Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ህገ መንግስቱና የተጎናፀፍናቸው መብቶች

0 314

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ህገ መንግስቱና የተጎናፀፍናቸው መብቶች

                                     ዳዊት ምትኩ

ኢትዮጵያ ከ80 በላይ የተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ያቀፈች አገር ነች፡፡ እነዚህ ማንነቶች ባለፉት የዘውድና ወታደራዊ አገዛዝ ዘመናት ማንነታቸውን እንዲሸሽጉ አሊያም ጨርሰው እንዲፍቁ የተገደዱበት ሥርዓቶች ነበሩ፡፡ በነገሥታቱ ዘመን የኢትዮጵያዊነት መለኪያ የራስ ማንነትን በመተው የገዥዎችን ቋንቋ መጠቀም፣ ባህልና ኃይማኖትን መከተል፣ ገዥዎቹ የደገፉትን መቀበልና መስሎ መታየትን ነበር፡፡

በመሣፍንታዊ ሥርዓተ መንግሥት “አንድ አገር” የመፍጠርና የማቃናት ሂደት፤ “አንድ ቋንቋ፤ ባህል፤ ኃይማኖትና  አገር” በሚል ፍልስፍና ማንነትን በማፈን የተከናወነ ሆኖ ከኢኮኖሚ ጭቆና ጋር በማስተሳሰር የተፈፀመ ነበር፡፡ በነገሥታት ዘመን ሌሎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችም የማይታሰቡ ነበር፡፡ የሥርዓቱን ፍፁማዊነት ለመግለጽ “ንጉስ አይከሰስ፤ ሰማይ አይታረስ” በሚል ተረት ይገለጽ ሁሉ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡

ዘውዳዊውን ሥርዓት ተክቶ የመጣው የደርግ አስተዳደር በዘውድ ዘመን የነበረውን የማንነት አፈናና የኢኮኖሚ ጭቆና አጠናክሮ ቀጥሎበታል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነታቸውን ለማስከበር በአፄው ዘመን የጀመሩትን ትግል ለማጥፋት አስከፊ ጭፍጨፋ ፈፅሟል፡፡ ማንነትን የማስከበርና እኩልነትን የማረጋገጥ የመብት ጥያቄዎችን በሠላማዊ መንገድ ማንሳት ይቅርና ማሰብ በራሱ የሕይወት ዋጋን ያስከፍላል፡፡

ርሶ አደሮች ምርታቸውን በገበያ ዋጋ እንዳይሸጡ የዋጋና የኮታ ቁጥጥር ሥርዓት በመዘርጋት፤ ሀብታቸውን፣ ጉልበታቸውንና እውቀታቸውን አሟጥጠው ለተሻለ ምርታማነት እንዳይሰሩና ኑሯቸውን እንዳይለውጡ ነፃነታቸውን ያፈነ ሥርዓት ነበር፤ ደርግ ይከተለው የነበረው፡፡

የኢትዮጵያ ሕብረ ብሄራዊ ፌዴራል ሥርዐት የተመሠረተበት አንዱ መሠረታዊ አስተሳሰብ ያለፉት መንግሥታት የፈጠሯቸውን የተዛቡ ግንኙነቶችን ማስተካከል ነው የሚባለውም ያለምክንያት አይደለም፡፡

ይህም ሲባል በዋነኛነት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የኃይማኖቶች እኩልነትን ማረጋገጥ ነው፡፡ ዜጎች ቋንቋቸው፣ ባህሎቻቸው፣ ታሪኮቻቸውና የማንነት መገለጫዎቻቸውን እንዲያስፋፉና እንዲያሳድጉ የሚያስችላቸው እኩል እድል መፍጠር ማለት ነው፡፡   የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከታሪካቸው የወረሱትን በጎ ትስስር በማጎልበት በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አዲስ የሕዝቦች ግንኙነት መፍጠር ከፌዴራላዊ ሥርዓቱ መሠረታዊ አስተሳሰቦች አንዱ ነው፡፡ ኢትዮጵያን በአዲስ የግንኙነት መሠረት የመገንባት ጉዳይ የሁሉም ማንነቶች የጋራ እቅድ ነውና፡፡

ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በአገራዊ አጀንዳዎች ላይ የመወሰን ሥልጣንና ኃላፊነት እንዲኖራቸው በማድረግ በኢትዮጵያ እድገትና ሥልጣኔ ላይ እንዲረባረቡ የሚያስችላቸው ምህዳር መፍጠርም ያስፈልጋል፡፡ ይህ ዓይነቱ አዲስ ግንኙነት ኢትዮጵያን በፅኑ መሠረት ላይ ለመገንባት የሚያስችል ሰፊ አቅምና ጠንካራ ጉልበት እንዲኖር ያስችላል፡፡ የጋራ አስተዳደር የተፈጠረበት አንዱ መነሻ እምነትም ሁሉም ማንነቶች የኢትዮጵያ ባለቤቶች ለማድረግ ነው፡፡

እንዲሁም ማንነቶች በአካባቢ ጉዳዮችና እነሱን በሚመለከቱ አጀንዳዎች ላይ ወሳኞቹ እንዲሆኑ ማድረግ አንዱ መሠረታዊ እምነት ነው፡፡ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የእለት ተእለት አኗኗራቸውንና የወደፊት ሕይወታቸውን በሚወስኑ አጀንዳዎች ላይ የሚወስንላቸው ከላይ የሚጫን ኃይል እንዳይኖር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ይህንን እውን ማድረግ ማለት “አንድ ቋንቋ፣ ባህል፣ ኃይማኖት” የሚለውን ያለፉት ገዥዎች ሌጋሲ ለማስወገድ ያስችላል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በጉዳዮቻቸው ላይ ባይተዋር የሆኑበትን የተዛባ ግንኙነት በማስቀረት ከአካባቢያዊ አጀንዳ ተነስተው ለአገር ግንባታ የሚበጁ በጎ ሀሳቦች እንዲያመነጩ የሚያስችል አስተሳሰብ ነው፡፡

ዜጎች በልማት አጀንዳ ተሳታፊ ስላልነበሩ ህይወታቸውን የሚለውጥ ሀብት የማፍራትና ከአገሪቱ ሀብት በፍትሃዊነት የመጠቀም መብት አልነበራቸውም፡፡ የሕብረ ብሄራዊ ፌዴራል ሥርዓቱ አንዱ መሠረታዊ እምነት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ነው፡፡

አገሪቱ የምትመራባቸው መሠረታዊ መርሆዎች፣ ፖሊሲዎችና ሕጎች የሚመነጩት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ፍላጎቶችን ለማሟላት በመሆኑ እያንዳንዱ የመንግሥት እንቅስቃሴ ከዚህ አንፃር ይቃኛል፡፡ የመንግሥት ሥልጣን፣ መንግሥት የሚያራምዳቸው እምነቶች፣ የሚከተላቸው መርሆዎችና ፓሊሲዎች ምንጭ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ናቸው፡፡ ስለሆነም የፌዴራል ሥርዓቱ ልዩ ባህሪያት የአወቃቀር መልኮች፣ የሥልጣን ክፍፍልና ትስስር መሠረታዊ መነሻ የሕዝብ ልዕልና ነው የሚባለውም ለዚሁ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓቱ አባል መንግሥታት የተደራጁት በመሠረቱ በብሔር ብሔረሰብ ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ባለፈው ታሪክ ማንነቶች የተነፈጉትን መብት፣ ታፍኖ የነበረውን ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ባህልንና ሌሎች የማንነት መገለጫዎች በህገ መንግሥት ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ተፈፃሚ ማድረግ የሚችሉት ይህንኑ አወቃቀር በመከተል ስለሆነ ነው፡፡

ማንነቶች የተዛባውን ግንኙነት መወገዱን ማረጋገጫ መሣሪያ እንደሆነ ስላመኑበትና በዚህ አወቃቀር አዲስ የእኩልነት ግንኙነትና የጋር ህልውና እንዲመሠረት ስለወሰኑ የተከተሉት አወቃቀር ነው፡፡ ይህ ነው የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት አንዱ ልዩ ባህሪ ተደርጎ የሚወሰደው፡፡ ባደጉት አገራት በተለምዶ የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት ተደርገው የሚወሰዱት ሕዝቦች  ናቸው፡፡ ይህ አስተሳሰብ የቡድን መብቶችን ወደ ጎን መተውን ብዙዎች ምሁራን ይስማሙበታል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የአዲሲቷን ኢትዮጵያ የወደፊት ዕድል የመወሰን ሥልጣን ባለቤት መሆን እንዳለባቸው በወኪሎቻቸው አማካይነት ይፋ አድርገዋል፡፡ በምሥረታው ወቅት የገቡትን ቃል በአፈፃፀም ሂደት እንዳይዛነፍ የመጠበቅ ኃላፊነት የሚሰጣቸውን ህገ መንግሥት የመተርጎም ሥልጣን ወስደዋል፡፡ የዚህ ድንጋጌ ቁልፍ ትርጉም በመከባበር፤ በመተማመንና በመተባበር በእኩልነት አብሮ የመኖር ስምምነት ነው፡፡

የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት የግል መብቶችን ለማረጋገጥ ወሣኝ እንደሆነ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚቴ ይገልፃል፡፡ ብዙ ፀሐፊዎች የቡድን መብቶች ከግል መብቶች ተለይተው መገደብ የሌለባቸው እንደሆኑ ይገልፃሉ፡፡ የግል መብቶችን በማረጋገጥ ብቻ የቡድን መብቶችን ማረጋገጥ እንደማይችል፣ የቡድን መብቶችን የሚከለክል ሥርዓት የግለሰብ መብቶችን ብቻ በማስከበር የተሟላ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሊሆን እንደማይችል ይከራከራሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ ያደጉ የዴሞክራሲ አገሮች የቡድን መብቶችን በተሟላ መልኩ ባለመረጋገጣቸው ምክንያት የቡድን መብት ጥያቄዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከሩ የአገራቱን ውስጣዊ ሠላም በማናጋት ላይ ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያን ሁኔታ ስንመለከት ደግሞ የብሔሮችና ብሔረሰቦች እሥር ቤት ልትሆን የቻለችው የቡድን ማንነቶች ማፈን ዋነኛ የጭቆና መገለጫ ስለነበር ነው፡፡

ይህን ጭቆና በትግል በማስወገድ የራስ አስተዳደር መብትን በማረጋገጥ ብቻ የሚመለስ አልነበረም፡፡ ህገ መንግሥቱን በማፅደቅ ሂደት ሲነሱ የነበሩ ጥያቄዎችና ክርክሮች ይህንን ግልፅ ያደርጋሉ፡፡ የአንዳንድ ብሔሮች የፖለቲካ ድርጅቶች ከጅምሩ የመገንጠል ጥያቄ አንስተዋል፤ አንዳንዶች ደግሞ ነባሩ የተዛባ ግንኙነት በፈጠረባቸው ሥነ ልቦናዊ ጫና ምክንያት በሰንደቅ ዓላማ ቀለማት አመራረጥ ሳይቀር በስፋት ተከራክረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት አንዱ ልዩ ባህሪው የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብት በማረጋገጥ ህብረትን ማስቀጠል መቻሉን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት የአመሠራረት ሂደት ሁለት ባህሪያት ያካተተ ነው፡፡ የደርግ ሥርዓት እንደተወገደ የነበሩና ቀጥሎ የተፈጠሩ የፖለቲካ ፖርቲዎች በመሠረቱ በብሔራዊ ማንነት የተደራጁ ሆነው የያዟቸው ዓላማዎችና ፍላጎቶች የተራራቁ ነበሩ፡፡

የአመሠራረቱ ሂደትም እነዚህን የተራራቁ ፍላጎቶች የነበሯቸው የፖለቲካ ኃይሎች ተቀራርበውና ተሰባስበው በህብረቱ እንዲቀጥሉ የተስማሙበት፤ የሥርዓቱ ባለቤትነት፤ ቅርፁና መሠረታዊ መርሆዎቹ በድርድርና በስምምነት የወሰኑበት ሂደት ነበር፡፡ የሥልጣን ክፍፍሉ በድርድርና በስምምነት ሲወሰን ማዕከላዊ መንግሥት እንዲኖርና ሥልጣኑም በህገ መንግሥቱ የተዘረዘረውን እንዲሆን የወሰኑት የብሔሮችና ብሔረሰቦች ተወካይ የፖለቲካ ኃይሎች ናቸው፡፡

በኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ከተደነገጉ የሕዝቦች መብቶች አንዱ የኃይማኖት እኩልነት ነው፡፡ መንግሥትና ኃይማኖት የተለያዩ መሆናቸውን፤ ሁሉም ሰዎች በመካከላቸው የዘር፣ የብሔር፣ የብሔረሰብ፣ የጾታ፣ የኃይማኖት ልዩነት ሳይደረግ እኩል የሕግ ጥበቃ እንደሚደረግላቸው፣ ማንኛውም ሰው የማሰብ፣ የሕሊናና የኃይማኖት ነጻነት፣ የመረጠውን ኃይማኖት ወይም እምነት ለብቻው ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን የማምለክ፣ የማስተማርና የመግለጽ መብት እንዳለው ህገ መንግሥቱ ደንግጓል፡፡

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ መንግሥት ለእነዚህ ድንጋጌዎች ልዩ ትርጉም የሚሰጣቸው የኃይማኖቶች እኩልነትና የእምነት ነጻነት ሳይረጋገጥ ያለፈውን የተዛባ ግንኙነት ማስተካከል አይቻልም ከሚል መሠረታዊ አስተሳሰብ በመነሳት ነው፡፡

አዲስ የኢትዮጵያዊነት ማንነት የመገንባት ጉዳይም ከእነዚህ መብቶች ጋር በቀጥታ የተቆራኘ ነውና፡፡ ሌላው ነጥብ ለሕዝብ የሚገደብ መብት መኖር የለበትም የሚል መሠረታዊ እምነት ስላለ ጭምር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በግልም ይሁን በቡድን የመረጡትን እምነት የመከተል መብታቸውን ማረጋገጥ የሕዝብ ልዕልና አንድ አካል ስለሆነ ነው፡፡ ስለሆነም መከባበርና መደጋገፍ ሁሉም የእምነት ተቋማት ሊከተሏቸውና በአማኞቻቸው ላይ ሊገነቧቸው የሚገቡ እሴቶች ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡

የእኩልነት ድንጋጌው መንፈስ አንዱ እምነት የሌላውን እምነት አስተምህሮና የእምነቱን ሥነ ሥርዓት ማንቋሸሽ፣ አሳንሶ ማየትና በአሉታዊ መልክ መተቸት የማይችል መሆኑን ያመለክታል፡፡ በዚህ እምነትና አስተሳሰብ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ዛሬ እጅ ለእጅ ተያይዘው የህዳሴ ጉዟቸውን ቀጥለዋል፡፡ ከላይ የጠቀስኳቸው አንኳር ዋና ዋና መብቶች በህገ መንግስቱ የተጎናፀፍናቸው በመሆናቸው ህገ መንግስቱን ልንጠብቀውና ልንንከባከበው ይገባል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy