Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የወጣቶችን ስራ አጥነት የመቅረፍ ተግባር

0 1,745

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የወጣቶችን ስራ አጥነት የመቅረፍ ተግባር

                               ዳዊት ምትኩ

ይህን ጠጣጥፍ ለማዘጋጀት መነሻ የሆነኝ በቅርቡ “ሞ ኢብራሂም” የተሰኘው የጥናትና ምርምር ፋውንዴሽን “የወጣቶች ሥራ አጥነት ችግር ከኢትዮጵያ በቀር በመላው የአፍሪካ አህጉር ችግር ነው” በሚል ርዕስ የ51 የአፍሪካ ሃገራትን ኢኮኖሚ በመዳሰስ ይፋ ያደረገው ጥናት ነው። ጥናቱ ባለፉት አስርት ዓመታት የኢትዮጵያ የሥራ አጥነት ችግርና የወጣቶች የስራ አጥነት ችግር መጠን አንፃራዊ በሆነ መልኩ መረጋገቱን አስታውቋል።

እርግጥ የፋውንዴሽኑ ጥናት ትክክል ነው። የኢትዮጵያ መንግስት በተጠቀሱት ዓመታት የወጣቶችን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ብዙ መንገድ ተጉዟል። በተለይም በቅርቡ መንግስት ለወጣቶች የስራ ፈጠራ መነሻ የሚሆን 10 ቢሊዮን ብር በላይ ተዘዋዋሪ በጀት መድቧል። ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮችም ከበጀታቸው በመቀነስ  በተመሳሳይ ሁኔታ በጀት መድበዋል። በዚህም ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት ዘርፈ ብዙ ጥረቶችን እያደረጉ ነው።

መንግስትና ህዝቡ እንዲሁም የከተማ መስተዳድርች ከበጀቶቻቸው በመቀነስ ለወጣቶች የመደቡት ገንዘብ የተትረፈረፈ በጀት ስላላቸው አይደለም። ይልቁንም መንግስት ለህዝቡ ካለው ህዝባዊ ወገንተኝነት የመነጨ ነው። እናም ይህን የህዝብና የመንገስት ገንዘብ በአግባቡ ለታለመለት ዓላማ በማዋል አርአያ መሆን ይጠበቅባቸዋል።   

እንደሚታወቀው ሁሉ በዓመቱ መግቢያ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ለህዝብና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች በጋራ መክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ “…የሀገራችን ወጣቶች የወደፊቷ ኢትዮጵያ ገንቢዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ዛሬ በምንገኝበት ወቅት የራሳቸው ፍትሃዊ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ፍላጐትና ጥያቄዎች ያሏቸው በመሆኑ እነዚህን በአግባቡ የመመለስ ጉዳይ ቀዳሚ ትኩረት ይሰጠዋል” በማለት ተናግረዋል።

ይህ የመንግስት አቋምም ከወጣቶች ጥያቄዎች መካከል ሁሉንም ችግሮቻቸውን አስተሳስሮ የመፍታት ዕድል የሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን የማረጋገጥ ጉዳይ በመሆኑ ከያዝነው ዓመት ጀምሮ ወጣቶች የስራና የሃብት ፈጠራ እድላቸው በተጨባጭ እውን እንዲሆንና እየሰፋም እንዲሄድ ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግ መግለፃቸው ይታወሳል።

ወጣቶች የዚህች ሀገር ገንቢዎች ናቸው። ሀገራችንን ከድህነት ለማውጣት በሚደረገው ትግል ፋና ወጊዎች ሆነው መንቀሳቀስ ይገባቸዋል። በወጣቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ ሀገርን ማበልፀግ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል። በእኔ እምነት እንደ ኢትዮጵያ ያለ በርካታ ቁጥር ወጣት ያለው ሀገር በወጣቱ ላይ ኢንቨስት አድርጎ ከወጣቱ አፍላ ጉልበት የሚያገኘውን ልማታዊ ፋይዳ ማረጋገጥ ካልቻለ ሁለት ችግሮች ሊያጋጥሙት ይችላሉ። አንደኛው በርካታ ቁጥር ያለው ስራ አጥ ወጣት ይፈጠርና ይህ ስራ አጥ ኃይልም የራሳቸው አጀንዳ ያላቸው የውስጥና የውጭ ሃይሎች መጠቀሚያ ሆኖ ለሁከትና ብጥብጥ በር የሚከፍት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ሀገራት ከወጣቱ ማግኘት የሚገባቸውን የልማት ተጠቃሚነት ዕውን ማድረግ አይችሉም።

እርግጥ ስራ የሌለው ወጣት ማናቸውንም ጉዳዮች እንደ ስራ ሊመለከት ይችላል—የሁከት ተግባርንም ቢሆን። ይህ ደግሞ የተረጋጋ ሰላምና የልማት ስራ የሚከናወንበትን ሀገር ሊረብሽና ወደአልተፈለገ አቅጣጫ ሊወስድ ይችላል። ለዚህ አባባሌ በቅርቡ በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው የሁከት ተግባር ሁነኛ አስረጅ ይመስለኛል። ወጣቶች በየአካባቢያቸው ካለው የመልካም አስተዳደር ችግር በተጨማሪ በሚፈለገው መጠን ስራ ሳይፈጠርላቸው በመቆየቱ፤ ለሀገራችን የውጭ ጠላቶች ለሚላላኩ የጥፋት ሃይሎች ፀረ-ኢትዮጵያ አጀንዳ ሰለባ ሆነው ነበር።

ይህ ሁኔታም በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉ የሚዘነጋ አይደለም። እናም አስቀድሞ ወጣቱን በሚፈለገው መጠን በስራ እንዲታቀፍ ማድረግ ቢቻል ኖሮ፤ የተከሰተው ጥፋት ዕውን አይሆንም ነበር—ከሀገራዊ ልማት ተጠቃሚ የሆነ ወጣት በምንም መልኩ የሀገሩን ጥቅም በመፃረር የሌሎች ባዕዳን ሃይሎች መጠቀሚያ ሊሆን ስለማይችል ነው። እናም የኢፌዴሪ መንግስት ከዚህ ዓመት ጀምሮ ወጣቱን አቅም በፈቀደ መልኩ አደራጅቶ ከልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ፕሮግራም ቀርፆ ወደ ስራ መግባቱ ይበል የሚያሰኝ ተግባር ይመስለኛል።

ወጣቱ ኃይል አፍላ ጉልበት ያለው በመሆኑ፤ ሀገራት ይህን ለስራ ዝግጁ የሆነ ጉልበት በሚገባ መንገድ መጠቀም ይኖርባቸዋል። ይህን ጉልበት አጣጥሞ በተገቢው መንገድ መጠቀምም ለሀገራዊ ዕድገት ያለው ፋይዳ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። ወጣቶች በተፈጥሯቸው ሁሉንም ነገር የመስራት ስሜት የታደሉ ናቸው። እነርሱን በማናቸውም ሀገራዊ የልማት ትልሞች ውስጥ በማስገባት ማሳተፍ ስራዎችን በአፍላ ጉልበት እንዲሁም በፈቃደኝነትና በፍላጎት ስሜት ሊተገብሩት ይችላሉ።

ይህ ደግሞ የተያዙ ዕቅዶችን ለመፈፀምና የሚፈለገውን ሀገራዊ ዕድገት ለማምጣት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል። ስለሆነም በወጣቶች ላይ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ ውጤቱ መልሶ የሚከፍለው ሀገርን መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ለዚህም ነው— የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ለወጣቶች ተጠቃሚነት ትኩረት በመስጠት አባል ሀገራቱ ወጣቱን በስራ ፈጠራ በማነፅ ከአፍላ ጉልበቱ ሊጠቀሙ እንደሚገባ የመከረው።  

እርግጥ የኢፌዴሪ መንግስት ለወጣቶች የሰጠው ትኩረት የህብረቱን ፍላጎት አስቀድሞ የተገነዘበ ነው ማለት ይቻላል። ግና እዚህ ላይ ‘ወጣቶች ሀገራችን የሰጠቻቸውን ትኩረት እንደምን ሊጠቀሙበት ይገባል?’ የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል። አዎ! ምንም እንኳን የጥያቄው ምላሽ ሊኖር የሚችለው በወጣቱ ትጋት ውስጥ ቢሆንም፤ እኔም ለመነሻ ይሆኑ ዘንድ ጥቂት ግንዛቤ ማስጨበጫዎችን ለማንሳት እሞክራለሁ።

ወጣቱ የመንግስትን ትኩረትና የተመደበለትን ተንቀሳቃሽ ፈንድ በአግባቡ ለመጠቀም ራሱን ለስራ ዝግጁ ማድረግ ይኖርበታል። በእኔ እምነት ራስን ለስራ ማዘጋጀት አንድን ችግር ለመፍታት ግማሽ መንገድ እንደመሄድ ያህል ይቆጠራል። እናም ወጣቱ አስቀድሞ ራሱን ለማንኛውም ስራ ማዘጋጀት አለበት። ማንኛውም ስራ ከችግር መውጫ ቀዳዳ መሆኑን ማመን ይኖርበታል። በአጭሩ ወጣቱ ስራን ሳይንቅና ምናልባትም በስደት ቢሄድ ለባዕድ ሀገራት ሊያበረክተው የሚችለውን የጉልበት ስራ ዓይነት ጭምር ስራዎችን አክብሮ በመስራት የመንግስትን ትኩረት አሟጦ ሊጠቀምበት ይገባል። “ስራ ክቡር ነው” የሚለውን አርማ ከፍ አድርጎ ማውለብለብ ይጠበቅበታል። ያኔ ራሱን፣ ቤተሰቡንና ከምንም በላይ እያሰበችለት ያለችውን ሀገሩን መጥቀሙ አጠያያቂ አይሆንም።

ከዚህ በተጨማሪም ወጣቱ ስራ ፈጣሪ እንጂ ስራ ጠባቂ ሊሆን አይገባም። ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የፌዴራል መንግስትና ክልሎች ወጣቱ በስራ ውስጥ እንዲያልፍ ተንቀሳቃሽ ፈንድ አዘጋጅተዋል። ወጣቱ በዚህ ፈንድ እንደምን ራሱን ለስራ ዝግጁ ማድረግ እንደሚችል ማሰብ ይኖርበታል። በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ውስጥ የተመቻቸ የስራ ምህዳር አለ። ዋናው ነገር ይህን ምቹ የስራ ድባብ በፈጠራ ክህሎት አጅቦ እንዴት ውጤታማ ማድረግ እንደሚቻል ማወቁ ላይ ነው።

እናም አንድነት ኃይል በመሆኑ፤ በቅድሚያ ተደራጅቶ አዋጪ ስራን መምረጥ፣ የተገኘን ባጀት በስራ ላይ ብቻ ማዋል፣ እንደ አንድ ሆኖ ማሰብ፣ በተመረጠው ስራ ላይ በእኔነት መንፈስ መንቀሳቀስ እንዲሁም ከተጀመረው ስራ የሚገኝ ትሩፋትን በቁጠባና አግባብ በሆነ መንገድ ብቻ መጠቀም ከወጣቱ የሚጠበቁ ተግባሮች ናቸው። ስለሆነም ይህ ሀገር ተረካቢ ትውልድ በመንግስት በኩል የተዘጋጀለትን ስራ አጥነትን የመቅረፍ ተግባር ይጠቀምበት። ይህ ስራ አጥነትን የመቅረፍ ተግባር በእነ “ሞ ኢብራሂም” ፋውንዴሽን ሳይቀር በጥናት ላይ ተመርስቶ የተረጋጋጠ በመሆኑ አሉባልታዎችን ሳይሰማ በተዘጋጀለት የስራ ፈጠራ “ድግስ” ሊጠቀም ይገባል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy