Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ድርድርን በመሸሽ ድክመትን መሸፈን አይቻልም

0 330

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ድርድርን በመሸሽ ድክመትን መሸፈን አይቻልም

ወንድይራድ ሀብተየስ

ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን እየገነባች ያለች አገር ነች፡፡ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገለጫዎች ከሆኑት አበይት ጉዳዮች መካከል አንዱ የሆነውን የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን  መተግበር ከጀመረች ሁለት ዓስርት ዓመታትን አስቆጥራለች። የኢፌዴሪ ህገመንግስት የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገሪቱ የመኖር አስፈላጊነት ለተለያየ አስተሳሰብ  እንዲጎለብት ምክንያት መሆናቸውን  በማመን  የብዙሃን ፓርቲዎች አሰራር በአገሪቱ እንዲዳብር ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል። ይሁንና የአገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች ምቹ ሁኔታ ቢፈጠርላቸውም ለአገሪቱ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት መዳበር የሚጠበቀውን ያህል አስተዋጽዖ ሲያበረክቱ አልታዩም። አብዛኞቹ ብልጭ ድርግም እያሉ ቢሆንም አሁን ላይ በአገር አቀፍ ደረጃ ብቻ  ከ20 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች  ይንቀሳቀሳሉ።  

እንደእኔ ዕይታ በአገራችን ከተቋቋሙት ፓርቲዎች መካከል አገሪቷ የምትፈልገውን የዴሞክራሲ ስርዓት  የሚያጠናክር  የተሻለ አማራጭ አለኝ  የሚል ተቀናቃኝ ፓርቲ እስካሁን አላየሁም። እነዚህ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች የህዝቡን ችግር ችግሬ ነው ሲሉ፣ የአገሪቱን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሊያጎለበት  የሚችል ስራ ሲያከናውኑ አላየሁም። ይልቁንም አገራችን ያስመዘገበቻቸውን ዓለም ዓቀፍ ዕውቅና የተቸራቸውን ድሎቻችንን  ቀድሞ ሲያጣጥሉ ነበር። አሁን ላይ በግድ  አምነው ተቀበሏቸው እንጂ!  

በርካታዎቹ ፓርቲዎች  የተፈጠረላቸውን መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው ራሳቸውን ከማጠናከር ይልቅ እርስ በርስ ሲነቋቆሩ፣  ሲነታረኩ አልፎ አልፎም አመራሮቻቸው ጎራ ለይተው ሲናረቱ ሰምተናል፣ ተመልክተናል። ለዚህ ደግሞ ከማንም በላይ ራሳቸው የጉዳዩ ግንባር ቀደም  ተዋንያን  ነን የሚሉት አመራሮቻቸው የሚፅፏቸውን መፅሐፍቶች መጥቀስ ይቻላል። በእነዚህ መፃህፍት ላይ በመካከላቸው ያለው ሽኩቻ፣ መናናቅ፣ መጠላላት፣ መጠላለፍ የተጠመዱ መሆናቸውን አንብበናል፣ ተመልክተናል፣ ሰምተናል።  በሌለና ገና ባልተገኘ የስልጣን  ምኞት እርስ በርስ መጠላለፍ ለሁሉም ፓርቲዎች መገለጫ ነው ባልልም ለበርካታዎቹ  በተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚስተዋል ችግር ነው።  የአገራችን አንዳንድ የተፎካካሪ ፓርቲዎች አዲስ ነገር መጣ ወይም ምርጫ ደረሰ በተባለ ቁጥር መሰባሰብ፣ መጣመር፣ ግንባር መፍጠርና መዋሃድ ይቀናቸዋል። ትንሽም ሳይሰነባብቱ ደግሞ ፍርድ ቤት መጓተት፣ ከዚያም መበታተን እጣ ፈንታቸው ይሆናል።

እንደእኔ የሰሞኑ የመኢአድና የሰማያዊ ፓርቲ አካሄድም ከድሮው የተለየ ይሆናል ብዬ አላምንም።  የማይተማመን ባልንጀራ በየወንዙ ይማማላል እንደሚባለው የአገራችን ተቀናቃኝ ፓርቲዎችም ሁሌም ከዚህ አካሄድ የጠሩ አይደሉም። በየጊዜው ተማምለው ይዋሃዳሉ ትንሽም ሳይቆዩ ሆድና ጀርባ ሆነው ሲነቃቀፉ ይስትዋላሉ።  ፋና ብሮድ ካስት ኮርፖሬሽን በሸራተን አዲስ አዘጋጅቶት በነበረው የኢትዮጵያ የዴሞክራሲና የፌዴራል ስርዓት ከየት ወደየት በሚል ውይይት ላይ አቶ ልደቱ አያሌው   እንደነገሩን በተቃውሞ ጎራ የተሰለፉት የአገራችን የፓርቲ አመራሮች ዋንኛ የፖለቲካ ስራቸው አድርገው እንደማይወስዱት እንዲሁም የራሳቸውን ጥንካሬ ለህዝቡ አማራጭ አድርገው ከማቅረብ ይልቅ የኢህአዴግን ድክመት ሲያወሩ እንደሚውሉ ሰምተናል። በመሆኑም የፓርቲው አመራሮች ስራዬ ብለው ያልያዙትን ዕምነት እኛ እንድንቀበላቸው መጠበቃቸው የዋህነት ይመስለኛል።  

ካለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ወዲህ አገራችን  በፍጥነት መልማት መጀመሯን ተከትሎ በርካታ መሰናክሎች አጋጥመዋት ነበር። ይሁንና ሁሉንም ችግሮች በህዝቡ አርቆ አስተዋይነትና በመንግስት በሳል አመራር አልፈናቸዋል። ለአብነት ያህል ሽብርተኝነትና አክራሪነት አንዱ የአገራችን ስጋት ናቸው። የእኛ አገር አንዳንድ የተፎካካሪ ፓርቲዎች  ይህን ስጋት አሳንሰውት መንግስት የፈጠረው አድርገው ለማውራት ዳድቷቸው ነበር። የምስራቅ አፍሪካ ጂኦፖለቲክስ በራሱ በአገራችን ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለመረዳት የግድ ፖለቲከኛ መሆንን አይጠይቅም። ይሁንና ይህን የአገራችን ስጋት የሆነውን ሽብርትኝነት ለማውገዝ ያመማቸው ፓርቲዎችን ተመልክተናል። ይህን ዓይነት አካሄዳቸው  ከህዝብ ምን ያህል እንዳራቃቸው እንኳን በአግባብ የተረዳት አይመስለኝም።

 

አክራሪነት የሽብርተኝነት መፈልፈያ ሆኖ ሳላ አክራሪነት በአገራችን የለም ብለው የሚናገሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ተመልክተን ለእነሱ እኛ አፍረን ነበር። የአክራሪዎችን ርካሽ ድጋፍ ለማግኘት ሲባል የሚደረግ የፖለቲካ ውስልትና ካልሆነ እውነት አጥተውት አልነበረም።  አንዳንዴ ሳስበው የእኛ አገር የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የሽብር ጅምላ ጨራሽነትን በአግባቡ አለተረዱት ይሆን ስል ራሴ እጠይቅና ራሴው መልሼ “አውቆ የተኛ” የሚል ምላሽ እሰጣለሁ። ምክንያቱም ምስራቅ አፍሪካ ለሽብርትኝንት ስጋት የተጋለጠ ተብሎ የተፈረጀ  አካባቢን  ከመሆኑ ባሻገር አገራችን የሽብርተኞች ዒላማም ነበረች። ይህ ሆኖ ሳለ  አክራሪነት  በኢትዮጵያ የለም ብለው  የተከራከሩት ጉዳዩን አጥተውት ሳይሆን ሆን ብለው የፖለቲካ ትርፍ ያስገኝልናል ብለው ነበር።

 

ሁሉን የማጥላላትና የመሸምጠጥ መጥፎ ፖለቲካዊ አካሄድ አገራችን ለጀመረችው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታም ሆነ  የፀረ-ድህነት ትግል የሚበጅ ባለመሆኑ አንዳንድ የአገራችን ተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ከዚህ ጭፍን የጥላቻ አካሄድ ሊወጡ የሚገባ ይመስለኛል።  በቅርቡ እንኳን አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የጥልቅ ተሃድሶ ሂደትን ሲያጣጥሉ ተደምጠዋል። ጥልቅ ተሃድሶው ለአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት መጎልበት የበለጠ ዕድል የሚፈጥር ነው። አንዳንዴ ሳስበው የአገራችን ተፎካካሪ የፖለቲካ ሃይሎች መንግስት (ገዥው ፓርቲ)  በምተሃት  ከሰማይ ዳቦ ማዝነብ ቢችል እንኳን መልካም ነገር ነው ብለው መቀበል ይቸገራሉ።

የአገራችን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ነጠላ ዜማ የፖለቲካ ምህዳሩ ጠቧል፣ አሳታፊ አይደለም ተገፋን ወዘተ የምትለዋ  ዝማሬ ናት። ይሁንና በቅርቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድርን መድረክ የተባለው የፓርቲዎች ስብስብ ትንንሽና ከአንድ ፓርቲ የማይጠበቅ ምክንያቶችን በማቅረብ ከድርድሩ ራሱን አግሏል። ይህን አይነት አካሄድ ለአገራችን የፖለቲካ ህይወት መዳበር የሚፈይደው ነገር አይኖርም። ችግር የለም አይባልም፤ ነገር ግን ከመነጋገር እንጂ በመሸሽ መፍትሄ አይገኝም። አገራችን የመድበለ ፓርቲ ስርዓትን እውን ካደረገች ሁለት አስርት አመታት አስቆጥራለች። በእነዚህ ጊዜ ሁሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ችግሮቻቸውን ውስጣዊ ከማድረግ ይልቅ ውጫዊ ማድረግ ይቀናቸዋል። ይህ አይነት አካሄድ ደግሞ ለበሽታቸው መደሃኒት እንዳያገኙ አድርጓቸዋል።  

በህገ መንግስታችን በግልፅ እንደተደነገገው የስልጣን ብቸኛ ምንጭ ከምርጫ ኮሮጆ የሚገኝ የህዝብ ድምፅ መሆኑ እየታወቀ በዚህ መንገድ  ምኞታቸው አልሳካ ያላቸው አንዳንድ የአገራችን ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሁለተኛ አማራጭ ብለው የሚያስቧትን  መንገድ ማማተርንም አይተዋትም። ኢህአዴግ በጥልቅ ተሃድሶው የአገሪቱን የዴሞክራሲ ስርዓት ያጎለብታል ካለው አካል ጋር ለመነጋገር ሁኔታዎችን ባመቻቸበት ወቅት እንኳን መድረክ የተባለው የፓርቲዎች ከስብስብ ራሱንከድርድር  ማገለልን የመረጠው እኔ ያልኩት ካልሆነ ከሚል ራስ ወዳድነት የተነሳ ነው። በዕርግጥ መድረክ ኖረም አልኖረም ድርድሩ ከ20 በሚበልጡ ፓርቲዎች መካከል መቀጠሉ አይቀርም። ይሁንና ነገ ደግሞ ይኸው ፓርቲ ሌላ ምክንየት መደርደሩ አይቀርም።  

የአገራችን ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የህዝብን ቀልብ ሊገዛ የሚችል አማራጭ ፖሊሲና ስትራቴጂ ሊያቀርቡ ባለመቻላቸው በምርጫ አሸንፈው መውጣት አልቻሉም። የሚያስገርመው አንዳንዶቹ ፓርቲዎች የውስጥ መተዳደሪያ ደንብ እንኳን በወጉ ሳይኖራቸው አገርን የሚያህል ነገር ለመምራት ይፈልጋሉ።

እንደመድረክ ያሉ ፓርቲዎች ችግራቸውን በመወያየት ከመፍታት ይልቅ ከድርድር በመሸሽ መፍትሄ የሚገኝ ይመስላቸዋል።  እንደነዚህ ያሉ ፓርቲዎች ሁሌም ለችግራቸው ምንጭ ውጫዊ ሁኔታዎች ብቻ እንደሆኑ አድርገው በማሰብ ህዝብን ለማደናገር “የፖለቲካ ምህዳሩ ጠቧል” የምትል ዘውትር የማትሰለቻቸው ዜማ ማቀንቀንን ይወዳሉ። በተገኘውስ መቼ ተጠቅማችሁበት ቢባሉ መልስ የላቸውም።’

ድርድርን  አልፈልግም የሚል እምነት ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች አገራችን ለጀመረችው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የሚያበረክቱት አስተዋጸኦ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ቢኖርም ባይኖርም፣ የማይጠቅም አሊያም የማይጎዳ ከሆነ በፓርቲነት መቀጠሉ ለአባሉም ለደጋፊውም የሚበጅ አይመስለኝም። በመሆኑም መድረክ የተባለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ አካሄዱን ቢያስተካክልና ወደ ድርድሩ ራሱን ቢመልስ መልካም ይመስለኛል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy