Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሱ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ከ205 ሚሊዮን ብር በላይ ግብር በማጭበርበር ቅጣት ተጣለበት

0 1,907

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከ205 ሚሊዮን ብር በላይ ግብር ባለመክፈልና አሳሳች ሰነድ በማቅረብ ወንጀል ጥፋተኛ የተባለው በብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ሥራ ተሰማርቶ የሚገኘው የሱ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና ሥራ አስኪያጁ፣ በጽኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ ውሳኔ ተሰጠ፡፡

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዓቃቤ ሕግ በኅዳር ወር 2005 ዓ.ም. ክስ የመሠረተባቸውና ላለፉት አራት ዓመታት ከአራት ወራት ክሱን ሲከላከሉ ከርመው ጥፋተኛ የተባሉትና የቅጣት ውሳኔ የተላለፈባቸው፣ የሱ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና ሥራ አስኪያጁ አቶ ኢሳያስ ተክሉ ናቸው፡፡ የአክሲዮን ማኅበሩ ከፍተኛ ባለድርሻና ባለቤት አቶ ዮሐንስ ሲሳይ አራት ዓመታት ከሁለት ወራት ታስረው ሲከራከሩ ከከረሙ በኋላ፣ የተመሠረተባቸውን ክስ ሙሉ በሙሉ ማስተባበል በመቻላቸው ጥፋተኛ ሳይባሉ በነፃ ተሰናብተዋል፡፡

የባለሥልጣኑ ዓቃቤ ሕግ የመሠረተውን ክስ ሲመረምር የከረመው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስምንተኛ ወንጀል ችሎት ሌላው የቅጣት ውሳኔ ያስተላለፈው፣ በየሱ ድርጅት ባለቤት አቶ ዮሐንስ ቤተሰቦች የተመሠረተ መሆኑ በክስ ዝርዝሩ የተገለጸው ሸበል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና በሥራ አስኪያጁ በአቶ ኃይሉ አሰፋ ላይ ነው፡፡

የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃይሉ በሌሉበት ክርክሩ በመካሄዱና ቀርበው ሊከራከሩ ባለመቻላቸው በ16 ዓመታት ጽኑ እስራትና 370 ሺሕ ብር እንዲቀጡ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡ ሸበል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርም የ16 ዓመታት ጽኑ እስራትና የ370 ሺሕ ብር ቅጣት ተጥሎበታል፡፡ ነገር ግን ሕጋዊ ሰውነት ያለው ድርጀት በመሆኑና ከአሥር ዓመታት በላይ የሚያስቀጣ ውሳኔ ስለተላለፈበት፣ የዓመታት ቅጣቱ ወደ ገንዘብ ተቀይሮ በድምሩ 670 ሺሕ ብር እንዲቀጣ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

የሱ ኃላፊቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በዋናነት ቅጣቱ የተወሰነበት ከ1996 ዓ.ም. እስከ 2002 ዓ.ም. ድረስ በነበሩት የግብር ዘመናት መክፈል የነበረበትን የንግድ ትርፍ ግብር አሳውቆ ባለመክፈሉና በግብር ዘመኑ አትርፎ እያለ መክሰሩን የሚያሳይ የሐሰተኛ ወይም አሳሳች ማስረጃዎችን በማቅረቡ መሆኑን፣ ፍርድ ቤቱ የሰጠው ውሳኔ ያስረዳል፡፡፡

በአቶ ዮሐንስ ከፍተኛ ባለድርሻነትና በወንድማቸው በአቶ ያሬድ ሲሳይ ሞላ የተመሠረተው የሱ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ ብረታ ብረት ማምረትና መሸጥ የንግድ ሥራ ዘርፍ በ555,000,000 ብር ካፒታል የተመሠረተ ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ ከውጭ አገር በሚያስገባው የብረታ ብረት ወይም ቆርቆሮ ግብዓትን የተወሰነውን ጥሬ ዕቃ ግብር ለመሰወር እንዲያመቸው፣ በአቶ ዮሐንስ ዘመዶች ለተመሠረተው ሸበል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከማምረቻ ዋጋ በታች በሆነ አነስተኛ ዋጋ በዱቤ ሽያጭ እያስተላለፈ፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለአቶ ዮሐንስ ገቢ ያደርግ እንደነበር የባለሥልጣኑ ዓቃቤ ሕግ የመሠረተው ክስ ያስረዳል፡፡

ድርጅቱ ካፒታሉን እያሳደገ እያለ በየግብር ዘመኑ ኪሳራ በማሳወቅ ከ1996 ዓ.ም. እስከ 2002 ዓ.ም. ባሉት የግብር ዘመናት ውስጥ 81,551,644 ብር የንግድ ግብር አሳውቆ መክፈል ሲገባው፣ አለመክፈሉንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሮ አቅርቧል፡፡

የሱ ከ1996 ዓ.ም. እስከ 2002 ዓ.ም. ውስጥ 451,756,618 ብር ጠቅላላ ገቢ ያገኘ ቢሆንም፣ 539,096,747 ብር እንደከሰረ በማስመሰል ሐሰተኛ ወይም አሳሳች ማስረጃ ማቅረቡንም ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

የባለሥልጣኑ ዓቃቤ ሕግ በክሱ እንዳስረዳው የሱ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከ1996 ዓ.ም. እስከ 2002 ዓ.ም. ውስጥ ባከናወናቸው ተጨማሪ እሴት ታክስ የሚከፈልባቸው ግብይቶች፣ መክፈል የነበረበትን 123,899,339 ብር የተጨማሪ እሴት ታክስ አሳውቆ መክፈል ሲገባው አለመክፈሉንም ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ድርጅቱ ሌላው ያደረገው ነገር በተጠቀሱት የግብር ዘመናት ተጨማሪ እሴት ታክስ የሚከፈልበት የ3,163,824,745 ብር እንዲያመቸው፣ የሽያጭ መጠኑን በመቀነስ 2,144,269,003 ብር እንደሆነ አድርጎ አሳሳች ማስረጃ ማቅረቡንም በዝርዝር ማስረዳቱን፣ ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሮ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል፡፡ ድርጅቱ ከ1996 ዓ.ም. እስከ 2002 ዓ.ም. ድረስ ያገኘውን 205,451,043 ብር ቀደም ብሎ በነበረው የድርጅቱ ካፒታል ላይ ማለትም 555,000,000 ብር ላይ ደምሮ ወደ 825,000,000 ብር ከፍ ያደረገ በማስመሰል ለጥሬ ዕቃ መግዣና የባንክ ዕዳ መክፈያነት ከሌላ ሕጋዊ ገንዘብ ጋር በማቀላቀል፣ በሕገወጥ መንገድ ያገኘውን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረቡንም ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ በክሱ አስረድቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ በውሳኔው እንደገለጸው፣ ዓቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ምስክሮችን በማቅረብ በየሱ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ላይ፣ በባለ ከፍተኛ ባለድርሻ አቶ ዮሐንስና በሥራ አስኪያጁ አቶ ኢሳያስ ላይ ማስመስከሩንና ማስረዳቱን ፍርድ ቤቱ በውሳኔው ገልጿል፡፡ ዓቃቤ ሕግ እንደ ክሱ ማስረዳቱን በመግለጽም እንዲከላከሉ ወስኗል፡፡

አቶ ዮሐንስና አቶ ኢሳያስ እንዲከላከሉ ብይን የተሰጠባቸው የየሱ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርን በኃላፊነት ሲመሩ፣ ከላይ የተገለጸው የወንጀል ድርጊት እንዳይፈጸም ለመከላከል ተገቢ የትጋትና የጥንቃቄ ዕርምጃ መውሰድ የሚያስችል የሕግ ግዴታ እያለባቸው ግዴታቸውን ባለመፈጸምና ድርጅቱ ወንጀል እንዲፈጽም በማድረግ በግብረ አበርነት ወንጀል በመፈጸማቸው መሆኑን ፍርድ ቤቱ በውሳኔው አስረድቷል፡፡

አቶ ዮሐንስ 83,178,335 ብር ተጨማሪ እሴት ታክስ የሚከፈልበት ግብይት አከናውነው አሳውቀው ባለመክፈላቸው፣ 366,631,697 ብር ደግሞ ከፍተኛ ባለድርሻ ለሆኑባቸው አኬዳ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ኢያስ ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና ኢላና ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በብድር መልክ ማስተላለፋቸውን ዓቃቤ ሕግ ጠቁሞ፣ በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስለው ማቅረባቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ አቶ ዮሐንስ ከላይ የተጠቀሰውን ዓቃቤ ሕግ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ በአንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ በአንበሳ ኢንሹራንስ ኩባንያና በራያ ቢራ አክሲዮን ማኅበር ለአክሲዮን ድርሻ መግዣ እንዳዋሉትና ባለድርሻ ለሆኑባቸው በርካታ ድርጅቶች ያሏቸውን አክሲዮኖች ማሳደጊያ ማዋላቸውን ገልጾ ተከራክሮ ነበር፡፡ ነገር ግን አቶ ዮሐንስ በእሳቸው ላይ የባለሥልጣኑ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበባቸውን ክስ በብቃት መከላከል በመቻላቸው፣ ተጠርጥረው ከተከሰሱባቸው ክሶች በአራት ዓመታት ከሁለት ወራት በነፃ ተሰናብተዋል፡፡

የሱ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና ሥራ አስኪያጁ አቶ ኢሳያስ ተክሉ እንዲከላከሉ የተበየነባቸውን የወንጀል ድርጊት መከላከል ባለመቻላቸው የጥፋተኝነት ውሳኔ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ ድርጅቱ በአገሪቱ ልማት ላይ ያለውን ተሳትፎ ማለትም ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የ30 ሚሊዮን ብር ቦንድ መግዛቱን፣ ለትግራይ ልማት ማኅበር፣ ለአማራ ልማት ማኅበርና ሌሎች ማኅበራዊና የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ዕርዳታ ማድረጉን በቅጣት ማቅለያነት አቅርቧል፡፡ ቀደም ባሉት ዘመናትም የወንጀል ሪከርድ እንደሌለበት በመረጋገጡ አራት የቅጣት ማቅለያዎች ተይዘውለታል፡፡ ሥራ አስኪያጁ አቶ ኢሳያስም የልጆች አባትና የቤተሰብ ኃላፊና ታማሚ መሆናቸውን፣ የወንጀል ሪከርድ የሌለባቸው መሆኑንና ያላቸው ማኅበራዊ ተሳትፎ መልካም መሆኑ በመረጋገጡ፣ ለእሳቸውም አራት የቅጣት ማቅለያ ተይዞላቸዋል፡፡ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግም ምንም ያቀረበው የቅጣት ማክበጃ ሐሳብ ባለመኖሩ የወንጀል ድርጊቱ ዝቅተኛና መካከለኛ በሚል ተይዞላቸዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የቅጣት ማቅለያውን በመውሰድና ባለው ፈቃደ ሥልጣን መሠረት የሱ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በዘጠኝ ዓመታት ጽኑ እስራትና በ210 ሺሕ ብር እንዲቀጣ ወስኖ፣ ድርጅቱ ሕጋዊ ሰውነት ያለው ድርጅት በመሆኑ የእስራት ቅጣቱ ወደ ገንዘብ ሲቀየር 40 ሺሕ ብር ስለሚያስቀጣው በድምሩ 250 ሺሕ ብር እንዲቀጣ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

አቶ ኢሳያስም የተያዘላቸውን የቅጣት ማቅለያ በመውሰድና ከቅጣት ማንዋሉ ጋር በማገናዘብ፣ እንዲሁም ፍርድ ቤቱ የተሰጠውን ፈቃደ ሥልጣን በመጠቀም በሰባት ዓመታት ጽኑ እስራትና በ130,000 ብር እንዲቀጡ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አአስተዳደር የቅጣት ውሳኔ የተላለፈባቸውን የአቶ ኢሳያስን እስራት ተከታትሎ እንዲያስፈጽም፣ የሸበል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃይሉ አሰፋን የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተከታትለው በመያዝ ለማረሚያ ቤት በማስረከብ የተወሰነባቸውን የ16 ዓመታት ጽኑ እስራት እንዲፈጽሙ፣ በሁሉም ፍርደኞች ላይ የተላለፈው የገንዘብ ቅጣት ለሚመለከተው የፋይናንስ ክፍል ገቢ እንዲደረግ ትዕዛዝ ሰጥቶ ፍርድ ቤቱ መዝገቡን ዘግቶ ወደ መዝገብ ቤት መልሷለ፡፡ የቅጣት ውሳኔ የተሰጠው በአቶ ዮሐንስ ንጉሥ (ዳኛ) በወ/ሮ ብርቱካን አየለ (ዳኛ) አብላጫ ድምፅ ሲሆን፣ አቶ ኑረዲን ከድር (ዳኛ) በውሳኔው ተለይተው የውሳኔ ሐሳባቸውን በመዝገቡ ላይ አስፍረዋል፡፡eporte

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy