Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኮሚሽኑ ሪፖርት ገለልተኛና ተዓማኒ ነውን?

1 432

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

 

የኮሚሽኑ ሪፖርት ገለልተኛና ተዓማኒ ነውን?
ዘአማን በላይ
የኢፌዴሪ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በቅርቡ ለህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ከሰኔ 2008 ዓ.ም እስከ መስከረም 2009 ዓ.ም በአንዳንድ የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች የተከሰተውን ሁከት እንዲሁም በደቡብ ክልል ጌዴኦ ዞን በተፈጠረው ብሔር ተኮር ግጭት ምክንያት ያደረገውን ጥናት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ አቅርቧል። በሪፖርቱ ላይ በተጠቀሱት አካባቢዎች ላይ ለተፈፀመው የሰብዓዊ መብት ሪፖርት የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎችና ግለሰቦች ተጠያቂ እንዲሆኑ ምክረ-ሃሳብ ለምክር ቤቱ አቅርቧል። እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ይህ የኮሚሽኑ ምክረ-ሃሳብ ሁሉንም አካል በየደረጃው በህግ እንዲጠየቁና የጉዳዩ ተዋናዮች ሁሉ የድርሻቸውን እንዲወስዱ ያደረገ ነው። ይህም እዚህ ሀገር ውስጥ ማንም ሰው ከህግ በላይ እንዳልሆነ ያሳየ ተግባር ነው።
ያም ሆኖ ግን ‘መንግስት የሚያከናውናቸው ማናቸውም ተግባሮች ትክክል አይደሉም’ ብለው የሚያስቡ አንዳንድ ፅንፈኛ ዲያስፖራዎች ኢትዮጵያ ሰላም ውላ ሰላም ማደሯን የማይሹ ሃይሎች፤ ይህን የኮሚሽኑን አሰራር ‘ገለልተኝነቱን ያልጠበቀና ተዓማኒ ያልሆነ ነው’ በማለት ሊያጣጥሉት ሲሞክሩ ይስተዋላል። ይህ ፈፅሞ ትክክል አይደለም። በእኔ እምነት እንዲህ ዓይነቱ ገና ባልዳበረ ዴሞክራሲ ውስጥ የመንግስት አካላትን የሚያብጠለጥልና በዚያኑ ልክም ተጠያቂ እንዲሆኑ የሚያደርግ ብሎም ሌሎች የሁከትና የግጭት አቀጣጣዮችን በልካቸው በህግ እንዲጠየቁ የሚያደርግ ሪፖርት በምን ዓይነት ስሌት ገለልተኛ እንደማይሆንና ኢ-ተዓማኒ ሊሆን እንደሚችል ለማንም ግልፅ አይደለም።
ኧረ ለመሆኑ በፅንፈኛው ዲያስፖራና ለሀገራችን ሰላም የማያስቡ ፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች እንደምን ሁሉንም አካል ያካተተና በልኬታቸው እንዲጠየቁ የጠየቀ ሪፖርት ገለልተኛ አይሆንም? እርግጥ የእነዚህ አካላት ፍላጎት ግልፅ ነው። ይኸውም እነዚህ ሃይሎች በሀገራችን የተከሰተው ሁከትና ግጭት ሳያባራ በዚያው እንዲቀጥል የሚፈልጉና የዚህ ጉዳይ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑት በየደረጃው ያሉ የመንግስት አካላትም ይሁን ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዳይጠየቁ የሁከቱ አራጋቢ ሆነው እንዲዘልቁ ከፍተኛ ፍላጎት ስላላቸው ነው።
ይሁንና ለእነርሱ ፍላጎት ሲባል የዜጎች ሰብዓዊ መብት ሊደፈጠጥና የህግ የበላይነት ሊጣስ አይችልም። የህግ የበላይነት በሌለበት ሁኔታ መብት ሰጨና ነሺ ጉልበተኞችና ህግን በመፃረር ፖለቲካዊ ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሚሹ የነውጥ ኃይሎች እንዲሆኑ የሚፈቅድ ሥርዓት እዚህ ሀገር ውስጥ አልተገነባም። እዚህ ሀገር ውስጥ እየተገነባ ያለው ሥርዓት ማንም ሆነ ማን ህግን ጥሶ የህዝቦችን መብት ለመጋፋት ከሞከረ አሊያም ከተጋፋ በዚያው ልክ ተጠያቂ የሚያደርግ እንጂ የህግ የበላይነትን የሚፃረሩና በዜጎች ደም እንዳሻቸው ለመነገድ የሚሹ ኃይሎችን የሚታገስ አይደለም።
ያም ሆነ ይህ ፅንፈኞችና ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች ያሻቸውን ቢሉም፤ እዚህ ላይ ስለ የኢፌዴሪ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ገለልተኝነት መግለፅ ተገቢ ይመስለኛል። እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደግሞ በሀገራችን በተካሄደው ምርጫ ህዝቡን ወክለው ፓርላማ የገቡ እንደራሴዎች ስብስብ ነው። ይህም የኮሚሽኑ ተጠሪነት ለእነዚሁ የህዝብ እንደራሴዎች መሆኑን የሚያረጋገጥ ነው። በሌላ አገላለፅ የኮሚሽኑ ገለልተኛነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም። ‘ለምን?’ ከተባለ፤ የኮሚሽኑ ማናቸውም ክንዋኔዎች በእነዚሁ የህዝብ እንደራሴዎች ዕይታና ክትትል ስር ስለሆነ ነው።
እርግጥ እዚህ ላይ አንዳንድ ሁሉም ጉዳይ እንደ እነርሱ የሚመስላቸው ሃይሎች ‘ሁሉም እንደራሴዎች የገዥው ፓርቲ አባላት ስለሆኑ በአስፈፃሚው አካል ላይ ተገቢውን ቁጥጥር ሊያደርጉ አይችሉም’ የሚል እሳቤ በውስጣቸው ሊመላለስ ይችላል። ሆኖም እሳቤው እንደ ማንኛውም ሃሳብ በሃሳብነቱ ብቻ ቅቡል ቢሆንም፤ ሃቁን ግን ከህገ መንግስቱና እንደራሴዎቹ ራሳቸው በፓርላማ ቆይታቸው ከሚያከናውኗቸው ጠንካራ የቁጥጥር ስራዎች በመነሳት ለመገንዘብ የሚከብድ አይደለም።
እንደሚታወቀው በህገ መንግስቱ አንቀፅ 54 (4) ላይ፤ የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት አባላት የመላው ህዝቦች ተወካዮች መሆናቸውንና ተገዥነታቸውም ለህገ መንግስቱ፣ ለህዝቡና ለህሊናቸው ብቻ መሆኑ ተደንግጓል። ተግባራቸውን የሚከውኑትም ከዚሁ ድንጋጌ አኳያ ብቻ ነው። እርግጥ የምክር ቤቱ አባላት ስራ አስፈፃሚውን የሚቆጣጠሩት፤ ስህተቶች ካሉ በወቅቱ ታውቀው በፍጥነት እንዲስተካከሉ፣ በህዝቡ የሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢ ካልሆኑ ለማብራራት እንዲቻል፣ ተገቢ ከሆኑ ደግሞ በወቅቱ የመፍትሔ ርምጃ እንዲወሰድባቸው ለማድረግ ነው። ይህም ማንኛውም የስራ አስፈፃሚ አካል በመንግስት በጀት ቢመደብለትም ተግባሩን ግን በህዝብ ወገንተኝነት እንዲፈፅም እንደራሴዎቹ ክትትልና ቁጥጥር ብሎም የማስተካከያና የእርምት ርምጃዎች እንዲወሰድ እንዲያደርጉ ዕድል ይሰጣቸዋል።
ለነገሩ ስራ አስፈፃሚው የራሱን ዕቅድ ለመገምገም የሚያስችለው አሰራርና ስርዓት ያለው ነው። ዳሩ ግን ይህ ብቻ በቂ አይደለም። ምክንያቱም ፈፃሚው አካል ምንም እንኳን ራሱን በራሱ ሲገመግም ትክክለኛ ግምገማ ሊያካሂድ ቢሞክርም፣ ሁኔታዎችን ከራሱ ምልከታ አኳያ ማየቱ የሚቀር አይደለም። በመሆኑም ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው የህዝብ እንደራሴዎችና ሌሎች በአፈፃፀሙ ላይ ያልነበሩ ወገኖች የራሳቸውን ነፃ ግምገማ እንዲያካሂዱ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ መሆኑ አያጠያይቅም። እንዲህ ዓይነቱ አሰራር ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን የሚከተሉ ሀገራት የተለመደም ነው።
ያም ሆኖ አብዛኛዎቹ የገዥው ፓርቲ አባላት ከአፈፃፀም ስራው ነፃ ስለሚሆኑ፤ ከአስፈፃሚው ዕይታ ነፃ በሆነ አኳኋን ሁኔታዎችን የማየት ዕድል ይኖራቸዋል ተብሎ ይታመናል። ከዚህ በተጨማሪም ሥርዓቱን እንደ ሥርዓት ለማስቀጠል ህዝባዊ አደራ ያለባቸው ስለሆነ የአስፈፃሚውን ተግባራት ነፃ ሆነው ይገመግማሉ ተብሎ ይታሰባል። እናም የህዝብ እንደራሴዎቹ ትልቅ የግምገማ አቅም ናቸው።
ለነገሩ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን የመሳሰሉ ተቋማት ሲጀመር የተቋቋሙት ሥርዓቱ ራሱን በራሱ ለማረም (Check and Balance) እንዲያስችለው ታስቦ ነው። በእነዚህ ምክንያቶች ሳቢያም ተጠሪነታቸው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆኑ እንደ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዓይነት ተቋማት ገለልተኝነታቸው ጥያቄ ውስጥ ሊገባ የሚችልበት ምክንያት ሊኖር አይችልም—ሁሉንም ነገር በተዛነፈ ዕይታ ለመመልከት ካልተፈለገ በስተቀር።
እናም አንድ ሥርዓት ራሱን በራሱ ለማረም በራሱ ፈቃድ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንንና የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋምን የመሳሰሉ “አራሚ” ድርጅቶችን አቋቁሞ የዴሞክራሲ መርህን እውን ለማድረግ እየሰራ ያለ ሥርዓት ተመልሶ ራሱን እንዳያርም የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ገለልተኛ እንዳይሆን ያደርጋል ብሎ ማሰብ ቀልድ ነው። በራስ ህልውና ላይ እንደ መቀለድም የሚቆጠር ይመስለኛል። እናም ቢያንስ በሰከነና ህዝብን በሚያማክል መንገድ ትችትን መሰንዘር ተገቢ ነው። አሊያ ግን እዚህ ሀገር ውስጥ ሁሉንም ነገር በባለቤትነት መንፈስ በሚከታተለው ህዝብ የትዝብት ዕይታ ውስጥ መግባት ይሆናል። አንድን ጉዳይ መንግስት ስላከናወነው ብቻ እንዲያው በደፈናው ‘ትክክል አይደለም” ብሎ ማሰብም ሁሉንም ነገር በራስ መነፅር ከማየት የሚመነጭ ነው። ሁሉንም ነገር በራስ መነፅር ማየት ደግሞ፤ የሌላውን በጎ ነገር ለማየት የማያስችል ግርዶሽን መፍጠሩ አይቀርም። ታዲያ እንዲህ ዓይነቱ የተጋረደ ምልከታ በተሳሳተ መነፅር ዕውነታን አዛንፎ መመልከትን መፍጠሩ አይቀርም። በመሆኑም እዚህ ሀገር የተቋቋሙ የዴሞክራሲ ተቋማትን በጥላቻ መንፈስና የራስን ፖለቲካዊ ፍጆታ ለማሳካት ሲባል ብቻ “ገለልተኛ አይደለም” እያሉ አራምባና ቆቦ መርገጥ ተገቢ አይደለም።
በእኔ እምነት በመግቢያዬ ላይ በጠቀስኳቸው የሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ተፈጥሮ የነበረውን ሁከትና ግጭት ለመመርመር የኢፌዴሪ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ያህል የገለልተኝነት ሚና ሊወጣ የሚችል ተቋም የለም። የትኛውም የውጭ ተቋም በሀገራችን ውስጥ የተከሰተውን ሁከትና ግጭት እንደ የኢፌዴሪ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ያህል ቅርብ ሆኖ ሊያጣራ አይችልም። በምርመራው ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ሀገርኛ ጉዳዩችን በጥልቀት ለማየትና በአግባቡ ለማገናዘብ ከኮሚሽኑ ውጭ ማንም ቅርብ ሊሆን አይችልም።
እርግጥ እዚህ ላይ የኮሚሽኑን አቅም በዚህ ፅሑፍ መገምገም ባይቻልም፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን አቅሙን እያሳደገ መሆኑን ከሪፖርቱ ሚዛናዊነት ለመረዳት አይከብድም። ሌላው ቀርቶ የትኛውም አካል በሰፈረው ቁና መሰፈሩ እንደማይቀር ያቀረበው ሚዛናዊ ምክረ-ሃሳብ ተቋሙ ምን ያህል አቅሙን እያጎለበተ መምጣቱን የሚያሳይ ይመስለኛል። እናም “ገለልተኛው” ፈረንጅ ካልሆነ በስተቀር የኮሚሽኑ የምርመራ ውጤት ተዓማኒ አይደለም ብሎ ለመሞገት መሞከር ‘ፈረንጅ አምላኪ’ ከመባል በስተቀር ሌላ ትርጉም ሊሰጠው የሚችል አይመስለኝም።
የኮሚሽኑ የምርመራ ስራ እንደ ማንኛውም የምርመራ ሂደት ሳይንሳዊ መንገድን ተከትሎ ስለሚከናወን የተዓማኒነት ጥያቄ ይነሳበታል ብሎ ማሰብ አግባብነት ያለው አይመስለኝም። እንደሚታወቀው አንድ የምርመራ ጥናት በሳይንሳዊ መንገድ ሲካሄድ፤ የመረጃ ምንጮቹ ገለልተኛነት፣ የአጠናን ዘዴው “ወንዜነት” የሀገሪቱ ህጎችና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ከግምት ውስጥ ይገባሉ። ከዚህ አኳያ ኮሚሽኑ ምርመራውን ሲያካሂድ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ የመረጃ ምንጮቹን መርጧል። ዋነኛው የመረጃ ምንጭም ተጎጂውና ጎጂው የህብረተሰብ ክፍልና የመንግስት አካላት ናቸው። ተጎጂውን በአካባቢው በመገኘት በማነጋገርና ከዚያም ለችግሩ መንስኤ ናቸው የተባሉ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችን በመጠየቅ መረጃ አሰባስቦ ለሪፖርቱ የሚሆን ግኝትን አጠናቅሯል።
ከጥናቱ “ወንዜነት” አኳያም እንደ ኮሚሽኑ በቅርበት ወሳኝ ግብዓቶችን ሊያገኝ የሚችል ተቋም የለም። የሁከቱና የግጭቱን ታሪካዊ ዳራ ወደ ኋላ ሄዶ በመቃኘት አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አዛምዶ ትክክለኛ ድምዳሜ ላይም መድረስ ችሏል። የኮሚሽኑ መርማሪዎች ከህብረተሰቡ አብራክ የወጡ እንደመሆናቸው መጠን፤ የህዝቡ ችግሮች ችግራቸው፣ ስቃዩ ስቃያቸው በመሆኑ መሬት ላይ ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎችን ለመገንዘብና ተገቢው ድምዳሜ ላይ ለመድረስ አስችሏቸዋል።
ድምዳሜዎቹን ከሀገሪቱ ህጎች ጋር በማገናዘብ በመንግስት አካላት፣ በተቃዋሚ ፓርቲዎችና በተዋናይ ግለሰቦች የተፈፀሙ ጉዳዮች ተመጣጣኝ መሆኑንና አለመሆኑን በገለልተኝነት እንዲያገናዝቡም አድርጓቸዋል። ይህ ዕውነታም ሀገሪቱ የምትመራበትን ህገ መንግስትና ከእርሱ የሚመነጩ ህጎችን በመመርኮዝና ከህዝቡ ትክክለኛ ፍላጎት ጋር በማያያዝ ተዓማኒ የሆነ ሪፖርት እንዲያቀርቡ አስችሏቸዋል። በእነዚህ ሁሉ ጉዳዩችም የኮሚሽኑ ሪፖርት በምንም ዓይነት መስፈርት የተዓማኒነት ጥያቄ ሊነሳበት የሚችል አይደለም። እናም ኮሚሽኑ በሳይንሳዊ መንገድ ባካሄደው ምርመራ ሊመሰገን እንጂ ሊወቀስ የሚችልበት ሚዛን የሚደፋ መከራከሪያ ሊኖር የሚችል አይመስለኝም።

  1. Tessdubrtwill says

    Nice explanation. Thanks Mr. Zaman BelayBelay!!

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy