Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ፕሬዚዳንት ትራምፕ የአሜሪካ መከላከያ ኃይል በአልሸባብ ላይ ተጨማሪ ጥቃት እንዲፈጽም ፈቀዱ

0 361

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የመከላከያ ኃይሉ በአልሸባብ ላይ የአየር ጥቃትን ጨምሮ ተጨማሪ ወታደራዊ ዕርምጃ እንዲወስድ ፈቀዱ፡፡ሐሙስ መጋቢት 21 ቀን 2009 ዓ.ም. የፔንታጎን ቃል አቀባይ ካፕቴን ጄፍ ዴቪስ በሰጡት መግለጫ፣ በሶማሊያ የተለያዩ ጥቃቶች በመፈጸም በሽብር ተግባር ላይ የተሰማራው አልሸባብን ለመደምሰስ የአገሪቱ አየር ኃይል ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖችን) በመጠቀም ጭምር ወታደራዊ ዕርምጃ እንዲወስድ፣ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ትዕዛዝ መስጠታቸውን አስታውቀዋል፡፡

የአሜሪካ መንግሥት በሶማሊያ ሊወስደው ያቀደው ይኼው የአየር ጥቃትና የምድር ወታደራዊ ዕርምጃ አልሸባብን በመዋጋት ላይ የሚገኘው የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል (አሚሶም) እና የሶማሊያ የፀጥታ ኃይሎችን ለመደገፍና ለማጠናከር ያለመ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ውሳኔው ፕሬዚዳንት ትራምፕ የአሜሪካ ንፁኃን ዜጎች ከማናቸውም ዓይነት ጥቃት ለመከላከል የጦር ኃይላቸውን እንደፈለገው ዕርምጃ እንዲወስድ ሊፈቅዱ ይችላሉ በማለት ሲቀርቡ የቆዩ ወሬዎችን የሚያጠናክር ነው እየተባለ ነው፡፡

በቅርቡ ፕሬዚዳንቱ ወደ ሶሪያና ኢራቅ ተጨማሪ የጦር ኃይል መላካቸውም እንደ ማሳያ ይጠቀሳል፡፡

በቅርቡ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው የሰላም ማስከበር ሥልጠና ማዕከል በአፍሪካ የአሜሪካ የጦር ኃይል (አፍሪኮም)፣ ከአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች የጦር አዛዦችና ከአሚሶም የጦር አመራሮች ጋር የሶማሊያን ፀጥታና ደኅንነት በተመለከተ ምክክር ማድረጉ አይዘነጋም፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ የአፍሪኮም ኮማንደር ጄኔራል ቶማስ ዋልድሃውዘር፣ አሜሪካ በሶማሊያ የምትከተለው የፀጥታ ፖሊሲ እንዲቀየርና ከአልቃይዳ ጋር ትስስር ያለው አልሸባብ ላይ ጥብቅ ዕርምጃ እንዲወሰድ ጥያቄ ማቅረባቸውን ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡

አሜሪካ በሶማሊያ ውስጥ እምብዛም ብዛት የሌላቸው ወታደሮች አሏት፡፡ እስከ ዛሬ ሶማሊያን ዋና የጦር ቀጣና ተደርጋ አልወሰደችም ነበር፡፡

ሰሞኑን ፕሬዚዳንት ትራምፕ የፈረሙት መመርያ ግን ሶማሊያ ውስጥ ግልጽ የፀጥታ ሥጋት መኖሩን የሚያመላክትና ጠንከር ያለ ወታደራዊ ዕርምጃ ለመውሰድ የሚፈቅድ ነው ተብሏል፡፡

በዚሁ አዲሱ መመርያ መሠረት የአሜሪካ የጦር አዛዦች ከዋሽንግተን ምንም ዓይነት የፖለቲካ ውሳኔ ሳያስፈልጋቸው የመሰላቸውን ወታደራዊ ጥቃት በአልሸባብ ላይ እንዲወስዱ የሚያስችል ነው፡፡

ከአዲሱ የአሜሪካ ወታደራዊ ዕቅድ ጋር በተያያዘ ለአልጄዚራ አስተያየታቸውን የሰጡት የኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ የአፍሪካ ቀንድ የፀጥታ ተንታኝ አቶ ራሺድ አብዲ፣ አሜሪካ ይህን ውሳኔ ለመውሰድ የተነሳሳችው ከአልሸባብ የተወሰነ ቡድን ተነጥሎ ከአይኤስ ጋር እየሠራ መሆኑን ስለተገነዘበች መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ባለፈው ዓመት የአሜሪካ አየር ኃይል ከ14 ጊዜ በላይ የአየር ጥቃት ፈጽሟል፡፡ በርከት ያሉ የአሸልባብ ከፍተኛ አመራሮች (ሐሰን አሊ ዶሬና አብዱላሂ ሐጂ ዳውድን ጨምሮ) መገደላቸው ይታወሳል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy