“ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ታላቁን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ መገንባቷ አገሬ የተፈጥሮ ሃብቷን በአግባቡ እንድትጠቀም መንገድ አሳይታለች” ሲሉ የታንዛኒያው ፕሬዚዳንት ጆን ፖምቤ ማጉፉሊ ገለጹ።
ፕሬዚዳንት ዶክተር ጆን ፖምቤ ጆሴፍ ማጉፉሊ ዳሬሰላም ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
በተለይም ግንባታው ከተጀመረ ነገ ስድስተኛ ዓመት ስለሚሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲገልጹ “ከኢትዮጵያ አልፎ ለታንዛኒያም ትርጉም አለው” ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ።
“የአባይ ውሃ የጋራ ሃብት በመሆኑ አጠቃቀሙ ሁሉንም አገሮች ያማከለና የማንንም ጥቅም የማይነካ መሆን አለበት” ብለዋል።
ለዚህም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ታላቁን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ እየገነባች “መንገዱን አሳይታናለች” ብለዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የማመንጨት አቅም ወደ 6 ሺ 450 ሜጋ ዋት አድጓል።
ታንዛኒያ እስካሁን 1 ሺ 500 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ነው ያላት፤ ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ሃይል ሚያስፈልጋት በመሆኑ “የኢትዮጵያን ተሞክሮ መውሰድ አለብን” ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ።
“ተፈጥሮ አድሎናል፤ ነገር ግን አልተጠቀምንበትም፤ እናንተ ስትራቴጂና ቴክኒክ አላችሁ። እኛም ሃብታችንን በአግባቡ እንድንጠቀምና የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ እንድንገነባ የባለሙያ እገዛ ልታደርጉልን ይገባል” በማለት ነው የተናገሩት።
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ታላቁን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ መገንባት በመጀመሯ “አገሬ የተፈጥሮ ኃብቷን በአግባቡ እንድትጠቀም መንገድ አሳይታለች” ሲሉም ነው ፕሬዚዳንት ማጉፉሊ የገለጹት።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሌሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፤ ግንባታው ሲጠናቀቅ አገራቸው 400 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል መግዛት እንደምትፈልግ ጠቁመዋል።
በኤሌክትሪክ ኃይል ዘርፍ ታንዛኒያ ከኢትዮጵያ ተሞክሮ በመውሰድ የአገሪቷን የኃይል እጥረት የማቃለልና ዘርፉንም ተወዳዳሪ የማድረግ ፍላጎት እንዳላት ተናግረዋል።
በተመሳሳይ ፕሬዚዳንቱ ማጉፉሊ፤ ታንዛኒያ በቴሌኮም ዘርፍም የኢትዮጵያን ተሞክሮ መጋራት እንደምትፈልግ መግለጻቸውንም ነው ኢዜአ ከስፍራው የዘገበው።
“በታንዛኒያ በርካታ የቴሌኮም ኩባንያዎች አሉ፤ ኢትዮጵያ ያላት ግን አንድ ነው፤ ይሁንና የእኛዎቹ ተደምረው የሚያስገኙት ውጤት ከኢትዮጵያ ጋር አይወዳደርም፤ የእነርሱ የቴሌኮም ዘርፍ ውጤታማ፣ ትርፋማና የአገሪቷን ኢኮኖሚ በመደገፍ ላይ የሚገኝ ነው” ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ትልቅ የሆነውን የካርጎ ማዕከል በታንዛኒያ ዳሬሰላም ለመክፈት መዘጋጀቱ ለአገሪቷ መልካም አጋጣሚ መሆኑንም ነው ያስረዱት።
“አየር መንገዱ በርካታ አውሮፕላኖችና መዳረሻዎች ያሉት ስኬታማ ተቋም ነው” ያሉት ፕሬዝዳንት ማጉፉሊ፤ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም ተወዳዳሪ የሆነ ትልቅ ኩባንያ መሆኑን ገልጸዋል።
በታንዛኒያ የካርጎ ማዕከል ማቋቋሙ ቱሪዝም፣ ንግድና ኢንቨስትመንት ከማስፋፋት ባለፈ ኢትዮጵያንም የአማራጭ ወደብ ተጠቃሚ ያደርጋታል።
በተለይም “ሁለቱ አገሮች በቀንድ ከብት ውጤታማ ስለሆኑ የቆዳ ኢንዱስትሪ ዘርፍን ለማስፋት ያግዛል” ብለዋል።
እናም የኢትዮጵያ አየር መንገድን በመጠቀም “በወጪ ንግድ ያለንን ተሳትፎ ማሳደግ እንችላለን ነው” ያሉት።
ፕሬዝዳንቱ “ሁለቱ አገሮች ተመሳሳይ ራዕይ ያላቸው በመሆኑ አዲሲቷ ታንዛኒያንና አዲሲቷ ኢትዮጵያ ለመገንባት በጋራ እንሰራለን” በማለትም ነው ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳዩት።