Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የጥልቅ ተሃድሶው ግብ ምን ነበር?

0 337

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የጥልቅ ተሃድሶው ግብ ምን ነበር?

ሰለሞን ሽፈራው

ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ውስጣዊ ችግሮቹን ከመቸውም ጊዜ በተሻለ ጥልቀት ለመፈተሸና ትርጉም ባለው መልኩ ለመቅረፍም ጭምር ያለመ ተሃድሶ ማካሔድ ከጀመረ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ በዚህ መሰረትም፤ ከመስከረም 2009 ዓ.ም ጀምሮ ያሉትን ወራት በሙሉ፤ መንግስትና ገዥው የፖለቲካ ፓርቲ ይፋ ያደረጉት የጥልቅ ተሃድሶ መድረክ ሲካሔድ የቆየባቸው ነበሩ ብንል ስህተት አይሆንም፡፡

በተለይም ደግሞ፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ የተያያዘቸውን ፈርጀ ብዙ የልማት ጉዞ ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማድረግ የሚያስችለንን አመራር ይሰጣል ተብሎ ስለታመነበት በምርጫ ያሸነፈበትን የህዝብ ድምጽ ያገኘውና የመንግስት ስልጣን ላይ ያለው ገዥ ፓርቲ ኢህአዴግ፤ የጥልቅ ተሃድሶውን አስፈላጊነት በተመለከተ አበክሮ ሲናገር የተደመጠበት አግባብ ሲታወስ፤ ጉዳዩ የተለየ ግምት ይሰጠው ዘንድ ምክንያት ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡ እናም የግንባሩ ከፍተኛ የአመራር አካል ተደርጎ የሚወሰደው፤ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ፤ ነሀሴ 15 ቀን 2008 ዓ.ም ያወጣውን መግለጫ ተከትሎ በይፋ የተጀመረው የጥልቅ ተሃድሶ መርሐ ግብሩ፤ አራቱን የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ባማከለ መልኩ ከከፍተኛው የስልጣን ዕርከን እስከ የታችኛው የፓርቲ መዋቅር ድረስ ደረጃ በደረጃ ቁልቁል የወረደበትን የግምገማ ሂደት ስንታዘብ መቆየታችን የሚካድ ጉዳይ አይደለም፡፡

ለወራት በዘለቀ ተከታታይ የግምገማ መድረክ አማካኝነት፤ በተለይም የገዢውን ፓርቲ ድርጅታዊ ቁመና አስተማማኝ ጫንቃ እንዲኖረው ለማድረግ ያለመ የመዋቅር ማጥራት እንቅስቃሴ ሲጀመር ስሞን ሁለት ዓይነት ስሜት የተንፀባረቀበትን የድጋፍና የተቃውሞ አስተያየት አስከትሎ እንደነበርም ማስታወስ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ስለሆነም፤ ያኔ የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር መክሮ ዘክሮ ይፋ ያደረገውን የጥልቅ ተሃድሶ አስፈላጊነት፤ ደግፈን የፃፍን ዜጎች የመኖራችንን ያህል፤ ጉዳዩን አምርረው ሲቃወሙት የተስተዋሉ ወገኖች ጥቂት እንዳልነበሩም ነው እኔ በግሌ የማስታውሰው፡፡

ኢህአዴግና መንግስት ራሳቸውን በጥልቀት ለማደስ የሚያስችላቸውን ሰፊ የግምገማ መድረክ ለመክፈት ስለመወሰናቸው ለህዝብ ይፋ ያደረጉበትን፤ መግለጫ አስፈላጊ እንዳልሆነ ቆጥረው ተቃውሟቸውን ሲገልፁ የተስተዋሉት ወገኖች “የገዢው ፓርቲ ዳግም ተሃድሶ የእባብ ነው ወይስ የንስር አሞራ?” ከሚል ምፀታዊ ጥያቄ ጀምረው ጉዳዩን ለማጥላላትና የተለመደ የኢህአዴግ መሪዎች “ማደናገሪያ” እንደሆነ የሚያስመስል ማጥላላት የተንፀባረቀበትን ሃሳብ መሰንዘራቸውን በተለይም አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ያኔ ካስነበቡን ትችታቸው መረዳት ይቻላል፡፡

“ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ሀገር መምራት ስላቃተኝ እነሆ ስልጣኔን ህዝብ ይረከበኝ ማለት ሲገባው፤ ዛሬም እንደገና እታደሳለሁ የሚለን፤ እንደ እባብ ከላይ ያለውን ቆዳውን ብቻ አውልቆ ጥሎ አዲስ የሚመስል ገፅታ በማሳየት ዕድሜውን ለማራዘም ስለፈለገ ነው እንጂ፤ እንደ ንስር አሞራ ትርጉም ያለው የባህሪ ለውጥ በሚያስከትል መልኩ ለመታደስ አይደለም”  የሚል ጭብጥ የነበረውን የተቃውሞው ጎራ ፖለቲከኞች የማጥላላት ዘመቻ በፊታውራሪነት የጀመሩት አቶ ሞሺ ሰሙ እንደሆኑም ማስታወስ ይቻላል፡፡ ከዚያም ደረጀ በላይነህ የሚባሉ የጋዜጣው አምደኛ “ኢህአዴግ ላባዎቹን አራግፎ ንስር ሊሆን አይችልም” ሲሉ በደመደሙበት ርዕስ ያቀረቡት ሌላ የማጥላት ፅሁፍ የአቶ ሞሼን ሃሳብ ለጠቁበት፡፡ እንዲሁም ዶክተር ዳኛቸው አሰፋንና ዶክተር በድሉ ዋቅጅራን ጨምሮ፤ ሌሎችም ስርዓቱን አምርረውና አክርረው ሲቃወሙ የምናውቃቸው የመዲናችን ልሂቃን፤ ተመሳሳይ አቋም ያንፀባረቁበትን ጸረ ተሃድሶ የማጥላላት ዘመቻ ተቀላቅለው እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ከዚህ አኳያ የሚገለፅ የተቃውሞ ፖለቲካ  የሚያራምዱት ወገኖች በወቅቱ ያነሱት ሃሳብ ሲጠቃለል “ኢህአዴግ ያረጀ ያፈጀ ፓርቲ እንደመሆኑ መጠን ሊታደስ አይችልምና ይልቅስ የአራት ኪሎውን ቤተመንግስት ለኛ አስረክቦ ወደሚሔድበት ይሂድልን” እንደማለት የሚቆጠር ቅኝት ያዘለ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡

እናም በወቅቱ፤ ይህን የፅንፈኛ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች አቋም እንደማልቀበለው ለመግለጽ ፈልጌ “በቅሎ አትወልድም፤ የሚወልድም አትወድም” በሚል ርዕስ የፃፍኳትን ትችት አዘል ማስታወሻ፤ “የኢህአዴግን ማሊያ ለብሰው እንዲጫወቱ ተልዕኮ የተሰጣቸው የእነርሱው ደጋፊዎች፤ በእጅ አዙር የሳንሱር መቀሳቸው ውድቅ አድርገውብኛል፡፡ ይህን ስልም ደግሞ ኢህአዴግ መራሹ የኢትዮጵያ ህዝቦች የትግል መስመር፤ በረጅም ታሪኩ ያጋጠሙትን መሰል ፈተናዎች ተጋፍጦ እያለፈ ዛሬ ላይ ለመድረስ የቻለባቸውን ጠቃሚ የፖለቲካዊ ባህል እሴቶች ጠብቆ እንዳይቀጥል የሚያደርግ እክል የመፍጠሩን የፅንፈኛ ተቃዋሚዎች ደባ፤ በመፈፀም ረገድ፤ ለሚደረግ እንቅስቃሴ ራሱው ገዥ ፓርቲ ውስጥ ተሰግስገው ስርዓቱን የመገዝገዝ እኩይ ተልዕኮ በተሰጣቸው የመንግስታዊው ስራ “ኤክስፐርቶች” አማካኝነትም ጭምር የሚከወንበት አግባብ መኖሩን ልብ ትልሉኝ ዘንድ ማስገንዘቤ ነው፡፡

ከዚህ ዓይነቱ የትምክህትና የጠባብ ብሔርተኝነትን ጽንፈኛ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ በማቀንቀን የሚታወቁት ተቃዋሚ ቡድኖች፤ ፌደራላዊ ስርዓቱን በህዝብ ዘንድ አመኔታ እንዲያጣ ለማድረግ ሲሉ ከሚፈፅሙት ደባ ጋር በተያያዘ የእክል ፈጠራ ተግባር ላይ የሚሰማሩትን ወገኖች “የኢህአዴግን ማሊያ ለብሰው የሚጫወቱ” እያሉ የሚገልፅዋቸውም ያለምክንያት አይደለም፡፡ ይልቅስ ተጠቃሾቹ መሀል ሰፋሪ ሃይሎች በተለያዩ ቁልፍ በሚባሉ የመንግስታዊ ስራ መዋቅሮች ውስጥ ተሰግስገው፤ ከሚፈጽሙት የተቃውሞ ፖለቲካ ደባና ከሚያደርጉት ቡድናዊ የእክል ፈጠራ እንቅስቃሴ አኳያ “የኢህአዴግን ማሊያ ለብሰው በመጫወት ስርዓቱን ከውስጥ ቦርቡረው ለመጣል የሚታገሉ” ተደርገው እንዲወሰዱ ቢያስችላቸው የሚያስገርም ጉዳይ አይሆንምና ነው፡፡

እንግዲያውስ እንደኔ እምነት ከሆነ፤ የገዥው ፓርቲ አባል ድርጅቶች ከዚህ ከያዝነው የ2009 በጀት ዓመት መጀመሪያ አንስተው ሲያካሒዱት የቆየው የጥልቅ ተሃድሶ መድረክ፤ አስፈላጊ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው፤ ቢያንስ “የኢህአዴግን ማሊያ ለብሰው እንዲጫወቱ” ሲባል መዋቅሩ ውስጥ ከላይ አስከታች ተሰግስገው የሚገኙትን መሀል ሰፋሪ  ቡድኖች  ከአፍራሽ እንቅስቃሴያቸው እንዲታቀቡ የሚያደርግ የእርምት እርምጃ መውሰድን የሚጨምር ሲሆን ይመስለኛል፡፡ በተለይም የፖለቲካ ድርጅት አባል የሚያሰኛቸውን ጭምብል እያጠለቁ በማምታታት ብቻ የማይገባቸው የመካከለኛና እንዲሁም የዝቅተኛ አመራር ደረጃ ላይ ተቀምጠው፤ ቅንጣት ያህል የኢህአዴግነት አዝማሚያ የማይስተዋልበትን ትምክህት፤ አሊያም ደግሞ የጠባብ ብሔርተኝነት አስተሳሰባቸውን የሚያንፀባርቅ ፅንፈኛ አቋም ሲያራምዱ የሚታዩና መላው የሀገራችን ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነታቸው ተረጋግጦ የሚኖሩባትን ፌደራላዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት ሲሉ ያስቀመጡትን ሕገ መንግስታዊ ቃል ኪዳን የመሸርሸር ተልዕኮ እንዲያስፈፅሙ የተነገራቸው ያህል ዜጎችን በብሔር ተወላጅነታቸው እየፈረጁ ጎራ ለይተው አላስፈላጊ ፍጥጫ ውስጥ እንዲገቡና እርስ በርስ ወደመጠላለፍ በሚወስድ ጭፍን የጥላቻ ስሜት የጎሪጥ እንዲተያዩ የሚያደርግ አሉታዊ ሚና በመጫወት ላይ ያሉትን አካላት በቸልታ ማለፍ ማለት፤ ሃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው ሊባል የሚችል ይመስለኛል፡፡      

ይህን የምንልበት መሰረታዊ ምክንያትም፤ ኢህአዴግ መራሹ የኢትዮጵያ ህዝቦች ትግል የሚመራበትን የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመር አስፈላጊነት ከሀገራችን ተጨባጭ እውነታዎች ጋር በተገናዘብ መልኩ ተረድተው ሳያምኑበት ጭምር፤ የግንባሩን አባል ድርጅቶች እየተቀላቀሉ ፖለቲካዊ ስልጣን አስከመጨበጥ የመድረስ ዕድል የገጠማቸው አንዳንድ የፌደራሉ መንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ ወገኖችና እንዲሁም ደግሞ በየክልላዊ መስተዳድሮቹም ጭምር የማይገባቸውን የሃላፊነት ቦታ ይዘው የሚገኙት መሰሎቻቸው፤ በህዝቡ ላይ እያደረሱ ያሉትን አጠቃላይ እንግልት ማስቀረት እስካልተቻለ፤ ብዙ የተባለለት የጥልቅ ተሃድሶው መርሐ ግብር የሚጠበቀውን ያህል አመርቂ ውጤት ያመጣል ለማለት እንቸገራለንና ነው፡፡ ያ ሲሆን ደግሞ፤ ሁሌም ስርዓቱን በሀገራችን ህዝቦች ዘንድ አመኔታ እንዳያገኝ ለማድረግ ያለመ ፈርጀ ብዙ ሴራቸውን ከማውጠንጠንና የፈጣን ልማት ጉዟችንን ለመቀልበስ የሚሞክሩበትን ውስብስብ ፖለቲካዊ ደባ ከመፈፀም ቦዝነው ለማየውቁት፤ የቀለም አብዮት ናፋቂ ተቃዋሚዎች መርዘኛ ፕሮፖጋንዳ ይበልጥ የሚጋልጥ ክፍተትን እንደመተው የሚቆጠር ስህተትን ማስከተሉ እንደማይቀር ከወዲሁ መገመት የሚቻል ይመስለኛል፡፡

ስለዚህም ነው እንግዲህ እኔ እንደአንድ ለኢህአዴግ መራሹ የኢትዮጵያውን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ስር ነቀል የስርዓት ለውጥ ጉዞ መቀጠል ልባዊ ድጋፉን ከመግለጽ ቦዝኖ እንደማያውቅ ዜጋ፤ ዛሬም የጥልቅ ተሃድሶው ዋነኛ ግብ ምን እንደነበር ደፍሬ ለመጠየቅ የተገደድኩበትን ርዕሰ ጉዳይ ማንሳቴ፡፡ ስለሆነም፤ ካሳለፍነው የ2008 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ፤ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግና የኢፌዲሪ መንግስትም ጭምር በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሲናገሩለት ስለቆዩት፤ በጥልቀት የመታደስ ወቅታዊ አጀንዳ አስፈላጊነት ድጋፌን ለመግለጽ የሞከርኩባቸውን በርካታ ፅሁፎች ሳቀርብ እንደመሰንበቴ መጠን፤ እነሆ አሁን ላይ ደግሞ የጠበኩትን ያህል ትርጉም ያለው ውጤት መጥቶ ባለማየቴ ምክንያት፤ ለመሆኑ ግን የጥልቅ ተሃድሶው ዋነኛ ግቦች ምን ምን ነበሩ? የታለመላቸውን “ታርጌትስ” በእርግጥ እየመቱ ናቸው ወይ? ወዘተ የሚሉ ነጥቦችን አነሳ ዘንድ ወድጃለሁ፡፡

ይልቁንም ደግሞ፤ አብዛኛዎቹ ኢህአዴግን አምርረውና አክርረው በመቃወም የሚታወቁት የሀገራችን ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሚያራምዱት ፅንፈኛ አቋም አኳያ ሲታይ፤ በአንፃራዊ መልኩ ለዘብ ያለ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ምክንያታዊ ተቃውሞን ሲያሰሙ ከሚደመጡት ፓርቲዎች መካከል የአንዱ መሪ የሆኑት፤ የአቶ ተሻለ ሰብሮ፤ መጋቢት 2009 ዓ.ም ታትሞ ከወጣው “ጊዜ” የተሰኘ የግል መፅሔት ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ “በኛ እምነት የኢህአዴግ ተሃድሶ በቂም አስፈላጊም አይደለም” ሲሉ ያሰመሩበትን ትችት የሰጡበት አጠቃላይ ማብራሪያ እኔ የምጋራቸውን ነጥቦችም ያካተተ ሆኖ ማግኘቴ እቺን ማስታወሻ እንድፅፍ አድርጎኛል፡፡ ስለዚህም፤ ግንባር ቀደም የጉዳዩ ባለቤት ተደርጎ እየተወሰደ ያለው ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ እንደመሆኑ መጠን፤ የሀገራዊ ፖለቲካችን ወቅታዊ የመወያያ አጀንዳ እንደሆነ ስለቀጠለው የጥልቅ ተሃድሶ አስፈላጊነት ጉዳይ፤ እየተደመጡ ላሉ የህዝብ ቅሬታ አዘል ጥያቄዎች የሚያጠግብ ምላሽ ሰጥቶ ሹክሹክታዎችን ማጥራት ይጠበቅበታል ባይ ነኝ፡፡

ምንም እንኳን የኢህአዴግ ስራ አስፈፀሚ ከሰሞኑ በሰጠው መግለጫ ላይ “የጥልቅ ተሃድሷችን ግምገማ ሂደት ችግሮቻችንን በውል ለይተን የተረዳንበትና እንዲሁም በቀጣይነት ለመታገል የሚያስችሉንን ጠቃሚ ግብዓቶች ያገኘንበት መድረክ ነበር” የሚል ድርጅታዊ አቋሙን ይፋ ማድረጉ ባይካድም፤ ግን ደግሞ አሁንም መግለጫው እንብዛም የሚያጠግብ ዝርዝር መረጃ የሰጠ ሆኖ እንዳላገኙት የሚናገሩ ወገኖች ጥቂት አይደሉም፡፡ ለአብነት ያህልም “የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ሰሞነኛው መግለጫ በትምክህትና በጠባብ ብሔርተኝነት ፅንፈኛ አስተሳሰብ ምክንያት ሀገራችን መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆማ እንደነበር በጥልቅ ተሃድሶው የግምገማ መድረክ መረጋገጡን ማሳወቁ ጥሩ ነገር ሆኖ ሳለ፤ የተባሉት የአመለካከት ችግሮች እያስከተሉብን ያለውን አሳሳቢ አደጋ ለመቀልበስ የሚያስችል የመፍትሔ እርምጃ ስለመውሰድ አለመውሰድ ጉዳይ በቂ ማብራሪያ የተሰጠበት አለመሆኑ ሲታይ ግን፤ አሁንም የግንባሩ ከፍተኛ አመራር ጉዳዩን በተመለከተ ቁርጥ ያለ የጋራ መግባባት ላይ አለመድረሱን ነው የሚጠቁመው” የሚል አስተያየት ያላቸው ዜጎች አጋጥመውኛል፡፡

ለማንኛውም ግን፤ ከኢህአዴግ ከፍተኛ የአመራር አካላት መካከል አንዱ የሆኑት፤ የፌደራል ጉዳዮችና የአርብቶ አደር ልማት ሚኒስቴሩ አቶ ካሳ ተክለብርሃን፤ ማክሰኞ ሚያዝያ 3 ቀን 2009 ዓ.ም “ቆይታ ከሚሚ ስብሐቱ ጋር” የሚል ርዕስ ባለው የዛሚ ኤፍ ኤም 90.7 ሬዲዮ ጣቢያ ሳምንታዊ ፕሮግራም ላይ ቀርበው፤ በተለይም የጥልቅ ተሃድሶውን ውጤት አለማምጣት የሚመለከት ጥያቄ ላነሱ አድማጮች በሰጡት ምላሽ ምን ብለው እንደነበር ማስታወስ ይቻላል፡፡ እናም ክቡር ሚኒስቴሩ “የጥልቅ ተሃድሶ ግምገማችን የስርዓቱን ህልውና የሚፈታተኑ ዋነኛ ችግሮቻችን የትኞቹ ናቸው? በሚለው ቁልፍ ጥያቄ ላይ የጠራ የጋራ ግንዛቤ የተወሰደበትን ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር አስችሎናል” የሚል ምላሽ ነው የሰጡት፡፡

“ችግሮችን መለየት ብቻውን ኢህአዴግ ራሱም ጭምር ያመነባቸውን አሳሳቢ አደጋዎች ለመቀልበስ ያስችላልን?” ተብለው ሲመለሱም አቶ ካሳ “ችግሮችን ለይተናል ማለት እኮ በዚያው ልክ የመፍትሔ እርምጃ ለመውሰድ የሚረዳንን ቀጣይ ትግል ለማካሔድ እንድንችል የሚፈቅድ ምቹ ሁኔታ ፈጥረናል ማለት ነው እንጂ ጥልቅ ተሃድሶው በቃ እዚሁ ላይ የሚቆም ተግባር ይሆናል ማለት አይደለም” ነበር ያሉት፡፡ በጥልቅ ተሃድሶው የግምገማ መድረክ ተጨባጭ ማስረጃ የቀረበበትን ድክመት አሳይተው በተገኙ የአመራር አካላት ላይ አስፈላጊው የእርምት እርምጃ ሲወስድ መቆየቱንም አክለው የተናገሩት የፌደራል ጉዳዮች እና የአርብቶ አደር ልማት ሚኒስቴሩ “በተረፈ ግን ያለምንም መረጃ የሚወሰድ የጅምላ እርምጃ ራሳችንንም የሚጎዳ ውጤት ያስከትል እንደሁ እንጂ ሌላ ጥቅም ይኖረዋል ብለን አናምንም” ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

እውነቱን እንነጋገር ከተባለ፤ ችግሮችን በቅጡ ለይቶ ለማወቅየሚረዳ ምቹ ቅድመ ሁኔታን የማሟላት ስራ መስራት መቻል በቀላሉ የማይታይ ጠቃሚ ጎን እንዳለው የሚያከራክር ጉዳይ አይደለምና እኔ በግሌ አስፈላጊነቱ ላይ ችግር የለብኝም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሰከን ባለ መንፈስ የተቃኘ የውስጣዊ ችግር አፈታት ዘዴ ኢህአዴግ መራሹን የኢትዮጵያ ህዝቦች የትግል መስመር ከአብዛኛዎቹ የሀገራችን ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለየና የተሻለ ተደርጎ እንዲወሰድ የሚያደርግ ጠቃሚ ድርጅታዊ ባህል ስለመሆኑም ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡

ይህ በጎ ጎኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን፤ ችግሮችን የመለየት ስራ መስራት በራሱ ግብ ሊሆን እንደማይችል አለመዘንጋት ግድ ይላልና ነው እኔም “የጥልቅ ተሃድሶ ግብ ምን ነበር?” ስል ለመጠየቅ መገደዴ፡፡ ስለዚህም ጥያቄው የሌሎች በርካታ የስርዓቱ ደጋፊ ዜጎች ጭምር እንጂ የኔ ብቻ እንዳልሆነ ከማመኔ የተነሣ በዚህ መልኩ ላቀርበው መገፋፋቴን ስገልጽ፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የኢፌዲሪ መንግስት ባለድርሻ አካላትም ትኩረት ሰጥተው ያጤኑት ዘንድ እንደሚገባ ተስፋ በማድረግ ነው፡፡ ምንም እንኳን ገዥው የፖለቲካ ፓርቲ በዘመቻ መልክ የሚካሄድ የእርምት እርምጃ መውሰድ አለበት ብዬ ባላምንም ቅሉ፤ ግን ደግሞ ኢህአዴግነትን ለቀለም አብዮት ናፋቂ ቡድኖች ሕጋዊ ከለላ መስጫነት አድርገው ሊያውሉት የሚሞክሩትን ወገኖች ላይ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ይገባል ባይ ነኝ፡፡

“በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ” እንዳልነበረ ብሒሉ

ዕልፍ አዕላፍ ድንጋይ ወርውረው፤ አንድም ወፍ መምታት ያልቻሉ….

መጥኖ የመደቆስን፤

ዓልሞ የመተኮስን፤

ሰውኛ የሂወት ጥበብ፤ ከሂደት ያልተማሩ

ድስት ጥደው የሚያለቅሱት፤ ሰነፎች ሲደናበሩ

አሁንም እንደትናንቱ፤ በቸልታ ከታለፉ?

ከወዲሁ ነው መጠርጠር፤ አጥፍተውን እንዳይጠፉ!!

 

መዓ ሰላማት!

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy