የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚያከብረውና የሚያስከብረው የውጭ ሃይሎችን ፍላጎትን ለማሟላት አሊያም ለማስደሰት አለመሆኑን መረዳት ያሻል። ከዚህ በተጨማሪም ሀገራችን ውስጥ በውጭ ሃይሎች አማካኝነት የሚዘወሩ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሊኖሩ እንደማይችሉ ማወቅ ያስፈልጋል።

ለዚህ ጥሩ ምክንያት የሚሆነው መብቶቹ የሚከበሩት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የዘመናት ትግል ውጤት እንዲሁም የሀገሪቱ የመኖርና ያለመኖር ህልውና ጉዳይ መሆናቸውን መንግስት በፅናት ስለሚያምን ብቻ ነው። እናም ሀገራችንን የማይገልፅና “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” እንዲሉት ዓይነት ጭፍን ዲስኩር ከትዝብት ውጪ የሚያስገኘው ጥቅም ባለመኖሩ ነገሮችን በእርጋታና በሰከነ ሁኔታ መመልከት ይገባል።

በአጠቃላይ ሀገራችን  በራሷ  ልማታዊ  ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ እየተመራች  በአሁኑ ወቅት  ፈጣንና  ተከታታይ  ዕድገት  ማስመዝገቧ ‘ከኒዩ – ሊቢራሊዝም  በስተቀር  ሌሎች  አማራጮች  ለዕድገት  አያበቁም’ ብሎ  የሚያስበውን  አክራሪ  ተቋም  በአያሌው  ብስጭት  ውስጥ ይከተዋል። በዚህም ሳቢያ ሁሉንም ሀገራዊ ትልሞች ለመቃወም ይሞክራል።

ሆኖም የመደራጀትና ሃሳብን በነፃነትየመግለፅ መብት በማንም የማይገደብ ብቻ ሳይሆን በህገ መንግስቱም ከለላ የተሰጠው መሆኑን ማወቅ አለበት። የሰው ወርቅ ስለማያደምቅ የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ በህገ መንግስታቸውና በራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ እየታገዙ መብቶቹን ይበልጥ ማስከበራቸው አይቀርም።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy