Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገትና የአረንጓዴ ልማት ቁርኝት!

0 461

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገትና የአረንጓዴ ልማት ቁርኝት!

አባ መላኩ

በቅርቡ የመዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ያወጣው መረጃ  በኢትዮጵያ 83 በመቶ ህዝብ ነዋሪነቱ በገጠር እንደሆነ ያመለክታል። ይህ ማለት በርካታው የአገራችን ህዝብ አኗኗር በአንድም ሆነ በሌላ ከግብርና ጋር የተሳሰረ እንደሆነ መገመት አያዳግትም ። በመሆኑም በዚህ መሰረተ ሰፊ በሆነው ዘርፍ ላይ የሚደረግ ርብርብ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል መንግስት በመረዳቱ፤ በግብርናው ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ርብርብ  በማካሄድ ላይ ይገኛል። በዚህም ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ችሏል።   በየዓመቱ  በግብርናው ዘርፍ  በአማካይ ስምንት በመቶ ዕድገት በማሳየት ባለፉት 15 ዓመታት ተከታታይ ለውጥ  ማስመዝገብ በመቻሉ በገጠር የሚኖረው ሕዝብ የለውጡ  ቀጥታ ተጠቃሚ  መሆን ችሏል።

 

የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማብቂያ ላይ የግብርናው ዘርፍ  ከአጠቃላይ ዓመታዊ የአገር ውስጥ ምርት ከ38 በመቶ  አካባቢ ድርሻ እንዳለው ጥናቶች አመላክተዋል። የግብርናው ዘርፍ የአገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ወይም ሞተር ይሁን አንጂ  መንግስት በቀጣይ  የአገሪቱን ኢኮኖሚ  ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር ተጨማሪ ስራዎችን በማከናወን  ላይ ይገኛል።  ይህ ሽግግር ከአካባቢ ጋር የተጣጣመ እንዲሆንም የአረነጓዴ ልማት ስትራቴጂን በመንደፍ  በመተግበር ላይ ይገኛል።  

 

ኢትዮጵያ  ግብርናውንና ኢንዱስትሪውን ለማስተሳሰር በምታደርገው ጥረት  የአረንጓዴ ልማትን ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን  ከመስራቷ ባሻገር  የኢኮኖሚዋ የጀርባ አጥንት የሆነውን ግብርናውን  ለማዘመን የሚያስችሉ በርካታ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን  በመተግበር ላይ ነች።  እነዚህ ግብርናን ለማዘመን የሚያስችሉ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችም  ለአረንጓዴ ልማት መጠናከር  ድርሻ  እንዲኖራቸው ተደርገው  የተቀረጹ ናቸው።   የአካባቢን ጥበቃ መሰረት ያላደረገ ፕሮግራም በየትኛውም መስፈርት ወጤታማ ሊሆን አይችልም።  

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢንዱስትሪ አማካሪ ሚኒስትር የሆኑት ዶክተር አርከበ እንዳሉት “የግብርና ዘርፉን ሳያሳድግ የማምረቻ ዘርፉን ያሳደገ አገር እስካሁን አላየንም ፤ በመሆኑም አገራችን ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት ሰጥታ በመስራት ላይ ነች ብለዋል።  እንደዶክተር አርከበ ገለጻ ለሁሉም አገሮች  ግብርና ዕድገት መሰረት መሆኑን ነው።  ኢትዮጵያም ለዘርፉ ቅድሚያ ትኩረት በመስጠት በዓለም ፈጣን ዕድገት ማስመዝገብ  ችላለች።  በምስራቅ አፍሪካ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች ያለችው ኢትዮጵያ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ የአገሪቱ   አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት ወይም ጂዲፒ ከ12 ቢሊዮን ወደ 72 ቢሊዮን ዶላር  ማለትም በስድስት እጥፍ ማሳደግ ችላለች። ይህ የሚያሳየው በግብርናው ዘርፍ የተመዘገበው  ዕድገት ለአገር ኢኮኖሚ  መለወጥ መሰረት መሆኑን ነው።  

የዛሬ አነሳሴ እንኳን ስለግብርና ዘርፍ ስኬት ለማብራራት ሳይሆን  የኢትዮጵያ ፈጣን ዕድገትና የአረንጓዴ ልማት ስራዎቻችን ተመጋጋቢነት ለማሳየት ያክል ነው።  የበርካታዎቹ አገራት በተለይ በተፈጥሮ ሃብት ላይ የተመሰረተ ዕድገት እያስመዘገቡ ያሉ አገራት  የኢኮኖሚ ዕድገታቸው  በአካባቢ ላይ  ከፍተኛ ብክነት  በመፍጠር ላይ ነው። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆኑት ነዳጅ አምራች የሆኑ አገራት ለአካባቢ ብክለት ትልቅ ድርሻ በማበርከት ላይ ናቸው።  ይሁንና የኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት  ከአካባቢ ብክለት የጸዳ ነው ማለት ይቻላል።

በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፖሊሲውንና የአረንጓዴ ልማቱን ማጣጣም” በሚል ርዕስ  በቅርቡ አንድ አውደ ጥናት ተካሂዶ ነበር።  የአውደ ጥናቱ ትኩረት  በኢትዮጵያ   የኢንዱስትሪዎችና የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂውን  ትስስር   ምን እንደሚመስል ለማየት  ነበር። የጥናት ቡድኑ መሪ ፕሮፌሰር ያዕቆብ ሙሉጌታ እንዳሉት የአገሪቱ የኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን መሰረት እንዲያደርግ የመንግስት የፖለቲካ ቁርጠኝነቱን በመኖሩ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት  ስራዎቿ  ውጤታማ  ለመሆን በቅታለች  ብለዋል።  

እንደጥናቱ ብድን መሪ አገሪቱ አሁን በያዘችው አቅጣጫ ከቀጠለች ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገቷ በአካባቢ ላይ ጫና ሳይፈጥር ወይም  ለአካባቢ ደህንነት  ተስማሚ እንደሆነ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ጎራ ትቀላቀላለች ብለዋል።  ፕሮፌሰሩ አያይዘው በበርካታ አገሮች ፈጠን ልማትና የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ጎን ለጎን አልሄዱም። በኢትዮጵያ ግን  ፈጣን እድገትንና የአካባቢ ጥበቃን አብረው ማስኬድ ተችሏል።  

ፕሮፌሰር ያዕቆብ ሙሉጌታ  የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ትክክለኛ መሆንና መንግስት ይህን ለማስፈጸም ያለው ቁርጠኝነት  በበርካታ አገራት የዘርፉ ተግዳሮት ሆኖ ሳለ፣ በኢትዮጵያ  ፈጣን ዕድገትንና አረንጓዴ ልማትን  አጣጥሞ በማስኬድ ተጨባጭ ውጤት ማስገኘት እንደተቻለ  በጥናቱ   እንደተረጋገጠ ተናግረዋል።

በመሆኑም በቀጣይም  የኢትዮጵያ መንግስት የአገሪቱን  የኢኮኖሚ ዕድገት ከአረንጓዴ ልማት ጋር በማጣጣም በመጪዎቹ  አስር አመታት መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች  ተርታ ለመቀላቀል  ጥረት በማድረግ ላይ  ይገኛል። መንግስት በሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ትኩረት የሰጠው ነገር አንዱ ዘላቂ ልማትን ከአካባቢ ደህንነት ጋር እንዲጣጣም ማድረግ ላይ ነው።  የአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚ ግንባታ ስትራቴጂ መሠረታዊ መነሻው የአከባቢ ሙቀት ሳቢ ጋዞች ልቀትን በመቀነስ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ነው።  የመንግስት ትኩረት ግብርናን በማዘመን  ማለትም  የሰብልና የእንስሳት ምርትን  በማሳደግ  የአርሶ እና  አርብቶ አደሩን  ገቢ  በቀላሉ  ማሻሻል ነው።

በሰብል ምርትና እና እንስሳት እርባታ የተሻሻሉ አሰራሮችን በመጠቀም  የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ  ሲባል  ለእርሻ የሚሆን ያለተጨማሪ መሬት ወይም ደን መጨፈጨፍ    ሳያስፈልግ የአርሶና አርብቶ አደሩን ገቢ ማሳደግ ማለት ነው። የግብርና መሬትን ከማስፋፋትና የከብትን ቁጥርን ከመጨመር ይልቅ፤  ባለው መሬት ላይ ግብዓትን  በአግባቡ በመጠቀም እንዲሁም  በውሱን የእንሰሳት ቁጥር  በዘመናዊ ቴክኖሎጂ  በመጠቀም አርሶና አርብቶ አደሩ ብዙ ሳይለፉ የተሻለ ተጠቃሚ የሚሆበትን አሰራር ማስፈን ይቻላል። ደኖችን እንዳይጨፈጨፉ መንግስት የተለያዩ ስትራቴጂዎችን በመተግበር ላይ ይገኛል። በዚህም ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል።  

በበርካታ አገሮች ለአካባቢ ብክለት ዋንኛ ምንጭ ተደረጎ የሚወሰደው ሃይል ለማመንጨት የሚደረግ ጥረት ነው። በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ የሃይል ምንጮች  ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል መልኩ ከውሃና ነፋስ መሆናቸው መንግስት ለአካባቢ ጥበቃ የሰጠውን ትኩረት ያሳያል። ኢትዮጵያ መንግስት  ከታዳሽ ሃይል በማመንጨት ለጎረቤት አገራት ጭምር በስፋት ለማቅረብ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን በመተግበር ላይ ነው።  ከዚህ ጎን ለጎን መንግስት  ከዘመናዊ ኢነርጂ ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎች በአገሪቱ በተለይ በገጠር አካባቢ በስፋት በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል። ዛሬ በአገራችን ከተሞች  በኤሌክትሪክ ማብሰል  በስፋት እየተለመደ በመምጣቱ ለማገዶ ተብሎ የሚጨፈጨፈው ደን በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነስ ላይ ነው።  በኢትዮጵያ እየተገነቡ ያሉ ዘመናዊ የባቡር አገልግሎቶችም  በኤሌክትሪክ ሃይል የሚሰሩ በመሆናቸው ለአካባቢ ተስማሚ  ናቸው።  

ሌላው ኢትዮጵያ መንግስት በስፋት እየሰራው ያለው የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂው አካል የሆነው የተፋሰስ ልማት ስራዎች ናቸው።  ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብቻ በሁሉም  አርሶና አርብቶ  አደር አካባቢዎች መንግስት ሰፊ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን እንዲከናወኑ ህብረተሰቡን ማነሳሳት በመቻሉ ተጨባጭ ለውጦችን  በመላ አገሪቱ  ማስመዝገብ ችሏል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የገጠሩ ነዋሪ በአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ላይ በፍቃደኝነት  በመሰማራታቸው በርካታ አካባቢዎች ማገገም ብቻ ሳይሆን ፍጹም መቀየር  ጀምረዋል።  ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሆነችው የትግራይ ክልሏ አብረሃ ወኣጽበሃ ቀበሌ ናት።  ይህች ቀበሌ በነዋሪዎቿ ጥረት ፍጹም መቀየር ያሳየች ዓለም ዓቀፍ ተሞክሮ ሊወሰድባት የሚገባ ቀበሌ ናት፤ አርሶና አርብቶ አደሩ አምኖበት የተፋሰስ ስራ ማከናወን ከቻለ በአጭር ጊዜ አካባቢውን መቀየር እንደሚችል  ኢትዮጵያ  ጥሩ ማሳያ ናት።  

በኢትዮጵያ በየዓመቱ በአስር ቢሊዮኖች የሚቆጠሩ አገር በቀል ችግኞች  በመልማት ላይ ናቸው።   ችግኞችን በማልማትና ደኖችን መንከባከብ  በመቻሉ የአገሪቱ የደን ሽፋን  ከነበረበት 3 በመቶ አካባቢ  አሁን ላይ ወደ 15 በመቶ  ከፍ ማድረግ ተችሏል። ይህ ታላቅ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂው አንዱ አካል ነው። ይህን ተግባር አጠናከሮ መቀጠል እጅግ አስፈላጊ ነው።

በአካባቢ ጥበቃ ስራ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ መሆን በመቻሉ አሁን ላይ የአካባቢ ነዋሪዎች ጉትጎታና ቅስቀሳ አያስፈልጋቸውም። አርሶና አርብቶ አደሩ  በየዓመቱ  ለአካባቢ ጥበቃ ስራ ጊዜ ሰጥቶ  ሁሉም በነቂስ ወጥቶ  በፍቃደኝነት  በመተግባር ላይ ይገኛል። በዚህም  በበርካታ የአገራችነ አካባቢዎች በተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ስራዎች በርካታ  ወጣቶችና ሴቶች  ተጨማሪ የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል።  ከዚህ ባሻገር  ምርትና ምርታማነት በማደጉ የአገሪቱ  የግብርና  ውጤት  እጅጉን ተሻሽሏል። በዚህም የአርሶ አደሩ ገቢ በጣም ተሻሽሏል።   

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy