Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“የማይታየው እጅ”!

0 338

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“የማይታየው እጅ”!

ስሜነህ

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 43 (2) ላይ የዜጎችን በተናጠልም ሆነ በጋራ ያላቸውን የመሳተፍ መብት በተመለከተ ‹‹ዜጎች በብሔራዊ ልማት የመሳተፍ በተለይም አባል የሆኑበትን ማኅበረሰብ የሚመለከቱ ፖሊሲዎች እና ፕሮጀክቶች ላይ ሀሳባቸውን እንዲሰጡ የመጠየቅ መብት አላቸው፤›› በማለት ይደነግጋል፡፡ ይህ ደግሞ የህልውናችን ጉዳይ ነው ከምንለው የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ጋር በቀጥታ የተገናኘ ነው። ጉዳዩ ጥልቀት ያለው ተሃድሶ ከተደረገ እና እየተደረገ በሚገኝበት በዚህም ሰዓት ላይ መሻሻል ያላሳየ ስለመሆኑም ብዙዎች ማሳያዎች ጠቅሰው እየሞገቱ ነው ። በእርግጥም ሙገታቸው ትክክል ይመስላል።  

የፖሊሲ ጥናት እና ምርምር ማዕከል ‹‹መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አንፃር የሕዝብ ተሳትፎ ማነቆዎች፣ መንስዔዎች እና የመፍትሔ ሀሳቦች›› በሚል ርዕስ ለአንድ ዓመት ያህል ሲያስጠና የቆየውን የጥናት ውጤት ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በሳሮ ማሪያ ሆቴል ይፋ ባደረገበት ጊዜ የተገለጸው መረጃ ያመላከተውም ይህንኑ መሆኑ አንዱ ማረጋገጫ ነው። ይህ መጣጥፍም  ከዚህ ጥናት ተነስቶ የችግሩን ስፋት እና ጥልቀት ከተያያዝነው የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴዎች አንጻር የሚፈትሽ እና መሻሻል ስለማሳየቱ ምክንያቶች ናቸው የተባሉ ግኝቶችን በማጣቀስ መፍትሔዎችን ለማመላከት በመሞከር እዛው ሳለ የሕዝብ ተሳትፎ አንደኛው አማራጭ እና ማሳያ ይሆናል።

በአንድ አገር የዴሞክራሲ ሥርዓት ስለመዳበሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ስለመፈታታቸው እና ጠንካራ የሆነ ለውጥ ስለመመዝገቡ ከሚመዘንባቸው መሥፈርቶች ውስጥ አንዱ የሕዝብ ተሳትፎ ያለበት ደረጃ ነው፡፡ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የበለፀጉ አገሮች ከሚታወቁባቸው ባህሪያት አንዱ እና መሠረታዊ ጉዳይ ተደርጎ የሚወሰደው፣ ውጤታማ የሆነ የሕዝብ ተሳትፎ መኖር እንደሆነ ብዙዎቹ ይስማማሉ፡፡ በዋናነት የሕዝብ ተሳትፎ የሚረጋገጥባቸው በተቋማት ደረጃ የሚታይ ሲሆን፤ ወሳኝ ሚና ከሚጫወቱት መካከልም የሕዝብ ምክር ቤቶች፣ የብዙኃን እና የሙያ ማኅበራት እና ሚዲያ ይገኙበታል፡፡

በዚህ አግባብ ስለመልካም አስተዳደር የሕዝብ ተሳትፎ ማጠየቂያ የሚሆኑትም በዋናነት እነዚሁ ተቋማት ይሆናሉ ማለት ነው። ሕዝብ ይወክሉኛል፣ የእኔን ችግር፣ ሀሳብ እና አስተያየት እንደኔ ሆነው ለመንግሥት አካላት ያቀርቡልኛል፣ አስፈጻሚው እኔን ማገልገሉን ይከታተሉልኛል፣ ይቆጣጠሩልኛል የሚላቸው የሕዝብ ምክር ቤቶች የሕዝብ እንደራሴነታቸውን በትክክል ሲወጡ፣ የሕዝብ ተሳትፎን በሚያረጋግጥ ሁኔታ መሥራት ሲችሉ እና አስፈጻሚውን በሙሉ ዓቅሙና በሕገ መንግሥቱ መሠረት መቆጣጠር መቻል አለመቻላቸው  ዋነኛው እና መሠረታዊው ማጠየቂያ ነው።  

የብዙኃን እና የሙያ ማኅበራትን ጨምሮ ሚዲያው በጀርባቸው ያለውን በርካታ አባላቸውን ወክለው የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ እና በመልካም አስተዳደር ረገድ ያላቸውን ንቁ ተሳትፎ በማሳደግ መንግሥት እና ሕዝብን የማገናኘት ሚናቸውን መጫወት መቻል እና አለመቻላቸውም ሌላኛው የሕዝብ ተሳትፎ ማረጋገጫ እና ማጠየቂያ ነው፡፡

በነዚሁ የማጠየቂያ መንገዶች መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አኳያ ለአንድ ዓመት ያጠናውን ጥናት ይፋ ባደረገው የፖሊሲ ጥናት ማዕከል ሠነድ ላይ ቁልፍ ሆነው ከወጡ የአመራር ችግሮች ውስጥ የሕዝብ ተሳትፎ አንዱ ሆኖ ወጥቷል።ይህ ችግር ደግሞ በራሱ ከሚያመጣው ችግር በበለጠ ለሌሎች ችግሮች መንስዔ ከመሆን ባሻገር የዴሞክራሲ ባህል እንዳያድግ፣ መልካም አስተዳደር እንዳይሰፍን እና ሕዝብ ባለው ሁኔታ እንዳይረካ በማድረግ በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት እንዲሻክር ያደርጋል በማለትም የችግሩን ግዝፈት ይገልጻል፡፡

በተለያዩ የሕዝብ አደረጃጀቶች፣ በምክር ቤቶች እና በሕዝብ መገናኛ ብዙኃን ያሉ እጥረቶች እና ውስንነቶች የሕዝብን ተሳትፎ ገትተውት እንደቆዩ የሚገልጸው ጥናት፤ በሚሠሩ ሥራዎች ውስጥ የሕዝብ ተሳትፎ ከሌለ ዴሞክራሲ ሊጎለብት እንደማይችል እና ዜጎችም መብቶቻቸውን መጠየቅ የማይችሉ መሆኑን ስለሆነም ሞጋች እና ንቁ ማኅበረሰብ መፍጠር ስለሚያስቸግር ጉዳዩ አሳሳቢ መሆኑን ያትታል፡፡

ይህ ጥናት ትኩረት ያደረገው በከተሞች እና በአራት የገጠር ወረዳዎች ሲሆን፣ አራት ክልሎች እና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ተካትተዋል፡፡ በእነዚህ ክልሎች የሚገኙ የብዙኃን ማኅበራት፣ የሕዝብ ምክር ቤቶች እና የብዙኃን መገናኛ ድርጅቶች የጥናቱ የትኩረት መስኮች ሆነው ቀርበዋል፡፡

በዚህ ጥናት ግኝት ተደርጎ የተወሰደው የመጀመሪያው ጉዳይ ‹‹የሕዝብን ዓቅም፣ ሚና እና ኃይል በሚገባ አለመረዳት›› የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ችግር ሕዝብ በሚመለከተው ጉዳይ ላይ እንዳይሳተፍ፣ ሀሳብ እና አስተያየቱን እንዳይሰጥ በማድረግ በሕዝብ ተሳትፎ ሊገኝ ይችል የነበረውን ያህል ውጤት እንዳይመጣ ተግዳሮት እንደሆነ ተብራርቷል፡፡ በዚህም የአመለካከት እና የግንዛቤ ችግር የሕዝብን ዓቅም፣ ሚና እና ኃይል በሚገባ ካለመረዳት ጋር ተያይዞ የሚነሳ ቁልፍ ችግር መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ሕዝብን ከማሳተፍ ጋር ተያይዞ የታየው የአመለካከት እና የግንዛቤ ችግር በሦስት አካላት (በአስፈጻሚው፣ የሕዝብ ተሳትፎ በሚረጋገጥባቸው ተቋማት እና በሕዝቡ) ዘንድ መታየቱን የሚገልጸው ጥናት ከእነዚህ ከሦስቱ አካላት የአመለካከት እና የግንዛቤ ችግር ጎልቶ የታየው በአስፈጻሚው ላይ እንደሆነ ማረጋገጡን ይጠቅሳል፡፡

ከምክር ቤቶች ጋር ተያይዞ በአስፈጻሚዎች የአመለካከት እና የግንዛቤ ችግሮች በተለያየ ገጽታ ታይተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ምክር ቤቱ እንዲሰበሰብ አለመፈለግ፣ የሕዝብ ተወካዮች የመረጣቸውን ሕዝብ ለማወያየት ሲሄዱ የተለያዩ ምክንያቶችን በመፍጠር እና እንደ ሥጋት በማየት ሕዝቡ እንዲሰበሰብ ሁኔታዎችን አለማመቻቸት፣ በተለይ አዲስ አመራር አካላት የምክር ቤቱን ተግባር እና ኃላፊነት አሳንሶ ማየት፣ አስፈጻሚው አካላት ዘንድ ምክር ቤቱ ይቆጣጠረኛል እና የበላይ ነው የሚል አስተሳሰብ አለመኖር፣ ምክር ቤቱ ከተጠናከረ ይሞግተኛል፣ ጫና ያበዛብኛል ብሎ መፍራት እና እንዳይጠናከር መፈለግ፣ ምክር ቤቶች ሥራ የላቸውም የሚል የተሳሳተ አመለካከት መኖር፣ የምክር ቤቱን ሥራ እንደ ደጋፊ ሳይሆን እንደ ስህተት ፈላጊ አድርጎ የማየት የአመለካከት ችግር እና ጠንካራ የሕዝብ ጥቅም እና ፍላጎት ወክለው አስፈጻሚ አካሉን የሚሞግቱ ወይም የሚተቹ የምክር ቤት አመራሮች እና አባላት ሲገኙ የሕዝብ ሥልጣን ውክልና እንዳላቸው ያለማመን፣ በምክር ቤቱ የሚሰጡ አስተያየቶችን ምክር ቤቱ አስፈጻሚውን ለመጉዳት እና ለማጋለጥ እንዳደረገው አድርጎ መውሰድ እና ጠንካራ አቋም ይዞ ሲተች ምክር ቤቱ ‹‹ሊያጠፉን ነው›› የሚል ጩኸት እንደሚበረታ፣ ምክር ቤቱን እንደ አጋዥ ቆጥሮ ተገቢ ሚናውን እንዲጫወቱ ባለመደረጉ የተነሳ የሕዝብ ውክልናን በአግባቡ እንዳይወጣና በዚያውም የሕዝብን ተሳትፎ ውጤታማ እንዳይሆን እንዳደረገው በጥናቱ ተገልጿል፡፡

አስፈጻሚው በብዙኃን እና በሙያ ማኅበራት ላይ ያለው የአመለካከት እና የግንዛቤ ችግርን በተመለከተ አስፈጻሚው ማኅበራት የሕዝብ ተሳትፎን ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና የሚጫወቱ አካላት እንደሆኑ አለመቁጠር እና ማኅበራቱን የሚመለከቱ ፖሊሲዎች እና መመርያዎች ሲወጡ ሥርዓት ባለው ሁኔታ አሳትፈው አስተያየታቸውን አለመሰብሰብ፣ አንዳንዴም መመርያዎች ከወጡ በኋላ እንዲያውቁት እንደማይደረግም ተገልጿል፡፡ ‹‹መንግሥት ሁሌ የራሱን ወገን ጉዳይ እና ፍላጎት ብቻ ይዞ የሚሠራ ከሆነ አስቸጋሪ ይሆናል፤›› በማለትም የሚያስከትለውን ችግር ጥናቱ አብራርቷል፡፡

አስፈጻሚው በሚዲያው ላይ (በመንግሥት ሚዲያ) ላይ ያለው የአመለካከት እና የግንዛቤ ችግር በተመለከተ ከሚዲያው የሚነሱ ጥያቄዎችን በትክክል ተረድቶ ምላሽ አለመስጠት፣ ሚዲያው የመንግሥት ብቻ አንዳንዴም የኢሕአዴግ ነው ብሎ ማሰብ፣ በሚዲያ የሚዘገበው ጉዳይ ከአስፈጻሚ አካላት ፍላጎት ውጪ ከሆነም ‹‹የእኛ ሚዲያ አይደለም እንዴ?›› ማለት እና የሕዝብ ድምፅ ጭምር እንዳልሆነ ማሰብ፣ ሥኬታቸው ብቻ እንጂ ድክመታቸው እንዲዘገብ አለመፈለግ፣ ወዘተ. የሚሉ ችግሮች በአስፈጻሚው ላይ እንደተስተዋሉ የጥናቱ ግኝት አብራርቷል፡፡

መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የሕዝብ ተሳትፎ የማይተካ ሚና ያለው ጉዳይ መሆኑ ከላይ የተመለከተ እና ችግሩ ጎልቶ ታይቶባቸዋል ሲል የሚጠቅሳቸው አስፈጻሚዎችም ዘወትር በየመድረኩ ላይ የሚያነበንቡት መሆኑ እዚህ ጋር ልብ እንዲባል ያስፈልጋል፡፡ ልብ ከተባለ ዘንዳ ታዲያ ምክር ቤቶች ይህን እና ከላይ የተመለከቱ ሚናዎቹን በአግባቡ እንዳይጫወት ከሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች አንዱ እና ዋነኛው እነዚሁ አነብናቢ አስፈጻሚ አካሎች መሆናቸው የችግሩን ጥልቀት የሚያሳይ ይሆናል።  

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ከሕዝብ ምክር ቤቶች አንጻር ጥናቱ ያላያቸው እና በተለይ በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች እና የፌዴራል ምክር ቤትን ጨምሮ በሁለቱም የከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች ተወካይ ሆነው የሚቀርቡ አባላትን የውክልና አግባብ የተመለከተው ዋነኛው ችግር እንደሆነ ብዙዎች ይገልጻሉ። ይኸውም አዲስ አበባን እና ድሬ ዳዋን የሚወክሉ አባላት በቀጥታ በከተሞቹ ላይ ተወልደው አድገው እና ተምረው ስለከተሞቻቸው ችግር እና የሕዝቡን መሠረታዊ ችግሮች የሚያውቁ የየብሔራዊ ድርጅቶቹ አባላት ሳይሆኑ፤ ከክልል የመጡ እና ሁለት እና ከዛ በላይ ለጥቂት ዓመታት በከተሞቹ ላይ የኖሩ የሕዝቡን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የአኗኗር ዘይቤ የማያውቁ፤ ከተማውን ቀርቶ ስለጎረቤታቸው የማያውቁ በዕድር እና መሰል አደረጃጀቶች ተሣትፎ የሌላቸው የአፓርታማ ነዋሪዎች መሆናቸው ከላይ ስለተመለከተው የሕዝብ ተሣትፎ ሊታይ የሚገባው ነው። ከልጅነት እስከ ዕውቀት በአንደኛው ክልል አሳልፎ በሥራ እና በሹመት ምክንያት አዲስ አበባም ይሁን ድሬ ዳዋ በአስፈጻሚነት ወይም በፈጻሚ ሥራ ወይም ሹመት ቢመጣ ብዙም ላይቸግር ይችላል። ችግር የሚሆነው እንበልና ከልጅነት እስከ ዕውቀት ወለጋም እንበለው ባህር ዳር ወላይታም ይሁን መቀሌ ላይ ኖሮ አንደኛውን የአዲስ አበባ ክፍለ ከተማ ወክሎ የከተማው እና የፌዴ ራሉ ምክር ቤት አባል ሲሆን ነው። የወከለው ክፍለ ከተማ እና ወረዳ ላይ ብቅ እንዲል እና በአጋጣሚም እንኳ የወከለውን ማኅበረሰብ ድምጽ ሊሰማ የሚያስችለው ቢያንስ ተወካዩ በወከለው መንደር ለመምጣት የሚያስገድደው ምክንያት ሲኖረው ብቻ ነው።

ዕድር ኖሮት ለቅሶ የማይመጣ ከሆነ ፤ ቤተሰብ ኖሮት ቢያንስ ለዓመት በዓል የወከለው መንደር ለመምጣት የማይችል ከሆነ የወከለውን ሕዝብ ሳይሆን፤ በምክር ቤቱ ላይ የሚያንጸባርቀው ለመሄድ ምክንያቶች ባሉት የትውልድ ቀዬው ላይ የሚገኙ እና ሌላ ተወካይ ያላቸውን ማኅበረሰቦች ነው። ስለሆነም ድርጅቱም ሆነ ግንባሩን የፈጠሩት ብሔራዊ ድርጅቶች ከተዋጽኦ አኳያ በከተሞቹ ላይ ጥርሳቸውን የነቀሉ እና የማኅበረሰቡን ችግር የሚረዱ ይልቁንም ከላይ የተመለከቱ ንቅናቄዎችን በቀላሉ መፍጠር የሚችሉ አባላት ሳያጣ ከላይ የተመለከተው ዓይነት የውክል እና አግባብ መከተሉ ምናልባትም ማዕከሉ ብጥናቱ ከጠቀሳቸው ከላይ የተመለከቱ ችግሮችም በላይ መሆኑን አጢኖ ማስተካከል ያስፈልጋል።

ወደ ማዕከሉ ጥናት ስንመለስ የምክር ቤቶች በተፅዕኖ ሥር መውደቅ የሚለውም ግኝት ትኩረት የሚያሻው ይሆናል፡፡ ከምክር ቤቶች የሥራ ባህሪይ እና ተልዕኮ አኳያ በአስፈጻሚው ተፅዕኖ ሥር መውደቅ ጋር ተያይዞ የሚነሳው የሥራ መደበላለቅ፣ በሙስና እንዲተሳፉ በር መክፈቱን እና ወደ ምክር ቤት የሚመጡ ቅሬታዎችን እና አቤቱታዎችን በቀላሉ ለመፍታት አዳጋች መሆኑን የጥናቱ ውጤት አመላክቷል፡፡ በተፅዕኖ ሥር መውደቅ በብዙኃን እና በሙያ ማኅበራትም አካባቢ የሚታይ ችግር እንደሆነ ጥናቱ አመላክቷል፡፡ የሚዲያ አመራሮች በአስፈጻሚ ጫና ስለሚደርስባቸው ሚዲያው በራሱ አቋም እንዳይንቀሳቀስ እንዳደረገ፣ ሚዲያውን የሚጎትቱት አካላት በርካታ እንደሆኑ፣ እንደ ሚዲያ ተቋም ያለበት ትልቁ ፈተና ‹‹የማይታየው እጅ›› እንደሆነ እና ጣልቃ ገብነቱ እና ተፅዕኖው ፊት ለፊት እና በድብቅ እንደሚደረግ ጥናቱ ይፋ አድርጓል፡፡

የሕዝብ ተሳትፎ የሚረጋገጥባቸው ተቋማትን የሚያጋጥመው ሌላው ችግር የማስፈጸም ዓቅም ክፍተት እንደሆነ ጥናቱ ያሳያል፡፡ ስለሕዝብ ውክልና ግንዛቤ የሌላቸው እና በምክር ቤት አባልነት ለመወዳደር መመዝገባቸውን እና መመረጣቸውን የማያውቁ የዓቅም ውስንነት ያለባቸው የምክር ቤት አባላት መኖር አንዱ ችግር መሆኑን የተመለከተው የጥናቱ ግኝት ያለምንም ጥናት በተጨባጭ የሚታይ እውነታ ነውና በቶሎ ሊገቱ ከሚገባቸው ጉዳዮች መካከል ዋነኛ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል፡፡

ስለመልካም አስተዳደር ማነቆዎች ጥናቱ ይፋ ያደረጋቸው በርካታ ችግሮች ቢሆኑም ዋነኛ ማጠየቂያው እና ማጠንጠኛው  ከሆነው የሕዝብ ተሳትፎ አንጻር ግን ከላይ የተመለከቱት ዋነኞቹ ናቸው። ስለሆነም ከነዚህ አደረጃጀቶች ሰፈር የማይታየውን እጅ ማንሳት አልያም ቆርጦ መጣል የህልውናችን ጉዳይ ስለሆነው መልካም አስተዳደር እና የጥልቅ ተሃድሶው ቁልፍ ጉዳይ ስለሆነው ዴሞክራሲን የማጥለቅ መሠረታዊ ጉዳይ ይሆናል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy