Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ፊት ለፊት ከኢፌዴሪ ም/ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጋር

0 419

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ፊት ለፊት ከኢፌዴሪ ም/ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጋር
ዘአማን በላይ
(ክፍል አንድ)
ዕለተ-አርብ። ተሲያት 10 ሰዓት ላይ። ከሳምንት በፊት። ጋዜጠኞች፤ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ሰብሳቢ ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን ቢሮ ተገኝተናል። ም/ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተደራራቢ ስራዎች የሚበዙባቸው ቢሆንም፤ ለቃለ መጠይቅ ቢሯቸው እንድንገኝ ይሁንታቸውን የሰጡን በፈጠነ የአጭር ጊዜ ቀጠሮ ነው። ቢሯቸው የመገኘታችን ምስጢርም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተጀመረበትን ስድስተኛ ዓመት ክብረ በዓል አስመልክቶ መሆኑን ስንገልፅላቸው፤ “በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ ወቅታዊ መረጃዎችን ለህዝብ ማድረስ ተገቢና ትክክለኛ ነው” በማለት እንደ የግድቡ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢነታቸው ስለ ጉዳዩ ሊነግሩን ፈቃደኛ ሆኑ። እናም እርሳቸውን ይህን ፅሑፍ በምታነቡት፣ የግድቡ ባለቤትና ጠባቂ በሆናችሁት የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ስም ምስጋናዬ ይድረሳቸው እላለሁ።…
ይህ ፅሑፍ የህዳሴው ግድብ ዙሪያ ብቻ የሚያጠነጥን ነው። የዚህ ፅሑፍ አቅራቢ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ያደረግናቸውን አንኳር ጉዳዩችን በመምዘዝ ለታዳሚዎቼ አቅርቤያለሁ። ለአቶ ደመቀ ካቀረብንላቸው ጥያቄዎች መካከል፤ የመላው የሀገራችንን ህዝቦች የስድስት ዓመታት ተሳትፎን በጥንካሬና በድክመት እንዴት ይገመግሙታል የሚለው አንዱ ነው። አቶ ደመቀ ለዚህ ጥያቄያችን ምላሽ የሰጡን ፕሮጀክቱ ሀገራዊ መሆኑንና ሁሉም ዜጋ ብርቅዬ አጀንዳው አድርጎ የያዘው እንደሆነ የገለፁልን አፅንኦት ሰጥተው ነው። በግድቡ የስድስት ዓመት ጉዞ የህዝቡን ጠንካራ ተሳትፎ አስመልክተውም፤ “…በእነዚህ ዓመታት ጉዞ ውስጥ ሊሰመርበት የሚገባው ስድስቱን ዓመታት ሙሉ የህዝቡ ተነሳሽነት እንዲሁም ባለቤትነት ስሜት ግለቱን እንደጠበቀና ቃሉን እንዳጠናከረ መቀጠሉን ነው።…” በማለትም ግድቡን በራሱ ገንዘብ፣ ዕውቀትና ጉልበት ያለ አንዳች ማቋረጥ ርብርብ እያረደገ መሆኑን ይገልፃሉ።
ይህን አባባላቸውንም መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የግድቡ መሰረት ድንጋይ ሲጣል ታላቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ የተናገሩት፤ ግንበኛው እኛው፣ መሐንዲሱ እኛው፣…ያሉትን፤ የሀገራችን ህዝቦች የባለቤትነት ፊርማ ያረፈበት ታላቅ ፕሮጀክት ሲሉ የገለፁትን፤ …የኢትዮጵያ ህዝብም ይህን ፕሮጀክት ለመገንባት ከመንግስት ጎን እንደሚቆም እርግጠኛ መሆናቸውን የተናገሩትን እንዲሁም ህዝቡ ደርግ የወደቀበትንና የሀገራችን የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ጮራ የፈነጠቀበት ግንቦት 20 በዓል ላይ ህዝቡ የገባውን ቃል ኪዳንና ግድቡን ለመገንባት ያሳየውን ተነሳሽነት ጭምር በማጣቀስ ያብራሩታል። አዎ! ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ “…የዛሬ ስድስት ዓመት የመሰረት ድንጋዩ ሲቀመጥ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በታላቁ መሪያችን የተላለፈው መልዕክት፣ በዚያኑ ዓመት የግንቦት 20 በዓል ሲከበር የተላለፈው መልዕክት በሁሉም ልብ ያደረ፣ ሁሉንም ያነቃነቀ ነበር። ያኔ የተፈጠረው ስሜትና ግለት እስካሁን ድረስ አለ። ያ ግለትና ያ የባለቤትነት መንፈስ ዛሬም ተጠናክሮተጠናክሮ ቀጥሏል።…” ሲሉ ነበር—የህዝቡ ተሳትፎ በስድስት ዓመቱ ውስጥ ግለቱን እንደጠበቀ ዛሬ ላይ መድረሱን የገለፁት።
ርግጥም አቶ ደመቀ እንዳሉት መላው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በግድቡ ግንባታ ላይ ከጅምሩ ጀምሮ ያደረጉት ተሳትፎ የሚያስደምም ነው። ለዘመናት አንገቱን ሲያስደፈው በነበረው ድህነት ላይ ዘመቻ የከፈተ ህዝብ፤ ከድህነት መውጣት እንደሚችል አንድ ማሳያ የሆነውን ግድብ ለመገንባት ባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ ባልተቋረጠ፣ በጋለ የባለቤትነት ስሜትና የ‘እለወጣለሁ’ ፅኑ መንፈስ ቢንቀሳቀስ የሚገርም አይሆንም። ምክንያቱም ይህ ህዝብ ድህነትን የመቅረፍና ከፍ ሲልም የማስወገድ የልማት አጀንዳን የሞት ሽረት ያህል ስለሚመለከተው ነው።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንንም፤ ይህ ስሜት በሆነ ቦታ ላይ በሆነ የህብረተሰብ ክፍል ላይ ብቻ ያልተመሰረተ፣ ይልቁንም ከዳር እስከ ዳር በሀገሪቱ በሁሉም ማዕዘን ባለቤትነት እንደተጋጋለና እንደጠነከረ መቀጠሉን እንዲሁም የስራው አስፈፃሚ አካላት የሚያከናውኑት ቅንጅታዊ ስራ የጥንካሬው መሰረት መሆኑን ያስረዳሉ። በመሆኑም የህዝባዊ ተሳትፎውን ጥንካሬ በሶስት መንገዶች ይገልፁታል። አንደኛው፤ የህዝብ ባለቤትነት ሲሆን፤ ሁለተኛው ከዚህ ጋር አያይዞ የተያዘው ግልፅ አቋምና በዚያ ላይ እየተገነባ የመጣው ቁመና ነው። ሶስተኛ ደግሞ፤ ስራውን ለመምራት የፕሮጀክት ማኔጅመንቱ፣ የሃብት አሰባሰቡ፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ ስራው የሚጠይቀውን ሁሉ በቁርጠኝነት ለመፈፀም እየተደረገ ያለው ርብርብ እንደሆነ ገልፀዋል።
አቶ ደመቀ ከህዝቡ ተሳትፎ አኳያ ያሉ ውስንነቶችንም ሳይጠቅሱ ማለፍ አልፈለጉም—ከዚህ አንፃር የሚታዩ ድክመቶች ከህዝቡ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ሳይሆኑ ከማስተባበር አኳያ ያዝ ለቀቅ የማድግ ሁኔታዎች መኖራቸውን በመግለፅ። እናም የሚታዩትን ድክመቶች “…ህዝቡ ይህን ያህል ግለቱና ባለቤትነቱ ተጠናክሮ እያለ፤ ከወር እስከ ወር፣ ከዓመት አስከ ዓመት ያን ግለቱን የሚመግብና ወደፊት የሚያራምድ ድጋፍና የማስተባበር ስራ ላይ የተወሰነ ያዝ ለቀቅ ስላለ ነው” በማለት ጠቁመዋል። ታዲያ እነዚህን ድክመቶች ማሻሻል ከተቻለ ሀገራዊ ድባቡና ሁሉም ነገር ምቹ በመሆኑ የበለጠ መስራት እንደሚቻል እምነት እንዳላቸውም አስረድተዋል።
ርግጥም የህዝቡ ግለትና የባለቤትነት ስሜት ጠንካራ ስለሆነ ይህን አቅቦ መቀጠል የግድ ነው። የህዳሴው ግድብ በተወሰኑ ሁነቶች አሊያም መድረኮች ብቻ ሊታጠር አይገባም። ሁሌም የማደራጀት፣ የመደገፍና የተግባቦት ስራ መከወን የየዕለት ተግባር ሊሆን ይገባል። ይህ ከሆነም፤ በህዝቡ ውስጥ አሁን ያለው የጋለ የተነሳሽነት መንፈስ ይበልጥ ጎልብቶ፣ በግድቡ ግንባታ ላይ ከፍተኛ ለውጦች ሊመዘገቡ መቻላቸው አጠያያቂ የሚሆን አይመስለኝም። እናም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደጠቆሙት፤ በማስተባበርና በሌሎች ድጋፍ የመስጠት ስራዎች ላይ ያለው ያዝ ለቀቅ የማድረግ ሁኔታዎችን ማረም ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ መሆን የለበትም—ግድቡ የብሔራዊ ማንነታችን መገለጫ ነውና።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እርሳቸው ስለሚመሩት የህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤትም አውግተውናል። ምክር ቤቱ ግልፅ የሆኑ ተልዕዎችንና ሃላፊነቶችን ይዞ የተደራጀ መሆኑን ነግረውናል። በህግ የተቀመጠ ጭምር እንደሆነም። በዚህ መሰረትም ህዝባዊ ተሳትፎ እንቅስቃሴ በበላይነት የመምራትና የማስተባበር ሥራዎችን ዋና ዋና የትኩረት መስኮችን በመለየት ተግባሩን አከናውኗል። አቶ ደመቀ እነዚህን ዋነኛ ስራዎችን በአራት ከፍለው ያብራራሉ።
በቀዳሚነት ያነሱት የሃብት ማሰባሰብ ስራን ነው። ፕሮጀክቱ የሚሰራው በእኛው አቅም ከመሆኑም በባሻገር፤ ዋነኛው የገቢ ምንጭ የመንግሥት በጀት መሆኑን ያስታወቁት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከህዝቡ ደግሞ ትልቅ ትርጉም ያለው የሃብት ማሰባሰብ ሥራ በቦንድ ግዥና በመሳሰሉት ይከናወናል። ይህን በበላይነት የማስተባበርና የመመራት ሥራው ከሞላ ጎደል በጥሩ ሁኔታ መቀጠሉን ተናግረዋል። በዚህ መሰረትም በአጠቃላይ 12 ቢሊዮን ብር ቃል መገባቱንና እስካሁንም ወደ 10 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ መሰብሰቡን አውስተዋል። ይህም ቀላል ቀላል አለመሆኑን ያስረዳሉ— ድርቅን የማሰሉ ተፅዕኖች መኖራቸውን በማስታወስ። ያም ሆኖ ግን የመንግሥት ሰራተኞች በቤት ኪራይ እና በልዩ ልዩ መስኮች ዋጋ እየከፈሉ ቃል በገቡት መሰረት እስከ 6ኛው ዙር ድረስ አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።
በባለሃብቱ በኩል እንደ አጠቃላይ ሲታይ ሲታይ ምላሹ፣ አስተዋፅኦውና ድጋፉ በጣም ጥሩ መሆኑንና ለዚህም እስከ 30 ሚሊዮን ብር ድረስ ቃል ገብተው ቦንድ ገዝተው የተሸለሙ መኖራቸውን ያስረዳሉ። በአንፃሩም ከዕለት ጉርሱ እየቀነሰ አስተዋፅኦ ከሚያደርገው የመንግስት ሰራተኛ ጋር በንፅፅር ሲታይ ባለሃብቱ ከገባው ቃል አኳያ የሚፈለገውን ያህል ሄዷል ማለት የሚቻል አለመሆኑን፣ ያም ሆኖ አስተዋፅኦው ግን ቀላል አለመሆኑን አመልክተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለተኛ ደረጃ የገለፁት ፕሮጀክቱ ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር በኩል እጅግ የመበዛውን የህብረተሰብ ክፍል በዚህ አስተሳሰብ ዙሪያ እንዲሰለፍ ማድረግ መቻሉን ነው። ርግጥ በየትኛውም ሀገር ውስጥ ቢሆን ብሔራዊ መግባባትን በአንድ ጊዜ ማምጣት አይቻልም። ብሔራዊ መግባባት ማለት የአንድ ሀገር ህዝብ በሁሉም ሳይሆን በአብዛኛዎቹ ሀገራዊ ጉዳዩች መግባባት ሲችል ነው። ይህ ጉዳይ ሂደት እንደመሆኑ መጠን በጊዜ ዑደት ውስጥ ገቢራዊ መሆን የሚችል ነው። ለዚህም ነው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ “ብሔራዊ መግባባት ሲባል በየጊዜው እየተገነባ የሚሄድ ስለሆነ ይህ ብርቅዮ ፕሮጀክት በዚህ ዙሪያ ትልቅ አጀንዳ ሆኖ እየተሰራበት ነው” በማለት የገለፁት። እናም በዚህ ረገድ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር የተጠናከረ ስራ ተከናውኗል ህብረተሰቡ ለግድቡ ቦንድ የመግዛት፣ የገንዘብና የዕውቀት አስተዋፅኦ የማድረግም ብሎም ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ በተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ዘርፍ አርሶና አርብቶ አደሩ ከዳር እስከ ዳር ማነቃነቁንም አቶ ደመቀ ያስረዳሉ። በዚህ ረገድ የታዩት ጉዳዩችም በአዎንታዊነት የሚታዩ ናቸው።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሶስተኛ ደረጃ ያነሱት ፐብሊክ ዲፕሎማሲን የተመለከተ ነው። የህዝባዊ ተሳትፎው ማስተባበሪያ ምክር ቤቱ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የምትከተለው አተያይ በተፋሰሱ ሀገራት ጋር ያላት ተግባቦት በሚጠናከርበት ደረጃ ተሰርቷል። ከዚህ አንፃር የሚታዩ አፍራሽ እንቅስቃሴዎችን፣ የድሮውን ታሪክ ወደፊት እያመጡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ቦታ የሌለውን አስተሳሰብ ይዘው ለመራመድ የሚሹ ሃይሎችን ምልከታ ለመመከት፣ የሰለጠነና ዴሞክራሲያዊ የሆነ የተቀናጀ መንገድን ምክር ቤቱ መከተሉን አብራርተዋል።
ርግጥም በዙህ ፅሑፍ አቅራቢ እምነት፤ አሁን ባለንበት 21ኛው የሉላዊነት (Globalization) ክፍለ ዘመን ዓለም ወደ አንድ መንደርነት ተቀይራለች። ሉላዊው ዘመን በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረግ ስልጡን ዴሞክራሲያዊ ውይይትን፣ ሰጥቶ የመቀበል መርህንና በዚህም ሳቢያ የሚፈጠር የጋራ ተጠቃሚነትን ገቢራዊ ያደርጋል። ይህም አንዱ ከሌላው ጋር በመተባበር እጅ ለእጅ ተያይዞ ማደግን እንጂ በተናጠል ወይም ለብቻ ተደብቆ የሚመፈፀም አንዳች ነገር አለመኖሩን የሚያመላክት ይመስለኛል። እናም በ21ኛው ክፍለ ዘመን ማድረግ የሚቻለው በክፍለ-ዘመኑ እሳቤ ልክ እንጂ፣ በ19ኛው ክፍለ ዘመን (ለዚያውም በቅኝ ገዥዎች አስተሳሰብ) አይደለም። እናም ይህን “የኋላን ወደፊት” የማምጣትን ያልተገባ አስተሳሰብን በተጠናከረ የተግባቦት ስራ መቀልበስ ተገቢና ትክክል ይመስለኛል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤቱን ተግባሮች አስመልክተው በአራተኛ ደረጃ የገለፁት፣ መስሪያ ቤቱ የሚከተላቸውን መደበኛ አሰራሮችን ነው። በዚህም ምክር ቤቱ ሪፖርቶችን እንደሚገመግም፣ ለስራ አስፈፃሚው አቅጣጫ እንደሚሰጥ፣ አባላቱም የስራ ክፍፍል አድርገው የራሳቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ገልፀዋል። ስራ አስፈፃሚውም ክልላዊ ምክር ቤቶችን ክትትል ያደርጋል።
ምክር ቤቱ አቅዷቸው ያልሰራቸው ጉዳዩች ስለመኖራቸው የጠየቅናቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ፤ “ከተሰጡት የትኩረት መስኮች አኳያ አፈፃፀሙ በአዎንታዊ መልኩ የሚታይ ሲሆን፤ ትልቅና መሰረታዊ የሚባል አቅዶ ያልሰራው ነገር የለም። ሆኖም ዝርዝር ጉዳዩች በአንድ ዓመት ተፈፅመው ሳይሰሩ ወደ ሌላኛው ዓመት የተሸጋገሩ አሉ።” ብለዋል። በምሳሌነትም የህብረተሰቡን እንቅስቃሴ የበለጠ ለማጠናከር ቶክ ሾው የሚል ፕሮግራም ለሁለት ዓመት ያህል ተንከባሎ በዚህ ዓመት መተግበሩን ያነሳሉ። የፕሮጀክት እንቅስቃሴውን፣ የህዝብ ጉብኝቱን፣ በየዓመቱ የሚከበረውን በዓል የበለጠ ገላጭ በሆነ መልክ እየተሰራ ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍ እንዲሁም ለመማሪያ እንዲሆን የማድረግ ስራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል ረገድ የተወሰኑ የመንጠባጠብና በተሟላ ሁኔታ ያለመፈፀም ሁኔታዎች መኖራቸውንም ገልፀዋል። በየዓመቱ መሰረት ድንጋይ የተቀመጠበት ዓመት ሲጠጋ ሞቅ ያለ እንቅስቃሴ፤ በሌሎቹ ጊዜያት ደግሞ በስራ መወጠር ምክንያት ቀዝቀዝ የማለት ሁኔታዎች እንደነበሩና እነዚህን ገምግሞ ለማስተካከል መሞከሩንም አስረድተዋል። ያም ሆኖ ስራዎቹ በወሳኝነት ስኬታማና ውጤት ያመጡ መሆናቸውን አብራርተዋል።
ለአቶ ደመቀ ያቀረብንላቸው ሌላኛው ጥያቄ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለግድቡ እያደረጉት ያለውን ተሳትፎ የሚመለከት ነበር። እርሳቸውም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሀገር ውስጥ እንደተፈጠረው ስሜት ሁሉ፤ እጅግ የሚበዛው ለህዳሴው ግድብ ስኬት በሞራል፣ ለቦንድ ግዥ ቃል በመግባትና በመግዛት እያደረገው ያለው ድጋፍ የሚያበረታታ መሆኑን አስረድተዋል። እንቅስቃሴው በየዓመቱ ሲታይ አዎንታዊ መሆኑንና ዲያስፖራውን በተመለከተ ዕቅድ ሲያዝ ‘ምን ያህል የቦንድ ግዥ ይፈፀማል የሚል?’ ተብሎ በየሀገሮቹ ካለው የዲያስፖራ ቁጥር፣ ከየሀገሮቹ ህግና የፋይናንስ እንቅስቃሴ ጋር በተጣጣመ መልኩ ለመስራት ጥረት መደረጉን ገልፀዋል። በዚህ ረገድ የነበሩ ክፍተቶችን መሙላት መቻሉንም በማስረዳት ጭምር።
ታዲያ የዚህ ፅሑፍ አቅራቢ ስለ ዲያስፖራው የግድቡ ተሳትፎ ሳስብ፤ በቅድሚያ ወደ አዕምሮዬ የመጣው የሀገራችንን ልማትና ዕድገት ማየት የማይሹት እንደ አሸባሪዎቹ ግንቦት ሰባት፣ ኦነግና አምሳያዎቻቸው የባዕዳን ተላላኪ በመሆን በኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አንጡራ ሃብት እየተገነባ ያለውን ግድብ ቢቻላቸው ለማደናቀፍ የሚያከናውኑት ቀቢፀ-ተስፋ ነው። በቁጥርና በአመለካከት እጅግ የሚበዛውን ዲያስፖራ የማይወክሉት እነዚህ ጥቂት ቡድኖች፤ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን በማምታታት የተቆራፈደ የልመና ኮሮጇቸውን ለመሙላት የሚሯሯጡ ናቸው። ቡድኖቹ ቀቢፀ-ተስፋቸውን “በላም አለኝ በሰማይ ወተቷንም አላይ” ተስፋ ለማሳካት ሲሉ ከየትኛውም ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይል ጋር የሚሰለፉ ናቸው።
ያም ሆኖ የህዳሴው ግድብ የኢትዮጵያ ህዝቦች በዓባይ ውሃ ላይ የሚያኖሩትና ለመጪው ትውልድ የሚያወርሱት “የውሃ ላይ ሃውልት” በመሆኑ፤ ይህ ሃሳባዊ ተስፋቸው ጉም የመዝገን ያህል የሚቆጠር እንጂ ምንም ዓይነት ውጤት የሚያመጣላቸው አይደለም። አይችልምም። በእኔ እምነት በውጭ ያለው ዲያስፖራ የእነዚህ ጥቂት ቡድኖች ፍላጎት የሀገራችንን በራስ አቅም የመልማት መብትን መፃረር፣ ሀገራችን ስታድግ ሁሌም ‘እሬት…እሬት’ የሚላቸውን አካላት በማስደሰት እርጥባን ለማግኘት ሲሉ የህዝቡን ተነሳሽነት ማኮስመን እንዲሁም በገዛ ሀገራቸው ዕድገት ዓይናቸው ደም የሚለብስና ከባዕዳን ጋር የተሰለፉ “ባንዳዎች” ናቸው። እናም በውጭ የሚኖሩ ጥቂት ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በእነዚህ የባዕዳን ተላላኪዎች ‘በማጭበርበር ገንዘብ የመመንተፍ ስልት’ ሳይታለሉ፣ ድጋፋቸውን የሀገራቸው ህዝብ ይዞት ለተነሳው የልማት ትልም አሁን ካለው ይበልጥ መስጠት ያለባቸው ይመስለኛል።
እስቲ ከዚህ ግላዊ ምልከታዬ ልውጣና አሁን ደግሞ ወደ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ቃለ-ምልልስ ልውሰዳችሁ። ለአቶ ደመቀ ቀጥሎ ያቀረብንላቸው ጥያቄ፤ እርሳቸው የሚመሩት ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ስላከናወናቸው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራዎች ነው። እርሳቸውም የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አንዱና ዋነኛው ስራ በሀገር ቤት ውስጥ ህዝቡ የፈጠረውን ስሜትና ንቅናቄ ወደፊት ይዞ የሚጓዝ፣ ተገቢውን ወቅታዊ መረጃ እየሰጠ ለሀገራዊ መግባባት መሰረት እንዲሆንና እየተገነባ እንዲሄድ ማድረግ መሆኑን ገልፀዋል። ከተፋሰሱ የታችኛዎቹ ሀገራት ከፍ ባለ ስጋትና ጥርጣሬ ውስጥ የሚወድቁትን ለይቶ ግድቡ ሁሉንም ሀገራት የሚጠቅምና ምክንያታዊ መሆኑን እንዲገነዘቡ ማድረግ ሁለተኛው ስራ መሆኑን አስረድተዋል። እናም ከዚህ አኳያ ሁሉም የፋሰሱ ሀገራት ከራሳቸው ጥቅም አኳያ ሁኔታውን ስለሚመለከቱት፤ ሱዳኖች የወሰዱት አቋም መኖሩንና ግብፆችም በተነፃፃሪነት ለራሳቸው ብለው ፈትሸው የያዙት አቋም መኖሩን ይገልፃሉ። ፐብሊክ ዲፕሎማሲው ከዚህ አኳያ ትልቅ ሚና እንደነበረውና ወደፊት የህዝብ ለህዝብ ትስስሩ መጠናከር እንዳለበት በማስረዳት ጭምር።
ርግጥ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራው በዚህ ብቻ የታጠረ አይደለም። ከዚህ ከፍ ብሎም በዲፕሎማሲና በፐብሊክ ዲፕሎማሲ አካላት ውስጥ እንደሚሰራም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የዲፕሎማሲና የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አካል የሆነው የተለያዩ ተወካዩች ሀገር ቤት ሲመጡ ግድቡን እንዲመለከቱት፣ የመንግስት ኃላፊዎችና ዲያስፖራዎች ሲመጡም እንዲጎበኙና መሬት ላይ ያለውን ዕውነታ እንዲያዩ በማድረግ ሁሉም አምባሳደር ሆኖ በሄደበት ዓለም መልዕክቱን እንዲያስተላልፍ እናደርጋለን” በማለት የህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤቱን ተግባራት አስረድተዋል። የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችም ቦታው ድረስ ሄደው መሬት ላይ ምን እየተሰራ መሆኑንና ትክክለኛውን ገፅታ እንዲይዙ የማድረግ ተግባራት መከናወናቸውንም የሚገልፁት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ባለፈው 2008 ዓ.ም መጨረሻ ላይ የአሜሪካንና የጃፓንን አምባሳደሮች ጨምሮ አራት አምባሳደሮች ይፋዊ ጉብኝት ማድረጋቸውንና ይህም የዲፕሎማሲው አንድ አካል መሆኑን ጠቅሰዋል። ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ የተሳሳቱ ሃሳቦችንና አቅጣጫዎችን ለመመከት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያከናወናቸው ተግባራትም ውጤታማ እንደነበሩ አስታውቀዋል።
አዎ! አቶ ደመቀ እንዳሉት፤ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴው ግድብ ዙሪያ የሚነሱ የተሳሳቱ ሃሳቦችንና አቅጣጫዎችን መመከት የሁሉም ሀገር ወዳድ ዜጋ ድርሻ መሆን እንዳለበት ሊዘነጋ አይገባም። ሀገራችንና ህዝቦቿ ግድቡን እየገነቡ ያሉት በድህነት ላይ የከፈቱትን ዘመቻ በድል ለማጠናቀቅ ካላቸው ጥልቅ ፍላጎት እንጂ የትኛውንም የተፋሰሱን ሀገር ለመጉዳት አይደለም። እንዲያውም ግድቡ ተጠናቅቆ በሙሉ ኃይሉ የኤሌክትሪክ ኃይል ሲያመነጭ፤ ከዚህ ልማት የቀጣናውም ይሁን የተፋሰሱ ሀገራት ተጠቃሚ ይሆናሉ። እናም ከዚህ አኳያ የሚከናወኑ ተግባራትን ቦታው ድረስ ሄዶ በመረዳትና መልሶ ስለ ግድቡ ጠቀሜታ በማስረዳት ሆን ተብለው እየተሳሳቱ የሚቀርቡ አስተሳሰቦችን በመመከት ሁሉም ዜጋ ለሀገሩ አምባሳደር መሆን ይኖርበታል እላለሁ።
ውድ አንባቢያን፤ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ሰብሳቢ ጋር ፊት ለፊት ያደረግነው ቆይታ በዚህ አልተቋጨም። ቀሪውን ቃለ ምልልስ በክፍል ሁለት ፅሑፌ ይዤ እመለሳለሁ።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy