Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የመጀመሪያው እርከን

0 352

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የመጀመሪያው እርከን /ኢብሳ ነመራ/

ባለፉት ዓመታት ተደጋጋሚ ሲቀርበ የቆየው፣ በተለይ ባለፈው ዓመት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት ከጠቅላይ ሚኒስት ኃይለማርያም ጋር በተወያዩበት ወቅት ጎልቶ ወጥቶ የነበረው በገዢው ፓርቲ ኢህአዴግና በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሃከል ድርድር ይካሄድ የሚለው ጥያቄ ዘንድሮ ምላሽ ወደማግኘት ተሸጋግሯል። የድርድሩ ሂደት ከሁለት ወራት በፊት ተጀመሮ ሰሞኑን “የሃገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች የድርድር አሰራር ደንብ” የተሰኘ ሰነድ በማጽደቅ አንድ እርከን ተጉዟል። እርግጥ በሂደቱ ላይ ድርድር ከጀመሩት በሃገር አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ 22 ፓርቲዎች መሃከል፤ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መደረክ)፣ የመላው አማራ ህዝብ ድርጅት (መአህድ) እና ሰማያዊ ፓርቲ ራሳቸውን ከድርድሩ ውጭ አድርገዋል። የአንድ እርከን መራመድ የቻሉት የተቀሩት 19 የፖለቲካ ፓረቲዎች ናቸው።

እንግዲህ በሃገር አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱት 19 የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደዋናው ድርድር መሻገሪያ ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ይህ ተራርቀው በቆዩና አንዱ ሌላውን በጥርጣሬ ሲመለከት በነበሩ የሃገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሃከል የተደረሰ የመግባባት ጅምር በመድብለ ፓርቲ ሥርአት ግንባታ ሂደት ውስጥ እንደ ስኬት ሊታይ የሚችል ነው። ለረጅም ዓመታት ሲጠየቅ የቆየው በኢህአዴግና በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሃከል የሚደረግ ድርድር አንድ እርከን መራመድ እስከቻለበት ደረጃ ያለፈበትን ሂደት መለስ ብሎ ማስታወሱ ተገቢ ይመስለኛል።

ሲጠበቅ የኖረው በገዢው ፓርቲ ኢህአዴግና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሃከል የሚደረግ ድርድር ዘንድሮ እውን እንደሚሆን በተጨባጭ የታወቀው 5ኛው ዙር የመንግስት ሥልጣን ዘመን 2ኛው የሥራ ዓመት በተጀመረበት ወቅት ነበር። የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በዚህ ወቅት ለህዝብ ተወካዮችና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ባደረጉት ንግግር፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች መሃከል የሚደረግ ድርድር የዓመቱ አንዱ ክንውን መሆኑን አስታውቀው ነበር። ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ በንግግራቸው ያነሱት ሃሳብ በተደጋጋሚ የተጠቀሰ ቢሆንም ድርድሩን ለማካሄድ መንግስት እና/ወይም ገዢው ፓርቲ የነበራቸውን ፍላጎትና ተነሳሽነት ስለሚያሳይ፣ እንዲሁም ድርድሩ የድንገተኛ ውሳኔ ውጤት አለመሆኑን ስለሚያረጋግጥ ልጠቅሰው ወድጃለሁ።

ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ በፖለቲካ ፓርቲዎች መሃከል የሚደረገውን ውይይት አስመልክተው ባደረጉት ንግግር … የአገራችንን ዴሞክራሲ ለማጐልበት የተለየ እንቅስቃሴ ይደረጋል። ከዚህ አኳያ   አንዱ ቀዳሚ ስራ በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል በሚደረግ ድርድር የምርጫ ህጋችንን የማሻሻል ጉዳይ ይሆናል። አገራችን የምትመራበት የምርጫ ህግ በብዙ አገሮች እንዳለ የሚሰራበት ቢሆንም፣ ከእኛ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ድምፅ ሊሰማ የሚችልበትን አስተማማኝ ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ ከመገኘቱ ጋር የህግ ማሻሻያ ይደረጋል። ስለሆነም፤ የምርጫ ህጋችን የአብላጫ ድምፅና የተመጣጣኝ ውክልና ስርዓቶችን በትክክለኛ ሚዛን ያጣመረና የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ድምፅ የሚሰማባቸው ምክር ቤቶች እንዲኖሩን ለማድረግ በሚያስችል ሁኔታ እንዲስተካከል ይደረጋል። ይህም በፓርቲዎች መካከል በሚካሄድ የሰጥቶ መቀበል መርህ የሚገዛና አገራዊ ጥቅማችንን ማዕከል ባደረገ ግልፅነትን የተላበሰ የድርድር ሂደት የሚፈፀም ይሆናል ብለው ነብር።

በዚህ መሰረት ጥር 10፣ 2009 ዓ/ም ኢህአዴግን ጨምሮ በሃገር አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ 22 የፖለቲካ ፓርቲዎች ለድርድር በጠረጴዛ ዙሪያ ታደሙ። ከዚህ ግዜ ጀመሮ በድርድሩ አስፈላጊነት፣ ዓላማ እንዲሁም ድርድሩ በምን አኳኋን ይመራ በሚለው ጉዳይ ላይ ለ8 ጊዜ ያህል ተሰብስበው ተወያይተዋል። በእነዚህ ስብሰባዎች በየአጀንዳዎቹ የተለያየ አቋም እያቀረቡና አየተከራከሩ ስምምነት ላይ በመድረስ ነበር የተጓዙት።

በመጀመሪያው ስብሰባ ላይ ከኢህአዴግ ጋር መደራደርና መከራከር ያስፈልጋል ወይ? በሚለው ጉዳይ ላይ ነበር የተወያዩት። በዚህ ውይይት በሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ከኢህአዴግ ጋር መደራደር አስፈላጊ መሆኑ ላይ ተስማምተዋል። አያይዘው በድርድሩ ዓላማ ላይ ተወያየተው ስምምነት ላይ ደርሰዋል። የድርድሩ ዓላማ በሚል ስምምነት ላይ ከተደረሰባቸው መሃከል፤ ማሻሻያ የሚሹ ህጎችን ማሻሻል፣ ፓርቲዎች የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን በማጠናከር ለሃገሪቱ ሰላም፣ ዴሞክራሲና እድገት የሚኖራቸውን አስተዋፅኦ ማዳበር፣ የኢትዮጵያ ህዝብ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያቀርቡትን አማራጭ ሀሳብ ተረድቶ በግንዛቤ ላይ ተመስርቶ መወሰን የሚያስችለው ሁኔታ እንዲኖር ማድረግ፣ ለብሄራዊ መግባባት አስተዋፅኦ ማበርከት፣ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት የመድበለ ፓርቲ ስርዓቱን ማጎልበት የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው።

በመቀጠል በድርድሩ ሂደት ላይ የሚወያዩት የፖለቲካ ፓርቲዎች የድርድሩ የሚመራበትን የሥነስርአት ደንብ ለማቅረብ ተስማሙ። በዚህ መነሻ በአቋም የሚመሳሰሉ ፓርቲዎች ተቧድነው በአጠቃላይ በድርድሩ ላይ የሚሳተፉት ፓርቲዎች ኢህአዴግን ጨመሮ አራት ቡድን መሰረቱ። እነዚህም ኢህአዴግ፤ የአራት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት የሆነው መደረክ፤ ከኢህአዴግ፣ መኢአድና ኢዴፓ ውጭ ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክረ ቤት አባላት ስብስብ እንዲሁም ስድስት ፓርቲዎችን የተካተቱበት ኢዴፓ፣ ኢራፓ፣ መኢአድ፣ መኢዴፓ፣ ኢብአፓ እና ሰማያዊ ፓረቲን የያዘወ ስብድብ ነበሩ።

በዚህ አኳኋን በአራት የተቧደኑት የድርድሩ ተሳታፊ ፓርቲዎች የየራሳቸውን የድርድር ሥነስርአት ደንብ አቅርበው በአስራ ሁለት ጉዳዮች ላይ ሰፊ ወይይትና ክርክር ሲያካሂዱ ቆይተዋል። እነዚህ ጉዳዮች ከላይ የተመለከትናቸውን የድርድሩን ዓላማዎች ጨምሮ፣ የድርድርና የክርክር ተሳታፊ ፓርቲዎች፣ የድርድርና የክርክር አባል ፓርቲዎችና የፓርቲ ተወካዮች ብዛት፣ ምልዓተ ጉባዔና ውሳኔ አሰጣጥ፣ የድርድር አጀንዳ አቀራረብና የማቅረቢያ የጊዜ ገደብ፣ የድርድር አጀንዳ አወሳሰንና አጀማመር፣ የሚዲያ አጠቃቀም፣ የንግግርና የተናጋሪዎች አሰያየም፣ የድርድርና የክርክር አመራር፣ ታዛቢዎችና የሚኖራቸው ሚና፣ ሥነ ምግባርና ዲሲፕሊን፣ ድርድሮች የሚካሄዱበትን ቦታ የሚመለከቱ ናቸው።

በድርድሩ ሂደት የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ከእነዚህ ጉዳዮች መሃከል በአብዛኛዎቹ ላይ ስምምነት ላይ መድረስ ቢችሉም፣ በተለይ ሁለት ጉዳዮች ውይይቱን አንገዳግደውታል። ከእነዚህ ጉዳዮች መሃከል ቀዳሚው፣ ድርድሩ በተናጠል ወይም በተወካይ አልያም አንድ ለአንድ ይካሄድ የሚለው ሲሆን ሁለተኛው አደራዳሪ አካልን የሚመለከት ነው።

በተለይ መድረክ ድርድሩ ላይ ሌሎቹን ፓርቲዎች በመወከል አውራ ተደራዳሪ ልሁን ይህ ካልሆነ ድርደሩን ከኢህአዴግ ጋር ብቻዬን ላድርግ የሚል አቋም ይዞ ቀረበ። ሃያ ሁለቱም ፓርቲዎች በተገኙበት መደራደርን በፍጹም እንደማይቀበለውም አሳወቀ። መድረክ የድርድር ቅድመ ሁኔታም አስቀምጦ ነበር። በወንጀል ተጠርጣሪነት  በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙ የድርጅቱ አመራሮች ይፈቱ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የነሳ የሚሉ ቅድመ ሁኔታዎችን ነበር ያስቀመጠው። ከዚህ በተጨማሪ ሶስተኛ አደራዳሪ ወገን ያስፈልጋል የሚል አቋም ይዞ ነበር።

በድርድሩ ላይ የሚሳተፉት ፓርቲዎች በሙሉ የመድረክን የአወራ ተደራዳሪነት ጥያቄ ውድቅ አደረጉት። ሶሰተኛ አደራዳሪ ወገን ይኑር የሚለው ላይ ግን ከኢህአዴግ በስተቀር ሁሉም አንድ አይነት አቋም ያዙ። የኢህአዴግ አቋም ድርደሩ በተሳታፊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይመራ ሶሰተኛ አደራዳሪ ወገን አያስፈልገንም የሚል ነበር። የመላው ኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲም ሶስተኛ ወገን አደራዳሪ አያስፈልግም ከሚለው የኢህአዴግ አቋም ጋር የሚመሳሰል አቋም ነበር የያዘው። ፓርቲዎቹ በዚህ ጉዳይ ላይ መሰማማት ስላልቻሉ በቀጠሮ ተለያዩ።

በቀጠሮው መሰረት 7ኛ ስብሰባቸውን ለማካሄድ ሲገናኙ አብዛኞቹን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት የያዘው ስብስብ ሶስተኛ አደራዳሪ ወገን ያስፈልጋል በሚል ይዞት የነበረውን አቋም አነሳ። ለዚህ የአቋም ለውጥ ያቀረበው ምክንያት፤ ሰላማዊ በሆነች ሀገር በሰላማዊ ፓርቲዎች መካከል የሚደረግ ድርድር፣ ሰላምን ባጡ ሀገራት እንደሚደረገው አይነት በሶስተኛ ወገን አማካኝነት ሊደረግ አይገባውም፤ ማንም ሰው ከፖለቲካ አስተሳሰብ ነፃ እና ገለልተኛ ይሆናል ብለን ስለማናስብ ገለልተኛ እና ነፃ አደራዳሪ የሚለውን አንቀበለውም፤ አደራዳሪው መድረክ ከመምራት ባሻገር ሌላ ሚና ስለማይኖረው አያስፈልገንም የሚል ነበር። ሌላው ሶስተኛ አደራዳሪ ወገን ያስፈልጋል የሚል አቋም የያዘው የስድስት ፓርቲዎች ስብስብ አባላት በጉዳዩ ላይ በየፓርቲያቸው መክረው አቋም ለመያዝ ቀጠሮ አስያዙ።

በቀጠሮው መሰረት በ8ኛ ስብሰባ ላይ ሲገናኙ ከሰማያዊ ፓርቲ በስተቀር የተቀሩት ያለሶስተኛ  አደራዳሪ ወገን በድርድሩ ለመቀጠል መስማማታቸውን አሳወቁ። ፓርቲዎቹ ድርደሩ በሶስተኛ አደራዳሪ ወገን ይካሄድ የሚለውን አቋማቸውን በልዩነት አስመዝግበው ነው በድርድሩ ለመቀጠል የተስማሙት። በዚህ ሁኔታ ያለሶሰተኛ አደራዳሪ ወገን መደራደር ላይ ከተሰማሙ በኋላ፣ ድርድሩን “ራሳችን በዙር እንምራው ወይስ ከመካከላችን ቋሚ የድርድር መሪዎች እንምረጥ” በሚል አጀንዳ ላይ ሰፊ ውይይት ተካሄደ። በመጨረሻም ከመካከላቸው ቋሚ የድርድር መሪዎች ለመምረጥ ተሰማምተዋል። በዚህ መሰረት ከተዳራዳሪ ፓርቲዎቹ መሃከል ድርድሩን በቋሚነት የሚመሩ ሶስት ሰዎች ለመምረጥ ከስምምነት ደርሰዋል። እነዚህ አደራዳሪዎች፣ ድርድሩን በበላይነት የመምራት፣ አጀንዳ የማስወሰን፣ ለተደራዳሪዎች ጥሪ የማስተላለፍ፣ ለፓርቲዎቹ የንግግር ዕድል የመስጠት፣ የድርድሩ ሥነስርዓት መከበሩን የማረጋገጥ ሥራዎች ያከናውናሉ። በድርድሩ ወቅት ለሚነሳ የሥነስርዓት ጥያቄ ቅድሚያ የመስጠትና በአደራዳሪነት ተግባራቸው ገለልተኛና የመጡበትን ፓርቲ ሳይወክሉ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸውም ተሰማምተዋል። በደንቡ ከተሰጣቸው ሚና ውጪ ገለልተኛ ሳይሆኑ ቢቀሩ፣ ተደራዳሪ ፓርቲዎቹ በጉዳዩ ላይ ተወያይተው እንዲቀየሩ ያደርጋሉ።

ፓርቲዎቹ ከዚህ በተጨማሪ  በድርድሩ የሃገር ውስጥና የውጭ ታዛቢዎች እንዲሳተፉም ተስማምተዋል። በስምመነታቸው መሰረት ታዛቢዎቹ በድርድር ወቅት ከመታዘብ ውጪ ሃሳብ መስጠት አይችሉም። ይሁን እንጂ አንድ የድርድር አጀንዳ ካለቀ በኋላ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አስተያየት መስጠት ይችላሉ። ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ሆነው የሌላ አገር ዜግነት ያላቸው ሰዎች፣ የሚኖሩበት ሃገር ወይም የሚሰሩበት ተቋም ካልወከላቸው በስተቀር በሚካሄደው ድርድር ላይ በታዛቢነት መቅረብ እንደማይችሉም ተስማምተዋል። የታዛቢዎች ቁጥር በተደራዳሪ ፓርቲዎች እንዲወሰን ተስማምተዋል።

በድርድሩ ወቅት ተደራዳሪ ፓርቲዎች ሊከተሉት የሚገባ ሥነ ምግባር ላይም ተስማምተዋል። በዚሁ መሰረት በድርድሩ ወቅት ያለፍቃድ መናገርና ፍቃድ ሳያገኙ ሌላ ተደራዳሪ የሚያደርገውን ንግግር ማቋረጥ አይቻልም፤ ተደራዳሪ ፓርቲዎች በድርድሩ ሂደት አንድ አጀንዳ ሳያበቃ በጉዳዩ ላይ መግለጫ መስጠት አይችሉም። ይሁን እንጂ በጋራ ውሳኔ ላይ በተደረሰበት የድርድር አጀንዳ ላይ ተደራዳሪ ፓርቲዎች በጋራም በግልም መግለጫ መስጠት ይችላሉ። የድርድር ውሎን በተመለከተም ተደራዳሪዎች በተስማሙበት መሰረት በድርድር መሪዎች በኩል መግለጫ የሚሰጡበት እድል አለ። ድርድሩን አቋርጦ የወጣ ተደራዳሪ ፓርቲ በፅሑፍ ይቅርታ ጠይቆ በተደራዳሪ ፓርቲዎች ተቀባይነት ካላገኘ ወደድርድሩ አይመለስም።

ፓርቲዎቹ ድርድሩ በዝግ እንዲካሄድ፣ ከድርድሩ በኋላ ኮሚኒኬ ወጥቶ ለመገናኛ ብዙሃን እንዲሰጥ ለማድረግ ተስማምተዋል። ድርድሩ በመርህ ደረጃ ዝግ ቢሆንም ተደራዳሪ ፓርቲዎች ተስማምተው ለመገናኛ ብዙሃን ክፍት ለማድረግ የሚችሉበት ዕድል እንዲኖር ተስማምተዋል።

ፓርቲዎቹ ድርድሩ የሚካሄድበትንም ቦታ በተመለከተ ውይይት አካሂደዋል።  ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት ወይም በኢሲኤ አደራሽ ይካሄድ የሚለው ከቀረቡት አማራጮች መሃከል አንዱ ነበር። ይሁን እንጂ ሀሳቡ በአብዛኞቹ ፓርቲዎች ተቀባይነት ባለማግኘቱ  ድርድሩ  የህዝቦች የሉአላዊ ስልጣን መገለጫ በሆነው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲካሄድ መግባባት ላይ ደርሰዋል።

በመጨረሻም በስምንት ስብሰባዎች የተስማሙባቸውን ጉዳዮች የያዘ የአገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች የድርድር አሰራር ደንብ የሚል ስያሜ ያለው ሰነድ አጽድቀዋል።

እንግዲህ በሃገር አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሃገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ ለማስፋትና የሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ድምጾች በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመጣጣኝ ውክልና ማግኘት የሚችሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር ወደሚያስችል ድርድር ለመግባት አንድ እርከን ተራምደዋል። በስምንት ውይይትና ድርድር የተደረሰበት ይህ የመጀመሪያው እርከን በራሱ ጤናማ የመድብለ ፓርቲ ሥርአት ለመገንባት አስተዋጽኦ ከማበርከቱ በተጨማሪ ቀጣይ ድርድሮች ፍሬያማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያመለክታል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy