Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለሠብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ዋጋ ተከፍሏል!

0 406

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለሠብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ዋጋ ተከፍሏል!

ወንድይራድ ኃብተየስ

የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት የህዝቦችን እኩልነት ማረጋገጥ በመቻሉ በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በማድረግ የአገሪቱ አንድነት በጠንካራ አለት ላይ እንዲቆም አድርጎታል።  አድርጓል። ህገ-መንግስቱ የዜጎችን በህግ ፊት ያለምንም ልዩነት እኩል የህግ ጥበቃ እንደሚደረግላቸው ደንግጓል። በዘር፣ በብሔር ብሔረሰብ፣ በቀለም፣ በጾታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በማህበራዊ አመጣጥ፣ በሃብት፣ በትውልድ ወይም በሌላ አቋም በሰዎች መካከል ልዩነት እንደማይደረግና ሁሉም ሰዎች እኩል ተጨባጭ የህግ ዋስትና የማግኘት መብት እንዳላቸው በግልጽ ያስቀምጣል። ይህም ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በተግባር ተረጋግጧል።

ሕገ-መንግሥቱ ከመግቢያው ጀምሮ ሕዝቦች አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያ ማኅበረሰብ እንዲፈጥሩ፣ በህዝቦች መካከል መከባበርና መቻቻል እንዲጎለብት፣ የህዝቦችን አብሮነትና የአገሪቱን አንድነት ያጸና ሰነድ ነው። ከዚህም ባሻገር ሕገ-መንግሥቱ ሁሉም ዜጎች የሰባዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በእኩልነት መከበር እንዳለባቸው በግልጽ የሚደነግጉ አንቀጾችን አካቷል። የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት የብዙሃን ፓርቲ ስርዓትን በአገሪቱ እንዲተገበር ስለሚያዝ የትኛውም ፓርቲ በነጻነት እንዲንቀሳቀስ አስችሏል።

 

የፌዴራል  ስርዓቱም የህገ-መንግስታችን ውጤት ነው። የፌዴራል ስርዓታችን ውጤታማ የሆነው ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ በማድረጉ በህዝቦች መካከል መከባበርና መቻቻል እንዲሰፍን ዋንኛ ምክንያት ሆኗል። የፌዴራል ስርዓቱ ህዝቦች ባህላቸውን እንዲያጎለብቱ፣ ህጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ፣ ዜጎች በቋንቋቸው እንዲዳኙ፣ ወዘተ አድርጓል። ሕገ-መንግሥቱ በፌዴራሉ መንግስትና በክልል መንግስታት እንዲሁም በአንድ ክልል ውስጥ በሚኖሩ በሕዝቦች መካከል ስለሚኖር ዝምድና እና የጋራ መስተጋብር መሠረታዊ መርሆዎችን ያስቀምጣል።

 

አገራችን የፌዴራል ስርዓት ህዝቦች አካባቢያቸውን እንዲያለሙ መልካም ሁኔታን ከመፍጠር ባሻገር ፍተሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር አድርጓል። ዛሬ ላይ ሁሉም የክልል ከተሞቻችን አገር አቀፍ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ትላልቅ ኢቨቶችን ማስተናገድ ችለዋል። ከዚህ ቀደም እዚህ ግባ የሚባል መንገድ እንኳን ያልነበራቸው አርብቶ አደር አካባቢዎች ዛሬ ላይ የትላልቅ መሰረተ ልማት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። በአስር ሺዎች እንግዳን ማስተናገድ የግድ የሚለው እንደብሄራች፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች ያለ በዓላት ጅግጅጋ፣ አሶሳ፣ ጋምቤላን የመሳሰሉ ከተሞች ማስተናገድ ችለውል። ይህ የሚያመላክተው በአገራችን እየተመዘገበ ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት በመዕከል ወይም በተወሰነ አካባቢ አለመሆኑን ጥሩ ማሳያ ነው።

 

በህገ-መንግስታችን የሃይማኖት ነጻነትንም  አጎናጽፎናል። ዛሬ በአገራችን መንግስታዊ ሃይማኖትም ሆነ ሃይማኖታዊ መንግስት የለም። በሃይማኖት ምክንያት የሚደርሱ ተፅዕኖዎች ተወግደው ሁሉም ሃይማኖቶች በእኩልነት የሚስተናገዱበት ስርዓት ተረጋግጧል። በመሆኑም ሃይማኖቶች ሁሉ ተከባብረውና ተቻችለው የሚኖሩባት አገር መመስረት ተችሏል። ሁሉም ሃይማኖቶች አስተምህሮታቸውን በነጻነት የሌሎችን መብቶች አክብረው ማስተማር ይችላሉ። ይሁንና አንዳንድ ሃይሎች ይህን የሃይማኖት ነጻነት የሚለውን መርህ በተሳሳተ መንገድ ተረድተውታል አሊያም ሆን ብለው በማጣመም የግል ፍላጎታቸውን ለማሳኪያ ለመጠም ሲሯሯጡ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።

በህገ-መንግስታችን ማንም የፈለገውንና የቻለውን ያህል ሃብት የማፍራት መብትም አአጎናጽፏል። በደርግ የዕዝ ኢኮኖሚ ግለሰቦች ከተቀመጠላቸው የአምስት መቶ ሺህ ብር በላይ ሃብት ማፍራት አይፈቀድላቸውም ነበር። ይሁንና የኢፌዴሪ ህገመንግስት ይህን ገደብ በማንሳት ዜጎች በህጋዊ መንገድ ተወዳድረው እስከቻሉት ድረስ ሃብት ማፍራት እንዲችሉ መብት ሰጥቷል። በዜጎች የንብረት መብት ላይ የተጣለው ገደብ ተነስቶ ዜጎች ያልተገደበ ሃብት ማፍራትና የመጠቀም መብታቸውን በተግባር ላይ አውለዋል። ዛሬ በአገራችን በርካታ ሚሊዮነሮችን ማፍራት ችላለች በቅርቡ የወጣ አንድ አለም አቀፍ መረጃ በአገራችን በርካታ ሚሊየነሮች በመፈጠር ላይ ናቸው።  

በአገራችን የታየው ልማትና እድገትም ቢሆን የህገ-መንግስታችን ውጤት ነው። በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሠረት አገራችን በታሪኳ አከናውናው የማታውቃቸውን እጅግ ግዙፍ የሆኑ ባለ ብዙ ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚጠይቁ ፕሮጀክቶችን መገንባት ችላለች። ለአብነት ያህል ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነ የውኃ ኃይል ማመንጫ ግንባታ፣ የባቡር መስመር ዝርጋታ፣ ዘጠኝ ግዙፍ የስኳር ፋብሪዎችና የማዳበሪያ ፋብሪካዎች ግንባታዎች እንዲሁም ሰፋፊ አገር አቋራጭ የመንገድ ግንባታ፣ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አውታር ዝርጋታ ወዘተ በመካሄድ ላይ ናቸው። እነዚህ መሰረተ ልማቶች በሙሉ የህገመንግስቱ ውጤቶች ናቸው።

እያንዳንዷ ቀንና ሰዓት ሰላማችን የአገራችን ተጨማሪ ልማት መሆኗን በቅርቡ በኦሮሚያና በአማራ አንዳንድ አካባቢዎች በተቀሰቀሱት ሁከቶች ምን ያህል ልማታችንን እንደጎዳው መመልካት የሚከብድ አይደለም። የአገራችን የልማት ጥማት እጅግ ሰፊ ነው። እንኳን ቀንሰንለት በዚህ ፍጥነት እየሮጥን እንኳን የህብረተሰቡን የመልማት ፍላጎት ማሳካት አልተቻለም። የአገራችንን ዕድገት የተሻለ የምናደርገው በሰላማችን ላይ መደራደር ስናቆም ብቻ ነው። ይህን ስል መንግስትን መቃወም ተገቢ አይደለም ማለቴ አይደለም። ይሁንና ተቃውሞ ሰላማዊ መሆን መቻል አለባቸው። ህይወት በማጥፋትና ንብረት በማውደም የሚደረግ ተቋውሞ አገራችንን ወዳልተፈለገ ነገር እንደሚያመራት ግን ሊታወቅ ይገባል። ህገመንግስታችን በአገራችን ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ  በማድረጉ ልማታችን ሊፋጠን ችሏል። እንግዲህ የልማታችን ዋስትና ሰላማችን በመሆኑ በሰላማችን ላይ ድርድር መኖር የለበትም።

በህገ-መንግስት ሰብአዊ መብትን በተመለከተ ያስቀመጠው አብይ ድንጋጌ በስብዕና ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን የሚመለከት ነው። በህገ-መንግስት አንቀጽ 28 ላይ እንደተመለከተው አገራችን ባጸደቀቻቸው አለም አቀፍ ስምምነቶችና በሌሎች የኢትዮጵያ ህጎች በሰው ልጅ ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ተብለው የተወሰኑትን የሰው ዘር የማጥፋት፤ ያለፍርድ የሞት ቅጣት እርምጃ የመውሰድ፣  በአስገዳጅ ሰውን የመሰወር ወይም ኢ-ሰብአዊ የድብደባ ድርጊቶችን በፈጸሙ ሰዎች ላይ ክስ ማቅረብ እንደሌሎች ወንጀሎች በይርጋ እንደማይታገድና በህግ አውጭም ሆነ በማንኛውም የመንግስት አካል በምህረት ወይንም በይቅርታ እንደማይታለፉ ተሰምሮበታል። ይህ ድንጋጌ አገራችን  ለዜጎች ሰብአዊ መብቶች መከበር እስከምን ድረስ ጠንካራ አቋም እንዳላት የሚያመለክት ነው።  

እንዲሁም ዜጎች መረጃዎችን የማግኘት መብታቸውም ሕግ-መንግሥታዊ እውቅና አግኝቷል። የምንግሥት ሚዲያም የተለያዩ አስተሳሰቦችን በሚያስተናግድበት መንገድ እንዲመራ ሕገ-መንግሥት ያዝዛል። ይህም በመገናኛ ብዙሃኖች ተግባራዊ ሆኗል። ይሁንና አንዳንድ በነጻው ፕሬስ ስም የተቋቋሙ ጋዜጦችና መጸሄቶች ህገ-መንግስቱ የሰጣቸውን መብት ያለአግባብ በመጠቀም አገርንና ህዝብን ጥቅም በሚጎዳ አልፈውም ይህን መብትና ነጻነት የሰጣቸውን ህገመንግስት ሳይቀር ሲያጣጥሉ ነበር። ይሁንና ይህ ሁኔታ አሁን ላይ ተለውጧል። አዎ  ዛሬ ላይ ህገመንግስቱ ያስገኘው ጥቀሜታ በሁሉም አካላት በጽንፈኛው የዳያስፖራ ፖለቲከኞች ጭምር ተቀባይነት አገኝቷል። አዎ ይህ አንድ መልካም ጅምር ነው።

የዴሞክራሲ መብቶችን በተመለከተ ህገ-መንግስቱ በርካታ አንቀጾችን አካቷል። በእነዚህ አንቀፆች  አማካኝነት የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ሕጋዊ እውቅና አግኝተዋል። በዚህም መሠረት የዜጎች የአመለካከትና ሃሳብን በነፃ የመያዝና የመግለፅ መብት፣ ከዚሁ ጋር በተያያዘም የፕሬስና የሌሎች የመገናኛ ብዙኃን እንዲሁም የሥነ-ጥበብ ፈጠራ ነፃነት ተረጋግጧል።

ባለፉት ሥርዓቶች  በፕሬስ ላይ ይደረጉ የነበሩ የቅድመ ምርመራ እንቅስቃሴዎች በሕገ-መንግሥቱ አማካኝነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተወግደዋል። በመሆኑም ዛሬ በአገራችን ማንም በነጻነት ሃሳቡን በሰላማዊ መንገድ የመግለጽ መብቱ ተጠብቆለታል። የዜጎች የመምረጥና የመመረጥ መብትም ሕገ-መንግሥታዊ እውቅና አግኝቷል። የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን ያልተገደበ መብታቸውም ለመጀመሪያ ጊዜ እውቅና ያገኘው በዚህ ሕገ-መንግሥት አማካኝነት ነው። የሀገራችን ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደርና በክልል እና በፌዴራል አስተዳደሮች ውስጥ ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት መብታቸው እንደተከበረ ተደንግጓል።

ሕገ-መንግሥቱ ከፌዴራል ሥርዓቱ ለመነጠል ለሚሹ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚከተሉትን ሕጋዊ ሥርዓትም በግልፅ አስቀምጧል። ይህን ህጋዊ መስመር የሚከተል ማንኛውም መገንጠል የሚፈልግ አካል በህገመንግስቱ በሚያዘው መሰረት በአግባብ የሚስተናገድበት ሁኔታ ተቀምጧል። ህገመንግስታችን ይህን ያህል የዜጎችን ሰባዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያስጠበቀ እጅግ ዘመናዊ አስተሳሰብን የያዘ ሰነድ ነው። ሕገ-መንግሥታችን ዜጎች የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነት እና እንዲሁም በሕጋዊ መንገድ ለሕጋዊ ዓላማ የመደራጀት መብት እንዳላቸው ይደነግጋል። ዜጎች በአገራቸው ውስጥ በነፃነት የመዘወዋወር መብት እንዳላቸው፣ በፈለጉ ጊዜ ከአገር ወጥተው የመመለስ መብታቸው የተከበረ መሆኑን ሕገ-መንግሥቱ ያስቀምጣል።  

ሕገ-መንግሥቱ የዜግነትን መብት ያስከበረ ሲሆን የጋብቻ፣ በግል እና የቤተሰብ መብቶችንም በአዲስ መሠረት ላይ እንዲገነቡ አድርጓል።  ሕገ-መንግሥቱ ሴቶች ከወንዶች ጋር እኩል መብት እንዳላቸው ከማረጋገጡም በላይ ሴቶች በታሪክ በበታችነትና በልዩነት በመብታቸው የደረሰባቸውን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ይህንኑ ለማረም የሚያስችል የልዩ ድጋፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያዝዛል። ይህም በተግባር ላይ ውሎ ዛሬ ላይ በአንዳንድ መስኮች ሴቶችና ወንዶች እኩል ደረጃ ላይ ማድረስ ተችሏል።  

ሕገ-መንግሥታችን የህፃናት መብትን በተመለከተም ዝርዝር ድንጋጌዎችን አካትቷል። ህፃናት በሕግ የተቀመጡ መብቶቻቸውን ተጠቅመው ብቁ ዜጎች ሆነው እንዲያድጉ ሕገ-መንግሥታዊ ዋስትና ተደርጎላቸዋል። የሀገራችን ወጣቶች በሕገ-መንግሥቱ ላይ የሰፈሩ መብቶች ሁሉ ተጠቃሚዎች ናቸው። ብሶት የወለዳቸው እውነተኛ የህዝብ ልጆች በከፈሉት የህይወትና የአካል መሰዋዓትነት የአገራችን ህዝቦች የሚያጣሟቸውን ሰባዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን አጎናጽፈውናል። በአሁኑ ሰዓት ወጣቱ ትውልድ የሚያስፈልገው አገርን ከድህነትን ከኋላ ቀርነት ማላቀቅ እንጂ ስለጦርነት፣ ሞትና ስደት መሆን የለበትም።

የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት የዜጎች ሰባዊና ዴሞከራሲያዊ መብቶች ተከብረው ዜጎች በነፃነት የሚኖሩባት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ መሰረት ነው። ዜጎች በነጻነት መንግስትንም ሆነ የመንግስትን አሰራር መተቸት የሚችሉበት ስርዓት ተዘርግቷል። ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በመረጋገጣቸው በህዝቦች አብሮነት የአገራችን አንድነት ጠንካራ መሰረት ላይ እንዲመሰረት ሆኗል። እንዜጎች በነጻነት የፈለጉትን ሃይማኖት መከተል የሚችሉበት ሁኔታ ተመቻችቷል። የብዙሃን ፓርቲ ስርዓት አሰራር ተዘርግቷል። በሕጋዊ መንገድ የተመዘገቡ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገራችን በነጻነት ይንቀሳቀሳሉ።  ሃሳብን የመግለፅ መብት በመረጋገጡ ማንም የፈለገውን ሃሳብ የሌሎችን መብት  እስካልተጋፋ ድረስ የመግለጽ መብት አለው። ለብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና የህዝቦች ሠብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ዋጋ ተከፍሏል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy