Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሰው ወርቅ አያደምቅ

0 666

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሰው ወርቅ አያደምቅ

ብ. ነጋሽ

ሰዎች በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚዊና ፖለቲካዊ ቀወሶች መክንያት ከሚኖሩበት አካባቢ ወይም ሃገር ወደማያውቁት አካባቢ ወይም ሃገር ለመሰደድ የሚገደዱበት ሁኔታ የተለመደ ነው። ድርቅ የሚያስከትለው ተጽእኖ፣ ስራ አጥነት፣ የተሻለ ህይወት ይገጥመኛል የሚል ተስፋ ወዘተ ሰዎችን ለስደት የሚዳርርጉ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ናቸው። በማህበረሰብ ውስጥ የሚኖር መገለልና አድልዎ፣ የቤተሰብ መፍረስ፣ ወንጀል ሰዎች የመኖሪያ አካባቢያቸውን ለቀው እንዲሰደዱ ከሚያስገደዱ ማህበራዊ ሁኔታዎች መሃከል ተጠቃሽ ናቸው። ሰዎች በፍልሰት መልክ እንዲሰደዱ በማድረግ የሚታወቀው ፖለቲካዊ ሁኔታ ነው። የከፋ የሰብአዊ መብቶችና የዴሞክራሲያዊ ነጻነቶች ጥሰት፣ የህግ የበላይነት የሌለበት አምባገነናዊ ስርአት መኖር፣ ጦርነት . . . ሰዎች ሃገራቸውን ለቀው እነዲፈልሱ የሚያደርጉ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ናቸው።

አሁን ያለንበት ዘመን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ዓለም ከፍተኛውን የስደተኞች ቁጥር እያስተናገደች ያለችበት ወቅት ነው። ይህ የሆነው በተለይ በመካከለኛው ምስራቅ፤ ሶሪያ፣ ኢራቅና የመን የተፈጠረው የእርስ በርስ ግጭትና አይ ኤስ የተሰኘው እስላማዊ ቡድን የከፈተው የጂሃድ ጦርነት፣ በአፍጋኒስታን ከአስር ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ምእራባውያንና ምእራባውያን ያስቀመጡት መንግስት በአንድ በኩል ጣሊባን የተባለው ሃይል በሌላ በኩል የሚያካሂዱት ፍልሚያ፣ የሊቢያ መንግስት አለባ መሆን ያስከተለው የእርስ በርስ ግጭት፣ የቆየው የሶማሊያ ግጭትና የአለሸባብ እንቅስቃሴ፣ የደቡብ ሱዳን የእርስ በርስ ግጭት ዓለም ከሁለተኛ ዓለም ጦርነት ወዲህ ባልታየ ሁኔታ ፍልሰት ሊባል የሚችል የስደተኞች ቀውስ ገጥሟታል። ከእነዚህ አካባቢዎች በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች ወደምእራብ አውሮፓ ባህር ተሻገረው ይሰደዳሉ።

ከዚህ በተጨማሪ በኤርትራ ያለው አምባገነናዊ መንግስት በህዝቡ ላይ ባሳረፈው ፖለቲካዊ ጭቆናና የኢኮኖሚ ማሽቆልቆል ተስፋ የቆረጡ በርካታ ኤርትራውያን በየእለቱ በሁሉም የአቅጣጫዎች ሃገሪቱን ለቀው ይወጣሉ። ከአፍሪካ በባህር ወደምእራብ አወሮፓ ለመሻገር ከሚሞክሩት ስደተኞች መሃከል ኤርትራውያን ከፈተኛውን ቁጥር ይይዛሉ። በአሁኑ ጊዜ በየእለቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ወደኢትዮጵያ ይገባሉ።

የስደት ጉዳይ ኢትዮጵያውያንንም ይመለከታል። የኢትዮጵያውያን የሰደት ምክንያት ፖለቲካዊ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ ነው። አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ሰደተኞች ስራ ፈላጊዎች ናቸው። የተቀሩት ደግሞ ሃገር ውስጥ ከሚያገኙት የተሻለ ገቢ እናገኛለን በሚል ተስፋ የሚሰደዱ ናቸው። በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ የወጣቶች ስራአጥነት ችግር መኖሩ ባይካድም አጠቃላይ ሁኔታው ግን ከብዙዎቹ ከሳሃራ በታሽ ካሉ የአፍሪካ ሃገራት የተሻለ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። የኢትዮጵያ መንግስት ለወጣቶች ስራ አጥነት ችግር ልዩ ትኩረት በመስጠት ባለፉት አስር ዓመታት በተለያዩ የአነስተኛና ጥቃቅን የስራ ዘርፎች እስከአስር ሚሊየን ለሚደርሱ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠሩን መረጃዎች ያመለክታሉ። መንግስት ወጣቶችን በማደራጀት፣ ብድር በማቅረብ፣ የማምረቻና የመሸጫ እንዲሁም አገልግሎት መስጫ ዳሶችን ገንብቶ በመስጠት ወዘተ ስራፈጣሪ ወጣቶች የስራ እድል ማግኘት የሚችሉበትን ሁኔታ ፈጥሯል።

ይህም ሆኖ የሁሉንም ስራ አጥ ወጣቶች ፍላጎት ማርካት አልተቻለም። ኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር መጓደል ደግሞ መንግስት  ችግሩን ለማቃለል የሚደረገውን ጥረት በሚፈለገው ልክ ውጤታማ እንዳይሆን ያደረገበት ሁኔታ አለ። መንግስት ይህን መነሻ በማደረግ አዲስ የወጣቶች የእድገትና የለውጥ ፓኬጅ ነድፎ ተግባራዊ ማድረግ ጀመሯል። ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ የ10 ቢሊየን ብር ተንቀሳቃሽ ፈንድ መድቦ ፈንዱን ለሰራ ፈጣሪ ወጣቶች በብድር መስጠት መጀመሩም ይታወቃል። ከዚህ በተጨማሪ ሃገሪቱ ባለፉት አስራ አራት ዓመታት ያስመዘገበችው ተከታታይ ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት በሚሊየን ለሚቆጠሩ ዜጎች የስራ እድል እየፈጠረ መሆኑም የታወቃል። አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ የኢኮኖሚ እድገቱ ቀጣይነት ያለው መሆኑን ስለሚያመለክት በቀጣይነትም ሰፊ የስራ እድል ሊፈጠር እንደሚችል በእርግጠኝነት መናገር የሚያስችል ነው።

ከላይ በአጭሩ በግርድፉ የሰፈሩት አስረጂዎች በአጠቃላይ በሃገሪቱ ያለው ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ወጣቶች ተስፋ ቆርጠው ስራ ፍለጋ እንዲሰደዱ የሚያስገድድ ሁኔታ አለመኖሩን ያመለክታሉ። ይሁን እንጂ ስለየውጭ ሃገር ኑሮ ምንም ግንዛቤ የሌላቸው፣ ከተወለዱበት አካባቢ ገበያ ርቀው ሄደው የማያውቁ ለጋ የገጠር ወጣቶች ከሁሉም የሃገሪቱ አካባቢዎች ወደውጭ ሃገራት እየተሰደዱ ነው። የብዙዎቹ ወጣቶች የስደት መንስኤ ሃገር ውስጥ መኖር አለመቻል ወይም የመኖር ተሰፋ ማጣት አይደለም። ከዚህ ይልቅ በአጭር ጊዜ ሃብታም የመሆንና የተሻለ ህይወት የመኖር ጉጉት ነው። በየአካባቢው እንደአሸን የፈሉ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ደግሞ ይህን የወጣቶችና የወላጆቻቸውን ጉጉት በማይጨበጥ ተስፋ በመሙላት ያነሳሷቸዋል። ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎቹ የማይጨበጠውን ተስፋ የሚነዙት ለወጣቶቹ መልካም ከመመኘት ሳይሆን ህገወጥ ስራው የሚያስገኘውን ረብጣ ገንዘብ ለማፈስ ነው።  

በህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ከኢተዮጵያ የሚነሳው ስደተኛ በሶስት አቅጣጫ ነው የሚጓዘው። አንዱ በኬንያ በኩል ወደደቡበ አፍሪካ የሚደረግ ጉዞ ነው። ሁለተኛው የስደት መስመር በጀቡቲ ወደብ በኩል ባህር በመሻገር ወደመካከለኛው ምስራቅ የሚደረግ ሲሆን ሶስተኛው ወደሱዳን በመሻገር ሳህራ በረሃን በማቋረጥ በሊቢያ በኩል ባህር ተሻገሮ ወደምዕራብ አውሮፓ የሚደረግ ነው። ሶስቱም የሰደት ጉዞ መስመሮች ከፍተኛ የህይወት መጥፋት፣ አስከፊና ጸያፍ የሰብአዊ መብትና ክብር መደፈር፣ በህግ ቁጥጥር ስር የመዋል የመንገላታት፣ የትም ሳይደርሱ ከፍተኛ ገንዘብ አውጥቶ ወደሃገር ቤት የመመለስ ወዘተ ስጋቶች የተደቀኑበት ነው። ይህን ሁሉ ስቃይ አልፈው “ወደተስፋቸው” ሃገር የሚሻገሩትም የሚገጥማቸው ሁኔታ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎቹ የነገሯቸው ሃብት የሚዛቅበትና ተድላ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ተስፋ አስቆራጭ፣ በስቃይና እንግልት የተሞላ ህይወት ነው።

አብዛኞቹ ስደተኞች የሚገጥማቸው ከህግ ጥበቃና ከለላ ውጭ የሆነ ሰብአዊ ክብርን የሚነካ፣ የመኖር ዋስትና ያልተረጋገጠበት፣ የመስራትና የመንቀሳቀስ ገደብ ያለበት፣ ስራ ቢገኝ እንኳን የተለፋበትን ያህል ገቢ የማይገኝበት፣ . . . የኑሮ ሁኔታ ነው። ስደተኞቹ ከህግ ጥበቃና ከለላ ውጭ ስለሚኖሩ የኢትዮጵያ መንግስት ጥበቃ ሊያደርግላቸው የሚችልበት እድል እጅግ በጣም ጠባብ ነው። በለስ ቀንቷቸው ወደምዕራብ አውሮፓ የሚሻገሩትም ቢሆኑ፣ የሃገራቱ መንግስታት በኢትዮጵያ ለስደት የሚዳርግ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ እንደሌለ ስለሚያውቁ፣ የጥገኝነትና የስራ ፈቃድ የሚያገኙበት እድል እጅግ ጠባብ ነው።

የኢፌዴሪ መንግስት ከክልል መንግስታት ጋር በመቀናጀት በህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች አነሳሸነት የሚካሄደውን ህገወጥ ስደት ለመከላከል ጉዳይ ልዩ ትኩረት መስጠቱ ይታወቃል። ለዚሁ ዓላማ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ የክልል መንግስታት ተወካዮችን፣ የፌደራልና የክልል ፖሊስ ተጠሪዎን፣ የሃይማኖት ተቋማት  መሪዎችን ወዘተ ያቀፈ ሃገር አቀፍ ኮሚቴ ተቋቁማል። ይህም ሆኖ ግን ህገወጥ ስደትን መቆጣጣር አልተቻለም። በህገወጥ ስደት ህይወታቸውን  ያጡ ግለሰቦች ታሪክ፣ አስከፊ እንግልት የገጠማቸው ሰዎች ተሞክሮ በተጎጂዎቹ አንደበት ሲነገር የቆየ ቢሆንም፣ ከዚህ በይፋ ከሚነገረው እውነት ይልቅ ለሰው ህይወት ደንታ የሌላቸው ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎችና ደላሎች በየስርቻው የሚነዙት ባዶ ተስፋ የመደመጥ ጉልበት ያገኘበት ሁኔታ አለ።

የኢፌዴሪ መንግስት ዜጎች በህገመንግስት በተረጋገጠላቸው የመዘዋወር መብት መሰረት ወደፈለጉበት ሃገር የመሄድ መብታቸውን ያከብራል። ይህን መብት ሊከለክል አይችልም፤ በህገመንግስት የተረጋገጠ በመሆኑ። ይሁን እንጂ የዜጎቹ ሰብአዊ መብትና ክብር እንዳይጣስ ወደውጭ ሃገራት የሚደረግ ጉዞ ህጋዊ እንዲሆን ይፈልጋል። ይህ ደግሞ የህዝብ ውክልና ካለውና ለህዝብ ከቆመ መንግስት የሚጠበቅ ብቻ ሳይሆን መንግስት ይህን የማድረግ የህግም የሞራልም ግዴታ አለበት።

የኢፌዴሪ መንግስት ይህን መነሻ በማድረግ ወደውጭ ሃገራት በተለይ ወደመካከለኛው ምስራቅ ለስራ የሚሄጓዙ ዜጎችነ መብትና ነጻነት ለማሰከበር የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዷል። ከመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ጋር የሰራተኛ ጉዞ ስምምነቶን በማድረገ የህግ ማዕቀፍ ለማበጀትም ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። ወደመካከለኛ ምስራቅ ሃገራት የሚደረገውን የሰራተኛ ጉዞ ለግዜው በመገደብ የውጭ የስራ ስምሪት አዋጅ ማጽደቁም አንዱ ተጠቃሽ እርምጃ ነው። በህዝብ ሚዲያና በተለያዩ ሁነቶች ላይ የህገወጥ ስደትን አደገኝነት በተመለከተ ግንዛቤ ለመፍጠር የተደረገውም ጥረት የተፈለገውን ውጤት አሰገኝቷል ባይባልም እንደ በጎ እርምጃ ሊወሰድ ይችላል።

በህገወጥ መንገድ ወደሌሎች ሃገራት የዘለቁ ሰዎች በገቡበት ሃገር መንግስታት ተቀባይነት የላቸውም። የዚያ ሃገር ዜጎችም በበጎ አይመለከቷቸውም። ህገወጥ ስደተኞች በተጠጉበት ሃገር መንግስት፤ የሰላምና ጸጥታ ስጋት፣ የወንጀል መስፋፈት ስጋት እነደሆኑ አድርጎ ነው የሚመለከታቸው። የዜጎችን የስራ እድል የሚሻሙበት ሁኔታም በመኖሩ፣ የተጠጉበት ሃገር መንግስት ለዜጎቹ የስራ እድል ለመፍጠር የሚያወጣውን ፖሊሲ የሚያሰናክሉበት ሁኔታም አለ። ህገወጥ ስደተኞች በህገወጥነታቸው ምክንያት የቀረበላቸውን የስራ ቅጥር ክፍያ ከመቀበል ውጭ የመደራደር አቅም ሰለማይኖራቸው፣ የሃገራቱ ዜጎች የድርድር አቅም የሚያዳክሙበት ሁኔታ አለ። በመሆኑም ህገወጥ ስደተኞች በሚጠለሉባቸው ሃገራት ዜጎች በጥላቻ አይን የሚታዩበት ሁኔታ የተለመደ ነው። በደቡብ አፍሪካ ያለው ሁኔታ ለዚህ አስረጂነት ሊጠቀስ ይችላል።

ታዲያ፤ የሳኡዲ አረቢያ መንግስት ሰሞኑን በሃገሩ የሚኖሩ ህገወጦች በሙሉ በዘጠና ቀናት ውስጥ እንዲወጡ አውጇል። ይህ አዋጅ በህገወጥ መንገድ ከሃገር ወጥተው ወይም ህጋዊ ሆነው ለመንቀሳቀስ የተሰጣቸው ቀነ ገደብ ያለፈባቸውን ኢትዮጵያውያንም ይመለከታል። አዋጁ፣ በህገ ወጥ መንገድ ድንበር አቋርጠው የገቡ ስደተኞችን፣ ቋሚ ቦታ ሳይኖራቸው በመዘዋወር በህገ ወጥ መንገድ የሚሰሩ ስደተኞችን፣ የስራና የመኖሪያ ፍቃድ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ የውጭ ሃገራት ነዋሪዎችን፣ የስራ ፍቃድ ኖሯቸው ነገር ግን የመኖሪያ ፍቃድ መታወቂያ የሌላቸውን፣ ለኡምራና ሃጂ ተጉዘው በዚያው የቀሩ ወይም የቆይታ ጊዜያቸው ያለፈባቸውንና ያለ ሃጂ ፍቃድ የተጓዙ ምዕመናንን የሚመለከት ነው። ሃገሪቱን ለቀው እንዲወጡ የተቀመጠውን የጊዜ ገደብ በማያከብሩ ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ በአዋጁ ተደንግጓል። በጸጥታ ሃይሎች የቤት ለቤት አሰሳ ተካሂዶ፣ ህገ ወጥ ነዋሪዎቹ በህግ ይጠየቃሉ ይላል አዋጁ። ህገወጦቹን ያስጠጉና የሸሸጉ ያሀገሪቱ ዜጎችም ላይ የህግ እርምጃ እንደሚወሰድ አዋጁ ይገልጻል።

የሳኡዲ አረቢያ መንግስት በሃገሩ የሚኖሩ ህገወጥ የሌሎች ሃገር ዜጎችን ሲያባርር ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ከአራት ዓመት በፊትም ተመሳሳይ እርምጃ ወስዷል። በዚህ ጊዜ በርካታ ኢትዮጵያውያን የሃገሪቱ መንግስት ያወጣውን አዋጅ ችላ በማለት እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግስት ከተቀመጠው ቀነ ገደብ በፊት ወደሃገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ያመቻቸውን እድል ለመጠቀም ፍፈቃደኛ ባለመሆን ለክብረ ነክ የመብት ጥሰቶች መጋለጣቸውንና ከፍተኛ እንግልት እንደደረሰባቸው ይታወሳል። በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም አቀፍ የስደተኞች ማህበር ጋር በመተባበር በዘመቻ መልክ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዜጎቹን ወደሃገር ቤት እንዲመለሱ አድርጓል። በሃገር ቤት ያሉ ኢትዮጵያውያንም ወደሃገራቸው የገቡትን ወገኖቻቸውን ተቀብለው ጊዜያዊ ማረፊያ በመስጠት፣ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ በማቅረብና ወደየመጡበት በመሸኘት የሚደነቅ ተግባር አከናወነዋል። ይህ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው። ወደሃገር ቤት ተመላሾቹን በየአካባቢያቸው በዘላቂነት ለማቋቋምም ከፍተኛ ጠረት ተደርጓል። ሙሉ በሙሉ ማለት ባይቻልም በዘላቂነት የተቋቋሙ መኖራቸውም ይታወቃል።

ኡሁንም በሳኡዲ አረቢያ ህገወጥ ሆነው የሚኖሩ ዜጎች የተመሳሳይ አስከፊ ሁኔታ ጠርዝ ላይ ነው ያሉት። ስለዚህ ለክብረነክ የመብት ጥሰትና እንግልት ላለመጋለጥ በቀነ ገደቡ ወደሃገራቸው መመለስ አለባቸው። የኢፌዴሪ መንግስት በሳኡዲ አረቢያ የሚኖሩ ዜጎቹ የተቀመጠላቸውን የጊዜ ገደብ ሳይጠቀሙ ቀርተው በህግ ተጠያቂ እንዳየሆኑና ለእንግልት እንዳይዳረጉ እንቅስቃሴ ማድረግ የጀመረው አዋጁ በወጣ ማግስት ነው።

የኢፌዴሪ መንግስት  ህግ ተላልፈው በሳኡዲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሳይጉላሉ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ አዋጁ ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ በጀመረበት ዕለት ማግስት መጋቢት 21፣ 2009 ዓ/ም ከሳዑዲ ባለስልጣናት ጋር የሚመክርና አቅጠጫ የሚያስቀምጥ የልኡካን ቡድን ወደሳኡዲ አራቢያ ልኳል።  መንግስት ዜጎቹ ሳይጉላሉ ወደ ሃገራቸው በሰላም እንዲመለሱ ለማድረግ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እያስታወቀ ይገኛል። በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ኢትዮጵያውያኑን ወደሃገራቸው የሚመልስ አስተባባሪ ኮማንድ ፖስት ተቋቁማል። በሀገር አቀፍ ደረጃም እንዲሁ ስራውን የሚመራ ኮማንድ ፖስት ተደራጀቷል።

በሪያድ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲና ጅዳ ባለው ቆንጽላ ጽህፈት ቤት አማካኝነት ለዜጎች አስፈላጊውን መረጃ በማቅረብ ድጋፍ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል። የሳኡዲ አረቢያ መንግስት ባስቀመጠው የ90 ቀናት የጊዜ ገደብ ውስጥ ወደ ሃገራቸው ለሚመለሱ ኢትዮጵያውያን ከአራት ዓመት በፊት እንደተደረገው ወደ የመጡበት አካባቢ የሚመለሱበትና ቀጣይ ህይወታቸውን የሚመሩበት ሁኔታ ለመፍጠር መንግስት አስፈላጊውን ሁኔታ ለማመቻቸት መዘጋጀቱንም አስታውቋል።

በቅርቡም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር አክሊሉ ሃይለሚካኤል የተመራ የልዑካን ቡድን ወደ ሳኡዲ አረቢያ ተጉዞ በጉዳዩ ዙሪያ ከሃገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ተወያይቷል። የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ሃይለሚካኤል ከሳኡዲ አረቢያ የቆንስላ ጉዳዮች አቻቸው አምባሳደር ታሚሚ አልደውሰሪ ጋር ተወያይተዋል። በውይይቱ ኢትዮጵያውያኑን ወደሃገራቸው የማስመለሱን ሂደት በተረጋጋ መንፈስ ለማከናወንና የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሏቸው መንገዶች ላይ መክረዋል። ዶክተር አክሊሉ በሪያድና አካባቢው ከሚገኙ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ተወካዮች፣ የሃገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶችም ጋር ውይይት አድርገዋል።

በሪያድና በጂዳ የሚገኙ ሚሲዮኖች የጉዞ ሰነድ አሰጣጥ ሁኔታ የተቀላጠፈ እንዲሆንና በጉዳዩ ዙሪያ ሊያጋጥሙ በሚችሉ መሰናክሎች ላይ ውይይት ተካሂዷል። ከውይይቱ በኋላ ወደሃገራቸው የሚመለሱ ኢተዮጵያውያን በቀላሉ መውጫ ቪዛ እንዲያገኙ በሳኡዲ አራቢያ መንግስት በኩል ተንቀሳቃሽ ጽህፈት ቤቶች እንዲከፈቱ ተደርጓል። ይህን ተከትሎ ኢትዮጵያውያኑ የጉዞ ሰነድ መውሰድና ወደሃገራቸው መመለስ ጀምረዋል። ይህ ጽሁፈ እስከተዘጋጀበት ሰኣት ድረስ 420 ኢትዮጵያውያን ወደሃገራቸው ተመልሰዋል። ይህ ቁጥር በአጠቃለይ ህገወጥ ሆነው ከሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ጋር ሲነጻጻር እጅግ አነስተኛ ነው።

በውጭ ሃገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በድንገት ወደሃገራቸው እንዲመለሱ የሚያስገድድ ሁኔታ ሲገጥማቸው በስደት ያፈሩት ሃብት ስለሚያሳዝናቸው በፍጥነት ተነስተው ለመመለስ የሚቸገሩበት ሁኔታ መኖሩ ይታወቃል። የኢፌዴሪ መንግስት በዚህ ሳቢያ በሳኡዲ አረቢያ በህገወጥነት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሚገጥማቸውን ፈተና ለማቃለል፣ ሀገራቸው ሲመለሱ የግል መገልገያ እቃዎቻቸውን ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡ ፈቅዷል። ይህ ዜጎቹ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ወደሃገራቸው ተመልሰው ከእንግልትና ከህግ ተጠያቂነት እንዲድኑ ለማድረግ የተወሰነ ማበረታቻ ነው። የህገወጥ ስደተኞቹ ዘመዶችና ወዳጆች፣ በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያንም በሚችሉት መንገድ ሁሉ ወገኖቻቻው ሳይንገላቱና ክብራቸው ሳይዋረድ ወደሃገራቸው እንዲመለሱ ባገኙት አጋጣሚ  ሁሉ ማበረታታት ይጠበቅባቸዋል። በተለይ ሚዲያ፣ የህዝብም ሆነ የግል ሚዲያ በዚህ ረገድ ትልቅ ሃላፊንት አለበት። በህገወጥ መንገድ በሳኡዲ አረቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሃገራቸው ሰርተው መኖር የሚችሉበት እድል መኖሩን ሊያውቁ ይገባል። ሃገሪቱ እያስመዘገበች ያለው የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ በመሳተፍ ከእድገቱ መቋደስና የተሻለ ህይወት የመኖር ተስፋ እንዳላቸውም እንዲገነዘቡ ማደረግ ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ ሙሉ መብታቸውና ነጻነታቸው ተረጋግጦላቸው ሊኖሩ የሚችሉባት ቤታቸው ነች። ኢትዮጵያዊነታቸውን ማንም ሊቸራቸው፣ ሊቀማቸውም አይችልም። እናም ከሚያምረው የሰው ሃገር፣ የሚከበሩባት ባለተስፋዋ ሃገራቸው ኢትዮጵያ ትሻላቸዋለች።  የሰው ወርቅ አያደምቅ።      

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy