Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የዴሞክራሲ ተቋሞቻችንን መሻሻል

0 335

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የዴሞክራሲ ተቋሞቻችንን መሻሻል /ዮናስ/

ያሳየ ሪፖርት

ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ-ግብር የትግበራ ምዕራፍ የተሰኘውን እና ለዓለም አቀፋዊ እና አህጉራዊ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች ተገዢ መሆኑ የተነገረለትን ሠነድ ሀገራችን ይፋ ካደረገች እነሆ ሁለት ዓመታት አልፈዋል። ጥቅምት 15 ቀን 2007 ዓ⁄ም ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ባለድርሻ አካላቶች ሁሉ በተገኙበት ነበር በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር ይለማርያም ደሳለኝ አማካኝነት ሠነዱ ይፋ ለመሆን የበቃው ።

ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማክበር እና ማስከበር የሀገር ግንባታን ያህል ቁልፍ እና የህልውና አጀንዳ ነው። በመሆኑም ይህንኑ ከሕገ መንግሥቱ ጋር በማጣጣም ዝርዝር ሕጎች ማውጣት እና ለተግባራዊነቱ  በጽናት እና በትጋት በመሥራት መሠረታዊ ለውጥ ማስመዝገብ እንደሚያስፈልግ መርሐ-ግብሩ ይፋ በተደረገበት ሰዓት ተሰምሮበት የነበረ ጉዳይ መሆኑ ይታወሳል። የመብቶች ፍረጃ እና ቅደም ተከተል ሳይቀመጥ የጋራ እና የግል መብትም ሆነ ሌሎች መብቶች ሳይነጣጠሉ ተደጋግፈው የሚጠበቁበት ስርዓት መዘርጋት ለሠላም፣ ለልማት እና ለዴሞክራሲ ሥርዓቱ ጠንቅ የሚሆኑ ምክንያቶችን ለማስወገድ ያስችላል።

ለሰብዓዊ መብት መከበር እንቅፋት ከሚሆኑ ችግሮች መካከል፤ የመልካም አስተዳደር አለመስፈን አንዱ በመሆኑ በዘርፉ የሚስተዋለውን ችግር ለማስወገድ ከሕዝቡ ጋር ተከታታይነት ያለው ውይይት ማስፈለጉም አያከራክርም። በእርግጥ አሁን በሀገራችን ያለው ሁለንተናዊ ዕድገት ከሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ውጪ የተሣካ አለመሆኑም አያከራክርም። በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 13(2) መሠረት ዓለም አቀፋዊ እና አህጉራዊ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችን በመቀበል እና በማጽደቅ የሀገሪቷ የሕግ አካል ሆነው እንዲተገበሩ በማድረግ በዓለም ከሚገኙ ሀገራት ባልተናነሰ መልኩ ላፊነቷን በመወጣት ላይ መገኘቷ ይታወቃልና።  

የሰብዓዊ መብት ጉዳይ በሕገ መንግሥቱ በዋናነት ሁለት መሠረታዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ ያለመ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ አንደኛው ለዘመናት የግጭት ምክንያት የሆነውን ሥልጣን እና ሀብት በማዕከል እና በጥቂጥ ይሎች መከማቸት የፈጠረውን ችግር ለመመለስ ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና ያለው የፌዴራል ሥርዓት ማለትም ሥልጣን እና ሀብት በፌዴራል እና በክልሎች መካከል መከፋፈሉ እንዲሁም የሕዝቦች የማንነት ጥያቄ ለመመለስ ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት የሚቀበል መሆኑ ነው፡፡   ዋና መነሻውም ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር ከቻሉ የራሳቸውን ማንነት፣ ቋንቋ እምነት እና  ታሪክ ለማሳደግ እና ወደ ቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ ይችላሉ የሚል ነው፡፡

ዞሮ ዞሮ የመንግሥት ሥልጣን ምንጩ ሕዝብ /ዜጎች/ እንደሆኑ እና መንግሥትም ከሕዝብ ላገኘው ሥልጣን የዜጎችን መብት የማክበር ግዴታ እንዳለው የሚያስገነዝብ  ጽንሰ ሀሳብ ነው፡፡  

እነዚህ መብቶች እንደ አብዛኞቹ ፀሐፊዎች ሰው ሰው በመሆኑ ብቻ የሚጎናፀፋቸው መንግሥትም (ሕገ-መንግሥትን) ጨምሮ ዕውቅና ከመስጠት ባለፈ እነዚህን መብቶች የማክበር ግዴታ (ከሞላ ጎደል መንግሥት በዜጎች  መብት ጣልቃ ባለመግባት) ግዴታውን ሊወጣ ይችላል ተብለው የሚታሰቡ ናቸው፡፡ ይህ አገላለጽ ግን ለተወሰኑ መብቶች የሚገልጽ ቢሆንም ሁሉም የፖለቲካ እና ሲቪል መብቶች በዚህ ይገለፃሉ ማለት ትክክል አይደለም፡፡ ለምሳሌ ሠላማዊ ሰልፍ የማድረግ እና ፍትሕ የማግኘት መብት ከመንግሥት ብዙ እገዛ የሚጠይቁ መብቶች መሆናቸውን ብዙዎቹ ፀሐፊዎች ይገልፃሉ፡፡  

በጥቅሉ ባለፉት 10 ዓመታት ወደ ጋራ መግባባት የተደረሰበት ነጥብ ቢኖር መብቶች በየትኛውም ጎራ ይከፈሉ፤ ሁሉም መብቶች የማይነጣጠሉ እና የተያያዥ እንዲሁም በሁሉም የዓለም አካባቢ መፈፀም ያለባቸው መሆኑን ነው፡፡ ይህ ሲባል መብቶች በየሀገሩ የፍትሕ እና የፖለቲካ ተቋማት ተግባር ላይ ሲውሉ ሀገራቱ የየሀገራቸውን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ አያስገቡም ማለት አይደለም፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ፀሐፊዎች እንደሚሉት የዜጎች መብት በአንድ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ለብቻ ተነጥሎ የሚታይ ሳይሆን፤ ከተቋሞች ጥንካሬ፤ ከዴሞክራሲ ዕድገት፤ በተቋሞች መካከል የሥልጣን ክፍፍል እና (Checks and Balance) ከመኖር እና ካለመኖር ጋር የተቆራኘ እንደሆነ ነው፡፡

ሌላው ሰብዓዊ መብቶች ባንድ ሀገር እንዲፈፀሙ ቀዳሚው ኃላፊነት በሀገሪቱ ፍ/ቤቶች፣ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽኖች እምባ ጠባቂ እና ለሌሎች ተመሳሳይ ሀገራዊ ተቋሞች  የተሰጠ መሆኑ እና ይህ ተፈፃሚ ባልሆነበት ሁኔታ ብቻ ነው ዓለም አቀፍ ተቋሞች ጣልቃ ሊገቡ የሚችሉት የሚለው አስተሳሰብ ሰፊ ስፍራ መያዙም ስለአጀንዳችን ሊታወስ ይገባል፡፡ አጀንዳችን ከላይ ወሳኝ እንደሆኑ ከተመለከቱት ተቋማት መካከል ጥርስ የሌለው አንበሳ እንደሆነ አንዳንዶች ሲናገሩለት የነበረው  የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ነው። ኮሚሽኑ ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበ እና በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች አንዳንድ ቦታዎች፣ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ጌዲኦ ዞን ከሰኔ ወር 2008 ዓ.ም እስከ መስከረም 2009 ዓ.ም ተከስቶ የቆየውን ሁከት እና ብጥብጥ የተመለከተ የምርመራ ውጤት ሪፖርት ስንመለከት ግን ከላይ የተመለከተው ዕይታ ጭፍን የነበረ መሆኑን ለመረዳት ያስችለናል ። ይልቁንም ኢትዮጵያ ደረጃው ይነስ ይብዛ ካልሆነ ያስመዘገበችው ውጤት ከሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ማክበር እና ማስከበር ውጭ እንዳልሆነ የሚያጠይቅ ነው።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶ/ር አዲሱ ገ/እግዚአብሔር ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ በግልጽ እንደተመለከተው ሁከት እና ብጥብጡ በኦሮሚያ ክልል በ15 ዞኖች እና በ91 ወረዳዎች ማለትም በፊንፊኔ ዙሪያ፣ ምሥራቅ፣ ምዕራብ እና ሰሜን ሸዋ፣ በምዕራብ እና ምሥራቅ ሐረርጌ፣ በወለጋ፣ በምዕራብ ወለጋ፣ በቄለም ወለጋ፣ በጉጂ፣ በባሌ ፣በምዕራብ እና ምሥራቅ አርሲ እንዲሁም በአማራ ክልል በ6 ዞኖች እና 55 ወረዳዎች ማለትም በሰሜን ጎንደር ፣ በደቡብ ጎንደር፣ በባህር ዳር፣ በምዕራብ እና ምሥራቅ ጎጃም፣ በአዊ ዞን፣ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል በጌዲኦ ዞን 6 ወረዳዎች አዳርሷል።

የኮሚሽኑ ምርመራ መሠረት ያደረገው በዋንኛነት የኢፌዲሪ ሕገመንግሥት ምዕራፍ 3 የተቀመጡትን የሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ  መብቶች እንዲሁም ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት አጽድቃ የሕግ አካልዋ ያደረገቻቸው ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶችን ስለመሆኑም በሪፖርቱ ተመልክቷል። በዚህ መሠረት በሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች መካከል በሕይወት የመኖር መብት፣ የአካል ደህንነት መብት፣ የነጻነት እና እኩልነት መብት፣ የአመለካከት እና ሀሳብን በነጻ የመያዝ እና የመግለጽ መብት፣ የመሰብሰብ፣ ሠላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነት እና አቤቱታ የማቅረብ መብት፣ የመዘዋወር ነጻነት፣ ፍትሕ የማግኘት መብት፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ እና የባህል መብት የምርመራው የትኩረት ነጥቦች እንደነበሩ ዶ/ር አዲሱ ተናግረዋል።

በኮሚሽነሩ ሪፖርት መሠረት በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች በተቀሰቀሰው ሁከት እና ብጥብጥ ብቻ 462 ሲቪል ሰዎች፣ 33 የጸጥታ ኃይሎች፣ በድምሩ 495 ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል። 338 ሲቪል እና 126 የጸጥታ ኃይሎች በድምሩ 464 ሰዎች የአካል ጉዳት የደረሰ ሲሆን፤ በመቶ ሚሊየን የሚገመት የሕዝብ፣ የመንግሥት እና የግል ባለሀብቶች ንብረትም ወድሟል።

በተለይ በኦሮሚያ ክልል መስከረም 22 የተከበረው የእሬቻ በዓል ላይ የተሰቀሰቀሰውን ሁከት እና ብጥብጥ ለመቆጣጠር ከተተኮሰው አስለቃሽ ጢስ ለመሸሽ የሞከሩ ሰዎች ወደ ገደል በመግባታቸው እና በመረጋገጥ አደጋ የ56 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ኮሚሽኑ ባደረገው ሰፊ እና ጥልቅ ምርመራ ማረጋገጡን የሚጠቅሰው ሪፖርት፤ የሁከት እና የብጥብጥ ግልጽ አደጋ መደቀኑ እየታወቀ እና እየታየ በዓሉ እንዲካሄድ መደረጉ ኃላፊነት የጎደለው ውሳኔ መሆኑን  በመጥቀስ በዚህ ውሳኔ ውስጥ ያሉ የመንግሥት አካላት እና የበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴ አባላት በየደረጃው ሊጠየቁ የሚገባ መሆኑን ገልጿል። በተጨማሪም በዓሉ የሚካሄድበት እና ለሰዎች መሞት አንዱ መንስዔ የሆነው ሆራ አርሰዲ ገደል አስቀድሞ መደፈን ይገባው እንደነበር ዶክተር አዲሱ ጠቅሰው፤ ይህ ባለመደረጉ ለደረሰው አደጋ የሚመለከታቸው የአስተዳደር አካላት ተጠያቂ ናቸው ሲሉ ደግመው ደጋግመው ለምክር ቤት አባላቱ መግለጻቸው የኮሚሽኑን ነጻነት እና የቁርጠኝነት ልክ የሚያሳይ ነው። በእሬቻ በዓል ወቅት በስፍራው የተሰማሩ የኦሮሚያ ክልል የጸጥታ አስከባሪዎች ሁኔታውን ለማረጋጋት ትግዕስት በተሞላበት መንገድ ሙያዊ ተግባራቸውን መፈጸማቸው የሚያስመሰግናቸው ቢሆንም፤ ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ ብጥብጥ ለማስነሳት የተዘጋጁ ኃይሎች መኖራቸው እየታወቀ ተገቢውን እርምጃ በወቅቱ ባለመውሰዳቸው ተጠያቂ መሆናቸውን የተመለከተውም የኮሚሽኑ ማሳሰቢያ በተመሳሳይ የሚያሳየውም የተቋሙን ነፃ እና ገለልተኛነት  ነው።

ሪፖርቱ ሲቀጥል ጌዲኦ ዞን በ4 ወረዳዎች እና በ 2 የከተማ መስተዳድሮች ማለትም ዲላ ከተማ፣ ዲላ ዙሪያ ወረዳ፣ ወናጎ ወረዳ፣ ይርጋጨፌ ወረዳ፣ ይርጋጨፌ ከተማ እና ኮሸሬ ወረዳ ሁከት እና ብጥብጡ መስከረም 27 ቀን 2009 ከጠዋቱ 4፡00 ሰዓት ጀምሮ ለሁለት ቀናት መካሄዱን ያስታውሳል። የሁከቱ መንስዔ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የተሰጠ የይዞታ ውሳኔ ጉዳይ አንቀበልም የሚሉ ወገኖች ያስነሱት መሆኑን የሚገልጸው ሪፖርት ፤ በዚህ ሁከት እና ብጥብጥ ዘር እና ጎሳን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች መድረሳቸውን ያረጋግጣል። በዚህ ጥቃት 34 ሰዎች ሲሞቱ፣ 60 ሰዎች ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ 4 ሺህ ያህል ሰዎች ተፈናቅለዋል። በዚህ ድርጊት እጃቸው ያለባቸው  የመንግሥት የአስተዳደር አካላት እና ግለሰቦች ተጠያቂ መሆናቸውን በመግለጽ፤ የክልሉ መንግሥት ተፈናቃዮችን እና ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባው በሪፖርቱ ተመላክቷል።

በአማራ ክልል በ6 ዞኖች እና 55 ወረዳዎች ማለትም በሰሜን ጎንደር ፣ በደቡብ ጎንደር፣ በባህር ዳር፣ በምዕራብ እና ምሥራቅ ጎጃም፣ በአዊ ዞን፣ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል በጌዲኦ ዞን 6 ወረዳዎች እና ከተማዎች ሁከት እና ብጥብጥ መታየቱን የኮሚሽኑ ሪፖርት ያሳያል። በተለይም በሰሜን ጎንደር ዞን ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ ሰልፎች እና አለመረጋጋት የነበረ ሲሆን፤ ሕዳር 29 ቀን 2008 ዓ.ም በመተማ ወረዳ የነበረው በሕግ ዕውቅና የሌለው ሰልፍ ተከትሎ በተፈጠረው ሁከት እና ብጥብጥ በቅማንት ብሔረሰብ እና በአማራ ብሔር መካከል ግጭት ተነስቶ የሰው ሕይወት መጥፋት፣ አካል መጉደል እና ንብረት መውደም መንስዔ ሆኗል። በተጨማሪም በሰሜን ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ አካባቢ ብሔርን ማዕከል ያደረገ ጥቃት በትግራይ ተወላጆች ላይ መፈጸሙን ዶ/ር አዲሱ ገ/እግዚአብሔር በሪፖርታቸው አመላክተዋል።

አያይዘውም በ2008 ዓ.ም በተለያዩ አካባቢዎች “የወልቃይት የማንነት ጥያቄ አልተመለሰም፣ የአማራ ክልል ካርታ ተቆርጦ ወደ ትግራይ ክልል ሄዷል፣ የትግራይ ብሔር የበላይነት አለ፣ የራስ ዳሸን ተራራ የሚገኘው በትግራይ ክልል ውስጥ ነው ተብሎ በመማሪያ መጽሐፍ መታተሙ አግባብ አይደለም እንዲሁም በትግራይ እና አማራ ክልሎች መካከል የሚገኘው የጸገዴ ወሰን ጥያቄ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል” በሚሉ ምክንያቶች በተለያዩ ጊዜያት ሁከት እና ብጥብጥ እንደነበረ ሪፖርቱ ያስረዳል።

ይህ ሁኔታ እንዳለ ሆኖ የፌዴራል የጸረ ሽብር ግብረ ኃይል በጎንደር ከተማ ማራኪ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሽብር ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ሐምሌ 4 ቀን 2008 ዓ.ም ከለሊቱ 10፡30 ሰዓት ባለው ጊዜ ያደረገውን እንቅስቃሴ ተከትሎ ሁከት እና ብጥብጥ ተፈጥሯል። የነበረው አለመግባባት ወደ ተኩስ ልውውጥ አምርቶ የአካባቢው ነዋሪዎች እና የፌዴራል ፖሊስ አባላት የሕይወት መጥፋትን አስከትሏል። ይህን ችግር ተከትሎ እንደፌስ ቡክ ባሉ ማኅበራዊ ድረ ገጾች እና በኢሳት ቴሌቭዥን በኩል ሁከቱን ለማባባስ በመሞከሩ ሐምሌ 24 ቀን 2008 ዓ.ም በጎንደር ከተማ ሕገ ወጥ ሰልፍ መካሄዱን እና ይህንንም ተከትሎ በየአካባቢው ሰልፎች መካሄዱን የኮሚሽኑ ሪፖርት ይገልጻል።  

በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በተነሳው ሁከት 110 ሲቪል ሰዎች እና 30 የጸጥታ አባላት ሲሞቱ፣ 276 ሲቪል ሰዎች እና 100 የጸጥታ ኃይሎች ጉዳት እንደደረሰባቸው በሪፖርቱ ተጠቅሷል።

በሁሉም አካባቢዎች ለተነሱ ግጭቶች እንደመንስዔ ከተቀመጡት መካከል ሥር የሰደደ የመልካም አስተዳደር ችግር መኖር፣ የሥራ አጥነት፣ ሙስናን የብልሹ አሠራር መንሰራፋት፣ የልማት ዕቅዶች በወቅቱ ተግባራዊ መሆን ያለመቻል፣ የኑሮ ውድነት እና የመሳሰሉ ችግሮች ተመልክተዋል። በግጭቶቹ እጃቸው አለበት ከተባሉት መካከል በኢፌዴሪ ፓርላማ በአሸባሪነት የተፈረጀው ኦነግ፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረንስ፣ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔት ወርክ፣ በየደረጃው ያሉ ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ የመንግሥት አካላት በሕግ ሊጠየቁ እንደሚገባ የሚያሳስበው የኮሚሽኑ ሪፖርት በእርግጥም የዴሞክራሲ ተቋሞቻችንን መሻሻል እና ያላቸውን ጉልበት እየተጠቀሙ ስለመምጣታቸው ሲሆን፤ በዚህም የሕልውናችን ጉዳይ ነው ለምንለው መልካም አስተዳደር ሚናቸውን በመወጣት ወደምናስበው ደረጃ መድረስ የምንችልበት ሥርዓት መሠረት እየያዘ መምጣቱን ነው

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy