Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ጥልቁ ተሃድሶ ይጠናከር

0 305

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ጥልቁ ተሃድሶ ይጠናከር!/  ቶሎሳ ኡርጌሳ/

   ገዥው ፓርቲ (ኢህአዴግ) ሰሞኑን መግለጫ አውጥቷል። በመግለጫው ላይ ከጠቀሳቸው ውስጥ አንዱ የእንደገና መታደስ ወይም የጥልቅ ተሃድሶ ጉዳይ ነው። በዚህ መግለጫውም በጥልቀት የመታደስ የንቅናቄ መድረኮች በተቀመጠላቸው አቅጣጫ መሰረት መፈፀማቸውን አስታውቋል። ንቅናቄው በአመራሩ፣ በአባሉ፣ በሲቪል ሰርቫንቱና በመላው ህዝብ ሰፊና ተከታታይ ውይይት መደረጉንና በዚህም በመሰረታዊ አጀንዳዎቹ ላይ የጋራ መግባባት መፈጠሩንም ገልጿል። እንደገና በጥልቀት የመታደስ የንቅናቄ መድረኮች በቀጣይ ትግል የህዳሴ ጉዞውን ማደናቀፍ ከማይችሉበት ደረጃ ላይ በማድረስ ሀገራዊ ህዳሴውን እውን ለማድረግ ድርጅት፣ ፐብሊክ ሰርቫንቱ እና ህዝቡ ለለውጥ መነሳሳታቸውን  መግለጫው ያመለክታል።

ታዲያ ከዚህ መግለጫ በመነሳት በጥልቅ ተሃድሶው በመጠኑ ማውሳት የሚቻል ይመስለኛል። ይኸውም ጥልቅ ተሃድሶው ኢህአዴግ እንዳለው ግለቱን ጠብቆ እየተጓዘ መሆኑን፣ ያለ ህብረተሰቡ ድጋፍ እውን መሆን እንደማይችልና ማንኛውም ተሃድሶ በሂደት እንጂ በአንድ ጀንበር ብቻ እውን ሊሆን የማይችል መሆኑን ነው።

በተካሄደው ጥልቅ ተሃድሶ ሃሳቦች በየመድረኩ በነፃነት ተንሸራሽረዋል፤ ወደፊትም ይንሸራሸራሉ። ፐብሊክ ሰርቫንቱም ይሁን ህዝቡ የሚሰማቸውንና ለመልካም አስተዳደር እመርታ ተግዳሮት የሆኑ ጉዳዩችን እየለዩ ፊት ለፊት ገልፀዋቸዋል። በዚህም የሀገራችን ስልጣን ባለቤት የሆነው ህዝብ እየተካሄዱ ባሉት የውይይትና የግምገማ መድረኮች የመንግስትን ባለስልጣኖች ከሃላፊነታቸው እያነሳ ነው። ከዚህ አኳያ በደቡብ፣ በአማራና በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች ህዝቡ በግምገማው እየተካሄደ ያለው ሹም ሽር በምሳሌነት የሚጠቀሱ ይመስሉኛል። ይህም መንግስትና ገዥው ፓርቲ ከህዝቡ ጋር በመሆን ለመታደስ ያሳዩት ቁርጠኝነት ውጤት እያመጣ እንጂ፣ አንዳንድ ፅንፈኞች እንደሚሉት ውጤት አልባ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው።

እርግጥ በውይይቶቹና በግምገማዎቹ በቅድሚያ ለማግኘት የታሰበው የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ነው። እርሱን ተከትሎም አደረጃጀት እንዲከተል እየተደረገ ነው። ከአመለካካት አኳያ ፐብሊክ ሰርቪሱ ራሱን በአገልጋይነት መንፈስ እንዲያንፅ ማስቻል ነው። የህዝብ አገልጋይነቱን ለማረጋገጥም፤ በሚያከናውናቸው ማናቸውም ተግባራት መልካም አስተዳደርን ተመርኩዞ ተግባሩን መወጣት እንዳለበት የሚያስገነዝብ ነው። ይህን ለማከናወንም የኪራይ ሰብሳቢነትንና የሙስናን አስተሳሰቦችንና ተግባራትን የሚፀየፍ ፐብሊክ ሰርቪስ እንዲፈጠር ማድረግ ነው።

እርግጥ በየትኛውም ዴክራሲያዊ ሀገር ውስጥ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር ነባራዊ ክስተት ነው። ምንም እንኳን በሀገራችንም መንግሥትና ህዝብ በመገንባት ላይ የሚገኙት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ገና ለጋ ቢሆንም፤ እንደ ጀማሪ ዴሞክራሲያዊ ሀገር ከዚህ ነባራዊ ክስተት የፀዳንና ጉድለቶች የሉብንም ብሎ ለመናገር አይቻልም።

የኢፌዴሪ መንግስትና እርሱን የሚመራው ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ከህዝቡ ጋር በመሆን በየጊዜው በሚወስዷቸው በርካታ ርምጃዎች የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰቦች እየተቀረፉ ቢሆኑም፤ የሚፈለገው የአስተሳሰብ ለውጥ ሙሉ ለሙሉ ተገኝቷል ማለት አይቻልም። እንዲያውም አስተሳሰቦቹ እየገነገኑ ጫፍ ላይ እየወጡ ይመስላሉ። በአመዛኙ ኪራይ ሰብሳቢነትንና ሙስናን የሚፀየፍና እንደ ነውር የሚያይ የመንግስት ስራ አስፈፃሚን ብሎም ህዝብን በተሟላ ሁኔታ መፍጠር አልተቻለም።

በሰጪም ይሁን በተቀባይ መካከል ያለው አስተሳሰብ አንድና ተመሳሳይ ነው ማለት ይቻላል። ይህ የሆነውም ካለፉት ስርዓቶች ይዘናቸው የመጣናቸው ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ቅሪት አስተሳሰቦች ብሎም ልማቱ የፈጠራቸው አንዳንድ ሁኔታዎች አስተዋፅኦ ያደረጉ ይመስለኛል።

ፐብሊክ ሰርቪሱ ምንም እንኳን በሀገራችን ውስጥ ለተገኘው ልማት የበኩሉን ድርሻ ቢያበረክትም ከዚህ ነባራዊ የሀገራችን ሁኔታ ውጪ ሊሆን አይችልም። በመሆኑም ስልጣን የህዝብ ማገልገያ ሳይሆን የራስ መገልገያ ሊሆን ችሏል። ይህን አመለካከት ለመለወጥ ደግሞ በመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ የአስፈፃሚነት ስራን የሚከውኑት የፐብሊክ ሰርቪሱ አካላት በአመለካከት ብሎም በአደረጃጀት ለውጦች ውስጥ እንዲያልፉ ተደርጓል። በተለያዩ ክልሎች ውስጥም በርካታ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ተደርጓል፤ ከደረጃቸውም ዝቅ ብለዋል። ይህ አሰራርም በህዝቡ የነቃ ተሳትፎ ገቢራዊ እየሆነ ነው።

ማንኛውም ተሃድሶ ያለ ህዝቡ ድጋፍ ግቡን ሊመታ ስለማይችል በአሁኑ ወቅት ሁሉም የህብረተሰቡ ክፍል በቀጥታ በተሃድሶው ላይ ተሳታፊ እንዲሆን ተደርጓል። በዚህም ህዝቡ ራሱ ቀጥተኛ ተሳታፊ ሆኖ ችግሩን ከመግለፅ ባለፈ የማይመጥነውንና የስነ ምግባር ጉድለት አለበት ብሎ የሚያምነውን የመንግስት ስራ ፈፃሚን እየገመገመ ተገቢው ርምጃ የመውሰድ ተግባራት እንዲከናወኑ እገዛ አድርጓል። ይህም የህዝቡን ቀጥተኛ ተሳታፊነትና የባለቤትነት መንፈስን የሚያጠናክር ነው። ይህ የህዝቡ ተሳትፎም ወደፊትም ቢሆን ተጠናክሮ ይቀጥላል።

ርግጥ የተሃድሶ ስራ የዘመቻና የአንድ ጊዜ ጉዳይ አይደለም። በተለይም ለተሃድሶው አነሳሽ የሆነው መልካም አስተዳደርን የማስፈን ተግባር በሂደት እንጂ በአንድ ጀምበር እውን የሚሆን አይደለም። እንደሚታወቀው በማንኛውም ዴሞክራሲን የህልውና ጉዳይ አድርጎ በሚንቀሳቀስ ሀገር ውስጥ የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ቁልፍ ነው። ለነገሩ መልካም አስተዳደር የዴሞክራሲ አካልና መሠረት ነው። ስለሆነም መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታን በግብነት አስቀምጦ መረባረብ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑ አያጠያይቅም።

ታዲያ ይህን ዕውነታ በውል የተገነዘበው የኢትዮጵያ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስትም ሃሳቡን ወደ ድርጊት ለመለወጥ በጥረት የታገዙ ጠንካራ እንቅስቃሴዎችን ከጀመረ 26 ዓመታትን አስቆጥሯል። በእነዚህ ዓመታት በርካታ ተግባራቶች ዕውን ቢሆኑም የሚፈለገውን ያህል ውጤት ማምጣት አልተቻለም።

በተለይም በፐብሊክ ሰርቪስ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የአገልጋይነት መንፈስን የተላበሰ አሰራር አልተፈጠረም። በመሆኑም ይህን የአገልጋይነት መንፈስ ለመፍጠርና በመንግስት ስልጣን ያለመገልገል አመለካከትን ፈር ለማስያዝ ለማስያዝ የተደረገው ጥረት አበረታች ነው። ይህም ስራው ወደፊት እየተጠናከረና የተፈጠሩትን ችግሮች በአስተማማኝ መንገድ ለመፍታት አሁንም ተግቶ መስራት የሚያስፈልግ መሆኑን ያመላክታል።

ርግጥ የመልካም አስተዳደር ስራዎች ከህዝቡ ጋር በቅርበትና በቀጥታ የሚያገናኙ በመሆናቸውና የህዝቡ የእርካታ መለኪያዎችም ስለሆኑ ጥንቃቄ የሚያሻቸው ጉዳዩች ናቸው። ህዝቡ በሚሰጠው እርካታ ተገቢ ያልሆነና ህዝቡን ለምሬት የሚዳርግ ከሆነ ቅሬታ ከመፍጠሩም በላይ፤ የዜጎችን የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚነትን ያደበዝዛል።

መንግስት ለህዝቡ የሚሰጠው አገልግሎት በተገቢው ሁኔታ እንዳይፈፀምና ህዝብ ከመልካም አስተዳደር ትሩፋቶች ተጠቃሚ እንዳይሆን ያደርጋል። ይህ ደግሞ መንግስት የሚሰጠው የመልካም አስተዳደር አገልግሎት በልማትና በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ እንዲያሳርፍ ያደርጋል።

እነዚህ ዕውነታዎችም የህዝቡን አመኔታ በመሸርሸር ለሁከትና ለብጥብጥ መዳረጋቸው የሚቀር አይመስለኝም። በሁከትና በብጥብጥ ውስጥ የሚኖር ህዝብ ደግሞ ልማትንና ዴሞክራሲን ዕውን ሊያደርግ አይችልም። ከዚህ አኳያ በ2008 ዓ.ም የታየው ችግር ተጠቃሽ ነው። እንዲህ ዓይነት ችግሮች ዳግም እንዳይፈጠሩ ደግሞ ተሃድሶ ማድረግ ሁሌም ያስፈልጋል።

በየጊዜው የሚስተዋሉ ችግሮችን እየተከታተሉ ተገቢ ምላሽ መስጠትና ለዚህ የሚሆን መፍትሔ አደራጅቶ በማይቀለበስ መልኩ ለህዝብ ማሳወቅ የአንድ ጊዜ ስራ አይደለም። ሊሆንም አይችልም። ቀጣይነትና ተከታታይነት ያለው ሊሆን ይገባል። አሊያ ግን አበው እንደሚሉት “አለባብሰው ቢያርሱ…” ዓይነት መሆኑ የሚቀር አይመስለኝም።

ቀጣይነት ያለው የተሃድሶ ስራ ልማትን ለማፋጠንና ዴሞክራሲን በፅኑ መሰረት ላይ ለማኖር መደላድልን ይፈጥራል። ልማት ከተፋጠነና ዴሞክራሲው እንዲጎመራ የሚያስችል ምህዳርን በፅኑ መሰረት ላይ የሚያኖር ምቹ ሁኔታ ከተፈጠረም እንደ ሀገር የምናስበውን ራዕይ ለማሳካት አያጠራጥርም። እናም ይሀን ሀገራዊ ራዕይ ዕውን ለማድረግም ዳግም ተሃድሶ ሂደት እየጎለበት ችግሮችን እንዲፈታ ማድረግ ያስፈልጋል። እናም ጥልቁ ተሃድሶ ይጠናከር፣ ይበልጥ ይጎልብት እላለሁ።   

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy