Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የአየር ንብረት ለውጥና – ኢትዮጵያ

0 780

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የአየር ንብረት ለውጥና – ኢትዮጵያ

አባ መላኩ 

የአየር ንብረት ለውጥ የዓለም ሥጋት መሆን ከጀመረ ውሎ አደረ። በርካታ ዓመታትም ተቆጠሩ ፡፡ የአየር ንብረት ለውጡ በድርቅ ሣቢያ የግብርና ምርታማነት ቅናሽ እንዲያሳይ ዋነኛ ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህንን መነሻ በማድረግ የአየር ንብረት ለውጥ በምርትና ምርታማነት ሂደት ላይ የሚያደርሰውን አሉታዊ ተፅዕኖ በመገንዘብ አገራት ወሣኝ ተግባራት እያካሄዱ ነው። ከእነዚህ አገራት መካከል ኢትዮጵያ ተጠቃሽ ናት።

ኢትዮጵያ ለዚህ ውጤት በመልካም ተምሣሌትነት ልትጠቀስ የበቃችው ከፍተኛ የሆነ የጋዝ ልቀትን የመቀነስ፣ ከፀሐይ ኃይል ኤሌክትሪክ የሚያመነጭ ቴክኖሎጂዎችን በአማራጭነት የመጠቀም፣ የተፈጥሮ ሀብቷን በተገቢው የመገልገል፣ የተፋሰስ ልማትን የማስፋፋትና፣ የደን ልማትን በስፋት የማካሄድ ስትራቴጂዎችን በዋናነት በመቀበሏና ለተግባራዊነቱም ቁርጠኛ በመሆኗ ነው፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ በዓለማችን እጅግ አሳሳቢ እየሆነ የመጣ፣ ለኦዞን መሳሳትና በዓለም ላይ እየደረሱ ላሉ ተግዳሮቶችም መንስዔ ሲሆን ታይቷል፡፡ የዘርፉ ምሁራን እንደሚሉት ለእነዚህ ሁሉ ችግሮች በዋና ምክንያትነት የሚጠቀሱት ወደከባቢ አየር የሚለቀቁ የበካይ ጋዞች ልቀት መጨመርና የደን ሀብት እየተመናመነ መምጣት ነው፡፡  

ታዲያ ችግሮቹን ለመፍታት የበካይ ጋዝ ልቀትን መቀነስና የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን መከተል እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤን ማጎልበትና በደን ልማት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት የግድ ይሆናል። እነዚህም ዓለም የተስማማባቸው እውነታዎች ናቸው፡፡ በተለይም በግብርና ምርታማነት ላይ መሠረቱን ለጣለ ምጣኔ ሀብት የአየር ንብረት ለውጥ ምን ያህል ተፅዕኖ እንዳለው መረዳት ቀላል ነው።  

የአየር ንብረት ለውጥ በግብርና ምርታማነት ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተፅዕኖ ቀድማ የተገነዘበች አገር – ኢትዮጵያም የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን እየተከተለች ትገኛለች፡፡ ይህ ልማት ህዝቡን ተጠቃሚ ከማድረግ ባሻገር፤ ለአካባቢ ተስማሚ መሆኑን በተጨባጭ የተገኙ ውጤቶች ህያው ምስክር ናቸው፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን በመጠቀም በአካባቢ ጥበቃ ላይ በማከናወን ላይ ያለችውን ተግባራትንና እመርታዎችን በጥቂቱ እንመልከት፡፡

ማንኛውም አገር ሁኔታዎችን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ለማጣጣም መፈታት ያለባቸውን ችግሮች መዘርዘርና መፍትሄ ማፈላለግ ግድ ይለዋል፡፡ ለዚህ ተግባር ተስማሚ የሆነ፣ የሥራ ዕድልን የሚፈጥር፣ ምርትንና ምርታማነትን የሚያሳድግ የአካባቢ መራቆት ሂደትን የሚከላከል፣ አካባቢውን ለልማት ለማዋል ዕቃና አገልግሎት የማቅረብ እንዲሁም ቀጣይ አቅምን የሚያጎለብት፣ በጎ ተሞክሮን እና ቴክኖሎጂን ማሰስ ያስፈልጋል፡፡ በተለያዩ አካላት ሲተገበሩ ከነበሩ የአካባቢ እንክብካቤ ተግባራት በመነሳት መልካም ተሞክሮዎችንና ቴክኖሎጂዎችን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በማስፋፋት ሙከራ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡

ከዚህ በመነሳትም የአካባቢ እንክብካቤን መሠረት ያደረገ የእፅዋትና የፍራፍሬ ልማት ቴክኖሎጂን ወደ አገሪቱ በማስገባት ተግባራዊ መሆን ችሏል፡፡ ቴክኖሎጂው ተራራማና ደጋማ በሆኑ አካባቢዎች በዓመታዊ ሰብሎች አመራረት ምክንያት የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የእፀዋትና የፍራፍሬ ልማት እንዲሁም የአፈርና ውኃ እቀባ ሥራዎችን በማቀናጀት የሚከናወን ነው፡፡

ይህም የኅብረተሰቡን ገቢ በማሻሻል በተለይም ወጣቶችን እንደ ደን ቆረጣ ካሉ አካባቢን ከሚጎዱ የገቢ ማስገኛ መስኮች በማላቀቅ አማራጭ ወደሆኑ የገቢ ማስገኛ መስኮች እንዲዞሩ ያደርጋል፤ አድርጓልም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በእርሻ ላይ የተመሠረተው ምጣኔ ሀብት ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ሽግግር ያግዛል፡፡ ቴክኖሎጂው ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡ የሰብል፣ የዛፍ፣ የፍራፍሬና አትክልት ዝርያዎችን የእንስሳት ርባታና ድለባ፣ የንብ ማነብ ሥራን አቀናጅቶ በማልማት የገቢ ምንጭን ያሳድጋል።  

ክንዋኔው በምጣኔ ሀብቱ ላይ ከሚያደርሰው አዎንታዊ ተፅዕኖ ባሻገር፤ በተፈጥሮ ሀብት ላይ የሚያስከትለውን ጫና በመቀነስ ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል፡፡ ፊዚካላዊና ሥነ ህይወታዊ የአካባቢ ሥራዎችን በመተግበርም የተጎዱ አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙ በማድረግ የአፈር መሸርሸርን በመከላከል የአፈር ለምነትን ለመጨመር ያግዛል። በሌላ በኩልም ቴክኖሎጂው የእፀዋት እና እንስሳት ዓይነቶች እንዲበራከቱ አድርጓል፡፡ አካባቢውም በተለያዩ እፀዋቶች ሲሸፈን የአካባቢው ውበት ስለሚያምር ለኅብረተሰቡ የመዝናኛ ቦታን ስለሚያበረክት ንፁህ ከባቢን ለመፍጠር የሚደረገውን ርብርብም ያግዛል።  

የአካባቢ ጥበቃን መሠረት አድርገው እየተሰራባቸው ካሉ ቴክኖሎጂዎች መካከል፤ የተጎዱ መሬቶችን ከእንስሳትና ከሰው ንክኪ ነጻ በማድረግ እንዲያገግሙ የማድረግ ቴክኖሎጂ አንዱ ነው፡፡ ቴክኖሎጂው በእፀዋት ሽፋን መሳሳትና በአፈር ለምነት መቀነስ ሣቢያ የተጎዱና ምርታማነታቸው የተቋረጡ መሬቶች መልሰው እንዲያገግሙ ከማድረግ አንፃር የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡

ቴክኖሎጂው የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ እንዲያገግሙ ለማድረግ በየአካባቢው መልክዓ ምድር ሊተገበር የሚችል ነው፤ ለአካባቢው አየር ፀባይ ተስማሚ የእፀዋት ዝርያ በመምረጥ ተስማሚ የእርከን ዓይነቶችን መለየት እና የገቢ ምንጭ ሊያስገኙ የሚችሉ ተግባራት ተቀናጅተው የሚከወኑበት ሁኔታ በማጤን ኅብረተሰቡ የሚጠቀምበትን መንገድ ለማሳየት ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እንዲከናወኑ አስችሏል፡፡

ማኅበረሰቡም የተጎዱ ቦታዎች መልሰው እንዲያገግሙ የማድረግና የማልማት እንዲሁም እውቀትና ክህሎት እንዲያዳብር ያግዛል፡፡ የመሬት ጥበቃ ችግርን በማሳበብ ኅብረተሰቡ ከአካባቢው እንዳይሰደድ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የጓሮ አትክልቶችንና ፍራፍሬዎችን አልምቶ ራስንና ቤተሰብን ለመመገብ ብሎም ጤናው እንዲሻሻል በማድረግ ረገድ መንግሥት አስቀድሞ በሽታን ለመከላከል ለያዘው ዕቅድ የራሱን ድርሻ ይጫወታል፡፡

በዚህም ምክንያት በየአካባቢው ጠፍተው የነበሩ የእፀዋትና የእንስሳት ዝርያዎች በመመለስ ላይ ይገኛሉ፡፡ ቴክኖሎጂው ለአካባቢ ጥበቃ ከሚያደርገው ጉልህ ድርሻ ባሻገር፤ ከግብዓት አቅራቢዎች ጋር የአቅርቦት ትስስር በመፍጠር በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው አድርጓል፡፡ ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታው አስተማማኝ በመሆኑም ለቴክኖሎጂው ዘላቂነት ወሣኝ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

የተጎዱ መሬቶች መልሰው እንዲያገግሙ ለማድረግ የተለያዩ አገር በቀል ዛፎችን መትከል ዋነኛው አማራጭ ነው፡፡ ለዚህም በርካታ የችግኝ ማፍያ ጣቢዎችን በብዛት መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሀብቶችም ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን የዛፍ፣ የፍራፍሬና የአትክልት ችግኞችን ለገበያ በማቅረብ የሥራ መስክ በመፍጠር በኩል ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡ በአነስተኛ እና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች ለተደራጁ ግለሰቦች የሰብል ፍርፍሬና፣ አትክልት የዛፍ ችግኞችን አቀናጅቶ በማምረት የገቢ ምንጭን ማሳደግም ችሏል፡፡ ለአካባቢ ጥበቃ አጋዥ ናቸው ተብለው እየተሰራባቸው ካሉ ቴክኖሎጂዎች መካከል የቀርከሃ ልማትና ዕደ ጥበብ ቴክኖሎጂ ተጠቃሽ ነው፡፡ የቆላም ሆነ የደጋ የቀርከሃ ምርት፤ ለማገዶ፣ ለግንባታ ሥራዎች፣ ለቤት ውስጥ ቁሳቁሶች እንዲሁም ለኢንዱስትሪ ግልጋሎትነት መዋል መቻሉ የቀርከሃ ዕደ ጥበብ ውጤቶችን ከማምረትና ለገበያ ከማቅረብ በተጨማሪ ገቢ ያስገኛል፡፡

በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች እንደሚገልፁት የቀርከሃ ተክል ብዛት ያላቸው የሚጠላለፍ ረዣዥም ሥሮች ያሉት በመሆኑ አፈርን አቅፎ መያዝ የሚችል ነው፡፡ በአየር ውስጥ ያለውን ሙቀት አማቂ ጋዞችን በመምጠጥ የምድርን ሙቀት በመቀነስ ረገድም አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የተጎሳቀለ መሬት መልሶ እንዲያገግም ያግዛል። በመሆኑም መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶት እየሰራበት ይገኛል፡፡

እዚህ ላይ የአካበቢ ጥበቃን የተሻለ ለማድረግ የተፈጥሮን ሥነ ምህዳር ለመጠበቅ ከሚደረገው ርብርብ ባሻገር፤ የዕለት ተዕለት ኑሯችን የምንጠቀምባቸውን መሣሪያዎች መመልከት ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም አገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የጋዝ ልቀትን ለመቀነስ ከፀሀይ ኃይል ኤሌክትሪክ የሚያመነጭ ቴክኖሎጂዎችን በአማራጭነት እየተጠቀመች ነውና። ይህ ቴክኖሎጂ የፀሀይ ኃይልን በመሰብሰብ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚያስችል ነው፡፡ ከዚህ ቴክኖሎጂ የሚገኘው የኤሌክትሪክ ኃይል ታዳሽ በመሆኑ በዘላቂነት መጠቀም ይቻላል፡፡

በየትኛውም መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና በቂ ፀሀይ ጨረር በሚገኝባቸው አካባቢዎች ሁሉ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ቴክኖሎጂ ስለሆነም በአገሪቱ ተመራጭ ሆኗል፡፡ ታዲያ ቴክኖሎጂው በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያለውን አዎንታዊ አስተዋጽኦ ከዚህ ጋር አያይዞ ማንሳት ያስፈልጋል፡፡ በተለይም ንፁህ እና ዘመናዊ የምግብ ማብሰያ በመፍጠር ረገድ በጤና ላይ ሊደርሱ የሚችሉ እክሎችን በመቀነስ ዓይነተኛ ድርሻ ያለው መሆኑን በመገንዘብ፡፡ በአገሪቱ የሚኖረው ሰፊው ኅብረተሰብ አርሶ አደር በመሆኑ የኤሌክትሪክ መስመር ባልተዘረጋባቸው አካባቢዎች ተደራሽ በመሆን ከፍተኛ የኃይል አማራጭ ሆኖ ይገኛል፡፡ በባህላዊ የማገዶ አጠቃቀም ምክንያት ወደ አካባቢ አየር የሚለቀቁትን አሟቂ ጋዞችን የሚቀንስ ስለሆነም ለአካባቢ ብክለት መቀነስ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ በደን ሀብት ሽፋን ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጫናም ይቀንሳል፡፡ እንዲሁም የሞተር እና የነዳጅ ኃይል የማይጠቀም በመሆኑ ከድምጽ ብክለት የፀዳ ነው፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy