Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የንግድ ባንኮች ከውጭ ሀገር በሀዋላ ገንዘብ ለሚላክላቸው የሚያቀርቡት ሽልማት ቅሬታን ፈጥሯል

0 745

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የንግድ ባንኮች በውጭ ሀገር ያሉ ዜጎች ወደ ሀገር ውስጥ ገንዘብን ለሚያስልኩ እስከ ቤት የደረሰ የእድል እጣን ለመወዳደሪያነት ማቅረባቸው ከሀገሪቱ የምንዛሬ ተመን አሰራር ጋር የሚጋጭ ነው መሆኑን አስተያየታቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የሰጡ የዘርፉ አንቀሳቃሾች ይናገራሉ።

አሰራሩ ፍትሀዊ ያልሆነ የገበያ ውድድርን እያስከተለ ስለመሆኑም ያነሳሉ።

የህብረት ባንክ የቦርድ ሊቀ መንበር አቶ ዛፉ እየሱስ ወርቅ፥ የንግድ ባንኮች እየተከተሉት ያለው አሰራር ሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬን አስመልክቶ ካወጣችው ህግ ጋር ይጻጸራል ይላሉ።

አቶ ዛፉ እየሱስ ወርቅ እንደሚሉት አንድ ግለሰብ የውጭ ምንዛሬን በአንድ ንግድ ባንክ በኩል ስላስመጣ ባለ እጣ የሚያደርገው ኩፖን ተሰጥቶት በአጋጣሚ እጣው የሚወጣለት ከሆነ ባቀረበው የውጭ ምንዛሬ ላይ የሚሰጠው ተጨማሪ ገንዘብ ነው፤ ይህም የተመን ህጉን ይጥሳል ባይ ናቸው።

አንድ ግለሰብ ከመኪና ዋጋ በታች የውጭ ምንዛሬ ተልኮለት መኪና በእጣ ቢደርሰው ይህ መኪና ከውጭ ምንዛሬው ተመን በላይ ባንኩ እየከፈለው ስለሆነ አሰራሩ ከህጉ ጋር የማይሄድ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ዛፉ፥ ይህም ፍትሃዊ ያልሆነ የገበያ ውድድር ነው ብለዋል።

ለውጭ ምንዛሬ አስመጪዎች ሽልማት መስጠት በአንዱ ባንክ በኩል ሊመጣ የነበረን ምንዛሬ በሌላው ባንክ ሊያደርግ ይችል ይሆናል እንጂ እንደ ሀገር የውጭ ምንዛሬን ይጨምራል ብለው እንደማያምኑም ተናግረዋል።

ከዚህ ይልቅ ባንኮች የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ግኝት ለማሳደግ ኤክስፖርተሮችን ማበረታታት እና አገልግሎትን ማቀላጠፍ ላይ ነው ማተኮር ያለባቸው ይላሉ።

የኢትዮጵያ ባንኮች ማህበር እና የደቡብ ግሎባል ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አዲሱ ሀባ፥ በጉዳዩ ላይ ባንኮች ባደረጉት ውይይት ከመግባባት ላይ ባለመድረሳቸው እንደ ማህበር የያዙትን አቋም ከመናገር ተቆጥበዋል።

ሆኖም ባንኮች የውጭ ምንዛሬ ላመጣላቸው ማበረታቻን መስጠታቸው የብሄራዊ ባንክ ተመንን ይጥሳል የሚል አቋም የለኝም ነው ያሉት አቶ አዲሱ።

ይሁን እንጂ ከመኪና እስከ ቤት የደረሰው የባንኮች የመወዳደሪያ አካሄድ አሁን ባለው ሁኔታ ጉዳት ያስከትላል፤ በተለይም አነስተኛ ቅርንጫፍ ያላቸው ባንኮች የዚህ ተጋላጮች ናቸው ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።

አቶ አዲሱ ባንኮች የውጭ ምንዛሬ ግኝታቸውን ለማሳደግ የአሁኑ አይነት ውድድር ውስጥ ከሚገቡ ይልቅ አገልግሎታቸው ላይ ቢያተኩሩ እንደሚሻልም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ጥሩነህ ሚጣፋ በበኩላቸው፥ ባንኮች የውጭ ምንዛሬን በራሳቸው በኩል ለማስላክ እያደረጉት ያለው ነገር ፍትሀዊ ያልሆነ የገበያ ውድድር ስለማስከተሉ የደረሰን ቅሬታ የለም ብለዋል።

ባንኩ መሰል ቅሬታ ከቀረበለት ግን የሚያጤነው ይሆናል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በየአመቱ ከምታገኘው የውጭ ምንዛሬ ውጭ ሀገር ያሉ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለቤተሰቦቻቸው የሚልኩት ገንዘብ ወይንም ሬሚታንስ ከሸቀጦች ንግድም በልጦ ከፍተኛ ቦታን ይዟል።

ባለፈው አመትም ኢትዮጵያ በዚህ መንገድ 4 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ማግኘቷን መረጃዎች ያሳያሉ።

በካሳዬ ወልዴ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy