Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የፈለጉት ስራ ላይ መድረስ የሚቻለው የተገኘውን ስራ ማክበር ሲቻል ነው!

0 572

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የፈለጉት ስራ ላይ መድረስ የሚቻለው   የተገኘውን ስራ ማክበር ሲቻል ነው!

ወንድይራድ ኃብተየስ

የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት ዜጎች በአገር ውስጥ በየትኛውም ስፍራ ተንቀሳቅሰው በነጻነት የመኖርም ሆነ ሃብት የማፍራት መብታቸውን አረጋግጦላቸዋል።   ህገ-መንግስታችን ይህን ዋስትና ለዜጎች ቢያረጋግጥም  ባለፉት 22 ዓመታት በአፈጻጸም ችግር  የታዩ ህጸጾች  ግን አልነበሩም ማለት ግን አይቻልም።  በተለይ አማራ ክልል  በቅርቡ  ተከስቶ በነበር ሁከት ሳቢያ  በዜጎች ላይ ሰብዓዊነት የጎደለው ድርጊት  ተፈጽሟል። ይህን ድርጊት ሁሉም ሊያወግዘው በአገራችን መቼም የትም መደገም የሌለበት  የህዝቦችን አብሮነት የሚሸረሽር አካሄድ ነበር።  ይህን ጉዳይ እግረ መንገዴን አነሳሁት እንጂ የዛሬ አነሳሴ ይህን  በተመለከተ አይደለም።   

ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር አንዱ የአገራችን ተግዳሮት እየሆነ የመጣ ክስተት ሆኗል። መንግስት  ከአገር ውጭ የሚደረጉ ፍልሰቶች በህግ አግባብ እንዲመሩ የተለያዩ አሰራሮችን ዘርግቷል።  ይሁንና በርካታ ዜጎች ህይወታቸውን ለአደጋ በሚያጋልጥ ሁኔታ በህገወጥ መንገድ ወደ ውጭ አገራት  በተለይ ወደ መካከለኛው ምስራቅና ደቡብ አፍሪካ  በመጓዝ የከፋ ጉዳት እየደረሰባቸው  የገኛል፡፡  እነዚህ ዜጎች ህገወጥ ደላሎች የሚነግሯቸውን የፈጠራ ታሪክ በማመን  ንብረታቸውን በመሸጥ አሊያም ከፍተኛ ብድር  በመውሰድ  ያሰቡበት ቦታ ሳይደርሱ በርካታዎቹ ለከፋ  እንግልት ሲጋለጡ ቀሪዎቹ ደግሞ ህይወታቸውን እስከማጣት የሚደርሱበት ሁኔታን በተደጋጋሚ እየተመለከትን ነው፡፡ በዚህ መሰረት  መንግስት በተለይ  የውጭ አገር  የስራ ስምሪትን በተመለከተ  ቁጥጥር ቢያደርግም የተፈለገው  ውጤት አልመጣም። ለዚህ በርካታ ምክንያቶችን መዘርዘር ቢቻልም እንደእኔ  የህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ ያለማደረግ ጉዳይ ይመስለኛል።  

የሰዎች ዝውውርን በተመለከተ  ኢትዮጵያ  ሁለት ገጽታን የተላበሰች  አገር ትመስለኛለች። የመጀመሪያው በየቀኑ እጅግ በርካታ የውጭ አገር ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ የሚሰደዱባት አገር ለመሆን በቅታላች። ይህን በተመለከተ  የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከ800ሺ በላይ ከጎረቤት አገራትን ስደተኞችን አስጠልላለች። በሌላ በኩል ደግሞ  ቀላል የማይባል  ዜጎች   በተለያየ ምክንያት ወደ ሌሎች አገራት በህጋዊም ይሁን በህገወጥ ምክንያት  ይሰደዳሉ።  ትኩረቱን በሰዎች ፍልሰት ላይ ያደረገው ተቋም አይ ኦ ኤም መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ከሚሰደዱ ዜጎች መካከል አብዛኛዎቹ  ለሥራ እና የተሻለ ኑሮ ፍለጋ  ሲሆን፤ በአርብቶ አደሮች አካባቢ የሚደረግ ስደት ደግሞ  ደግሞ፤ ለእንስሳት ውሃ እና መኖ ፍለጋ ድንበር የሚያቋርጡበት ሁኔታን ማንሳት ይቻላል።   

በኢትዮጵያ ካለፉት 15 ዓመታት ወዲህ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች  እንደሆነ ቢታወቅም  የሰዎች ፍልሰት ግን  እንደቀጠለ ነው።  ይህ የሚያመላክተው  የኢኮኖሚ ዕድገት ማረጋገጥ ብቻውን ፍልሰትን ሊገታው አይችልም። ለፍልሰት ዋንኛው ምክናያት የግለሰቦች ፍላጎት ያለመርካት አንዱ ማሳያ  ነው።   

አንዳንድ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች እንደሚሉት የኢኮኖሚ ዕድገት  በአንድ አገር ስላለ ብቻ ስደት ይቆማል ማለት እንደማይቻል አስረግጠው ይናገራሉ።  ምክንያቱም  አገሪቱ የቱንም ያህል ፈጣን ዕድገት ብታስመዘገብም  የሁሉንም ፍላጎት ማሟላት አትችልም።  በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ  ለስደት ዋንኛ ምክንያት የግለሰቦች ፍላጎት እንጂ ፖለቲካዊ እንዳልሆነ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ከሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳንና ኤርትራ  ወደ አገራችን   እየተሰደደ ያለው ህዝቦች ምክንያታቸው በአገራቸው ያለው ግጭትና አምባገነን መሪዎች በሚፈጽሙባቸው በደል ሳቢያ ነው። የኢትዮጵያዊያን  የስደት ምክንያት ግን ከዚህ በፍጹም የተለየ ነው።   

ሰዎች በተፈጠሮቸው የተሻለ ነገር   ነው ብለው ለሚያስቡት ነገር ይጓጓሉ።  ይህም ማለት ሰዎች የቱንም ያህል የተሻለ ነገር ቢፈጠርላቸውም  የተሻለና ምቹ ነው ብለው ለሚያስቡት  ሁኔታዎችን መፈለጋቸው አይቀርም። ለዚህ  ጥሩ ማሳያ ይሆናል ያልኩት የዓለም ባንክ በአስር ዓመት ውስጥ ባጠናው መረጃ መሰረት በኢትዮጵያ ከሚገኙ ተቀጣሪዎች መካከል ገቢያቸው በጥሩ ሁኔታ ያደገው የቤት ሠራተኞች እንደሆነ አመልክቶ፤ ነገር ግን እነዚሁ አከላት በብዛት ወደ ዓረብ አገራት እጅግ በከፋ ሁኔታ እንደሚሰደዱ  ጥናቱ አሳይቷል።  ይህ የሚያረጋግጠው  ሰዎች በያዙት ነገር አለመርካታቸውን ነው።

ኢትዮጵያ  የኢኮኖሚ ዕድገቷን ከግብርና ወደ አምራች ኢንዱስትሪው ለማሸጋገር ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ላይ ትገኛለች።  ይህ የኢትዮጵያ ዕቅድ  ወቅታዊና ትክክለኛ ነው። ምክንያቱም አምራች ኢንዱስትሪው በአነስተኛ ስፋራ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል የሚያስገኝ ከመሆኑም ባሻገር ለዜጎች ዘመናዊ አኗኗር እንዲላመዱ የሚያደርግ ነው።  የአምራች ኢንዱስትሪው መስፋፋት በሰው ኃይል ልማት በተለይም  በመካከለኛና በከፍተኛ ደረጃ ለተማሩት ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር የሚያስችል መስክ ነው።   መንግስት  ከፍተኛ የሰው ሃይል የያዘውን የግብርና ዘርፍ በማዘመን ከኢንዱስትሪው ጋር ለማስተሳሰር  በርካታ ስራዎችን በመስራት ላይ ነው።

ሁሌም ባይሆን  አልፎ አልፎ  እንደምንመለከተው  በአገራችን የሚፈጠሩ የስራ ዕድሎች ብዛትና ዓይነት  ከወጣቶቻችን  ቁጥርና   ፍላጎት  ጋር  ባለመመጣጠን  ሳቢያ ለበርካታ  ወጣቶች የስደት ምክንያት ሆኗል። በአገራችነ በአሁኑ ወቅት በርካታ የስራ መስኮች ተፈጥረዋል። በአንዳንድ  መስኮች የሰው ሃይል አነሰን እስከማለት ደርሰዋል። በተለይ በግብርናው ዘርፍ የሰው ሃይል እጦት በርካታ ባለሃብቶች ሲማረሩ ይደመጣሉ። በእርግጥ  የአገራችን የክፍያ መጠን አነስተኛ ቢሆንም ለዜጎች የአካልና የህይወት ዋስትና አላቸው። ማንም ሰብዓዊ ክብራቸውን ሊገፋቸው አይቻለውም። ህገወጥ ስደት በህይወት ላይ ቁማር እነደመጫወት ያክል ነው። ከተሳካ ገነዘብ ማግኘት ካልሆነው ህይወትን አሊያም አካልን መገበር አይነት አካሄድ ነው።    

ወጣቶች የአገራቸውን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ማድረግ ይኖርባቸዋል።  አገራችነ ገና ታዳጊ ናት። ሁሉም ነገር  ማስተካከል ያለብን በእኛ ጥረት ነው። የስራ ባህላችን መስተካከል አለበት። በሰለጠኑት የምዕራብ አገራት  የምንሰማው ማንም ዜጋ  ገንዘብ የሚያስገኝ እስከሆነ ድረስ ስራ ሳይመርጥ የተገኘውን  ማንኛውንም ስራ  ይሰራል። በርካታ ታማሩና ደህና ገቢ አላቸው የሚባሉ ዜጎቻችን በስደት በሚኖሩባቸው የምዕራቡ ዓለም በተለይ በአሜሪካ  የተገኘውን ስራ እንደሚሰሩ ራሳቸው በአንደበታቸው ሲናገሩ አድምጠናል።  ይህ የምዕራቡ አለም የስራ ባህል ማደጉን በስደት ላይ ያሉ  ዜጎቻችንም  እነሱኑ መስለው  በመኖር ላይ ናቸው። ይሁንና የአገራችንን የስራ ባህል ስንመለከተው እጅግ ኋላቀር ሆኖ እናገኘዋለን።  አንዳንድ ቤተሰቦች ልጄ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ተምሮ እንዴት ይህን ይሰራል፣ አለፍ ሲልም እንዴት በዚህ ያህል ገንዘብ ይቀጠራል  በማለት የወጣቶችን የመስራት ሞራል ይገድላሉ። እነዚህ ቤተሰቦች ልጆቻቸውን ሃላፊነት እንዳይሰማቸው ከማድረጋቸውም በላይ ጥገኛ እንዲሆኑ አድርገዋቸዋል።  

ወጣቶቻችን  ይህ ስራ ይመጥነኛል ይህ ደግሞ አይመጥነኝም  የሚል ኋላቀር አስተሳሰብ መላቀቅ የኖርባቸዋል።  ስራ ክቡር ነው።  የፈለጉትን ስራ ማግኘት እስኪችሉ  ያገኙትን ስራ አክብረው መስራት ታላቅነት ነው። ለስራ  ያላቸው  አስተሳሰብ  እንደገና መፈተሽ ይኖርባቸዋል።  ስራ ማማረጥ የሚቻለው  በቂ የስራ ልምድ ማዳባር ሲቻልና  ለሌላ ስራ ፈጠራ መነሻ ኢኮኖሚያዊ  አቅም ማጎልበት ሲቻል ብቻ ነው።  

የፌዴራሉ መንግስት ለወጣቶች የስራ ፈጠራ መነሻ የሚሆን 10 ቢሊዮን ብር እንዲሁም   የክልል ማንግስታትና ከተማ አስተዳዳሮች ካላቸው በጀት በመቀነስ   ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት  ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ መድበዋል።  መንግስት ይህን ያህል ገንዘብ ለወጣቶች   የመደበው  የተትረፈረፈ  ወይም በቂ  በጀት ኖሮት ሳይሆን ለወጣቶች ካለው ህዝባዊነት የተነሳ መሆኑን  ወጣቱ ሃይል መገንዘብ ይኖርባታል። አገራችን ደሃ ናት።  በመሆኑም  ወጣቱ ከዚህ ደሃ ህዝብ ላይ  ተሰብስቦ  የተሰጣቸው ገንዘብ  በሃላፊንት ሊገለገሉበት ይገባል።

ወጣትነት ትልቅ አቅም ነው።  በመሆኑም ወጣቶች ሁሉን ነገር መንግስት እንዲያመቻችላቸው መጠበቅም የለባቸውም፡፡  የመንግስትና የህብረተሰቡ ብቻ ሳይሆኑ  ራሳቸው ወጣቶችም  ከየአካባቢው መስተዳድር ጋርም ይሁን ከሌላው አካል ጋር  በቅርበት  መስራት ይጠበቅባቸዋል።  ወጣቶች የገኙትን ብድር አብቃቅተውና  በሃላፊነት ስሜት  በመስራት ውጤታማ የሚሆኑበትን መስክ መምረጥና ጠንክረው መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ አንዳንድ ወጣቶች  ይህን ተዟዛሪ ወይም ተገላባጭ ፈንድ በነፃ የሚታደል ገንዘብ አድርጎ የመውሰድ ዝንባሌዎች ይስተዋልባቸዋል። ይህ እጅግ የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው። መንግስት ይህን ገንዘብ  ከሌላ በጀት ቀንሶ እንዳቀረበና  ነገ ስራ የሚፈልጉ ወጣቶችም የዚህ  እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ  የአሁኑ ወጣቶች ብድራቸውን በአግባቡ መመለስ ይኖርባቸዋል። ለዚህ ደግሞ ዋናው ነገር ቁጠባን ባህላቸው ማድረግ ይኖርባቸዋል።  

በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች  ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት ሲባል  ስራ አጥ ወጣቶችን   የመመዝገብ፣ የመለየት፣ ማደራጀትና የማሰልጠን   ስራዎች  በስፋት እየተከናወኑ ናቸው፡፡  በአጭር ጊዜም የብድር አገልግሎቱ  ይጀመራል። ወጣቶችም ስራን በማክበር ማለትም ያገኙትን ስራ በመስራት፣ የቁጠባ ባህላቸውን በማሳደግ እና  ልምድ ወይም ሙያ  በመቅሰም ነገ እቀየራለሁ የሚል ስሜት ሊያዳብሩ ይገባል።   ለብድር የሚቀርበው ገንዘብ   ወጣቶች የጠበቁትን ያህል ላይሆን ይችላል። ይሁንና  አብቃቅተው  ስራ መጀመር፣  እንዲሁም  የተሰማሩበትን የስራ መስክ በማክበርና በመውደድ ጠንክረው በመስራት ውጤታማ መሆን ይቻላል።  ከዚህም ባሻገር ቁጠባን ባህል በማድረግ  የዕለት ገቢ ላይ በመቆጠብ የተበደሩትን ገንዘብ በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ መመለስ ይጠበቅባቸዋል።  በአጠቃላይ ወጣቶች መንግስት በብድር የሰጣቸውን ገንዘብ በሃላፊነት ስሜት ሊጠቀሙበት ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy