Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሀገራችን ተፈላጊነቷ እየጨመረ ነው!

0 275

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሀገራችን ተፈላጊነቷ እየጨመረ ነው! /ቶሎሳ ኡርጌሳ/

              ከመሰንበቻው በኢፌዴሪ መንግስት አማካኝነት የተከናወኑትን የሁለትዮሽ ግንኙነት በአንክሮ የተከታታለ ሰው ኢትዮጵያ የቀጣናው ተፈላጊነቷ እየጨመረ መምጣቱን መገንዘቡ አይቀርም። በምዕራቡ ዓለም በኩል የአሜሪካ መንግስት ከፍተኛ ልዑካን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ከሀገራችን ጋር ያላቸው የጠበቀ ግንኙነት እንዲጠናከር ፍላጎት እንዳላቸው መግለፃቸው፣ የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ባለስልጣናት አዲስ አበባ በመገኘት ከኢትዮጵያ ጋር የሚያደርጉት ግንኙነት እንዲጠናከር እንደሚሹ መናገራቸው እንዲሁም የእንግሊዝ መንግስትም የኢትዮጵያ አጋርነቱን ማጎልበት እንደሚሻ በላካቸው ልዐካኑ አማካኝነት ማስታወቁ ከሚጠቀሱ ወሳኝ ኩነቶች ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው። ሰሞነኛው የቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌየር ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ያደረጉት ውይይትም እንዲሁ በአስረጅነት ሊቀርብ የሚችል ነው። ሌላ ሌላም።…

የምስራቁን ዓለም በተመለከተም ቻይና፣ ጃፓንና መሰል ሀገሮች ከሀገራችን ጋር ተሳስረው በመስራት የጋራ ተጠቃሚነትን ለማጎልበት እንደሚጥሩ በተደጋጋሚ ገልፀዋል። ወንድም ከሆኑት አፍሪካዊያን ሀገራት ውስጥም ከላይቤሪያ፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከኬንያ፣ ከታንዛኒያ፣ ከሞዛምቢክ፣ ከሶማሊያና ከአልጄሪያ ሀገራት ጋር እየተረገ ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚጠቀስ ነው። በቅርቡም የሱዳን ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ሐሰን አልበሽር አዲስ አበባ ተገኝተው ያደረጉት የሁለት ቀናት የስራ ጉብኝት፤ ኢትዮጵያ በምዕራቡም፣ በምስራቁም ይሁን በአፍሪካውያን ወንድሞቻችን ዘንድ ምን ያህል ተፈላጊ ሀገር እየሆነች እንደመጣች የሚያሳይ ይመስለኛል።

ታዲያ ለዚህ ሁሉ መነሻው የኢፌዴሪ መንግሥት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲሁም የአካባቢውንና ጎረቤት ሀገሮችን ለጋራ ጥቅምና ሰላም እንዲሰሩ የሚጋብዝ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲን መከተሉ የሚያጠያይቅ አይመስለኝም፡፡ ይህም እንደ ቀድሞዎቹ የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲዎች የሀገር ውስጥ ጉዳዮችን ቸል በማለትና ወደ ውጭ ያነጣጠረ ሳይሆን በቅድሚያ በሀገር ውስጥ ሰላም በማስፈን በማረጋጋት ላይ ትኩረት በማድረግ በከባቢያችን ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም እንዲፈጠርና የጋራ ልማትና ትብብር እንዲጠናከር ማድረግ ነው፡፡  

የሀገራችን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ብሔራዊ ጥቅማችንን የማስጠበቅና ሀገራዊ ህልውናችንን የማረጋገጥ እንዲሁም ሌሎችን በጠላትነት ሳይሆን በአጋርነት መንፈስ በመመልከት ሀገራት ከእኛ፣ እኛም ከእነርሱ ተጠቃሚ የምንሆንበትን መንገድ ቀይሷል። እርግጥም ፖሊሲው ከማንኛውም ሀገር ጋር የሚኖረን ግንኙነት በመሰረታዊ ሀገራዊ ጥቅማችን ደህንነት ላይ የተመሰረተ፣ እንዲሁም የልማትና የዴሞክራሲ ሂደቱ ስር እየሰደደና የሀገራችን ዕድገት እየተፋጠነ በሄደ ቁጥር ለአደጋ ተጋላጭነታችን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀንስ ያየሚያረጋግጥ ነው።

የኢፌዴሪ መንግስት ደህንነታችንን ለማስጠበቅ ዋናው መሣሪያ ልማትና ዴሞክራሲን በሀገር ደረጃ ማረጋገጥ እንደሆነ በፅኑ ያምናል፡፡ በዚህ ረገድ ተመስርቶም ዲፕሎማሲያችን በቂ ጥናት በማካሄድ አደጋዎችን ለመቀነስ፣ ግጭቶች ሲፈጠሩ በድርድር እንዲፈቱ ለማድረግ፣ በዚህ ሂደት ሊፈቱ ያልቻሉትን ለመከላከል አቅም መገንባት ወሳሽ መሆኑንም ያስረዳል።

ሀገራችን የምትከተለው የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ለተፈላጊነቷ መጨመር ምክንያት የሆነ ይመስለኛል። ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራትና ተቋማት ጋር የምታደርጋቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና እየጎለበተ መጥቷል፡፡ ልማታዊ ዲፕሎማሲውም ተጠናክሯል፡፡ በሰጥቶ መቀበል መርህ ከልዩ ልዩ ሀገሮች ጋር ግንኙነቷን በማጠናከር የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር እየሰራች ነው፡፡ በዚህም ውጤታማም በመሆን ላይ ትገኛለች፡፡

የሀገሪቱን የውጭ ግንኙነትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ስፍራ ለማጎልበትም ባለፉት 26 ዓመታት ያህል ሰፊ ጥረት ተደርጓል፡፡ ለሀገሪቱም ሆነ ለአካባቢው የተረጋጋ የፖለቲካ ሂደት እንዲኖር ግጭቶችና ውዝግቦች በሰላማዊ ጥረት እንዲፈቱ ብቻ ሳይሆን የሠላምና የትብብር አድማሱ እንዲሰፋ እያደረገች ትገኛለች፡፡

ኢትዮጵያ በምትከተለው በዚህ የትብብርና የሰላም ዲፕሎማሲ መርህ መሰረት በዓለም ዙሪያ ካሉት ሀገሮች ጋር ያላት ግንኙነት በጋራ ጥቅም ላይ እንዲመሰረት ሆኗል፡፡ በዚህም ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ትስስሯ ከኤርትራ በስተቀር ከሌሎች ሀገሮች ጋር ትልቅ ስፍራ መድረሱን ሰሞኑን የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የመስሪያ ቤታቸውን የስራ አፈፃፀም አስመልክተው ለኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት ላይ አስታውቀዋል፡፡

እርግጥ የኢፌዴሪ መንግስት ቀደም ሲል ሀገሪቷን ያስተዳድሩ የነበሩ መሪዎች ይከተሉት በነበረው የተሳሳተና ጎረቤት ሀገሮችንም ሆነ ሌሎችን በጠላትነት የመፈረጅ አካሄድ ላይ በፅንሰ ሃሳብም ሆነ በተግባር መሰረታዊ ለውጥ እንዲኖረው መደረጉ ሀገራችን አሁን ለምትገኝበት የተፈላጊነት ቁመና አብቅቷታል ማለት ይቻላል፡፡ ምን ይህ ብቻ፡፡ በሀገር ውስጥም የሀገሪቷ ዋነኛ ጠላት ድህነት ነው የሚል ፅኑና ቁርጠኛ እምነት ስለተያዘ ጭምር ነው፡፡ እናም ሀገሪቱ ከውርደት፣ ከኋላ ቀርነትና ከተለያዩ የስጋት ምንጮች ነፃ ልትሆን የምትችለው፣ ፈጣን የኢኮኖሚ ልማት እንዲሁም የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና መልካም አስተዳደር በተሳካ መንገድ እንዲካሄዱ ስለተደረገም ነው፡፡ የእነዚህ ድምር ውጤቶችም ሀገራችንን የተፈላጊነት ማማ ላይ እንድትወጣ አድርጓታል፡፡

ሀገራችን የምስራቅ አፍሪካን ሰላም ለማስጠበቅ ብሎም የዓለማችን ጠንቅ የሆነውን አሸባሪነትን በመዋጋት እያከናወነቻቸው ያለችው ተግባራትም ለተፈላጊነቷ መሰረት የሆኗት ይመስለኛል። በዓለምና አህጉር አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ ሰላም የማስከበር ተልዕኮ ረዥም ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከደርግ ውድቀት በኋላ የሰላም ግንባታ ዲፕሎማሲን በመከተሏ የአፍሪካ ቀንድን ጨምሮ የአህጉሪቱን ሠላምና መረጋጋት ለማጠናከር የሰላም አስከባሪ ኃይሏን በብሩንዲ፣ በሩዋንዳ፣ በላይቤሪያ፣ በሱዳን ዳርፉርና አብዬ ግዛቶች በሙሉ ፈቃደኝነትና በብቃት አሰማርታለች፤ አኩሪ ተግባርም በመፈፀም ላይም ትገኛለች፡፡ በሶማሊያም በአሚሶም ጥላ ስር ሆና አልሸባብን ለመደምሰስ በሚደረገው ጥረት ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተች ነው፡፡

እነዚህ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ስኬታማ መሆናቸውና በአሁኑ ወቅት ወደ ላቀ ደረጃ እየተሸጋገሩ መምጣታቸው እንዲሁም ሀገራችን ለሰላም መስፈንና አሸባሪነትን ለመዋጋት እያደረገችው ያለችው ጥረት ብሎም ሰላም የተናጠል ሳይሆን የጋራ አጀንዳ መሆኑን በማረጋገጧ ይበልጥ ተፈላጊነቷ እንዲጨምር አድርጓል፡፡ ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ የምትከተለው ሰጥቶ የመቀበል ፖሊሲ በሁሉም የዓለማችን ሀገራት በሚባል መልኩ ተፈላጊ አድርጓታል፡፡ እርግጥ አሁን በምንገኝበት ዓለም ውስጥ ለብቻ ሮጦ ማሸነፍ አሊያም ተጠቃሚ መሆን አይቻልም፡፡ ያለው አማራጭ ተያይዞ ማደግ ብቻ ነው። ተያይዞ ለማደግ ደግሞ በመርህ ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ የግድ ይላል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሁሉንም ወገን ተጠቃሚና አሸናፊ የሚያደርግ ፖሊሲ ደግሞ ተፈላጊ ያደርጋል፡፡ ሀገራችንም ያደረገችው ይህንኑ ነው፡፡ እናም ተፈላጊነቷ ይበልጥ እንዲደረጅ የምታከናውነውን የጋራ ተጠቃሚነትና የትኛውንም ሀገር የልማት አጋር አድርጎ የመቁጠር መርሆዋን ነገም ይበልጥ አጠናክራ ልትቀጥል ይገባል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy